
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ አበባ፡- የክልሉን ኢንቨስትመንት ለማፋጠን የወጣው የመሬት ካሳ አዋጅ ተሻሽሎ ሊተገበር ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ መድረሱን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨትመንት ቢሮ አስታወቀ፡፡
በአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨትመንት ቢሮ የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ያየህ አዲስ ለዝግጅት ክፍሉ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል የነበረው የመሬት ካሳ አዋጅ የክልሉን ኢንቨስትመንት ላይ ማነቆ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ቀደም ሲል የነበረው የመሬት ካሳ አዋጅ ተሻሽሎ ሊተገበር ከመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
ለአርሶ አደር የሚከፈል ካሳን አስመልክቶ እንዲወጣ የታሰበው አዋጅ በፌዴራል መንግስት ዘንድ አንድ ዓመት ቆይቷል፡፡ ወደ ክልል ከመጣ በኋላ ደግሞ ወራት ተቆጥረዋል የሚሉት አቶ ያየህ ፣ የአዋጁ ተግባራዊ አለመሆን ባለሀብቶችን በፍጥነት ለማስተናገድ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ፤ ክልሉ በፍጥነት መመሪያ አውጥቶ ከሚመለከታቸው አካላትን ጋር ባለመወያየቱና ወደ ሥራ ባለመግባቱ ከተማ አስተዳደሮችና የልማት ኮሪደሮች ባለሀብቶችን ለማስተናገድ ተቸግረዋል፡፡ ይህ አሰራር በአሁኑ ወቅት መፍትሄ ሊሰጠው ተቃርቧል። አዋጁ ተግባራዊ ሲሆን በሳምንታት የኢንቨስተሩን ጥያቄ መመለስ ይቻላል፡፡
አርሶ አደሩም በአሁኑ ወቅ ምርት እየሰበሰበ ሲሆን በወቅቱ ካሳ ካልተከፈለው ወደ መሬት ማረስ እና ማለስለስ ብሎም ዘር መዝራት ስለሚገባ በሚቀጥለው ዓመትም ተመሳሳይ ችግር የሚፈጥር መሆኑን የጠቀሱት ሃላፊው፤ በመሆኑም በፍጥነት አዲሱን አዋጅ ታሳቢ ባደረገ መልኩ ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባ በከፍተኛ አመራሮች መግባባት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡
ለዓመታት የክልሉ ኢንቨስትመንት ላይ ማነቆ የነበረ የመሬት ካሣ አዋጅ ተሻሽሎ ወደ ሥራ ሲገባም በክልሉ ከፍተኛ መዋዕዋለ ንዋይ የሚያፈሱ ባለሀብቶች እንደሚኖሩና ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንደሚኖርም እምነታቸው እንደሆነ አስታውቀዋል ፡፡
የደብረብረሃን ከተማ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃን ገብረሕይወት በበኩላቸው፤ የአዋጁ መዘግየት በከተማው እና በአካባቢው በሚካሄደው ኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል፡፡
በተለይም በአሁኑ ወቅት ወደ ከተማዋ የሚጎርፉ የአገር ውስጥ እና የውጭ አገር ባለሀብቶችን ለማስተናገድ እና የሚፈልጉትን አገልግሎት በወቅቱ ለመስጠት ፈታኝ ሆኖ መቆየቱን ጠቁመው፤ በተደጋጋሚ ከዞን እስከ ክልል ችግሩ እንዲፈታና ለሚመለከታቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡
አዋጁ በመዘግየቱ ባለሀብቶች በፈለጉት መንገድ ኢንቨስትመንት እንዳያካሂዱ ያደረጋቸው ሲሆን ከወረዳ እስከ ዞን ለሚገኙ አስተዳደሮችም ፈተና እንደነበርና አርሶ አደሩን ካሳ ከፍሎ መሬት እንዲለቅ የሚደረገው ጥረት በእጅጉ አስቸጋሪ ሆኖ መቆየቱንም ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም