ኢትዮጵያ ለዘመናት ከቆየችበት የድህነት ታሪክ ተላቃ አዲስ የዕድገትና የብልፅግና ስኬት ለማስመዝገብ ዘርፈ ብዙ ጥረቶች ውስጥ ትገኛለች።በተለይ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ በጀመረችው ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በርካታ ተስፋ ሰጪ ስኬቶች እየተመዘገቡ ይገኛሉ።ከእነዚህ ስኬቶችም ውስጥ ባለፈው ሳምንት ለመላ ኢትዮጵያውያን፣ ለኢትዮጵያ ወዳጆችና ለዓለም የተበሰረው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ አንዱ ነው።
ታላቁ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈለችበት ትልቁ ፕሮጀክቷ ነው።ኢትዮጵያ ይህን ግድብ እውን ለማድረግ የረጅም ጊዜ ፍላጎት ቢኖራትም ዕድገቷን በማይፈልጉ የውጭ አካላት ሴራና በውስጥም በነበሩ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች የተነሳ ከሃሳብ በዘለለ ወደተግባር ማስገባት ሳትችል ቆይታለች።በተለይ ግብጾች የኢትዮጵያን ደካማ ጎኖች በመጠቀም ለዘመናት በሰሩት የፖለቲካ ስራ ኢትዮጵያ ከየትኛውም አገር አባይን ለማልማት የገንዘብ ድጋፍ እንዳታገኝ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ ፖለቲካዊ ጫናዎችን በማድረግ ፕሮጀክቱ እውን እንዳይሆን ሲያደርጉ ኖረዋል።
ይሁን እንጂ እውነት ባለቤቷን መፈለጓ አይቀርምና ኢትዮጵያ ጊዜው ሲደርስ እነዚህን ለዘመናት የቆዩ ጫናዎች በጣጥሳ በመውጣት እነሆ የድል ምዕራፍ ላይ ደርሳለች።ከዘጠኝ ዓመታት በፊት የተጀመረው ታላቁ የህዳሴ ግድብም በአንድ በኩል በውስጥ ባንዳዎች የሚሰሩ ሴራዎች፣ በሌላ በኩል ደግሞ የግብጽና የሸሪኮቿ ጫና ሳያደናቅፈው ፍሬ ማፍራት የሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል።የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታም ሆነ የአገራችን የለውጥ ጉዞ በእያንዳንዱ እርምጃው ያልተፈታተነው እንቅፋት አልነበረም።በተለይ ለውጡ የግል ጥቅማቸውን ያሳጣባቸው የውስጥ አካላትም ሆኑ የውጭ ጠላቶች ለውጡን በማደናቀፍ የኢትዮጵያን ልማትና እድገት ለማደናቀፍ እንቅልፍ አልነበራቸውም።
እነዚህ ሃይሎች ለውጡ እውን እንዳይሆን ያልሸረቡት ሴራና ያልጠነሰሱት ተንኮል አልነበረም።ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ወደስልጣን የሚወጣውን ሃይል በማደናቀፍ በራሳቸው መስመር የአፈናና የጭቆና መንገዳቸው ለማስቀጠል ቢሞክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም ነበር።ከዚያ ለውጡ
እውን መሆኑን ሲገነዘቡ ደግሞ በመንግስት ውስጥ በመግባት ሃገርን የማተራመስ ስትራቴጂን በመንደፍ ተንቀሳቀሱ።
በተለይም በኅብረተሰቡ ውስጥ አስርገው ባስገቧቸው ህቡዕ የሴራ ገመዶች አማካይነት ህብረተሰቡን እርስ በርስ ለማጋጨት የሄዱበትና ዜጎችን ለዘመናት ከቆዩበት ቀዬ የማፈናቀል ተግባር አንዱ አሳፋሪ ድርጊታቸው ነበር።ይህ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ቢያስከትልም ለውጡን ግን መግታት አልቻለም።
ከዚያ በኋላ ስትራቴጂያቸውን በመቀያየር በአገሪቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር በርካታ ጥረቶችን አድርገዋል።ከነዚህ ውስጥ የሶስቱ ሰኔዎች ሴራና ያስከተለው ቀውስ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።በመጀመሪያው ሰኔ የታሰበው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን የመግደል ሙከራና ይህን ተከትሎ የታሰበው አገርን የማተራመስ እንቅስቃሴ ምን ያህል አገርን የማፍረስ ተልዕኮ ያነገበ እንደነበር የሚታወስ ነው።ከዚያ በኋላም በሁለተኛው ሰኔ የአማራ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የመከላከያ ሰራዊት ከፍተኛ ጄኔራሎች ግድያ ሌላው የሴራው አካል ነበር።ይህም የሚፈለገውን ግብ ሊያሳካ አልቻለም።
የሶስተኛው ሰኔ ሴራ ግን ከነዚህ በተለየ ሁኔታ ከውጭ ሃይሎች ጋር በቅንጅት የተሰራና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን የማደናቀፍና አገሪቱን የማፍረስ ትልቅ ተልዕኮን ያነገበ የጥፋት መንገድ ነበር።በዚህ ድርጊት የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ህይወት ከመጥፋቱም በላይ በቢሊዮን የሚቆጠር ሃብት የወደመበትና የኢትዮጵያ ጠላቶች የመጨረሻ ሃይላቸውን የተጠቀሙበት የጥፋት መንገድ ነው።
ነገር ግን እነዚህና ሌሎች በርካታ አገርን የማተራመስ እና የማፍረስ ሴራዎች ሁሉ ለውጡን ማደናቀፍ አልቻሉም።ይልቁንም መንግስት በአንድ በኩል የጀመረውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሌት ተቀን በመስራት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጥም ሆነ በውጭ የሚቃጡ ሴራዎችን እየመከተ እነሆ በየቀኑ ከፍታውን እየወጣ ይገኛል።የሰሞኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት ብስራትም ለለውጥ ሃይሉ እና ለመላ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የሞራል ስንቅ፣ ለጠላቶች ደግሞ የተስፋ መቁረጥ ምልክት ነው።ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያን የለውጥ ጉዞ የሚያደናቅፍ አንዳችም ሃይል አይኖርም።የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞም ልክ እንደታላቁ ህዳሴ ግድባችን ከጫፍ ደርሶ እውን ይሆናል።የጥፋት ሃይሎች የሁልጊዜ ስራ ለውጥን ማደናቀፍ ነው፤ የለውጥ ሃይሎችና የሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ስራ ደግሞ ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው።ነገር ግን እውነት ትመነምናለች እንጂ አትበጠስም እንሚባለው ጊዜያዊ ችግሮች ቢፈትኑንም ድሉ የመላው አገር ወዳድ ዜጎች ሆኖ ብልጽግናን ማረጋገጣችን እውን እንደሚሆን ሳንጠራጠር እጅ ለእጅ ተያይዘን ለልማት እንነሳ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2012