አዲስ አበባ፡- የህዳሴውን ግደብ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ በመጨረስ ወደስራ ለማስገባት በዲፕሎማሲው መስክ በተጠናከረ መልኩ መንቀሳ ቀስ እንደሚገባ ተጠቆመ። በመጀመሪያው ዙር የተያዘው ውሃ ለኢትዮጵያ የመደራደሪያ አቅም እንደ ሚፈጥር አስታወቁ።
በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ትምህርት መምህር እና የትምህርት ክፍል ሃላፊ የሆኑት ዶክተር ሞገስ ደምሴ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ የህዳሴውን ግደብ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ አልቆ ወደስራ እንዲገባ በዲፕሎማሲው መስክ በተጠናከረ መንቀሳቀስ ይገባል።
የዲፕሎማሲው ስራ እውቀቱ እና ክህሎቱ ባላቸው ሰዎች እንዲሳተፉ እና የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ዲፕሎማሲው ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠይቃል ሲሉ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለምአቀፍ ትምህርት መምህሩ አስገነዘቡ።
በግድቡ ዙሪያ የጀመርናቸውን ስራዎች ውጤታማ ለማድረግ የዲፕሎማሲ ስራ በጣም ወሳኝ ነው የሚሉት መምህሩ ፤ ይፋዊም ይፋዊም ባልሆኑ የዲፕሎሚሲ ስራዎች አሁን ካለው ከፍ ባለ ደረጃ ስራዎች ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። በተለይም ይፋዊ ላልሆኑ የዲፕሎማሲ ስራዎች ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ይፋዊ ያልሆነ ዲፕሎማሲ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ እና ባህልን መሰረት ያደረገ እንደሆነ የሚያስረዱት መምህሩ ፤ ይህም ባንድ ወቅት ታይቶ የሚጠፋ ሳይሆን ተከታታይነት ባለው መንገድ በደንብ ተጠንቶ ሊተገበር እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ኢትዮጵያ የተከተለችው መንገድ ብሄራዊ ጥቅም አስገኝቷል የሚሉት መምህሩ ፤ ወደፊትም ለሚኖረው ድርድር ግብፅ እና እና ሱዳንም በአንድ ልብ ወደ ድርድሩ እንዲመጡ ያስገድዳቸዋል ብለዋል።
በመጀመሪው ዙር የተያዘው ውሃ ለኢትዮጵያ የመደራደሪያ አቅም የፈጠረ እንደሆነ ገልጸዋል። ከአሁን በኋላ ያለውን ድርድር በጥሩ ሁኔታ እንዲጠ ናቀቅ የማስፈንጠሪያ አቅም መሆኑንም ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድቡን ፕሮጀክት ከአድዋ ጦርነት ጋር የሚመሳሰል የህዝብ አንድነት የታየበት መሆኑን ጠቁመው፣ ይህ አንድነት በዘላቂነት እንዲቀጥል መንግስት ተጠናክሮ መስራት እንደሚኖርበት መክረዋል።
በሀገር ህልውና እና በዴሞክራሲ መካከል ያለውን ሚዛናዊነት የመጠበቅ አካሄድ መኖር አለበት የሚሉት ዶክተር ሞገስ፤ የሀገርን ህልውና ባገናዘበ መልኩ የዴሞክራሲው ምህዳሩን ማስፋት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
የውስጥ አለመግባባቶችና የውስጥ ሽኩቻዎች ለውጭ ሃይሎች ሀገራችንን እንዲያተራምሱ እድል የሚከፍት መሆኑን ገልጸው ፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት አንድነታችንን እያጠናከሩ መሄድ ይገባናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2012
ሙሉቀን ታደገ