
አንተነህ ቸሬ
አዲስ አበባ፡- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያና ምላሽ የህ.ወ.ሓ.ት ጁንታ በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በአገሪቱ ላይ ሲያደርስ የነበረውን አሉታዊ ጫና ያሳየ እንደነበር የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሰጡት ማብራሪያ ለውጥ መጣ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን አገራዊ ሁኔታ የሚያስረዳ በጎ ገለፃ ነው። ማብራሪያው አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስራቸውን በነፃነት እንዳይሰሩና በአጠቃላይ የአገሪቱ ቁመና ላይ ሲያደርስ የነበረውን ጫና አመላካች ነው።
እንደርሳቸው ገለፃ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፃ የአገር መከላከያ ሰራዊት የደረሰበት አሳዛኝ ጥቃት እንዲሁም ሰራዊቱ የአገሪቱን ሕልውና ለማስጠበቅ የከፈለው መስዋዕትነት የተብራራበት ነው። ከዚህ በተጨማሪም በመከላከያውና በደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ ስለነበረው የብሔር የበላይነት እንዲሁም እርሳቸው ስለነበረባቸው ጫና ማብራሪያ መስጠታቸው በጉዳዩ ላይ ብዥታ ለነበረባቸው አካላት የጠራ መረጃ ለመስጠት አስተዋፅኦ ነበረው።
‹‹ብዙዎቻችን የኃይል አሰላለፍና የሁኔታ ትንተና ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማብራራት እንደሞከሩት በትሕነግ ላይ ቀደም ብሎ እርምጃ መውሰድ ይቻል ነበር ወይንስ አይቻልም የሚለው ጉዳይ በእኛም በኩል አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል›› ያሉት አቶ ጣሒር፣ ቡድኑ አሁን የደረሰበት ውርደት አገራዊ እፎይታ ሊሰጥ የሚችል እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው እንዳመለከቱ ተናግረዋል። ስለመጪው የአገሪቱ ሁኔታ ተስፋ የታየበት ገለፃ እንደነበርም አስረድተዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ትሕነግ በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ጥያቄ ማቅረባቸውን አድንቀው፤ ጥያቄው ተጠናክሮ ቀጥሎ ቡድኑ በአሸባሪነት መፈረጅ እንዳለበትም አሳስበዋል። ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ ትህነግ የመሰረታቸውን ተቋማዊ የጭቆና መዋቅሮችንና ሰነዶችን እንዲሁም በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አሰራሮችን በማስተካከልና ትርክቱን በመቀየር ቀጣዩን ጊዜ የተሻለ ማድረግ እንደሚቻልም አቶ ጣሂር ተናግረዋል።
የኦሮሞ ነፃነት ንቅናቄ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ሊቀ መንበር አቶ ደረጀ በቀለ በበኩላቸው፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ፈተናዎችን እንዳለፉ የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል። ማብራሪያው ህ.ወ.ሓ.ት የማፍያ ቡድን እንጂ አገር የሚያስተዳድር አካል እንዳልሆነም ያሳየ እንደነበር ጠቁመዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የህ.ወ.ሓ.ት ጁንታ በአገሪቱ ላይም ሆነ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ያደርሰው የነበረው ጫና ከፍተኛ እንደነበር ለማየት ያስቻለ ፣ ቡድኑ አገሪቱ ለሱ ብቻ እንደተሰጠች አድርጎ የሚያስብ እንደሆነ ያሳየ ነው ብለዋል።
‹‹ንግግራቸው የወደፊቷ ኢትዮጵያ የሁላችንም መሆኗን፣ ሕዝብንና አገርን የሚስጨንቅ ቡድን ቦታ እንደማይኖረውና ስልጣን ሕዝብን ማገልገያ ሊሆን እንደሚገባ ያመላከተ ቁም ነገር አዘል ንግግር ነው›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም