አዲስ አበባ፡- በሴቶች ስራ ፈጠራ ልማት ፕሮጀክት የብድርና የስልጠና አገልግሎት ሴቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የከተሞች ስራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ጥሪ አቀረበ፡፡
የኤጀንሲው ዳይሬክተር አቶ ዘነበ ኩሞ እና የሴቶች ስራ ፈጠራ ልማት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዮሃንስ ሰለሞን ትናንት በቢሯቸው በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ፕሮጀክቱ የሚሰጠው የስልጠና እና የብድር አገልግሎት ለስራ ፈጣሪ ሴቶች ትርፋማነት ያግዛል፡፡
በፕሮጀክቱ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ያቀረቡት አስተባባሪው ፣ በፌዴራል ከተሞች የስራ እድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ስር የሚገኘው የሴቶች ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ፕሮጀክት ከዓለም ባንክና ከተለያዩ መንግስታት የተገኘ የረዥም ጊዜ ብድር እየተተገበረ የሚገኝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
አቶ ዘነበ እንደገለጹት፤ የፕሮግራሙ የመጀመሪያ ክፍል 2005 ዓ.ም የጀመረ ሲሆን፤ ታህሳስ 2010 ዓ.ም የሚጠናቀቅ ነበር፡፡ የፕሮጀክቱ ውጤታማነት የዓለም ባንክ ባደረገው ግምገማ መሰረት የብድር ገንዘቡ ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ መዋሉ፣ ውጤታማ፣ ተግባራዊ ለውጥ ያስገኘና የተሰጠው ብድር 98 ነጥብ ሰባት በመቶ ተመላሽ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
በመጀመሪያው የፕሮጀክቱ ክፍል ከ28 ሺ በላይ አገልግሎት ፈላጊ ስራ ፈጣሪ ሴቶች ተመዝግበው 16 ሺ ያህሉ ስልጠና ወስደዋል፡፡ ከ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ብድር ለ10 ሺ ስራ ፈጣሪዎች ሴቶች ተሰጥቷል፡፡ በዚህም በአማካይ 256ሺ ብር አንድ ስራ ፈጣሪ ሴት ብድር የወሰደች ሲሆን፤ 55 ነጥብ ሰባት በመቶ የሰው ሃይል የመቅጠር አቅማቸው እንዲያድግ እና የድርጅታቸው ትርፍ ደግሞ በ44 ነጥብ 77 በመቶ እንዲጨምር እገዛ አድርጓል፡፡ በፕሮጀክቱ ከ12 አነስተኛ ብድርና ቁጠባ ተቋማትና ከልማት ባንክ የብድሩ ፋይናንስ ቀርቧል፡፡
የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ዮሃንስ ሰለሞን የፕሮጀክቱን ውጤታማነት በመመልከት የጃፓን መንግስት 50 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የጣሊያን መንግስት 15 ሚሊዮን ዩሮ በብድር መስጠታቸውን ጠቅሰው፣ በዚህም ፕሮጀክቱ ለሁለት ዓመታት እንዲራዘም መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በተገኘው ተጨማሪ የብድር ድጋፍ ከዚህ ቀደም ፕሮጀክቶቹ ይተገበር ከነበረባቸው አዲስ አበባ፣ ባህር ዳር፣ ሐዋሳ፣ መቀሌ እና አዳማ በተጨማሪ በጎንደር፣ አክሱም፣ አሰላ እና ዲላ ከተሞች በቀጣይ አገልግሎቱ እንደሚሰጥም አስታውቀዋል፡፡ የፕሮጀክቱ ብድር እስከ 36 ወር (ሶስት ዓመት) ድረስ ተመላሽ እንደሚሆን ተናግረው፣ የዓለም ባንክ ከአገር ውስጥ አንድ ማይክሮ ፋይናንስ ተቋም ጋር በጋራ በመሆን የተበዳሪዋን ፍላጎትና አቋም በመመዘን ያለማስያዣ ለማበደር ያካሄዱት የሙከራ ጥናት ተስፋ ሰጪ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ለሙከራ ያህልም ለ15 ስራ ፈጣሪ ሴቶች ብድር በመስጠት መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ከተሞች እና ከከተሞቹ እስከ 50 ኪሎ ሜትር ዙሪያ የሚገኙ አካባቢዎች የሚገኙ ስራ ፈጣሪ ሴቶች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉም ተገልጿል፡፡ የፕሮጀክቱን ስራ ፈጠራና የስራ ስልጠናውን ገና ወደ ስራ መግባት የሚፈልጉ ሴቶችም መውሰድ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡ 8658 በነጻ የስልክ መስመር በመደወል ተጨማሪ ማብራሪያ ማግኘት እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 18/2011
በሰላማዊት ንጉሴ