በመንግሥት መሥሪያ ቤት ሲያገለግሉ የነበሩ ጡረተኛ “ህዳሴው ግድብ መሸጡን ሰሙ ወይ?” ብዬ አወራኋቸው፤ “ግድቡ ተሸጠ ሲባል ቦንድ ለገዙት ዜጎች ነው።ግድቡ ሲጀመር ሦስት ጊዜ ቦንድ ገዝቻለሁ” አሉኝ።አይደለም ስላቸው “አይ እንግዴህ ዝም ብለህ አትዘባርቅ! አዛውንትና ባልቴት ለህፃናት ተረት ማውራት ያበዛሉ፤በተረት አህያ ጅብ ሊበላ ይችላል፤ ለተረት ምን ይሳነዋል? እኔ ህዳሴ ግድቡ ተሸጠ ብለው ሰዎች ሲያወሩ ሰምቻለው፤ ይሁንና ተረት ስለሆነ አልተገረምኩም።በርግጥም ግድቡ ቢሸጥ ኖሮ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎችን ዜናውን በመንገር የሚቀድማቸው አልነበረም።ተምረህ የለ እንዴ? አሉባልታ ስትከተል ቆመህ ያለአድማጭ እንዳትቀር” ብለው ገሰፁኝ፡፡
ዓባይ ከኢትዮጵያ ብቻ ከ19 ገባር ወንዞች ውሃ በማጠራቀም ወደ ሱዳን ካርቱም ካለው ነጭ አባይ ጋር የሚቀላቀል እና ወደ ግብፅ የሚፈስ ነው።ከቪክቶሪያ የሚመነጨው ነጭ ዓባይ 14 በመቶ ብቻ ሲሆን ከኢትዮጵያ የሚመነጨው ጥቁር አባይ 86 በመቶውን ድርሻ የሚይዝ ነው።ሐጋይ ኤርሊች የፃፉትን መጽሐፍ ኢትዮጵያ በ20ኛው ከፍለዘመን ላደረገችው ሽግግር ዓባይ ያለው ቦታ ግዙፍ መሆኑንና ብሔርተኝነትን ለመፍጠርም የማይተካ ሚና እንዳለው ይገልፃል፡፡
በያዝነው ክረምት የመጀመሪያው ሙሌት በሐምሌ ወር አጋማሽ የተጠናቀቀው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ለሀገራችን ዜጎችና ለኢትዮጵያውያን ወዳጆች ትልቅ የምሥራች ተስፋና ደስታ ነበር።ዓለም አቀፍ ወረርሽኝና በሽታ በሆነው ኮረና ዜጎች በአደባባይ መሰብሰብ ስለማይችሉ ደስታቸውን መግለፅ አልቻሉም እንጂ ተስፋን የሰነቀ ታላቅ የምስራች ስለነበር ዜጎች ደስታቸውን በአደባባይ ወጥተው ይገልፁ ነበር።ለዚህ ዋናው ምክንያቱ ደግሞ ለህዳሴ ግድብ ስንገዛ የነበረው የባንዳን ቅስም የሰበርንበት ነበርና ነው።
ሁሉም ኢትዮጵያውያን ሊሰሙት በጣም ሲጓጉለትና ለዚህም ፈጣሪያቸውን ሲማጸኑ የነበረውን ይህንን ታላቅ የምስራች ለማብሰር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በዕለቱ ባስተላለፉት የምስራች “ የህዳሴው ግድባችን የዚህ ትውልድ መለያ ማኅተም ሠርቶ የማሳካት ትምህርት የዘመናት ቁጭታችን መልስ ማግኘት መጀመሩን የምናበስርበት ፋና ነው።አንገታችንን ሊያስደፉ ሲከጅሉ ለነበሩት ሁሉ የጫኑብንን የድህነትና የኋላቀርነት ሸክም ወዲያ ልናሽቀነጥረው መቁረጣችንን ጮክ ብለን የምንነጋገርበት ድምፃችን ነው፡፡…” ብለዋል፡፡
የህዳሴው ግድብን ዳግማዊ የአድዋ ድል እያሉ የሚያወድሱትም አሉ።የአድዋው ድልም በቅኝ ገዢዋ ጣሊያን ላይ ከአራቱም አቅጣጫ የተሰባሰቡ ዜጎች በእምነት ብሄርና ድንበር ሳይከፋፈሉ ጦርነት ያወጁበትና የአፍሪካን ታላቅ ድል የተቀናጁበት ነው፤ በቅኝ ገዥዎች ለሚማቅቁ አፍሪካውያን ተስፋን የሰነቀ ነበር።በነጻነትና በጸረ ቅኝ አገዛዝ ትግሉና ድል ለአፍሪካ ምሳሌ እንደሆነው ሁሉ በህዳሴ ግድባችንም ለአፍሪካ ኢኮኖሚ ነጻነት መልካም ተምሳሌት ለመሆን ችለናል። ኢፍትሃዊነትንም በራሳችን አቅምና ጥረት አሸንፈን የዘመናት የኢትዮጵያውያንን ቁጭት ተወጥተናል።
በህዳሴው ግድብ ላይ የምናካሂደው ግንባታም የድህነትን ቀንበር የምንሰብርበት ነው።ግድቡ ኢትዮጵያውያን በብሄር፣ በመንደር ፣ በድንበር፣ በጎጥና በቆጥ በእምነት ሳይከፋፈሉ ብራቸውንና ላባቸውን ጠብ አድርገው የስኬቱን የመጀመሪያ ሙሌት ያዩበት ነው።ይህ አኩሪ ተግባር ደግሞ አፍሪካውያን መጀመር ብቻ ሳይሆን መፈጸሙንም አሳምረው እንደሚችሉ ያሳየንበት ነው።ስለሆነም ስኬቱን እያጣጣምን ለበለጠ ውጤት ልንሽቀዳደም ይገባል። ዓባይን ምክንያት አድርጎ በጦርነትና የግጭት ሰበብ የባንዳ ምንጭ ሆኖ ሲያውከን ከነበረው ታሪክም እንቀይር።በዚህም የባንዳዎችም የገቢ ምንጭ ጠፍ ይሆናል፤ ቅስማቸውም ይሰበራል፡፡
ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተካሄደው የግድቡ ግንባታ ሀገራችን የመጀመሪያውን ሙሌት ባለፈው ሐምሌ 15 ቀን አገባዳለች።ቀጣይ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ ደግሞ ዜጎች የተለመደ ትብብራቸውንና ርብርባቸውን ሊያደርጉ ይገባል።ለእኛ ዓባይ ራትና መብራት ብቻ ሳይሆን ኩራት የሚሆነን በምስራቅ አፍሪካ ራሳችንን ቀና የምናደርግበት ለብዙ ኢንዱስትሪዎች የኃይል ምንጭ፤ ለዜጎችም የሥራ ዕድል የሚፈጥርና ለቱሪስቶችም መስህብ ሆኖ የገቢ ምንጭ የሚሆን ነው።ስለዚህም ነው ደግመን ደጋግመን ጠቀሜታው ዘርፈ ብዙ ነው የምንለው፡፡
በግብርና የቆመውም የሀገራችን ምጣኔ ሀብት ዝናብን ተከትሎ የሚሄድ በመሆኑ ከእጅ ወደ አፍ የዘለለ ምርት ማግኘት አልተቻለም።ወንዞች ከዓመት ዓመት እየሞሉ በሚፈሱባት ምድር በበጋው ወቅት የመስኖ እርሻ የሚለማ መሬት አይታይም።
አንጋፋዎቹ ባንኮችም ሆኑ የአነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማት ዘርፉን በብድር ለመደገፍ ጥረት አያደርጉም።የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ከንጉሡ ጀምሮ እየመራና እየደገፈ ላለው ግብርና የሚመለከታቸው አካላት ድጋፍ ሊሠጡት ይገባል።እርግጥ ነው በያዝነው ዓመት ተስፋ ሠጪ ጅምሮች ታይተዋል፤ ዘርፉን በዘመናዊ ማረሻ፣ መከስከሻ እና መውቂያ ማሽኖች ለመምራት ለመስኖ አጋዥ የሚሆኑ ማሽኖች ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ሲሰጥ ማየቱ ራሱ ተስፋ ሠጪ ነው። የህዝብ ቁጥር እየጨመረ ከመሄዱ አንፃር የእርሻ መሬት ስፋትም በዚያው ልክ እንደ ሰዎች ግንባር እየጠበበ በመሆኑ መስኖ ተኮር እርሻዎች ሊስፋፉ ይገባል፡፡
ባለፈው ሰኔ 22/2012 ዓ/ም በግፍ ህይወቱን የተነጠቀውን ድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በማግስቱ በተለያዩ ከተሞች የጠፋው ህይወትና የወደመው ንብረት ወጣቶች በስሜታዊነት የፈፀሙት ክስተት ነበር፡፡ በዚህ እኩይ ድርጊት ንብረቱን አውድሙና የመሬት ባለቤት ትሆናላችሁ በሚል ማታለያ ከወጣቶቹ ጀርባ ሆነው ጥፋቱን የመሩት ባንዳዎች እንደሆኑ ጥርጥር አይኖረንም።በገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች የግብርና ምርቶችን በመስኖና በመሳሰሉ ዘዴዎች እያመረቱ የሚጠቀሙበትን መንገድ ማመቻቸቱ የክልል ግብርና ቢሮዎች ሥራ ሊሆን ይገባል።ይህም የኑሮ ውድነትን በመቀነስ ነዋሪዎችን ከነጋዴዎች ብዝበዛ የሚያላቅቅ ነው፤ ወጣቱን የሥራና የሀገር ፍቅርና የገቢ ምንጭ እንዲኖረው የበለጠ ምርታማ ለመሆን የሚያተጋው ነው።ማንም ድብቅ ዓላማን ያነገበ የሽብር ኃይል ወጣቱን እያሽከረከረ ለእኩይ ዓላማ የሚጠቀምበት ዘመን ይብቃ።ከዚህ ይልቅ የህዳሴ ግድባችንን ጨምሮ ሌሎች ምሳሌ የሆኑና አገራችንን የሚቀይሩ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እንትጋ!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2012
ይቤ.ከደጃች ውቤ