
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ አበባ፦ የትግራይ ህዝብ የህወሓት ወንጀለኛ ጁንታ በስሙ እየነገደበት እንደሆነ ገብቶት አንቅሮ የተፋው የዛሬ ሶስት ዓመት በፊት መሆኑን የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስታወቀ፡፡
የፓርቲው ዋና ጸሃፊ አቶ ጊደና መድህን በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ የትግራይ ህዝብ በተለይ ከለውጡ ሶስትና አራት ዓመት በፊት ጀምሮ የጁንታውን አመራሮች አንቅሮ ተፍቷቸዋል፡፡ በስሙ እየተከናወኑ ስላሉ ነገሮችም ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ይህንን ሁኔታ ግን የሚዘግብ የመገናኛ ብዙሃን በክልሉ አለመኖሩ ሁኔታው እንዳይታወቅ አድርጎታል፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት እንኳን በባስኔቲ፣ አብያዲ፣ እግረአሪባ፣ ዋጀራት፣ ራያና ሽሬ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ነበር፡፡ ባስኔቲ ላይ ህብረተሰቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመረጡ ሰዎችን አይወክሉንም በማለት አልተቀበለም ያሉት አቶ ጊደና፣ ይህንን የህዝቡን ተቃውሞ የሚዘግብ መገናኛ ብዙሃን ባለመኖሩ አደባባይ መውጣጥ አልቻለም ብለዋል።
በተመሳሳይ እግረሀሪባ (በመቀሌ አየር ማረፊያ አካባቢ) በጉልበት መሬታቸው የተቀማባቸው ነዋሪዎች ፖሊስን አባረው የራሳቸውን አስተዳደር እስከ መመስረት ደርሰው ነበር፤ በዚህ ሂደትም ብዙዎች መታሰራቸውንና መገረፋቸውን አመልክተዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም ወንጀለኛው ጁንታ ከአዲስ አበባ ተገፍትሮ መቀሌ ከመሸገ በኋላ ግን ህዝቡን አማራ እንዲሁም ሻዕቢያ መጣብህ፤ የፌዴራል መንግስቱ ጨፍላቂ ነው ፤በማለት ከፍተኛ የሆነ ፕሮፖጋንዳ ስራ ሰርቷል ያሉት አቶ ጊደና፣ ይህ ደግሞ ህብረተሰቡ በፌዴራል መንግስቱ ላይ እምነት እንዲያጣ እንዳደረገውም አመልክተዋል፡፡ በቀጣይም የፌዴራል መንግስት ይህንን የሚያጠራ ስራን መስራት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ነጻ በወጡት ነገር ግን የማንነት ጥያቄ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ መንግስት ከሚያስበው ጋር የማይሄዱ ስራዎች እየተሰሩ በመሆኑ ይህ ጁንታውን እስከ መጨረሻው ለመቅበር በምናደርገው ትግል ላይ አሉታዊ ሚና ስለሚኖረው በከፍተኛ ትኩረትና ጥንቃቄ ሊሰራ የሚገባው ነው፡፡
ከጁንታው እኩይ ተግባር አንጻር የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ሊመሰገን ይገባል፡፡ ምክንያቱም በአሰቃቂ ሁኔታ መከላከያውን ሲጨፈጭፉ ማይካድራ ላይ እንደዛ ዜጎችን ሲያርዱና በጅምላ መቃብር ሲቀብሩ የነበረው አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በሌላው ክልል የሚኖር የትግራይ ተወላጅ ላይ ሌላው ኢትዮጵያዊ እንዲነሳ ለማድረግ ነበር፤ ህዝቡ ግን ሩህሩህና ቀና ልብ ያለው በመሆኑ እነሱ ባሰቡት መንገድ አልሄደላቸውም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ከድህነት ወለል በታች ከሚኖሩ ዜጎች 27 ከመቶውን በመያዝ የትግራይ ህዝብ በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል ያሉት አቶ ጊዲና፤ የጁንታው ልጆች ግን በጣም ውድ በሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩበት፤ እና ራሳቸውም እጅግ የተቀናጣ ኑሮ የሚኖሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
እንደ አቶ ጊዲና ገለጻ፤ የኢፈርት ድርጅቶች ትልልቅ ኩባንያዎች ናቸው፤ ሲቋቋሙም በጦርነቱ ለተጎዱ የሰማዕታት ቤተሰቦችና የጦርነቱ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም በጦርነት የወደመን የትግራይ ክልል መልሶ ለማቋቋም በሚል ቅዱስ ሃሳብ ቢሆንም ፤ በሂደት ግን እነዚህ የጁንታ አባላት ኩባንያዎቹን በስማቸው ማዞራቸውን ፤ ከዛም አለፍ ሲል ከ20 ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ የውጭ ኦዲተር ወደነዚህ ኩባንያዎች ድርሽ እንዳይል መደረጉን አስታውቀዋል ።
ስለ ኢፈርት ትልልቅ ኩባንያዎች የሚታወቅ ነገር የለም፤ ራሳቸው ያቦኩታል፣ ይጋግሩታል፣ ይበሉታል ያሉት ዋና ጸሀፊው ፣ ከነዚህ ኩባንያዎች የትግራይ ህዝብ ምንም ያገኘው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። በጣም የሚያስገርመው ነገር የመሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ አቅራቢያ ያሉ ነዋሪዎች አዋራው ለመተንፈሻ አካላት ህመም አጋለጠን እባካችሁ መፍትሔ ስጡን ብለው ቢጠይቁ እንኳን ምላሽ አለማግኘታቸውን አመልክተዋል ።
መንግስት ለትግራይ ህዝብ ወገንተኛና ጠቃሚ መሆኑን፤ እንዲሁም ወጣቱ ላይ የተዘራውን አላስፈላጊ አረም በአጭር ጊዜ መንቀልና ወደ መስመር ማምጣት ከቻለ በእርግጠኝነት ህዝቡ ሙሉ በሙሉ ይህንን መንግስት ይደግፋል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ገለጻቸው በክልሉ ህጋዊ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ትግራይን በጋራ እንዲያስተዳድሩ ግልጽ የሆነ መልዕክት አስተላልፈዋል ያሉት አቶ ጊደና ፤ በመሆኑም አሁን እየተመሰረተ ያለው አስተዳደር በተቻለ መጠን አካታች ሊሆን እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ ስራ አስፈጻሚ ሽሬ ከተማ ተገኝተው ህዝቡን አወያይተው አዲስ አስተዳደር እንዲመረጥ ማድረጋቸው በጣም ጥሩ አካሄድ መሆኑን የገለጹት አቶ ጊደና፣ ከዚህ በኋላም ቢሆን በተቻለ መጠን ከጁንታው ጋር ወግነው ህዝቡን ያልበደሉ፣ ቅን ልቦና ያላቸውና ህዝብን ለማስተዳደር የሚፈልጉ ሰዎች ወደ ስልጣን እንዲመጡ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል፡፡
“የትግራይ ህዝብ ሊያውቅ የሚገባው የጁንታው እድሜ ማለቁን ነው፤ ስለዚህ ነጻ እየወጣ መሆኑን ተገንዝቦ እራሱን ወደማስተዳደር፣ ወደ ልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሊገባ ይገባል “ ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2013 ዓ.ም