በኢትዮጵያ ከ2013 እስከ 2022 ድረስ ያለው የ10 ዓመታት የልማት መሪ ዕቅድ ተዘጋጅቷል። የሀገሪቱ የቀጣይ 10 ዓመታት የልማት ዕቅድ ራዕይ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ ነው። ይህንን ራዕዩዋን ለማሳካት የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ በማገናዘብ በየዘርፉ የተለያዩ ዕቅዶች ታቅደዋል። በፕላን ኮሚሽን አስተባባሪነት በየዘርፎቹ ዕቅድ ላይ ውይይት ተካሂደዋል። ሁሉም ዘርፎች ለሀገሪቱ ራዕይ መሳካት ያቀዱትን ዕቅድ ለውይይት አቅርበዋል። በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ትልቅ ትኩረት የተሰጠው የአረንጓዴ ልማት ዘርፍ እየመራ የሚገኘው የአካባቢ፣ የደን፣ የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ለውይይት ቀርቦአል።
ዕቅዱ ሰፊና በርካታ ጉዳዮችን ያካተተ ነው። በዚህ ጽሁፍ የምንመለከተው የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ዙሪያ በቀጣይ ሊከናወኑ የታቀዱና ተግባራትን ነው።
በዓለም እጅግ አሳሳቢ እሆነ የመጣ የዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት እየተከሰተ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ ለመከላከል በሀገሪቱ ምን ለመሥራት ታቅዶል?፤ እንዴትስ ይከናወናል?፤ ለዘርፉ የሰጠችው ትኩረት ምን ይመስላል? የሚለው በዕቅድ ውስጥ መካተቱን መመልከት ተገቢ ይሆናል።
የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ዋና ዋና አላማዎች የሚባሉት የከባቢ ሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀትን መቀነስ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን መቋቋምና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ናቸው። ለመሆኑ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለውን ተጽዕኖ እንዴት መቋቋም ይቻላል? በእያንዳንዱ ዘርፎች ምን ቢከናወን ነው ተጋላጭነትን መቀነስ የሚቻለው? ከእያንዳንዱ ባለድርሻ አካላትስ ምን ይጠበቃል? የአካባቢ፤ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ዘርፍ በቀጣይ ሊያከናውን የያዘው ዕቅድ እነዚህን ጉዳዮች ያካተተ መሆን አለበት።
የአካባቢ፣ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ የዘርፉን የቀጣይ 10 ዓመት ዕቅድ አቅርበዋል። ዕቅዱ የዘርፉን ያለፉትን አፈፃፀም በመገምገም፤ ለቀጣይ 10 ዓመት የሚደረስባቸውን የልማት ግቦች ከሀገራዊ የልማት ትኩረት አቅጣጫዎች፤ ከዘላቂ የልማት ግቦች፤ ከአፍሪካ አጀንዳ 2063፤ አገራችን ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ የአካባቢ ስምምነቶች ትግበራ ደረጃ እንዲሁም ከዘርፉ ዓለም ዓቀፍዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎች ጥናትና ትንተና ጋር ከማስተሳሰርና በማጣጣም የክልሎች፣ የከተማ መስተዳድሮችና የሚመለከታቸው ፈፃሚ መሥሪያ ቤቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ደርጅቶችን በማሳተፍ በሰፊ ውይይት የተካሄደበት መሆኑንን አመላክተዋል።
ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ እንደሚናገሩት፤ የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ለዕቅድ መነሻ መደረጉን ነው። የካርቦንዳይኦክሳይድ የልቀት መጠን ቅነሳ በእያንዳንዱ ሴክተር በማካተት በማድረግ ከሚሠሩ ሥራዎች የዚህ ዓመት አፈፃፀም ሳያካትት 92.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የካርቦንዳይኦክሳይድ እኩሌታ የሙቀት አማቂ ጋዝ ልቀት መቀነስ ተችሏል። ይሄም አፈፃፀም ከተቀመጠ ግብ አኳያ የሚቀሩ ነገሮች መኖሩን የሚያሳይ ነው።
የሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ላይ የታዩ ተግዳሮቶች፤ ሙቀት አማቂ ጋዞች ለአየር ንብረት ለውጥ ለማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በተመለከተ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችንን መለካት የሚያስችል የአቅም ውስንነት መኖሩን ጠቁመው፤ እነዚህን የሙቀት አማቂ ጋዞችን መለካት፣ ሪፖርት ማድረግና ማረጋገጥ የሚያስችል ወይም የኤም አር ቢ ሲስተም የሌለ በመሆኑ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የቴክኖሎጂ የአቅም ግንባታ ሥራን የሚጠይቅ መሆኑን አመልክተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ትግበራ የሚውል የቴክኖሎጂ አቅርቦትና የፋይናንስ አቅርቦት በሚፈለገው ደረጃ አለመኖር፣ በዘርፉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ ውስንነት መኖር፣ የሲቪል ማህበራት፣ የግሉ ዘርፍና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ውስንነት ምክንያት የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት የመወጣት ክፍተት መኖሩ፤ በተለይ እንደ ዓለም ሆነ እንደ ሀገራችን የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ውስን መሆኑ ዘርፉ የሚፈለገው ውጤት ለማምጣት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች መሆናቸውን ያብራራሉ።
እነዚህን ታሳቢ በማድረግ የቀጣዩን የ10 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ መሪ ዕቅድ ማስቀመጥ ተችሏል፤ የሚሉት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፤ በዚህ መሠረት የልማት ዕቅዶቹ የትኩረት አቅጣጫዎች ለአየር ንብረት ለውጥ ለማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በሀገሪቱ የልማት ዕቅድ ውስጥ እንዲካተት ወይም እንዲተገበር እየተደረገ ቢገኝም በሚፈለገው ደረጃ አለመሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ አመልክተዋል።
የልማት ዕቅዶቹ የትኩረት አቅጣጫዎች፤ በሀገራዊ የማጣጣሚያ ዕቅድ ውስጥ በተለዩ ስልቶች አማካይነት ማህበረሰቡ የአየር ንብረት ተጽዕኖን እንዲቋቋም የትግበራ ሂደቱን የማስተባበርና እንዲተገበር በማስቻል፤ ከዘርፎች የሚለቀቀውን የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መጠን መቀነሱን በማረጋገጥ በየደረጃ እንዲተገበር መከታተል፤ ጠንካራ የአካባቢና የአየር ንብረት ለውጥ ድርድርና ዲፕሎማሲ በማድረግ ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የሚሆን የቴክኖሎጂ፤ የፋይናንስና የአቅም ግንባታ ድጋፍ ማሳደግ እንዲሁም በዘርፉ እየተተገበሩ ያሉትን ፕሮጀክቶች ፕሮግራሞች የታለመላቸውን አላማ ማሳካታቸውም ማረጋገጥ ላይ የሚያተኩሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የዘርፉ የልማት ዕቅድ ግቦች በመጀመሪያ ላይ የተቀመጠው ለአየር ንብረት ለውጥ ለማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ትግበራን ውጤታማን በማሻሻል 163 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ካርቦን ዳይ ኦክሳይድ እኩልታ ጋዝ መቀነስ ነው። ይህ ደግሞ በዓለም ደረጃ ከተቀመጠ 250 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ካርቦን መጠን መቀነስ ውስጥ የቀረው መቶ 163 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በአስር ዓመቱ ለመቀነስ የተቀመጠ ግብ መሆኑን ጠቁመው፤ ለእነዚህ የሚሠሩ ሥራዎች ዋና ዋና የዘርፍ አመላካቾች ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል።
በአመላካችነት የተቀመጡት ውስጥ ለምሳሌ የሙቀት አማቂ ጋዞች ልቀት መጠን 92.7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የዘንድሮ ዓመት ሳይካተት በሁለተኛ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መቀነስ ተችሏል የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ በአስር ዓመት ውስጥ 163 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ለመቀነስ የሚያስችል ሥራ መሥራት የሚጠበቅ ይሆናል። ይህንን ለመቀነስ የሚያስችል በየሴክተሩ አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ወይም ቴክኖሎጂ የሚያልቁ ቴክኖሎጂዎች እንዲጠቀሙ ማድረግ ወይም ደግሞ የተለቀቀውን የደን ልማት ሥራ መሥራት የሚያስፈልግ መሆኑን አመልክተው፤ የአረንጓዴ ተክሎችን በተለያዩ ሴክተሮች እንዲለሙ የማድረግ ሥራ የሚሠራ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ተሳትፎን ለማሳደግ የሚሠሩ ሥራዎች የዓለም አቀፉ የፓሪስ ስምምነት አካል ናቸው። በዚያ ልክ ለመሥራት ድርድሮች ላይ በመሳተፍ በሙሉ አቅምን በመገንባት ውጤታማ እንዲሆን ማስቻል የሚጠበቅ ተግባር ነው። በአስር ዓመት ውስጥ በሁሉም ድርድር መድረኮች ላይ በመሳተፍ የሀገራችንን ጥቅም ማስከበር ያስፈልጋል። የሀገራችንን ጥቅም ማስከበር ብቻ ሳይሆን በተለይ ኢትዮጵያ የምትወክላቸውን የታዳጊ አገራት ታሳቢ ማድረግ የሚሠራ መሆኑን አመልክተዋል። አክለውም የአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ለውጥ የአረንጓዴ ልማት ሚኒስቴርም ማድረግ እስካሁን ድረስ በዘርፎች እየተሠራ ሲሆን በሚፈለገው መጠን ወደታች በማውረድ አጠናክሮ የማስቀጠል ያስፈልጋል ብለዋል።
ሌላው አገራዊ የደንና የጥብቃ ቦታዎች ሽፋንን ከ15.5 በመቶ ወደ 30 በመቶ ለማሳደግ የተለያዩ ሥራዎች በመሥራት ነባሮች ደኖችን መጠበቅ አዲሶችን መትከል አንዱ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ ለዚህ አመላካቾች ከሆኑት አንደኛው የተዘጋጁ ችግኞች ናቸው። በዚህም በአስር ዓመቱ ውስጥ 40 ቢሊየን ችግኞችን ይዘጋጃሉ። የተጠበቁ ሰው ሠራሽና የተፈጥሮ ደኖች 34 ሚሊዮን ሄክታር ለማድረስና የተራቆተና ያገገመ 11 ሚሊየን ሄክታር የደን መሬት የማልማት ሥራ እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።
በዚህ የውይይት መድረክ የህዝብ ጥያቄዎች ተነስተው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ በቀጣይ አስር ዓመታት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ምን አይነት ስልት ተቀይሶአል? ሚኒስቴሩም ከማድረግ አንፃር፤ ሌሎች አማራጮችን ከማየት አንፃር ከክልሎች ጋር በቅንጅት ከመሥራት አንፃር የታቀደው ምንድነው? ምን መሆን ያለበት? እንዲሁም ዓለም አቀፍዊ ስምምነቶች የሀገራችንን ፍላጎትና ጥቅም መሠረት እንዲሆኑ ከማድረግ አንፃር ምን ታቅዶል? የሚሉት ይገኝበታል።
ለዚህ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲስጡ ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ሦስት ዋና ነገሮች ማየት ያስፈልጋል ይላሉ። በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅድ የነበሩት ክፍተቶች ምንድናቸው ለምንድነው የሚፈለገው ያህል መሄድ ያልተቻለው የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል። ይህንን ለማድረግ በመጀመሪያ ደረጃ ተቋማዊ አቅም ግንባታ ከላይ እስከታች የተቋሙን አቅም መገንባት የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ የተለያዩ ስትራቴጂዎች፤ ፍኖተ ኮርታዎች መመሪያዎችና ፖሊሲዎችንን በማውጣትና በመተግበር የሰው ሃይል አቅምና የቴክኖሎጂ አቅም የሚጠይቅ ነው። በተለይ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅድ መሠረት ሊሆኑ የሚችሉ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል። ለምሳሌ ሀገራዊ የማጣጣም ሥራ አሳታፊ በሆነ መንገድ የተሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሌላው የአረንጓዴ ልማት ፍኖተ ካርታ ከ2020-2030 በእ.ኤ.አ የተዘጋጀ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ለማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሚኒስትሪም መመሪያ አቅጣጫ ከፌደራል ተቋማት ጋር አብሮ ለመሥራት የሚያስችል ከባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ማዘጋጀት እንዲሁም አንዳንድ ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለምሳሌ በግብርና፤ ውሃና መስኖ፤ በትራንስፖርት፤ ከጤናና ከተማ ልማት ጋር በመተባባር የአየር ንብረት ለውጥ ስትራቴጂ መዘጋጀቱን ይጠቅሳሉ። ለእያንዳንዱ ለእነዚህ ሴክተሮች CRG ለመከታተል የሚያስችል ዌብ ቤስድ የሆነ የክትትልና የግምገማ ሥርዓት መዘርጋቱን ተናግረዋል።
እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ ብሔራዊ የደን ሴክተር ፕሮግራምና እንዲሁም የአስር ዓመት የደን ዕቅድ ስትራቴጂ ተዘጋጅቷል። እንዲሁም በዚህ ዓመት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ዳሰሳ ጥናት ተካሂዶ እስካአሁን የነበሩትን ክፍተቶች ተለይተዋል። በተለይ ጥናቱ የሚያሳየው አብዛኛው ግኝት በቀጣይ ያሉብን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችል መሆኑንን የሚያሳየው ነው ብለዋል። በተጨማሪም በአሁን ጊዜ ብሔራዊ አየር ንብረት ዕቅድ የሚባለውን ለማሻሻል እየተሠራ ይገኛል። እነዚህ ሲጠናቀቁ ሚኒስትሪም የማድረግ ሥራውን በከፍተኛው ሁኔታ የሚያሰልጡ ይሆናል።
አደረጃጀትን በተመለከተም በፌዴራል ደረጃ በሁሉም ዋና ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ለአየር ንብረትለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ልማት ስትራቴጂ ተፈጥሯል። በክልሎች ደረጃም ወጥ ባይሆንም እስከ ወረዳ ድረስ አደረጃጀት ተፈጥሯል። ነገር ግን በቀጣይ አስር ዓመታት አንዱ ተግባር የሚሆነው ይህንን የዘርፉን መዋቅር ወጥ በሆነ መንገድ እስከታችኛው እርከን መሳለጥ ነው። ለዚህ ሥራ በተለይ ከአውሮፓ ሕብረት ዘንድሮ የተገኘ ድጋፍ አለ ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ ይህ ድጋፍ MRV የሚባለውን በፌዴራል ደረጃ የፈጠርነውን አቅም በክልሎችና በዘርፍ መሥሪያ ቤቶች በተለይ በሰው ሃይልና MRV የምርምር ተቋም የማቋቋም ሥራ ነው። ለዚህም የሚሆን የሦስት ዓመት ሀብት የተገኘ ሲሆን በቀጣይ ሦስት ዓመታት ለሚሠራው የአደራጃጀትና የአሠራር ሥርዓቱን የሚያሳልጥ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ፍቃዱ።
እንደ ፕሮፌሰሩ ማብራሪያ፤ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን በተመለከተ እንግዲህ እንዴት የሀገራችንን ጥቅም ለማሳለጥ ይቻላል የሚለውን ነው ሀገራችንን በርካታ ዘርፈ ብዙ ስምምነቶች ፈርማለች። በድርድሮች ግንባር ቀደም ሚና ትጫወታለች ይሄንን እንዴት ማስቀጠል ይቻላል የሚለው ማየት ተገቢ ይሆናል። በመጀመሪያ ደረጃ በብሔራዊ ጠንካራ የድርድር ቡድን አቅም መገንባት ነው። አቅም ከገንባን ቅድመ ዝግጅት ሥራ በአግባቡ ተሠርቶ በድርድር ጊዜም አስፈላጊው ተሳትፎ ማድረግ ይቻላል። የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታና ፍላጎት መሠረት ያደረገ ድርድር በማድረግ ጥቅም ማስገኘት ይቻላል። ለምሳሌ በሀገራችንን እየተሠሩ ያሉ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ ብንወስድ የዘንድሮው 5 ቢሊየን የዛፍ ችግኝ ተከላ ለአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ ግብዓት ከፍተኛ ሚና አለው። የአምናውም ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል። በሚቀጥሉት 4 ዓመታት እስከ 20 ቢሊየን ችግኞችን ለማድረስ የሚሠራ መሬት ላይ ትልቅ ሥራ ነው ። ስትራቴጂ ማዘጋጀት ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ መሬት ላይ የተሠሩ ሥራዎችንን አስፈላጊውን ሀብትና ቴክኖሎጂ ሊያስገኙ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኮፕ 26 እንግሊዝ አገር የሚካሄደው ኮፕ ወይም ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ የተባባሩት መንግሥታት ፈራሚ አገራት የሚደራደሩበት መድረክ ነው። እንደአቅጣጫ የተያዘው 27ተኛው የአፍሪካ ኮፕ ይሆናል ተብሎ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሳተፉት በመሆኑ 27ተኛው ኮፕ አገራችንን ብታስተናግድ ለሀገራችን ገጽታ ግንባታም ሀብት ለማግኘት፤ በርካታ የቱሪዝም ሊያመጣ የሚችል አጋጣሚን የሚፈጥር ነው። ይህንን ወደ ሀገራችን ለማምጣት ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን በማሳለጥ አጋጣሚ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በአጠቃላይ ከልማት አጋር አገራት ጋር ያለንን የአየር ንብረት ለውጥ ዲፕሎማሲ ትብብር በማጠናከርና ፕሮጀክቶች በጋራ በመቅረጽ በተለይ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ ያለውን ውስንነት በመቅረፍ ከተሠራ የታሰበው ግብ መምታት ይቻላል ሲሉ ያላቸውን እምነት በመግለጽ ሀሳባቸው አጠቃለዋል።
አዲስ ዘመን ሐመሌ 20/2020
ወርቅነሽ ደምሰው