
አስመረት ብስራት
የተለያዩ ተስፋ የሚሰንቁበት፤ ነገን በብሩህ መንፈስ የሚመለከቱበት፤ ሁሉንም ነገር ማየት መሞከር በሚያስደስትበት የእድሜ ክልል ላይ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው። በዘወዲቱ ሆስፒታል የማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ በሚሰጥበት ክፍል ውስጥ ከኤች አይቪ ቫይረስ ጋር ግብ ግብ መገጠም ግድ ሆኖባቸዋል።
ገሚሱ እድሜያቸው ለአካለ መጠን ሳይደርሱ የጀመሩት ግንኙነት ለዚህ ቫይረስ ሰለባ የዳረጋቸው፣ ገሚሱ ደግሞ ከወላጆቻቸው የተላለፈባቸው ናቸው። እነዚህ ህፃናትና ወጣቶች አፍላነታቸው በእድሜ ልክ በሽታ መጠቃታቸው እጅግ ልብ የሚነካ ነው።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከፌዴራል ኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ ጽህፈት ቤትና ሌሎች አጋር ድርጅቶች የ2013 ዓ.ም የዓለም ኤድስ ቀን አከባበር አካል የነበረውን የሆስፒታሉ ጉብኝት ላይ የተመለከትናቸው ህፃናትና ወጣቶች ምንም ያህል በሽታውን ተቀብለውት በጥንካሬ ቢኖሩም የበሽታው ስርጭት ግን ምን ያህል አስከፊ እንደነበር ለመመልከት ያስቻለ ነው።
በአዲስ አበባ የስርጭት መጠኑ ከሶስት በመቶ በላይ መሆኑን በፕሮግራሙ ላይ አግኝተን ያናገርናቸው በዘውዲቱ ሆስፒታል የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር አስቴር ሸዋአማረ፣ ዛሬም በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ከተያዙ መካከል ሴቶችና አፍላ ወጣቶች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ ብለዋል።
በከተማዋ ኤች አይቪ በደማቸው የሚገኙ ግለሰቦች 109 ሺ በላይ መሆናቸውን ያስታወሱት ዶክተሯ፣ ከእነዚህ መካከል እድሜያቸው ከ 15-24 የሚሆን ወጣቶች ከፍተኛ ቁጥር መያዛቸውን ጥናቶች እንደሚያሳዩ ተናግረዋል። በሀገራችን 76 በመቶ የሚሆኑ ወጣት ሴቶች ስለ ኤች አይ ቪ እውቀት የሌላቸው መሆኑን ነው ያስረዱት።
በዝግጅቱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ እንደሚሉት አዲስ አበባ ከጋምቤላ ቀጥሎ በከፍተኛ ሁኔታ የኤች አይቪ ስርጭት የሚታይባት ከተማ ናት። በጋምቤላ የኤች አይቪ የስርጭት መጠን ወደ አምስት በመቶ የሚጠጋ መሆኑን አስታውሰው፣ አንዳንድ የሀገሪቱ ከተሞች ላይም የስርጭት መጠኑ ከፍ ማለቱን ጠቅሰዋል።
ዶክተር ደረጀ እንደሚሉት በከተማዋ በአፍላ ወጣቶች ያለው የኤች አይቪ የስርጭት መጠን ከፍ ማለት ምክንያት መዘናጋት ነው። የተለያዩ አካላት ኤች አይቪ ላይ የሚሰጡት የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች መቀዛቀዛቸው በአዲሱ ትውልድ የስርጭት ምጣኔው ከፍ እንዲል ምክንያት መሆኑን ነው የሚያስረዱት።
የኤችአይቪ መከላከያና መቆጣጠያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር ፅጌረዳ ክፍሌ እንደሚሉት በከተማዋ ያለውን የኤች አይቪ የስርጭት መጠን አሳሳቢ የሚያደርገው በአፍላ ወጣቶች መካከል ያለው የስርጭት መጠን ከፍተኛ መሆኑ ነው። ለዚህም ኃላፊዋ እንደ ምክንያትነት የጠቀሱት ከስራ አጥነት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ነው።
“ስራ አጥነት ለኤች አይቪ የሚያጋልጡ ስፍራዎች እንዲውሉ ገፊ ምክንያት ነው” የሚሉት ዶክተሯ በከተማዋ ያሉ የኢንዱስትሪና የሆቴሎች መስፋፋት ሌላው እንደምክንያት ያነሱት ነው። በከተማዋ የመጤ ባህሎች መስፋፋትም እንደሚታይ የገለጹት ሲስተር ብርዛፍ የራቁት ዳንስ ቤት፣ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት፣ ጫት፣ ሺሻና ቡና ቤቶች መበራከታቸው ለኤች አይቪ መስፋፋት አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ለመሰማራት ከተለያዩ ከተሞች የሚመጡ ወጣቶች ቁጥር ከፍ ማለትም የስርጭቱ መጠን ከፍ እንዲል እንዳደረገው አብራርተዋል።
ጽህፈት ቤታቸው በከተማዋ ለኤች አይቪ ተጋላጭ ብሎ የለያቸውን የከተማዋ የህብረተሰብ ክፍሎችን ሲዘረዝሩ በትምህርት ቤትም ሆነ ውጭ ያሉ ወጣቶች፣ የቀን ሰራተኞች፣ የከባድ መኪና የረዥም ርቀት አሽከርካሪዎች፣ በወህኒ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች፣ በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች፣ እና በቅርቡ በተደረጉ ጥናቶች እንደታየው ደግሞ ባሎቻቸውን በፈቱ ሴቶች የስርጭት ምጣኔው ከፍ ያለ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶቹ በብዛት በሚገኙባቸው አካባቢዎች የትምህርት ስራውን ሊያውኩና ወጣቶቹን ለኤች አይቪ ሊያጋልጡ የሚችሉ መዝናኛዎችን ከትምህርት ቤት መራቅ አለባቸው የሚል አቋም ይዞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለመስራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት እኤአ በ2030 አዲስ በቫይረሱ የሚያዝ ግለሰብ መኖር የለበትም የሚል ራዕይ አስቀምጧል። በኢትዮጵያ የኤች አይቪ የስርጭት መጠኑ 0.9 በመቶ ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም