
ዋለልኝ አየለ
አዲስ አበባ፦ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ለሚመረቁ ሥራ ፈላጊዎች የበይነ መረብ የሥራ ዓውደ ርዕይ እንደሚካሄድ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን አስታወቀ። ዓውደ ርዕዩ አካላዊ ቅርርብን በማስቀረት ኮቪድ-19 ወረርሽኝን የሚከላከልና ሥራ ፈላጊዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ እንደሆነም ገልጿል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን የኮምኒኬሽንና ህዝብ ግንኙነት አማካሪ ወይዘሮ ተወዳጅ እሸቱ በተለይም ለአዲስ ዘመን ትናንት እንደገለጹት፤ የንግድ ሥራ ክፍል የሆነው ደረጃ ዶት ኮም ከኢፌዴሪ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ከህዳር 29 እስከ ታህሳስ 9 ቀን 2013 ዓ.ም የበይነ መረብ የሥራ ዓውደ ርዕይ ይካሄዳል። በዓውደ ርዕዩም የጅማ፣ የባህርዳር፣ የአዲስ አበባ እና ሌሎች አንጋፋ ዩኒቨርሲቲዎች ይሳተፋሉ።
እንዲህ አይነት የሥራ ዕድል ዓውደ ርዕይ በሌላው ዓለም ብዙ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚረዳ ያመለከቱት አማካሪዋ ፣ በኢትዮጵያም የተሻለ የስራ አድል ለመፍጠር ያስችላል በሚል ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።
በደረጃ ዶት ኮም አነሳሽነት ከዚህ በፊት በየከተሞች እየተዞረ በአካላዊ ቅርርብ የስራ እድል ለመፍጠር ይሰራ እንደነበር ጠቁመው ፤ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ብዙ ሰዎችን ማሰባሰብ ባለመቻሉ ስራውን በበይነ መረብ ዓውደ ርዕይ እየተካሄደ መሆኑን አመልክተዋል።
አገልግሎቱን በበይነ መረብ መሰጠቱ የአገልግሎቱን ተደራሽነት እንዳሰፋው የገለጹት አማካሪዋ፣ በበይነ መረብ አገልግሎት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደገባ ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎችን ማሳተፍ ተችሏል ብለዋል።
‹‹የሥራ ዕድል ፈጠራ አጀንዳው የመንግስት ኃላፊነት ብቻ አይደለም›› ያሉት ወይዘሮ ተወዳጅ፤ የግል ባለሀብቶችና ሌሎች ቀጣሪዎች ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። መንግስት በግል አስቀጣሪዎች የሚሰሩ የስራ ፈጠራ ስራዎችን እንደሚደግፍም ተናግረዋል።
የደረጃ ዶት ኮም ፕሮግራም ዳይሬክተር ወይዘሪት ሲሃም አየለ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ደረጃ ዶት ኮም ከማስተር ካርድ ፋንውዴሽን በሚያገኘው ድጋፍ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ጋር በመተባበር አዲስ ተመራቂዎችን ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ያገናኛል፤ ያስቀጥራል። ከተቀጣሪዎች ምንም አይነት ክፍያ አይቀበልም።
ደረጃ ዶት ኮም ከአንድ ሺህ በላይ ተመራቂዎችን ከ80 ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ማገናኘቱን የገለጹት ወይዘሪት ሲሃን፣ ህዳር 29 በሚከፈተው ዓውደ ርዕይ ከአራት ሺህ በላይ ተመራቂዎች እንደሚሳተፉም አስታውቀዋል ።
እንደ ወይዘሪት ሲሃን ገለጻ፤ ደረጃ ዶት ኮም ከቀጣሪ ድርጅቶች እና ከተመራቂዎች ጋር ማገናኘቱ ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለሥርዓተ ትምህርት ቀረጻ ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን ማግኘት ማስቻሉን ጠቁመዋል።
እንደ አሰራር ቀጣሪ ተቋማቱ ከተመራቂ ተማሪዎች ላይ ያጡትን ክህሎት ለደረጃ ዶት ኮም ያሳውቃሉ ያሉት ወይዘሪት ሲሃም ፣ ደረጃ ዶት ኮም በበኩሉ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት ሙያ አጡት የተባለውን ክህሎት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሳውቃል ብለዋል።
ደረጃ ዶት ኮም ከ25 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል ፈጠራ ክህሎትን በተመለከተ ሥልጠና መስጠቱን አስታውቀው ፣ በመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት 14 የሙያ ማበልጸጊያ ማዕከላት ማቋቀሙን ገልተጸዋል። ለስድስት ሺህ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል ማስገኘቱን አመልክተዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ለሦስት ሚሊዮን ወጣቶች የሥር ዕድል የመፍጠር እቅድ እንደነበረው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም