ዳንኤል ዘነበ
ወርሃ መጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም። በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቀነስ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ ተወሰነ። በአጭር ጊዜ የመማር ማስተማሩ ሂደቱ እንደሚመለስ ቢነገርም፤ የቫይረሱ አስጊነት የእውቀት በሮች ዳግም ለመክፈት የሚያስደፍር አልነበረም።
ይህም ከ25 ሚሊዮን በላይ እውቀትን ፍለጋ የሚማስኑ ተማሪዎች ከነእውቀት ረሀባቸው ከቤት ለመዋል ተገደዱ። 600 ሺህ የሚሆኑ እውቀትን መጋቢ መምህራንም እጣ ፈንታቸው ተመሳሳይ ሆነ። የአለም ህዝብ ስጋት ለሆነው ወረርኝ መፍትሄ በመጥፋቱ የሰው ልጅ የህይወት ኡደት ወደ መደበኛ መስመር መመለስ ዳገት እንደሆነ ቀጠለ። ይህም በመላ ኢትዮጵያ የተዘጉት የእውቀት በሮች ሳይከፈቱ ቀናት እንዲነጉዱ አደረገ።
ወራት ቢፈራረቁም፤ ትምህርት ቤቶችን መክፈት የማይሞከር ነበር። የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ የሚጠፋ ሳይሆን ከሰው ልጆች ጋር አብሮ የሚኖር ነው ሲል ማስታወቁን ተከትሎ የፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ አዘዘ።
ሚኒስቴሩ ላለፉት አስር ወራት ተዘግተው የነበሩ የእውቀት በሮች ወረርሽኙን እየተከላከሉ ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲሸጋገሩ ውሳኔ አሳለፈ። በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ይህን ተከትለው ከህዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ወደ መማር ማስተማሩ ሂደቱ ተሸጋግረዋል። ለአስር ወራት የተዘጉት የእውቀት በሮች ወደ አገልግሎት መመለሳቸውን በተለይ በወላጆች ላይ የእፎይታ ስሜት የፈጠሩ ሆነዋል።
በአዲሱ ገበያ ሴንት ሜሪ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሁለት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት ወይዘሮ ገልገሉ ታደሰ፤ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፤ ልጆቻችን በቤት ውስጥ እንዲቆዩ ተደርጎ እንደነበር ይናገራሉ። ይህም ልጆቹን ከለመዱት ነፃነት አፋቶ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና እንዲፈጠርባቸው ያደረገ መሆኑን በማስታወስ፤ ትምህርት ቤቶች በመከፈታቸው የልጆቹ አዕምሮ ከጫና ውጪ እንዲሆን የሚያስችልና እፎይታ የሚሰጥ መሆኑን ይገልፃሉ። ትምህርት መከፈቱ የሳቸው ልጆች ለአስር ወራት ከእውቀት ደጆች በመራቃቸውና ከቤት በመዋላቸው ከሚፈጠሩ የሥነ -ልቦና ችግሮች የሚያወጣ መሆኑን ያመላክታሉ።
በሌላ በኩል በሀገራችን ባህል፣ ወግና ልማድ ውጪ በሆነ መልኩ የህፃናት ጥቃት በሴትም በወንድም ቁጥሩ ባለፉት አስር ወራት በተለየ መልኩ እንደጨመረ በመገናኛ ብዙሀን ሲነገር መስማታቸውን ያስታወሱት ወይዘሮ ገልገሉ፤ በኮቪድ-19 ምክንያት ትምህርት ቤት በመዘጋቱና ህፃናት ቤት መዋላቸውን ተከትሎ በቤተሰቦቻቸው፣ በቅርብ ሰዎች፣ በአሳዳጊዎች የሚደፈሩና የፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሚሆኑ ህፃናት ቁጥር እንዲበዛ ምክንያት እንደሚሆን ይጠቁማሉ። ከዚህ አኳያ ትምህርት መጀመሩ እፎይታ ይሰጣል ሲሉ ሀሳብን ያጠቃልላሉ።
በተመሳሳይ በሰሜን ማዘጋጃ አካባቢ በሚገኘው ላዛሪስት አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ሶስት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ፤ በሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሆንም፤ ትምህርት ቤት በመከፈቱ ደስተኛ እንደሆኑ ይጠቁማሉ። ትምህርት ቤቶቹ የቫይረሱ ስርጭት መከላከል የሚያስችል የተሟላ ዝግጅት ማድረጋቸውን ማረጋገጫ መሰጠቱን የጠቆመው አቶ ብርሀኑ፤ የኮሮና ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችል ዝግጅት የተደረገ መሆኑ እንደ ወላጅ እፎይታ እንደተሰማቸው ይናገራሉ።
‹‹በዚህ ረገድ የእኔ ልጆች በሚማሩበት ትምህርት ቤት በመሄድ ከተመለከትኩት፤ ከልጆቼ ጠይቄ ከተረዳሁት ወረርሽኙን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ የመማር ማስተማር ሂደቱ እየተከናወነ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችያለው።›› ይላሉ።
አቶ ብርሀኑ አክለው፤ ትምህርት ሚኒስቴር ትምህርት ቤቶች በአንድ ክፍል ውስጥ 25 ተማሪዎችን ብቻ እንዲያስተምሩ መወሰኑን ይጠቁማሉ። የግል ትምህርት ቤቶች ውሳኔውን ባከበረ መልኩ ወደ መማር ማስተማር ሂደቱ መግባታቸውን ይገልፃሉ። የእሳቸው ልጆች የሚማሩበትን ትምህርት ቤት እንደማሳያ በመጥቀስ፤ ህዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት ቤቱ ወደ አገልግሎት ምዕራፍ የተሸጋገረ ሲሆን፤ ተማሪዎቹ በሁለት ፈረቃ ተከፍለው በአንድ ክፍል 25 ተማሪዎችን ብቻ በመያዝ እያስተማረ እንደሚገኝ ያመለክታሉ።
በኮቪድ-19 ምክንያት ባለፉት አስር ወራት ተዘግተው የነበሩት የእውቀት በሮች የአገልግሎት ምዕራፋቸውን መጀመራቸውን አስታውሰው ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ ስንታየሁ ወንዳጥር ናቸው። አቶ ስንታየው እንደሚናገሩት፤ በ2012 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ግማሽ ሴሚስተር ላይ ከመቋረጡ ትይዩ የ2013 ዓ.ም ትምህርት ዘመን ይጀመራል ከተባለበት ጊዜ የዘገየ ነበር። ይህም ልጆቻችን ያለፋቸውን የትምህርት ዘመን ለማካካስ የሚያስችሉ ሁኔታዎች መፍጠር ስለመቻሉ ጥርጣሬ እንዲያድርባቸው አድርጎም ነበረ።
አቶ ስንታየሁ፤ «ትምህርት ቢሮው ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ልጆቻችን በኮቪድ-19 ሳቢያ ያልተማሯቸውን ትምህርቶች እንዲማሩ የሚያስችል መደላድል መፈጠሩን ለማወቅ ችያለሁ። ተማሪዎቹ ከመደበኛው ትምህርታቸው ትይዩ ክለሳ እየተደረገ ይገኛል። ይህም እንደ ወላጅ እፎይታ ይሰጣል» ሲሉ ይጠቅሳሉ። የግል ትምህርት ቤቶች የማካካሻ ትምህርቱን ተግባራዊ ባደረገና፤ አካል ርቀትን በማስጠበቅ የቫይረሱን ስርጭት መከላከል በሚያስችል ሁኔታ የመማር ማስተማር ሂደቱን እየተከወነ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
ሚኒስቴሩ ትምህርት እንዲከፈት መወሰኑ ተከትሎ ከህዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች ወደ መማር ማስተማሩ መሸጋገራቸውን ለመገንዘብ ተችሏል። በተመሳሳይ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ደግሞ ከህዳር 28 ቀን 2013 ዓ.ም ትምህርት እንደሚጀምሩ ታውቋል። በግል ትምህርት ቤቶች ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ለወላጆች እፎይታ በሰጠ መልኩ የታየው የመማር ማስተማር ተሞክሮ ፤ በመንግስት ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ ገጽታ የተላበሰ እንደሚሆን ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ህዳር 28/2013