በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዘ የመጀመሪያው ሰው የተገኘው በመጋቢት ወር የመጀመሪያ ቀናት ነው። እስከ ትናንት ድረስ በተጠናቀረ መረጃ በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 19 ሺ 289 ደርሷል። የ336 ሰዎች ህይወትም በቫይረሱ ምክንያት ተቀጥፏል። 7 ሺ 791 ደግሞ ከቫይረሱ ማገገም ችለዋል። ይህም በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎች ማገገም የቻሉት 41 በመቶ ይህሉ ብቻ መሆናቸውን ያሳያል። እስካሁንም 437 ሺ 319 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ተደርጎላቸዋል። በአንድ ቀን ናሙናዎችን ወስዶ የመመርመር አቅምም 10 ሺን ተሻግሯል። ሆኖም ኢትዮጵያ ካላት አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር አንጻር እየተደረገ ያለው ምርመራ አነስተኛ የሚባል ነው። ከአንድ ሚሊዮን ሰዎች ውስጥ 3 ሺ 600 ያህሉን ነው መመርመር የተቻለው። የቫይረሱ የስርጭት መጠንም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመር ላይ ይገኛል። በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹን አንድ ሺ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለማግኘት 79 ቀናት ተቆጥረው ነበር። በሁለተኛ ዙር አንድ ሺ የቫይረሱ ተጠቂዎችን ለመመዝገብ ደግሞ ዘጠኝ ቀናት ተቆጥረው ነበር። አሁን ባለንበት ወቅት ግን አንድ ሺ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የሚያመለክት መረጃ ለማግኘት ከሁለት ቀን ያነሰ ጊዜ በቂ ሆኗል።
በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በጾታ አይን ሲታይ 61 በመቶ በቫይረሱ የተያዙት ወንዶች ሲሆኑ፤ ሴቶች 39 በመቶ ናቸው። የቫይረሱ ስርጭት በዕድሜ አንጻር ሲታይ በአገር አቀፍ ደረጃ አማካኝ የቫይረሱ ተጠቂዎች ዕድሜ 31 ነው። በቫይረሱ ከተያዙት ሰዎችም 89 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በታች ነው። ከዚህ ውስጥም ከ15 እስከ 49 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙት 76 በመቶ ይደርሳሉ። ይህም ቀደም ሲል ሲነገር ከነበረው በተቃራኒ ወጣቱ በከፍተኛ ደረጃ በቫይረሱ እየተጠቃ መሆኑን ያመለክታል። በህመም ምልክት ረገድም 92 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ናሙና ተወስዶ በላብራቶሪ ምርመራ እስኪረጋገጥ ድረስ ምንም አይነት የህመም ምልክት ያልታየባቸው ናቸው። ምልክቶቹን ያሳዩት ስምት በመቶ ያህሉ ብቻ ናቸው። አንድ በመቶ ያህሉ ደግሞ በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የህክምና እርዳታ ሲደረግላቸው ነበር።
እስካሁን ከተመዘገቡት ሞቶች ሁለት ሶስተኛ የሚሆኑት በአስክሬን ምርመራ ነው የኮቪድ 19 ቫይረስ በሰውነታቸው ውስጥ ይገኝ እንደነበረ የተረጋገጠው። በጤና ተቋማት ውስጥ ህይወታቸው ያለፈው አንድ ሶስተኛ ያህሉ ብቻ ናቸው። ከሟቾቹም 75 በመቶ ያህሉ የአዲስ አበባ ከተማ ኗሪዎች ናቸው። በ89 አስክሬኖች ላይ በተደረገ ምርመራም ከ55 በመቶ በላይ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች መሆናቸው ተረጋግጧል። በመጀመሪያዎቹ 36 ሞቶች ላይ በተደረገ ምርመራ ደግሞ 94 በመቶ ሟቾች የካንሰር፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ የደም ግፊትና የስኳር ህመምን ጨምሮ የተለያዩ ተጓዳኝ ህመሞች የነበሩባቸው ሆነው ተገኝተዋል። ቫይረሱ አገር ውስጥ በገባበት ሰሞን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር የቀጥታ ንክኪ የነበራቸውና የውጭ አገር የጉዞ ታሪክ የነበራቸው ናቸው። አሁን ግን ቫይረሱ ከሚገኝባቸው ሰዎች 69 በመቶ የሚሆኑት የጉዞ ታሪክም ሆነ የታወቀ ንክኪ የሌላቸው ሰዎች ሆነዋል። ይህም ቫይረሱ በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ያሳያል።
አዲስ ዘመን የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ከጤና ሚኒስትር ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ጋር ቆይታ አድርጓል እነሆ።
አዲስ ዘመን ፡- ጤና ሚኒስቴር ኮሮና ቫይረስ አገር ውስጥ ከመግባቱ በፊትና በኋላ እንዴት ያሉ ተግባራትን አከናውኗል ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- ቫይረሱ ከመግባቱ በፊትና ከገባም በኋላ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። ቫይረሱን ለመከታተልና ለመቆጣጠር በዋናነት ትኩረት ሰጥተን የሰራነው የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ነው። ስለቫይረሱ ምንነት፣ መተላለፊያ መንገዶቹና መከላከያ መንገዶቹ ምን እንደሆኑ ህብረተሰቡን ለማስተማር የጤና ባለሙያዎችን፣ ሚዲያ ተቋማትን፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የሃይማኖት አባቶችንና የመንግስት አካላትን በማሳተፍ ብዙ ጥረት ተደርጓል። ሰዉ ምን ያህል የባህሪ ለውጥ አምጥቷል የሚለው ራሱን የቻለ ጥያቄ ሆኖ ምላሽ ቢፈልግም፣ በተቻለ መጠን ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ ሰዉ ራሱን እንዲጠብቅና መከላከል እንዲችል ምንነቱን ማሳወቅ ነበር፤ በዚህ ላይ ብዙ ስራዎችን ሰርተናል። ብዙ ውጤትም ተገኝቶበታል። ለምሳሌ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መከላከያ ጭንብሎችን እንዲጠቀሙ ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመሆን የህግ አስገዳጅነቱ ተግባራዊ ተደርጓል። በተለይ ከተሞች አካባቢ ሰዎች የአፍና አፍንጫ መከላከያ ጭንብል እያደረጉ ይገኛሉ። ነገር ግን አጠቃቀሙ ላይ አሁንም ችግሮች ይስተዋላሉ። በትክክለኛው መጠቀም አለብን። ማስክ ካደረግን ከላይ ሙሉ አፍንጫችንና ከታችም እስከታች ድረስ አፋችን መሸፈን አለበት።
ሌላው እንግዲህ በዋናነት ተቋማትን የማዘጋጀት ስራ ነው የተሰራው። የለይቶ ማቆያ ማዕከላት ተቋቁመዋል። የማከሚያ ማዕከላትን አስፋፍተናል። በአዲስ አበባ ላይ ነበር የጀመርነው በኋላ ላይ ሁሉም ክልሎችና በቀሪው የከተማ አስተዳደር ላይ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። ሌላው የምርመራ ማዕከል ማቋቋም ነው። መጀመሪያ ላይ እንደሚታወሰው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድም የምርመራ ማዕከል አልነበረም። ናሙና ተወስዶ ወደ ደቡብ አፍሪካ ነበር የሚላከው። በኋላ ግን ይህንን የምርመራ ማዕከል እዚሁ አገር ውስጥ የመፍጠር ስራ አንድ ተብሎ አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የምርመራ ቤተ ሙከራ ማዕከል ውስጥ ተጀመረ። ይሄም በቂ ስላልሆነ የማስፋፋት ስራዎችን ሰራን። አዲስ አበባ ላይ አስፋፋን ከዚያ በክልሎችም በተመሳሳይ እነዚህ ማዕከላት እንዲገነቡ ተደረጉ። አሁን ላይ በአገራችን 46 ያህል የምርመራ ማዕከላት ተከፍተው ወደ ስራ ገብተዋል። ይህም በቀን 10 ሺ ናሙናዎችን የመመርመር አቅም ፈጥሮልናል። ሰሞኑን እየወጡ ያሉት ሪፖርቶች እንደሚያመላክቱት 10 ሺ ደርሰናል። አሁን የተወሰኑ ሂደት ላይ ያሉ አሉ እነሱ ሙሉ ለሙሉ ወደ ስራ ሲገቡ በአጠቃላይ በአንድ ቀን 15 ሺ ናሙናዎችን የመመርመር አቅም ይኖረናል። የምርመራ አቅምን ከመጨመር አንጻር ከአፍሪካ አገራትም በቀዳሚነት ደረጃ ካሉ አገሮች ተርታ ተሰልፈናል። በእርግጥ ከእኛ በጣም ርቀው የሄዱ እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት አሉ ስለዚህ በቂ ነው ማለት አንችልም።
ከውስጥም ከውጭም ግብዓቶችን የማቅረብ ስራም ተሰርቷል። በተለይም ደግሞ የመከላከያ ቁሳቁሶችን የማሟላት ስራ ተከናውኗል። መጀመሪያ አካባቢ ማስክ አገር ውስጥ አይገኝም ነበር። የእጅን ንጽህና የምንጠብቅባቸው ሳኒታይዘሮች አልነበሩንም። እነዚህ የመከላከያ ቁሳቁሶች በአገር ውስጥ እንዲመረቱ የተለያዩ ባለሀብቶችን የማነጋገርና የማወያየት ስራ በመስራት እዚሁ አገር ውስጥ እንዲመረቱና ጤና ተቋማት ላይ የነበሩ እጥረቶቸችን ለመሙላትና ገበያ ላይም እንዲቀርቡ ለማድረግ ጥረቶች ተደርገዋል። ይህ አሁንም በቂ ባይሆንም ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ በልገሳ መልክ የማሰባሰብ ብዙ ስራዎች ተሰርተዋል። ይሄ ሁሉ ሆኖም ግን ኢትዮጵያ እስከ 110 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ትልቅ አገር ነችና ሁሉም ነገር በሕዝቡ ቁጥር ልክ ነው ማለት አንችልም። የሚቀሩ ነገሮች አሉ ስለዚህ ከዚህ አንጻር ብዙ ስራ ይጠበቅብናል ለማለት ነው።
አዲስ ዘመን፡- ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ለአንድ ወር የሚቆይ የምርመራ ዘመቻ ይፋ ተደርጓል። የዘመቻው ዓላማ ምንድን ነው ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- በዘመቻው በሁለት ሳምንታት ውስጥ ሁለት መቶ ሺህ ምርመራዎችን ለማድረግ አቅደናል። ዘመቻው ምርመራ ብቻ አይደለም የራሱ ዓላማ ዓለው። በዋናነት ዓላማው ንቅናቄን መፍጠር ነው። መሰላቸትና መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለን ስለሆነ ሌሎች አገሮች ላይ ምንታዘባቸው ነገሮች አሁን ወደ እኛም መጥተዋል። በየቀኑ በኮቪድ 19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም በፍጥነት ጨምሯል። ለምሳሌ ሰሞኑን በአንድ ቀን እስከ 905 ሪፖርት ተደርጓል፤ ይሄ በጣም ትልቅ ቁጥር ነው። በተለይ አዲስ አበባ ላይ በአገር ደረጃ በቫይረሱ ከሚያዙ ሰዎች 70 በመቶ ያህሉ የሚገኙ በመሆኑ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው። ምርመራዎችን በስፋት ለማካሄድ አስበን ጎን ለጎን ግን የንቅናቄ ዘመቻ ለማድረግ ታዋቂ ሰዎችን እንደገና የማንቀሳቀስ፤ ባለሙያዎችን ለዚሁ ስራ የማዘጋጀትና ዳሳሳ የሚያደርጉ ቡድኖችን የማጠናከር ስራ ይሰራል። እያንዳንዱ ወረዳ ላይ ነው ይሄ የሚተገበረው። በየወረዳው ለዚህ ዝግጁ የሚሆኑ ባለሙያዎች፣ ሰራተኞች፣ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ህብረተሰቡን የሚያስተምሩ እርምጃም የሚወስዱ ሰው ግዴታው መሆኑን አውቆ ጥንቃቄ እንዲወስድ፣ ጥንቃቄ በማያደርግ ላይ ደግሞ ህብረተሰቡ ጫና ማሳደር እንዲችል ይሄን ሁሉ ማዕከል ያደረገ ዓላማ ያለው ዘመቻ ነው። በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ይፋ የተደረገው ይህ ዘመቻ ለአንድ ወር የሚቆይ ይሆናል። በዘመቻው የሚገኘው ውጤትም ቫይረሱ በህብረተሰቡ ውስጥ ያለውን የስርጭት መጠን ለመረዳትን በቀጣይ መከተል የሚገባንን አቅጣጫ በመጠቆም ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታል።
አዲስ ዘመን ፡- ሰባ በመቶ የቫይረሱ ስርጭት በአዲስ አበባ መሆኑን አስታውቃችኋል። በችግሩ ስፋት ልክ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚያስችል ስራ እየተሰራ ነው ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- አዲስ አበባ ላይ የስርጭቱን ሁኔታ ስናይ ከክፍለ ከተማ ክፍለ ከተማ ይለያያል። ከወረዳ ወረዳም ይለያያል፤ ከቀጠና ቀጠናም ይለያያል። ለምሳሌ ልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት ላይ በአንድ ሰው ምክንያት በርካታ ሰዎች በቫይረሱ በመያዛቸው ያጋጠመን ችግር ነበረ። እነዚህ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉና መንደሯም ጎስቋላ ነበረች። የቫይረሱ ስርጭት ግን አጅግ በጣም ከፍተኛ ነበረ። ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር ሆነን በአመራር ደረጃ ውይይት ከተካሄደ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በመንደሩ የሚገኙ ሰዎች እንቅስቃሴ እዲገደብ አደረግን። ለነዚያ ወገኖች የሚያስፈልጋቸው እንዲቀርብላቸው ተደረገ። የአመራሩ ቁርጠኝነትና ከጤና ባለሙያዎች ጋር የነበረው ቅንጅት እጅግ በጣም ጥሩ ስለነበረ በአካባቢው ላይ በጣም ጥሩ የሆነ ስራ ተሰርቶ ስርጭቱን የመግታት ስራ ተሰራ። ከተገኘው ውጤት በመነሳት በሌሎች አካባቢዎች ላይ ይህንን እንዴት መተግበር እንችላለን በሚል ውይይት አደረግን ስርጭቱ በጣም በሚበዛባቸው ሌሎች ክፍለ ከተሞች ላይም ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክሯል ውጤትም ተገኝቶበታል። ነገር ግን ስርጭቱ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሱ አንጻር አዲስ አበባ ላይ እየሰራን ያለነው ስራ በቂ ነው ማለት አልችልም። አሁንም ብዙ ውይይቶች ነው እየተደረጉ ያሉት። ከሌላው አካባቢ ለየት ባለ መልኩ ምን አይነት አገሮችና ስትራቴጂ መከተል አለብን በሚል ውይይቶች በመደረግ ላይ ናቸው። አንዱ የቀየስነው ስልት በስፋት ምርመራዎችን ማድረግ ነው። ከሌሎች በተለየ መልኩ አዲስ አበባ ላይ ቁጥሩ ከፍ ይላል። አሁንም ብዙ ሰዎች ስለመረመርን ብለን አልተውንም አዲስ አበባን። እያደረግን ባለነው ዘመቻ ውስጥም አዲስ አበባ አንድ አካል ሆና ምርመራውንም ይበልጥ የማስፋት እንዲሁም መዘናጋቱንና ቸልተኝነቱንም የማረም ተግባር ማዕከል ነው።
አዲስ ዘመን፡- የመመርመሪያ ኪት እጥረት አለ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- በፊት ላይ ነበረ፤ ነገር ግን ግብዓት የማሰባሰብ ስራ በጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ በተለያዩ አካላት፣ በአጋር ድርጅቶች፣ በግዢና በልገሳ ተገኝቶ በአንድ ቀን 10 ሺ የመመርመር አቅም ላይ ደርሰናል። አሁን እንደውም አንድ ሚሊዮን የመመርመሪያ ኪት ወደ አገር ውስጥ እየገባ ነው የሚገኘው። ባለፈው በጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተገገለጸው ግማሹ እጃችን ገብቷል ግማሹ ደግሞ እየገባ ነው ያለው። ለክልሎችና ለምርመራ ማዕከላትም እየተከፋፈለ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፡- የመመርመሪያ ኪት እጥረት ከሌለ የምርመራ ውጤቶች ልምን ይዘገያሉ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- በጣም ይዘገያል የሚል መረጃ የለኝም። ነገር ግን የሚዘገይበት የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ለምሳሌ የመመርመሪያ ማዕከላትን በበቂ ሁኔታ ገንብተን እያለን የሚወሰዱ ናሙናዎች ቶሎ ወደ ማዕከላት ያለመድረሳቸው የመጓጓዣ ችግር ሊሆን ይችላል፤ ሌሎች ማነቆዎችም አሉ። እንግዲህ ናሙና የሚወሰደው ከተለያየ ቦታ ነው። ማዕከላቱ ደግሞ በተወሰኑ ቦታዎች ነው ያሉት ወደዚያ እስኪደርሱ ድረስ መንገድ ላይ ሊቆዩ ይችላሉ። ጤና ሚኒስትር እነዚህን ማነቆዎች ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ታማሚዎች ከቤታቸው በአንቡላንስ የሚወሰዱበት መንገድ ብዙ ጥያቄ ያስነሳል። ሌሊት ላይ አንቡላንስ እየጮኸ መጥቶ ነው በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የሚወስደው። ይህን ሁኔታ ካለው የግንዛቤ ችግር አንጻር እንዴት ትመለከቱታላችሁ? አንቡላንሶች ድምጽ ሳያሰሙ የቫይረሱን ተጠቂዎች ከቤታቸው መውሰድ አይችሉም ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- አሁን ባለው መመሪያ አንድ ሰው ቫይረሱ ስለተገኘበት ብቻ ወደ ጤና ማዕከላት አይሄድም። ህመም የማይታይበት ከሆነ ቤት ውስጥ ራሱን ለይቶ የሚያቆይበት አመቺ ሁኔታ ካለ እዛው እንዲቆይም ይደረጋል። የአንቡላንስ ድምጽ አካባቢውን ይረብሻል በሚል ህብረተሰቡ የሚያነሳው ቅሬታ ካለ እንደ አስተያየት ወስደን ማየት እንችላለን። ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግረን ድምጽ ሳያሰማ መጥቶ ቫይረሱ የተገኘባቸውን ሰዎች እንዲወስድ ማድረግ ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በተለያየ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች በአስክሬን ምርመራ ቫይረሱ ሲገኝባቸው በኮሮና ቫይረስ ምክንያት እንደሞቱ ተደርጎ መረጃ መያዙ ተገቢ ነው ? ለምሳሌ አዲስ አበባ ውስጥ ከህንጻ ላይ ወድቆ የሞተ ሰው እንዲሁም ከፋ ውስጥ በጥይት የተገደለ ሰው በሬሳ ምርመራ ወቅት ቫይረሱ ተገኝቶባቸው የሟቾች ቁጥር መጨመሩ ተገልጾ ነበር። እነዚህ ሰዎች ምናልባት አደጋው ባያጋጥማቸው የማገገም ዕድል አይኖራቸውምን ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- ከሁሉም አስክሬኖች ላይ ናሙና ተወስዶ ምርመራ ይደረጋል ነገር ግን ቫይረሱ ስለተገኘበት ብቻ በኮሮና ቫይረስ ነው የሞተው ማለት አንችልም። መጀመሪያ አካባቢ የተወሰኑ ቦታዎች ላይ እንደዚህ አይነት ችግሮች አጋጥመውን ነበር። አሁን ግን ማስተካከያ አድርገናል፣ የሞቱ ዋና ምክንያ ምንድን ነው የሚለው ታይቶ ነው እንጂ ዝም ብሎ ሪፖርት አይደረግም።
አዲስ ዘመን ፡- ከአስክሬኖች ላይ ናሙና ከተወሰደ በኋላ ውጤቱ ሳይታወቅ ቀብር እንዲፈጸም መደረጉ የቫይረሱ ስርጭት እንዲጨምር አያደርግም ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- እንደሚታወቀው ሰው ሲሞት አስክሬን ቤት ውስጥ ሲሆን መሰባሰብ ስለሚኖር ንኪኪዎች ይፈጠራሉ። ከዚህ ጋር በተያያዘ ነው ማንኛውም ጤና ተቋም ላይም ይሁን ውጪ ሞት ሲከሰት ናሙና ተወስዶ ወዲያው እንዲቀበር የአፈጻጸም መመሪያ ማሻሻያ የተደረገው። ልደታ ላይም ሆነ ዱከም ላይ በቅርቡ ያጋጠመው ከለቅሶ ጋር በተያያዙ ንክኪዎች የተከሰተ ተጋላጭነት ነው። በአፈጻጸም መመሪያው ላይ ማሻሻያ ሲደረግ ውሎ ሳያድር ወዲያው እንዲቀበር ነው የተደረገው እንጂ የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች አሉ። አቀባበሩ ምን ያህል ሰው መገኘት እንዳለበትና የሚገንዙ ሰዎች ምን አይነት መከላከያ መልበስ እንዳለባቸው ራሱን የቻለ ፕሮቶኮል አለው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ መደረጉን የምትከታተሉበት ምንገድ አላችሁ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- አዎ ይሄ ክትትል ይደረገል። በየቦታው አሰሳ የሚያደርግ ቡድን አለን። የጤና ተቋማት እንዲህ ያለ ሪፖርት ያደርጋሉ። ማንኛውም ሰው ቢሞት በአካባቢው ለሚገኝ የጤና ተቋም ሪፖርት ይደረጋል። ከዚያም ፕሮቶኮሉን በጠበቀ መልኩ የምርመራ ናሙና ተወስዶ የቀብር ስነ ስርዓቱ ይፈጸማል።
አዲስ ዘመን፡- በኢትዮጵያ ቫይረሱ ምን አይነት ባህሪ እንዳለው ለመረዳት ከአስክሬንና ከማህበረሰቡ በሚወሰዱ ናሙናዎች ላይ በተደራጀ መንገድ የሚደረጉ ጥናቶች አሉ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- አዎ እንደ ኢትዮጵያ በህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቱዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሚመራ ራሱን የቻለ ጥናት የሚያደርግ ቡድን ተዋቅሮ ወደ ስራ ገብቷል። ብቻውን አይደለም የሚሰራው የዩኒቨርስቲ ተቋማትን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የምርምር ተቋሟትን፣ አድቫይዘሪ ካውንስል የሚባሉ ምርምር ላይ የሚሰሩ አጥኚዎችን፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትርን እና በጉዳዩ ላይ እውቀትና የምርምር ልምድ አላቸው የሚባሉ ታዋቂ ሰዎችን ያሳተፈ ምርምር እየተከካሄደ ነው ያለው። ይህ ስራ ቫይረሱን በመከላከልና በመቆጣጠር ስራ ላይ የምንሰራው አንዱ አካል ነው። ስለዚህ የምርምር ስራ እንደ አንድ ክንፍ ተደርጎ ተወስዶ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ፡- በቅርቡ ጤና ሚኒስትር ቫይረሱ አገልግሎት ሰጪ በሆኑ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑን ጠቅሶ ተቋማቱ የሰራተኞቻቸውን ደህንነት እንዲያረጋግጡ ማሳሰቢያ ሰጥቶ ነበር። ምክረ ሀሳብ ከማቅረብ ባለፈ ችግሩ እንዲቀረፍ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር የተወሰደ እርምጃ አለ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- በመጀመሪያ ደረጃ የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው ለዚህ በሽታ ተጋላጭ የሆነው በሚል የሰራነው የመለየት ስራ አለ። ከመንግስት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ከግሉም አገልግሎት ሰጪ የሆኑ፣ በተለይ ብዙ ደንበኞች ያሏቸው ተጋላጭ ናቸው። በተለይም ፊት ለፊት ሆነው ደንበኛን የሚያስተናግዱ ህብረተሰብን አገልጋዮች በከፍተኛ ደረጃ ተጋላጭ ናቸው። የግብዓት ስርጭትም ሲደረግ ይህ ከግምት ይገባል። ይሄን ተጋላጭነት መሰረት ያደረገ አጠቃላይ የመከላከለልና የመቆጣጠር ስራ እየሰራን ነው ያለነው። ተጋላጭነቱ በሚሰፋባቸው ተቋማትና አካባቢዎች ላይ እኛም የመከላከሉንና የመቆጣጠሩን ስራ በዚያው ልክ እየሰራን ነው። አንድ ተቋም ሰራተኛውን ከቫይረሱ መከላከል ካልቻለ ለራሱም ይከስራል። ስለዚህ መጀመሪያ የራሱን ሰራተኛ ከቫይረሱ እንዲከላከል ከዚያ ደግሞ የሚመጣውን ደንበኛ ከቫይረሱ እንዲከላከል የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሰራን እንገኛለን። ሆኖም ግን መድረስ የሚገባንን ያህል ደርሰናል አንልም።
አዲስ ዘመን፡- እስካሁን ምን ያህል የጤና ባለሙያዎች ለቫይረሱ ተጋልጠዋል ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- እስካለንበት ሰዓት ድረስ በተጠናቀረ መረጃ 499 የጤና ባለሙያዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። አብዛኞቹ ያገገሙ ቢሆንም በቫይረሱ የተያዙበት ሁኔታ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን ፡- የጤና ባለሙያዎቹ ተጋላጭነት እየጨመረ የመጣው ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል የሚያስችሏቸው የመከላከያ ቁሳቁሶች አቅርቦት በበቂ ደረጃ ባለመሟላቱ እንደሆነ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። ቫይረሱ አገር ውስጥ ከገባ ስድስት ወራት ቢቆጠሩም እነዚህ መሰረታዊ የመከላከያ ቁሳቁሶች አሁንም ለጤና ባለሙያዎች በበቂ ደረጃ እየቀረቡ አይደለም። ምን ስትሰሩ ነው የከረማችሁት ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- በእርግጥ የጤና ባለሙያዎችን ተጋላጭ የሚያደርጋቸው የመከላከያ ቁሳቁስ እጥረት ብቻ አይደለም። የመከላከያ ቁሳቁስ ፒፒኢ (ፐርሰናል ፕሮቴክቲቭ ኢኩዩፒመንት) የሚባለው በጣም ወሳኝ ነው። ነገር ግን እሱ ብቻ በቂ ነው ማለት አይደለም፤ ዋናው አጠቃቀሙ ነው። የጤና ባለሙያውም ሆነ ማንኛውም ሰው በትክክል መጠቀም አለበት። በተጨማሪም በየትኛው ጊዜ ላይ ይበልጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት እያንዳንዱ የጤና ባለሙያም ሆነ ሌላው ዜጋ ማወቅ መቻል አለበት። እጥረቶቹን ለመቅረፍ ብዙ ስራዎችን ሰርተናል። በተለይም የጤና ተቋማት ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ ስርጭት እንዲከናወን ተደርጓል። ከፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ግብዓቶችን የማቅረብና የማድረስ ብዙ ስራ ተሰርቷል። እንዳልከው ግን እጥረቱ አሁንም ሙሉ ለሙሉ ተቀርፏል ማለት አንችልም። ይሄ በሂደት የሚሆን ነገር ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በጤና ተቋማት ብቻ በአንድ ቀን ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ማስክ ጥቅም ላይ ይውላል። እንግዲህ ይሄ ከፍተኛ ቁጥር ነው። በዛው ልክ ግብዓቶችንም ለመጨመር ሀገር ውስጥም እንዲመረት ከውጭም በግዢና በርዳታ እንዲገባ እያደረግን ነው ያለነው። መጀመሪያ አካባቢ ከነበረው ነገር ጋር ስናነጻጽረው አሁን በጣም ጥሩ የሚያስብል ደረጃ ላይ ነው ያለው፤ ተሻሽሏል ነገር ግን በጣም ብዙ ይቀራል። ምክንያቱም 110 ሚሊዮን ህዝብ ነው ያለን። ከዚህ ውስጥ ይበልጥ ተጋላጭ የሆነውን ህዝብ እንኳን ብንወስድ በቁጥራቸው ልክ አቅርቦት አለ ማለት አልችልም።
አዲስ ዘመን፡- ቫይረሱን ለመቆጣጠር በሚሰራው ስራ ላይ በግንባር ቀደምትነት እየተሳተፉ ካሉት የጤና ባለሙያዎች 70 በመቶ ያህል የኮንትራት ተቀጣሪዎች ናቸው። ነገር ግን በኮንትራት ተቀጥረው ለሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች የተጋላጭነት ክፍያዎች፣ የማበረታቻ አበልና ጊዜያዊ የመኖሪያ ቤት አበል እንደ ቋሚ ተቀጣሪዎች እየተሰጠን አይደለም። ምክንያቱ ምንድን ነው ? ተገቢ ነው ብለውስ ያምናሉ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ፡- ጥቅማጥቅምን በተመለከተ የሚኒስትሮች ምክር ቤት መመሪያ አወጥቷል። የተጋላጭነት ክፍያ ማንን ይመለከታል የሚለው መመሪያው ላይ በግልጽ ተቀምጧል፤ እሱን ማየት ነው። መመሪያው የሚመለከተው በሙሉ ይሰጠዋል የሚከለከልበት ምክንያት የለም። አበል የሚከፈላቸውም ማን ማን ናቸው የሚለው አንድ ሁለት ሶስት ብሎ እዚያ ላይ አስቀምጧል። መመሪያው ከሌለህ እሰጥሃለው የሚለውን አይተህ መዘገብ ነው።
አዲስ ዘመን፡- መመሪያው ቋሚ እና የኮንትራት ሰራተኛ ብሎ ለይቶ ያስቀምጣል ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ፡- እኔ መመሪያውን በዝርዝር አላየሁትም። እኔ የምመልስልህ ምንድን ነው መመሪያው ውስጥ ከተካተተ ሁሉም ያገኛል።
አዲስ ዘመን ፡- ለኮቪድ ብቻ የሚያገለግል በአጠቃላይ ምን ያህል መካኒካል ቬንቲሌተር ወይም አጋዥ የመተንፈሻ መሳሪያ አለ ? ተጨማሪ ግዢ ለመፈጸም እየተደረገ ያለ ጥረትስ አለ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ ፡- መካኒካል ቬንቲሌተር የሚባለው የመተንፈስ ችግር ያለባቸውን ሰዎች የሚያግዝ መሳሪያ ሌሎች የጤና ተቋማት ላይ አይሲዩ ውስጥ ያሉትን ሳይጨምር ለኮቪድ ብቻ እስካሁን ባለኝ መረጃ 400 ድረስ ማዘጋጀት ተችሏል። ይሄ ግን በቂ አይደልም። በሽታው ሊሰፋ ይችላል። ጽኑ ህሙማን ላይ ያሉ ሰዎች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው ያለው። ሰሞኑን እየወጣ ያለውን ሪፖርት ካየህ በጣም እየጨመረ መጥቷል። ከዚህ አንጻር የመካኒካል ቬንቲሌተር መሳሪያዎችን ቁጥር የመጨመር ስራዎች ጎን ለጎን እየሠራን ነው። በግዢና በእርዳታ በማሰባሰብ ላይ ነን። በግዢ ወደ 500 የሚሆን ሂደቱ አልቆ ግዢ ተፈጽሟል 120 አካባቢ የሚሆነው መጋዘናችን ውስጥ ገብቷል፤ የተቀረው ደግሞ በሂደት ላይ ነው ያለው። ሌላው ደግሞ ቀደም ሲል እንደተነገረው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ መሰረት የአሜሪካን መንግስት እርዳታ አድርጓል። ከአሜሪካን መንግስት የተገኘው የመካኒካል ቬንቲሌተር አንድ ሺ ነው። በአራት ምዕራፍ በመርከብ ወደ አገር ውስጥ የማጓጓዝ ስራ ተጀምሯል የመጀመሪያውን ዙር ነገ በአሜሪካን ኤምባሲ አምባሳደሩ በተገኙበት 250 ያህሉን እንረከባለን። የተቀሩት ደግሞ በቀጣይ የሚመጡ ይሆናል፣ በተለይ የሁለተኛው ዙር 250 በቅርቡ እጃችን ይገባል ብለን እናምናለን። ሌሎች መንገዶችንም እያየን ነው። መታደስ ያለባቸወን እናድሳለን አሁን 400 ላይ የደረስነውም አንድም ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በመጠገን ጭምር ነው። በጥገናው ሂደት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ እገዛ አድርጎልናል።
አዲስ ዘመን፡- በአገር ውስጥ መካኒካል ቬንቲሌተርን ጨምሮ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለማምረት እየጣሩ ላሉ የተለያዩ የፈጠራ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ድጋፍ ታደርጋላችሁ ? እስካሁንስ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ተሰርቶ ተገቢውን ሂደት አልፎ ስራ ላይ የዋለ የፈጠራ ስራ አለ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጋር ሆነው የፈጠራ ስራዎችን ያቀረቡ ብዙ ባለሙያዎች አሉ። ጥንካሬው ምንድን ነው የጎንዮሽ ጉዳቱስ ምንድን ነው በሚል እየተገመገመ ነው ያለው። የፈጠራ ባለቤትነት መብት ለመስጠት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና በሚመለከተው ማዕከል በኩል ስራዎች እየተሰሩ ነው ያሉት። እስካሁን ሁሉም በሂደት ላይ ነው ያሉት ገና ጥቅም ላይ መዋል አልጀመሩም። የራሱ የአፈጻጸም መመሪያ ተዘጋጅቶለታል። በአገር ውስጥ የሚመረት ማበረታቻ ያገኛል። ከዚህ ቀደም በጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደተነገረው እንደዚህ አይነት ክህሎት ያላቸውን ሰዎች የመሸለምና የማበረታታት ስራዎች ጎን ለጎን ይሰራሉ። ከዚህ አንጻር በቅርብ ጊዜ ውስጥ በአገር ደረጃ ይመረታሉ የሚል እምነት አለን፣ ያቀረቡም አሉ ማረጋገጫ የመስጠት ስልጣን ያለው አካል ስላለ እነሱን ብትጠይቁ መረጃ ታገኛላችሁ።
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን የዓለም የጤና ድርጅት ቫይረሱ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ ይችላል የሚል መረጃ ይፋ አድርጓል። በዚህ ረገድ እየተደረገ ያለ የተለየ ዝግጅት አለ ?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- የዓለም የጤና ድርጅት በዛ ልክ ራሳችንን እንድናዘጋጅና ጥንቃቄዎች እንዲደረጉ ነው እንጂ ሙሉ ለሙሉ ቫይረሱ ለዓመታት ከሰው ልጅ ጋር እንደሚቆይ ማረጋገጫ አልሰጠም። የቫይረሱ ባህሪ መቶ በመቶ ይሄ ነው ብሎ ለመናገር የሚቀሩ ጥናቶች አሉ። ግን ደግሞ ለማንኛውም ዝግጅት ማድረግ ጥሩ ነው። ምናልባትም ቫይረሱ ለረጅም ጊዜ ሊዘልቅ ከቻለ በሚል አቅማችንን የማሳደግ ስራ እየሰራን ነው። ህብረተሰቡ በሽታውን በደንብ እንዲገነዘበውና ቸልተኝነቱን እንዲያስወግድ ግንዛቤ ለማስጨበጥ የምንሰራቸው ስራዎች ለዘለቄታው ውጤት የሚያስገኙ ናቸው። ለምሳሌ ቫይረሱ የሚቆይ ከሆነ ሰዉ ምን አይነት የኑሮ ስልት ነው የሚያስፈልገው ? እንደምታውቀው ሰላምታ የምንለዋወጥበት መንገድ ተቀይሯል፤ ይሄ ኮሮና ያመጣው ነው። በሽታው የሚቀጥል ከሆነ ደግሞ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ሰዉ ከጎረቤቱ ጋር ብሎም ከቤተሰቡ ጋር እንዴት ነው መኖር ያለበት በሚል ራሱን የቻለ ስትራቴጂ ተቀርጾ ህብረተሰቡንና የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማሳተፍ ህብረተሰቡ ለዘለቄታው ራሱን ከቫይረሱ የሚከላከልበትን ባህል እንዲያዳብር ስራዎች መሰራት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- የባህል ህክምና አዋቂዎች ቫይረሱን ለማከም የሚያስችል መድኃኒት ለማበልጸግ በሚያደርጉት ጥረት ተሳታፊ ነበራችሁ። እንቅስቃሴው አሁን ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- ስለዚህ ጉዳይ መረጃ የምታገኘው ከኢኖቬሽንና ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ነው። እኔ ምንም አይነት መረጃ ልሰጥህ አልችልም።
አዲስ ዘመን፡- ጥያቄዎቼን ጨርሻለሁ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ተገኔ ረጋሳ፡- እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2012
የትናየት ፈሩ