ኢትዮጵያ በ‹አረንጓዴ አሻራ› ዘመቻ ችግኞችን በመትከል እያደረገች በምትገኘው ጥረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በምሳሌነት ተጠቃሽ እንድትሆን አድርጓታል። በተለይ ከዓምና ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ ትኩረት የተሰጠው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ ዘመቻ በአንድ ጀምበር ከ350 ሚሊዮን በላይ ችግኞች በመትከል በዓለም አቀፍ በጊነስ ታሪክ መዝገብ እንድትሰፍር ያደረገም ነበር። ችግኝ መትከል ብቻ ሳይሆን ለመንከባከብና ለማጽደቅም ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ፤ ባለፈው ዓመት ከተተከሉት ችግኞች ከ84 በመቶ በላይ መጽደቃቸውም ይታወሳል።
በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ማሳረፍ መርሐ ግብር አምስት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል እቅድ ተይዞል። ለዚህም አስፈላጊ የሆኑ ችግኞች ተዘጋጅተው ተከላ እየተካሄደ ይገኛል። የኮቪዲ 19 ቫይረስ የፈጠረው ተጽዕኖ እንዳለ ሆኖ፤ ገና የተከላ ጊዜ የወር ከግማሽ ዕድሜ እየቀረው 4 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ይፋ አድርጓል።
የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ሀገሪቱ ለዘመናት ትታወቅበት ከነበረው ድህነት የምትላቀቅበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ እንደምትገኝ ማሳያ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ በሰው ልጆች ጤንነት እና የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። አሁን ላይ በከርሰ ምድርና በካባቢ አየር ላይ እየታየ ያለው የተፈጥሮ ክስተት እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ለዚህ ደግሞ የተጎዱ መሬቶች መልሰው እንዲያገግሙ በማድረግ የተለያዩ ሀገር በቀል ዛፎችን መትከል ዋነኛው አማራጭ ነው።
ችግኝን መትከልና መንከባከብ የዛሬ መሠረት ለነገ የመኖር ህልውና ነው። ችግኞች ተተክለው ደን ለመሆን የአንድ ጀምበር ተግባር ሳይሆን በርካታ ዓመታትን የሚፈጅ በመሆኑ በአግባቡ መትከል ብቻ ሳይሆን መንከባከብ ጠቀሜታው እጅግ የላቀ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ። በአረንጓዴ ልማት ዙሪያ የተጀመሩ ሥራዎች በማስቀጠል ለነገ የማይባል ዘርፈ ብዙ ፋይዳ የሚሰጥ በመሆኑ ከዚህም በበለጠ ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ መሥራት ያስፈልጋል።
የችግኝ በመትከል በትኩረት በመሥራት የተመናመኑ የደኖች ወደ ነበሩበት በመመለስ ፤ ካልሆነም የተፈጥሮ ሀብትን ከጥፋት በመታደግ በረሃማነትን ለመከላከል፤ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ እንዲያገግም በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ለመቀልበስም ያስችላል ተብሎ ይታመናል።
የችግኝ ተከላው ለደን አመቺ ናቸው በተባሉ ሥፍራዎች፤ በተፋሰስ አካባቢዎች፣ በጥብቅ ደኖች፤ በወንዝ አካባቢዎች፤ በእያንዳንዱ መኖሪያ አካባቢዎች እየተካሄደ ይገኛል። በተለይ ሀገራችን የግዙፍ ፕሮጀክቶችን መሰረት የሆኑ በተፋሰስ አካባቢዎች ላይ የችግኝ ተከላው በስፋት እየተካሄደ ይገኛል። ተፋሰሶች ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያለውን የውሃ ሀብት መገኛ ሆነው በዘላቂነት እንዲቀጥሉ ለማድረግ ስነ-ምህዳሩን ከተለያዩ ጉዳቶች ለመጠበቅ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን
መሥራት እጅግ አስፈላጊ ነው። በዚህ ረገድ ምን ታቅዶ ምን እየተሠራ ነው? ለሚለውን ምላሽ እንዲሰጡን የተፋሰስ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ከሆኑት አቶ ጌታቸው ግዛው ጋር ቆይታ አድርገናል።
አቶ ጌታቸው ግዛው እንደሚገልጹት፤ አሁን ላይ በተፋሰስ ልማት በዋናነት እየተሠራ ያለው የአረንጓዴ ልማት ሥራ ነው። የአረንጓዴ ልማት ደግሞ ለተፋስስ ልማቱ መሠረት ነው። ለዚህም ምክንያቱ ተፋስሱ ሲጠበቅ የውሃ ሀብቱ በግኝትም ደረጃ አስተማማኝ ይሆናል፤ ጥራቱም ይጠበቃል፤ የድርቅንም ሆነ የጎርፍ አደጋ መቋቋም ያስችላል። ከዚያም በተጨማሪ መሠረተ ልማቶችን የሚጠበቅባቸውን አገልግሎቶች መስጠት የሚችሉት ተፋሰሱ ላይ ያለው ልማት ተጠናክሮ ሲቀጥል ነው።
እንደ ተፋሰስ ልማት ባለስልጣን በፕሮጀክት ደረጃ ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጉ ተግኞች ተተክለዋል። ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ተብለው በተለዩ ቦታዎች በጣም ተጋላጭ በሆኑ ንዑስ ተፋሰሶችና የውሃ መሠረተ ልማት ማዕከል አካባቢዎች ተከላው በዋናነት ይካሄዳል። ችግኞቹም ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ የእጽዋት አይነቶችን ያካተቱ ናቸው። በተፋሰስ ልማቱ ላይ ቀደም ብሎ በበጋ ወቅት ስነአካላዊ ሥራዎችን ይሠራሉ የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ በእነዚህ ስነአካላዊ ሥራዎች የተጠናከሩ ተፋሰሶች በክረምት ወቅት ደግሞ በሥነ ህይወታዊ ሥራዎችን ወይም በችግኝ ተከላ መርሐ ግብር የሚሸፈኑ በመሆኑ ሁለቱ አብረው ተመጋግበው እንዲሄዱ እየተደረገ ነው። ስለሆነም የችግኝ ተከላ ሥራዎች የሚካሄዱት በተጠበቁ አካባቢዎች በመሆኑም የጽድቀት መጠናቸውም የተሻለ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ተፋሰሶች ቶሎ እንዲያገግሙ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንን አመልክተዋል።
ሀገራችን አስራ ሁለት ተፋሰሶች አሏት። ከዚህ ውስጥ ሦስቱ ደረቃማ ተፋሰሶች ፣ የስምጥ ሽለቆ ሐይቅ ተፋሰስና ሌሎቹ ስምንቱ እርጥበታማ ተፋሰስ የምንላቸው፣ ወንዝ ያላቸው ተፋሰሶች ናቸው። ኑ በሀገር ደረጃ የተዘጋጀው አምስት ቢሊዮኑም ችግኝ በእነዚህ ተፋሰሶች ስፋራዎች ውስጥ የሚተከል መሆኑን ነው አቶ ጌታቸው የሚናገሩት። ።
እንደ አቶ ጌታቸው ገለጻ፤ የአረንጓዴ ልማት ሥራው የተፋሰሱን ደህንነት ከመጠበቅ አንጻር የሚኖረው ፋይዳ የማይተካ ነው። በተለይ የውሃ መሠረተ ልማቶች አካባቢዎችና በአጠቃላይ ሁሉም ተፋሰሶች ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው። በዚህ ረገድ ትኩረት ከተሰጣቸው ውስጥ የአባይ ተፋሰስ አንዱ ነው። የአባይ ተፋሰስ ሦስት ክልሎችን የኦሮሚያ፤ የአማራና የቤንሻንጉል ክልል የሚጋራ ነው። እነዚህ ሦስቱ ክልሎች በተለይ የአማራና የኦሮሚያ ክልሎች በዘንድሮ ዓመት ያፈሉት ችግኞች መጠን እጅግ ከፍተኛ ነው። የኦሮሚያ ክልል ከሦስት ቢሊዮን በላይ ችግኞችን፤ የአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን አዘጋጅቷል። ይህ ተፋሰስ እነዚህ ክልሎች የሚጋራ እንደመሆኑ መጠን ሰፊ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የሚሠራበት እንደሆነ ያብራራሉ።
ከሀገራዊ ፋይዳው፣ ካለው የፕሮጀክቱ ግዙፍነትና ከብዙ ምክንያቶች አንጻር የህዳሴ ግድብ ትልቅ
ትኩረት የተሰጠው ግድብ ነው የሚሉት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ በዚህም ዓመት አብዛኛው የተፋሰስ ልማት ሥራዎች በአረንጓዴ ልማት ትኩረት ያደረጉ ሥራዎች ናቸው። በሚቀጥሉት ዓመታትም የተፋሰሶችን ልማት በተጠናከረ መልኩ ለማስቀጠል የሚያስችሉ ሰፊ ጥናቶች የተጠኑ መሆኑን ጠቅሰዋል። ጥናቱን ማዕከል ባደረገ መልኩ የአንድ እቅድና የአንድ ሪፖርት ሰነድም እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ይናገራሉ። የአባይ ተፋሰስ ብዙ ባለድርሻ አካላት ያቀናጀ በመሆኑ፤ በአባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች በብዙ አካላት ሊሠሩ ይችላሉ። እነዚህን ሁሉ ሰብሰቦ አንድ እቅድ በማድረግ ሪፖርቱም በዚያው ልክ ሰፋ ብሎ የሚዘጋጅበት ሁኔታ ላይ እየተሠራ መሆኑን ይገልጻሉ።
ይህንን በአንድ በማቀናጀት ተፋሰስ ውስጥ ብቻ ምን ያህል ችግኞች ተፈልተዋል? ምን ያህሎቹስ ጸድቀዋል? ምን ያህል ሄክታር በችግኞች ተሸፍናል? እነዚህ የተሠሩ ሥራዎች ምን ጥቅም አስገኝተዋል? በምን ያህል መጠን የአፈር መጠረግ ሂደቱን ቀንሰውታል የሚለውን መለካትና መገምገም በሚያስችል ደረጃ ባለሙያዎችን ያሳተፈ እቅድ እየተዘጋጀ ያለንበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፤ በሚቀጥሉት ዓመታትም በዚሁ ልክ ትኩረት በመስጠት የሚሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ አቶ ጌታቸው ማብራሪያ፤ የዘንድሮ አምስት ቢሊዮን ችግኞችን ተከላ በተመለከተ በሀገር አቀፍ ደረጃ በግንቦት 28 ጀምሮ በይፋ ከተበሰረበት ዕለት ጀምሮ ሁሉም ክልሎችም እንደየነባራዊ ሁኔታዎቻቸው ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር በተጣጠመ መልኩ በስፋት ወደ ተከላ መግባታቸውን ይናገራሉ። እስከአሁን ድረስ ባለው ተከላ ከ4 ነጥብ 1 ቢሊዮን በላይ አካባቢ ችግኝ መተከል መቻሉን ጠቁመው፤ ይህንን ዓመት ከሌላው ለየት የሚያደርገው ለሀገር በቀል ችግኞች ልዩ ትኩረት መሰጠቱ አንደኛው ሲሆን ፤ ሁለተኛ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ታሳቢ ባደረገ ለዚያ ምላሽ እንዲሆን ቀደም ተብሎ በተዘጋጀው ፕሮግራም ሀገራዊ የነበረውን በአንድ ጀምበር ችግኝ የመትከል መርሐ ግብር በተራዘመ መንገድ ለማካሄድ እንዲያስችል ተደርጎ የሚካህድ መሆኑ ነው። ሁሉም ክልሎች በየራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ምቹ ቀን በመመረጥ ወስነው እንዲተክሉ በማሰብ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ በየክልሎች እንዲሆን መደረጉን ይናገራሉ። በዚህም እስከአሁን በነበረው ችግኝ የተከላ መርሐ ግብር የአማራ ክልል ፤ የትግራይ ክልል ፤ቤንሻንጉል፤ ደቡብ ክልል፤ በአሮሚያ ክልል፤ የአዲስ አበባ መስተዳድርና የሱማሌ ክልል በአንድ ጀምበር ለመትከል ሰፊ መርሐ ግብር ተካሄዷል። የተቀሩት ክልሎች በወሰኑት ቀን የሚያካሄዱ ይሆናል በማለት አብራርተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ በዚህ ወቅት እንደ ዓለም ሆነ እንደ ሀገራችን እየተፈታተነ ያለው የኮቪድ 19 ቫይረስ ነው ። እንደልብ በሚፈለገው ልክ በአንዴ በርካታ ሰዎችን በማንቀሳቀስ ተከላውን ለማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ የለም። ተከላውን በተራዘመ መርሐ ግብር እንዲሄድ በማድረግ ሰዎች ርቀታቸውን ጠብቀው ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ተከላውን እንዲያካሄዱ እየተደረገ መሆኑን ይናገራሉ። ኮቪድ 19 እንደ አምናው የህዝብ ንቅናቄን በማድረግ በርካታ
ሰዎችን በአንድ ተሸከርካሪ ይዞ ለመሄድ ፈታኝ የሆነ ተግዳሮት መሆኑንም አመልክተው፤ እንደመፍትሔ ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ ሁሉም ሰው በየቤቱ ለችግኝ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችን በመለየት፤ በቤተሰብ ደረጃም፤ ግለሰብ ደረጃ፤ አነስ ባለ የችግኝ ተከላ ቡድን በሚል ክልሎች አደራጅተው እቅዱን ለማሳካት ጥረት እየተደረገ ያለበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ።
‹‹በችግኝ ተከላ ከታዩ ተግዳሮቶች በላይ የአየር ንብረቱና ክረምቱ ቀደም ብሎ መግባቱን ምቹ ሁኔታን በመፈጠሩ ምክንያት ብዙ ቦታዎች ላይ የችግኝ ተከላ ለማካሄድ አልተቸገርንም። ይሄም የተዘጋጁ ችግኞች እንዲጸድቁ አስተዋዕኦ ይኖረዋል›› የሚል እምነት እንዳላቸው ይገልጻሉ። ማህበረሱም ለዚህ ዓይነት ዘመቻ ንቅናቄ አዲስ አይደለም የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ ባለፈው ዓመት ውጤታማ የሆነ ሥራ ተሠርቷል። ከዚያ ተሞክሮ መሠረት በማድረግ ባለፉት ዓመታት የነበሩ ተግዳሮቶች አስቀድመን በመገምገም የነበሩ ክፍተቶች ማረም የሚያስችል ዝግጅት በመደረጉ ከኮቪዲ 19 ቫይረስ ውጪ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታ አልገጠመንም ሲሉ ተናግረዋል።
እስከአሁን ባለው የተከላ ሂደት እየተተከሉ ያሉ ችግኞችም ለተከላ የደረሱ መሆናቸውንና የችግኝ እጥረት ያላጋጠመ መሆኑን የሚጠቀሱት አቶ ጌታቸው፤ የቅንጅት አሠራሩም በተሻለና ጠንከር ባለ መልኩ እየተካሄደ መሆኑን ይናገራሉ። የተቀሩት በዚህ ቀን ይጠናቀቃሉ የሚባልበት ሁኔታ ባይኖርም የክረምቱ ሁኔታ ዘግይቶ የሚደርስባቸው ቀድመሞ የሚወጣባቸው አካባቢዎች ታሳቢ በማድረግ እስከ ነሐሴ አጋማሽ ድረስ የተከላ መርሐ ግብር የሚቀጥል መሆኑን ይናገራሉ።
ችግኝ መትከል ግብ አይደለም ያሉት ኃላፊው፤ ባለፉት ዓመት በርካታ ችግኞች ተተክለዋል። ከነዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን የሚሆኑት ችግኞች መኮትኮት፤ ማረም ፤ ውሃ ማጠጣት መቻሉን ገልጸዋል። ባለፈው ዓመት በነበረው የድህረ ተከላ እንክብካቤ በመጀመሪያው ዙር የጽድቀት መጠን ወደ 84 በመቶ የጸድቀት መጠን ነበረ ሲሆን፤ በሁለተኛው ዙር የፅድቀት መጠን የግንቦት ወር መጨረሻ አካባቢ የተካሄደው ዳሰሳ ወደ 78 በመቶ የሚሆኑ ችግኞች መጽደቃቸውን ማረጋገጥ ተችሏል።
‹‹ከዚህ በፊት ከነበሩት አፈጻጸሞች ይህንን እንደ አፈጻጸም ስናየው የተሻለ ነው ብለን እንወስዳለን፤ ይህ በተከላ ወቅት ተካለውን የሚያካሄደው ማህበረሰብ ቃል በገባው መሠረት የተከላቸውን ችግኞች በማረም፣ በመኮትኮት፣ በመንከባከብና በመጠበቅ የነበረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው›› ያሉት አቶ ጌታቸው ይህም ችግኞቹ እንክብካቤውም እንዳልተለያቸው የሚያሳየው ቢሆንም ከዚህም በላይ መሥራት እስከ ጥግ በመሄድ የሚችል አቅም መኖሩን ያስገነዘበ ነው ብለዋል።
የዘንድሮ ችግኞች በስፋት እየተተከሉ ይገኛሉ የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ ህብረተሰቡ የተከለውን ችግኝ በሚገባ በመንከባከብ ላይ በስፋት መሥራት አለበት። ስለሆነም ሁሉም ማህበረሰብ በተካላ ላይ እንደተረባረበ ሁሉ ለእንክብክቤው ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2012
ወርቅነሽ ደምሰው