መርድ ክፍሉ
ከፌዴራል ኤች.ኤይ.ቪ/ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው፤ የኢትዮጵያ የኤችአይቪ የስርጭት ምጣኔ ዜሮ ነጥብ 93 በመቶ ሲሆን በዚህ ስሌት መሰረት 669 ሺ 236 ያህል ወገኖች ኤች.አይ.ቪ በደማቸው እንደሚገኝ እና ከእነዚህም ውስጥ 413 ሺ 547 ወይንም 61 ነጥብ 8 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ያስረዳል።
የስርጭት ምጣኔ ከክልል ክልል፣ ከቦታ ቦታ፣ በከተማና በገጠር እንዲሁም በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚለያይና በኤችአይቪ የመያዝ ምጣኔ ከጊዜ ወደጊዜ በሚፈለገው መጠን እየቀነሰ አለመሆኑ ተመልክቷል።
በየዓመቱ ህዳር 22 ቀን የሚከበረው የአለም የኤድስ ቀን ዘንድሮም “ኤች.አይ.ቪን ለመግታት ዓለምአቀፋዊ ትብበር፣ የጋራ ኃላፊነት” በሚል መሪ ቃል በሀገሪቱ ለ33ኛ ጊዜ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል። በሀገር አቀፍ ደረጃ በለሚ ኢንደስትሪያል ፓርክ ህዳር 22 ቀን 2013 ዓ.ም ተከብሮ ውሏል። በእለቱም በአገሪቱ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት እየቀነሰ ቢመጣም ስጋትነቱ ግን አሁንም ድረስ አለመጥፋቱ ተመልክቷል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደሚናገሩት፤ የኤች አይቪ ስርጭትን የመግታት ጉዳይ በጤናው ዘርፍ ተቋማት ርብርብ ብቻ ውጤት የሚገኝበት አይደለም። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆነ ተቋምና ድርጅት በቅንጅት መስራት አለበት።
በአገሪቱ ያለው የቫይረሱ ስርጭት ሁኔታ በአንጻራዊ በየዓመቱ እየቀነሰ መምጣቱን ልዩልዩ ጥናቶች የሚያመላክቱ ቢሆንም በተለይም ይበልጥ ተጋላጭ በሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በጋምቤላ ክልል፣ በብዙዎቹ የሀገሪቱ ከተሞች፣ ወደ ከተማነት በማደግ ላይ በሚገኙ ትናንሽ መንደሮች፣ በኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ በተሰማሩ ወጣቶች፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ በግዙፍ የአበባ ልማት እርሻዎችና በመሳሰሉት በርከት ያሉ ሰዎች ተሰባስበው በተሰማሩባቸው የስራ ዘርፍ አካባቢዎች፣ የቫይረሱ ስርጭት በሚፈለገው ልክ ሲቀንስ አለመታየቱን ይጠቁማሉ።
ችግሩን በአግባቡ በመረዳትና የሚያስከትለውን ቀውስ በመገንዘብ፣ ችግሩን ሊፈታ በሚያስችል ደረጃ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ርብርብን፣ የከፍተኛ አመራሩን፣ የክልል የኤች አይቪ/ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ምክር ቤቶችን፣ በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት ተቋማትን፣ የኪነጥበብ ባለሙያዎችን፣ የሀይማኖት አባቶችና ተቋማትን፣ የሚዲያውን፣ የአጋር ድርጅቶችንና መሰል አደረጃጀቶችን ትኩረት አላገኘም፤ በጋራ ትብብር፣ በሀገራዊ ሀላፊነት፣ በጠንካራ ቁርጠኝነት፣ በሀገር ፍቅር ስሜት የተያዘ አጀንዳ አለመደረጉንም ይጠቅሳሉ።
በመሆኑም ኤች አይቪ/ኤድስን ስርጭት የመግታት ጉዳይ፣ በሽታን ከመከላከል የላቀ ትርጉም ያለው መሆኑን በመገንዘብ የማህበራዊ ቀውስ፣ የስነልቦና ስብራት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት ማነቆ፣ የሀገር ገጽታ ጥላሸት መሆኑን በመረዳት፣ ስርጭቱን ለመግታት፣ ሀገራዊ ትብብርና የጋራ ሃላፊነትን መውሰድ እንደሚገባ ያመላክታሉ።
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሀንስ ጫላ እንደሚናገሩት፤ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከፍተኛ ተፅዕኖ ካሳረፈባቸው ዘርፎች መካከል የኤች አይ ቪ ኤድስ መቆጣጠር ዘርፍ አንዱ ነው። የኮሮና ወረርሽኝ ሁሉም የፀረ ኤች አይ ቪ ኤድስ የንቅናቄ ዘመቻ ሙሉ ለሙሉ እንዲቆሙ ከማድረግ በላይ በጤና ተቋማት ይሰጡ የነበሩ የኤች አይ ቪ ኤድስ የህክምና አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሮ ነበር።
በኮቪድ 19 ወቅት የታየውን ርብርብ የኤች አይ ቪ ኤድስን ወረርሽኝ ለመግታት መደገም እንዳለበት የሚናገሩት ዶክተር ዮሀንስ፤ በአዲስ አበባ ያለው የኤች አይ ቪ ስርጭት ምጣኔ ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ በሶስት ነጥብ ሁለት በመቶ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ በፊት በከተማው የስርጭት ምጣኔ ከፍ እንዲል ያደረገው የአጋላጭና የተጋላጭ ሁኔታዎች አሁንም ድረስ እየተስተዋሉ መሆኑን ያመለክታሉ።
የአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ኤድስ አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ በአለም አቀፍና በአገር ደረጃ የተቀመጠውን ራዕይና ስትራቴጂዎችን መሰረት በማድረግ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ በመጥቀስ፤ በሂደትም ተቀዛቅዞ የነበረው የፀረ ኤች አይ ቪ እንቅስቃሴ በተወሰነ መልኩ ወደ ነበረበት ለመመለስ የተቻለ ሲሆን በጤና ተቋማትም የሚሰጡ የጤና መርሃ ግብሮችም እየተሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።
የፌደራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ፤ ኤች አይቪ ኤድስ በአገሪቱ በተከሰተባቸው በመጀመሪያዎቹ ሁለት አስርት አመታት ውስጥ፣ በየዓመቱ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሞት ምክንያት በመሆን፣ አረጋውያንን ያለ ጧሪ፣ ህፃናትን ያለ አሳዳጊ በማስቀረት፣ ማህበረሰባችንን ለከባድ ማህበራዊ፣ ስነ ልቦናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የጨመረ፣ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑን ይናገራሉ።
በኢትዮጵያ 14ሺህ 843 ሰዎች በየዓመቱ አዲስ በኤች.አይ.ቪ የሚያዙ ሲሆን 67 በመቶ የሚሆነው ዕድሜያቸው ከ30 ዓመት በታች የሚገኙ ወጣቶችና ህጻናት ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ 20 በመቶ አዳዲስ የተያዙ ሰዎች ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 24 ዓመት የሚሆኑ ወጣቶችና 19 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከዜሮ እስከ 4 ዓመት የሚገኙ ህጻናት ናቸው። ይህ የሚያሳየው ዛሬም የኤች.አይ.ቪ ስርጭት ሁኔታ አሳሳቢና ከችግሩ ለመላቀቅ እስከዛሬ ከተሰራው የበለጠ ሁሉን አቀፍ ትብብርና የጋራ ሀላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ ዶክተር ፅጌረዳ ገለፃ፤ ከ500 ሺህ በላይ የሚሆኑ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኝ ሰዎች የጸረ.ኤች አይ.ቪ መድሃኒት ቢውስዱም በአጠቃቀም ሂደት የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ከውጭ ሀገር ለጋሽ ድርጅቶች በብዙ ድካም በተገኘ ገንዘብ በውጭ ምንዛሬ እየተገዛ የሚመጣውን የጸረ ኤች.አይ.ቪ መድሃኒት በትክክልና በሀኪም ትዕዛዝ ብቻ ካልተወሰደ የዜጎችን ህይወት ከሞት መታደግ አይቻልም።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013