አንድ ራቅ ያለ ጉዞ የሚወድ ነጋዴ ነበር። እናም በመንገዱ ሁሉ የሚገጥመው ያስገርመዋል። ይህ የመጣው ደግሞ ሩህሩህ በመሆኑ የተነሳ ነው። በተለይ የሚያሳዝን ነገር ሲመለከት ያለቅሳል። የተመለከተው ሰውም «ሁሉም ያልፋል አትዘን» ይሉታል። ከዕለታት በአንድ ቀን በጉዞው እንዲህ ገጠመው። በአንድ ስፍራ በኩል እያለፈ ነበር ድርጊቱ ሲከወን ያየው። አንድ ገበሬ፣ አንድ ሰውና አንድ በሬ አቆራኝቶ ያርሳል። ሰውየውና በሬው በአንድ ቀንበር ስር ሆነው እያረሱ ገበሬው ያለ ርህራሄ ሁለቱንም በጅራፍ ይገርፋቸዋል።
በዚህ ጊዜ ነጋዴው ባየው ነገር በጣም ስላዘነ አለቀሰ። በቀንበሩ ስር ያለው ሰውዬ ግን ቀና ብሎ አየውና «ምን እያደረክ ነው? ለእኔ ማልቀስ አይገባህም። መንገድህንም ቀጥል እዚህ አትቁም» አለው። ነገር ግን ነጋዴው አሁንም እያለቀሰ «ይህ የጭካኔ ተግባር ነው። እንዴት የሰው ልጅ እንደ በሬ ቀንበር ይጎትታል?» አለ። ሰውየውም «ግድ የለም ሁሉም ነገር ያልፋል፣ የእኔም ስቃይ እንዲሁ ያልፋል» አለው። ነጋዴውም ትንሽ አልቅሶ መንገዱን ቀጠለ።
ዓመት ቆይቶ በዚያው ስፍራ ሲያልፍ የሆነውን ነገር አስታወሰና ሰውዬው እንዴት እንደሆነ የአካባቢውን ነዋሪዎች ጠየቀ። እነርሱም «ፈጣሪ ወደታች ሲመለከት የሰውየውን ስቃይና እንባ አይቶ አሁን ንጉስ አድርጎታል። ከዚህ በኋላ ስቃዩ አብቅቶለት፤ አገረ ገዢያችንም ሆኗል» አሉት። ነጋዴውም በሰማው ነገር በጣም ተደስቶ ያለበትን ቦታ ጠያይቆ ቤተ መንግስቱ ደረሰ። ወደ ውስጥ ዘልቆም ሰውየው እውነትም ንጉስ ሆኖ ሲያየው ደስታው ከመጠን አለፈ። ንጉሱም ነጋዴው ሲደሰት አይቶት «አንተ ሰው ምን እያደረክ ነው? ስለምንስ ነው የምትደሰተው?» ብሎ ጠየቀው።
ነጋዴውም «አምና በዚህ ስፍራ እያለፍኩ ሳለ አንድ ምስኪን ሰው ከበሬ ጋር ተጠምዶ ሲያርስ በማየቴ እጅግ በጣም አዝኜ ነበር። ስመለስ ደግሞ ሁሉም አልፎ ንጉስ ሆኖ አገኘሁት» አለው። ንጉሱም አስታወሰውና «ልጄ ሆይ፣ በቀንበሩ ስር የነበረውን ምስኪን ሰው በማስታወስህ ፈጣሪ ይባርክህ። ነገር ግን ባለፈው እንዳልኩህ ነገሮች ይለወጣሉና የእኔም ሕይወት እነሆ ተቀይሮ ንጉስ ሆኛለሁ። አሁንም ሁሉም ነገር ያልፋልና፣ ሁሉም ነገር ይለወጣልና ይህም ስለሚያልፍ ብዙ አትደነቅ» ብሎ በሰላም ሸኘው።
ዓመት ጠብቆ ሲመጣም እንዳለው ነገሮች ተለውጠው ቆዩት። ንጉሱ አርፏል። ስለዚህም መቃብሩ ጋር ሄዶ ሃዘኑን ተወጣ። በሐውልቱ ላይ ጎላ ጎላ ባሉ ፊደላት «ሁሉም ነገር ያልፋልና ይህም እንደዚሁ» የሚል መልዕክትን አንብቦ ነፍስ ይማር በማለት ጉዞውን ቀጠለ። በዓመቱ በዚያው ስፍራ ሲያልፍ መቃብሩን ለመጎብኘት አሰበና ወደ ቦታው ተጓዘ። ግን ሰውዬው እንዳለው ሁሉም አልፏል። በከተማዋ አዲስ ፕላን መሰረት ስፍራው ፎቆች ተገንብተውበታል።
የዓለም ነገር እንዲህ ተለዋዋጭ ነው፡፡ ዛሬ በማግኘት የታደለ ነገ በማጣት ይፈተናል፡፡ ዛሬ በደስታ የፈነደቀ ነገ በሃዘን ይቆራመዳል፡፡ ዛሬ በሀገሩ በነጻነት የሚመላለስ ነገ በስደት ሀገር አንገቱን ሊደፋ ይችላል፡፡ ዋናው ማጠንጠኛችንም በስተመጨረሻ የተጠቀሰው የስደት ጉዳይ ነውና ሰሞኑን የጸደቀው አዋጅ በዚህ ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ዛሬ አንጻራዊ መረጋጋት በሰፈነባት አገራችን ለስደተኞች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር መታደላችንን እንደ ጸጋ እንቁጠረው እንላለን፡፡
ዛሬ ላይ በሌሎች አገራት እንደሚታየው ሁሉም ያልፋል ተዘንግቶ ስደተኞችን ላለመቀበል በር መዝጋት ተጀምሯል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት ደግሞ በተቃራኒው ከመቀበል አልፈው ያለንን እንቋደስ እያሉ ይገኛሉ። አብሮ መኖር፣ አብሮ መስራት ለኢትዮጵያውያን ልምድ ነውና እድገት የሚመጣው ያለን አብሮ በመቋደስ እንደሆነ በማሰብ ስደተኞች በአገሪቱ የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው የሚስያችልና ሌሎችም ምቹ ሁኔታዎችን የሚያሳልጥ አዋጅ መጽደቁ ተገቢ ነው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከ900 ሺ በላይ ስደተኞችን ተቀብላ ታስተናግዳለች፡፡ እነዚህ የዓለም ዜጎች የሚገባቸውን ክብር እንዲጎናጸፉ የተሄደበት መንገድ ይበል የሚያሰኝ ነው ፡፡ ሰው በሰውነቱ መከበር አለበት፤ ለእድገት መሰረት በሆነው ስራ ዘመኑን ማሳለፍ ይገባዋል፤ ይህ እንደ ሰው የሚለገሰው መብቱ ነው ከሚል መንፈስ የጸደቀው አዋጅ አለምን ለሰው ልጅ ምቹ ለማድረግና ለውጥን ለማፋጠን ስለሚያግዝ ተገቢነቱ አጠያያቂ አይደለም፡፡
ለስደተኞች አመቺ ህግ ማውጣቱ አገሪቱን በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ ያደርጋታል፡፡ ስደተኞች የአገሪቷን ህግ አክብረው ሲሰሩ አገር ትለማለች። ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ ያላትን መልካም ልምድ ዓለም የበለጠ እንዲረዳው ያደርጋል። ከጎረቤት አገሮች ጋር ያለውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ያጠናክራል፣ ሰፊ የስራ እድል ለመፍጠርና በኢትዮጵያ የስደተኞች አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ለማሻሻል እድል ይሰጣልና ተግባራዊነቱ ላይ መስራት አለበት። ስደተኞች የጊዜ ጉዳይ ከሀገራቸው ቢያስወጣቸውም ሁሉም ነገር ያልፋልን በተግባር በማሳየት ክፉው ቀን እንዲያልፍ እንተባበር፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 19/2011