
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ አበባ፦ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ዓላማ ለዓለም ለማሳወቅ የሰራችው ዲፕሎማሲ ስኬታማ እንደነበር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም ገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በትግራይ ክልል የነበረውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ዓላማ ለዓለም ለማሳወቅ የተሰራውን የዲፕሎማሲ ስራ አስመልክቶ ትናንት በሰጡት መግለጫ ፣ የፌዴራል መንግስት ሲያከናውን የነበረውን ህግ የማስከበር ተግባር ዓላማ ለዓለም መሪዎች ለማስረዳት የተሰሩ የዲፕሎማሲ ስራዎች ስኬታማ እንደነበሩ አስታውቀዋል።
በአፍሪካና አውሮፓ በአካል፣ በበይነ መረብ፣ በስልክና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የህግ ማስከበሩን ዘመቻ አላማ ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የማስረዳት ስራ መከናወኑን ያመለከቱት ቃል አቀባዩ፣ በተለይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በጎረቤትና በአውሮፓ አገሮች ባደረጉት ጉብኝት ውጤታማ ነበር ብለዋል።
በዲፕሎማሲ ስራው ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል በፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የመጡ ለውጦችን ለዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ማስረዳት መቻሉን ጠቁመው ፣ የህወሓት ጁንታው አመራሮች ለውጡን መጻረራቸውንና ወደ ለውጡ እንዲመለስ የፌዴራል መንግስት የሰጣቸውን ሰፊ እድል ማሳየት መቻሉን ገልጸዋል።
የጁንታው አባላት የተሠጣቸውን እድል ከመጠቀም ይልቅ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በገንዘብና በአደረጃጀት የሽብር ስራዎችን ሲደግፉ እንደነበር ማስረዳት መቻሉን ጠቁመው ፣ ህገ ወጥ ቡድኑ በሰሜን እዝ ላይ በፈጸመው ጥቃት ህግ ለማስከበር የተወሰደው እርምጃ የውስጥ ጉዳይ መሆኑን በማስረዳት ውጤታማ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን አብራርተዋል።
ህግ የማስከበር ተግባሩ ንጹሃን ዜጎችን ሳይጎዳ መጠናቀቁን ከሩሲያ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይና ሌሎች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር በስልክ ውይይቶች መደረጋቸውን አንስተዋል። በውይይቱም ድርድር ማድረግን በተመለከተ ህጋዊ ከሆነው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር እየተደረገ መሆኑንና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የማስረዳት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ወደ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ ከአገሪቱ መንግስት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም