“የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጽህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ እንደተገለጸው፤ በዚህ ዝናባማ ወር ውስጥ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በነበረው መልካም የዝናብ ሁኔታ በመጀመሪያው ዓመት ለመሙላት የታቀደው የውሃ መጠን ሞልቶ፤ ውሃው በግድቡ አናት ላይ እየፈሰሰ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የግድቡ የውሃ ሙሌት ሐምሌ አጋማሽ ላይ እንደሚጀምር ቁርጠኝነቱን ሲያሳውቅ ነበር” ሁሌም ቢሆን ልንሰማው የምንጓጓለትን ይህንን ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በደስታ ያሰከረ ዜና ያነበብነው ከቢቢሲ አማርኛው ገጽ ነው። ይህ የዜና ምንጭ አክሎም መግለጫውን ተከትሎ “በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የእንኳን ደስ አለን መልዕክት ሲለዋወጡ አምሽተዋል” ሲል ዘግቧል።
ከትርፋቸው ሳይሆን ከጉድለታቸው ከጉሊት ቸርቻሪ እስከ ቀን ሰራተኛ፤ ከተማሪ እስከ መምህር ወጣት አዛውንቱ፣ ሙስሊም ክርስቲያን ዋቄፈታው ማንም ሳይቀር መቀነቱን ፈቶ ላቡን አንጠፍጥፎ ባፈራው ሀብት የገነባው ግድብ ፍሬ አፍርቶ ለፍጻሜ ሲቃረብ ሲያይ እንዴት አይደሰት? እንዴትስ አይፈነድቅ? የህዳሴውን ግድብ ፍጻሜ ሳታሳየኝ አትግደለኝ ሲሉ የተማጸኑትስ እንዴት ፈጣሪያቸውን አያመሰግኑ?
ዓባይ አፈርና ውሃ ሳይሆን የኢትዮጵያን ደምና ወዝ ይዞ ለዝንተ ዓለም ወደ ውጪ ፈሷል። ከዚሁ ታላቅ ጸጋችን አጠገብ የሚኖሩና ዓባይ በበራቸው የሚያልፍ የጎጃም፣ የጎንደርና የወለጋ ወገኖቻችን በማገዶ ጭስ ዓይናቸው እየተጨናበሰ እሱ ግን ባዕድን ብርሃን በብርሃን፤ ምርት በምርት ሲያደርግ ቆይቷል። ይህን ታላቅ ጸጋ የያዘች አገር በድህነትና በጉስቁልና ስሟ ሲነሳና ዜጎቿ ሲሸማቀቁም እልፍ ዓመታት ተቆጥረዋል። ከዓለም ታላላቅ ወንዞች አንዱ የሆነው የዓባይ መፍለቂያ የሆነች አገር በ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ከ40 በመቶ በላይ ህዝቧ የኤሌክትሪክ ብርሃን አያገኙም ሲባልስ እንዴት ያሸማቅቃል። አንተማ ግዑዝ ነህ ምን ታደርግ ሁሉ ነገር የሚጠበቀው ከእኛ ነው ሲሉም ኢትዮጵያውያን ጥርሳቸውን ነክሰው በቁጭት ጊዜ ሲጠብቁለትም ኖረዋል።
ለሁሉም ጊዜ አለው እንዲል መጽሀፉ ቁጭትና ቁዘማው መጋቢት 2003 ላይ በቃህ ተባለና ኢትዮጵያውያን
የማንንም እጅ ሳይጠብቁና ብድርና እርዳታ ሳይፈልጉ በታላቁ ወንዛችን ዓባይ ላይ ታላቁን የህዳሴ ግደብ ለመገንባት ወስነው ውሳኔያቸውን መተግበር ጀመሩ። በዓባይ ጉዳይ አንጀቱ ሲያርር የኖረውና ቁጭት ያንገበገበው ኢትዮጵያዊም በእናቱ ማህጸን እና በመቃብር ካለው ውጪ ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ እንዲሁም ካለበት የዓለም ክፍል ሁሉ ሆ ብሎ ለድጋፍ ተነሳ። ያለምንም ልዩነትም በቦንድ በ8100 እና በሌሎችም ድጋፉን ያለምንም ስስት ለገሰ።
ግድቡም የመሬት ውስጥ ሥራዎቹን በስኬትና በጥንቃቄ አገባዶ እነደጎረምሳ ልጅ በቁመት ከፍ አለ። በመሃል ገጥመውት የነበሩትም የኤሌክትሮ ሜካኒካልና ኤሌክትሪካል ሥራዎች መጓተት በለውጥ ኃይሉ አመራር ታክሞም በበለጠ ጥራትና ፍጥነት ሥራው ተቀጣጥሎ ቀጠለ። የዚህም ውጤት ሀምሌ 15/2012 ዓ/ም ለሰማነው የብስራት ዜና መሰረት ሆነንና የግድባችን የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ያለምንም ኮሽታና ጩኸት ለፍሬ መብቃቱ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ተበሰረ። በዚህም መላ ኢትጵያውያን አንጀታቸው ቅቤ ጠጣ፤ እስከግድቡ ፍጻሜም ዓይናቸውን ከግድቡ ላይነቅሉና እጃቸውን ላያጥፉ ቃል ገቡም።
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የግድቡን ውሃ ሙሌት ባበሰሩበት ወቅት ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተነሳን አንዳችም ነገር ለመፈጸም እንደማይሳነንና የኢትዮጵያን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደምንችል በታላቁ የህዳሴ ግድባችን አስመስክረናል። ይሁንና በዚህ ብቻ ልንኩራራና ልንቆም ግን አይገባም። ሌሎቹንም የጀመርናቸውን አገር የሚለውጡ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በዚህ ወኔ ተነሳስተን ለፍጻሜ ማብቃት ይኖርብናል የሚል መልክት አስተላልፈዋል።
እውነት ነው ታላቁ የህዳሴ ግድብን የመሰለ ኢፍትሃዊነት የተሸነፈበትን ታላቅ ፕሮጀክት አይደለም መጨረስ መጀመሩ በራሱ ያኮራል። ያለምንም ልመናና እርዳታ በራሳችን አቅም መገንባታችንም ኩራታችንን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል። ይሁንና ግድቡን ለፍጻሜ ለማብቃት ቀሪ ስራዎች ስላሉና ድህነትን ከአገራችን የመቅረፉ ሥራም ገና ብዙ ጥረትን የሚጠይቀን ስለሆነ ለቀጣዩ አገራዊ ብልጽግና በበለጠ ወኔና ብርታት መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21/2012