የማያረጅ ውበት የማያልቅ ቁንጅና
የማይደርቅ የማይነጥፍ ለዘመን የፀና
ከጥንት ከፅንሰ አዳም ገና ከፍጥረት
የፈሰሰ ውሃ ፈልቆ ከገነት።
ነበር ያለችው እጅጋየው ሽባባው አባይ በሚለው ዜማዋ። እውነት አባይን በቅርበት ለተመለከተው የሆነ ውስጥ የሚነካ የተለየ ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ ውብ የተፈጥሮ ፀጋ ነው።
አባይ ጣና ላይ ሲፈስ ጥቁር ቀለሙን ፅፎ ውሃው ሳይቀላቀል ሲያልፍ፤ ከጣናም ከወጣ በኋላ በዝምታ የባህር ዳር ከተማን አቋርጦ ሲወርድ ለተመለከተው እንደልብ ወዳጅ ሆድ እያባባ የሚሰናበት ያህል ልብ ይነካል። ከዚህ ቀጥሎ ጢስ አባይ ሲደርስ ደግሞ ከላይ ተወርውሮ ሲወርድ፤ ከዛ ተመልሶ ደግሞ ጭስ የመሰሉ ትናንሽ የውሃ ነጠብጣቦችን ይዞ ሲመለስ ለተመለከተው ልብን በሃሴት ጮቤ የሚያስረግጥ ውበት ያሳያል።
እንኳን ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ሀገራችንን ሊጎበኙ ለመጡ ቱሪስቶች ይቅርና ከማህፀኗ ለፈለቅኩት ለኔ እንኳን ሳይቀር ሀገሬ ድንቅ ምድር እንደሆነች የፈጣሪ ውብ ስራ አንደሆነች ማመልከቻ ነው። ስለአባይ ማንሳት ከጀመርኩ ማቆሚያ የለኝም። አሁን ደግሞ ከሁሉ የሚልቀው ጉባ ላይ የከተመው ታላቁ የህዳሴ ግድብ የሀገር ኩራት እውነተኛ የኢትዮጵያዊነት ወኔን የሚቀሰቅስ ነው።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ̋እንኳን ደስ አላችሁ የመጀመሪያው ዙር የግድቡ የውሃ ሙሌት ስራ በስኬት ተጠናቋል” ብለው ለህዝቡ ሲያበስሩ ልቤን ፈንቅሎ የወጣው ስሜት ከልቤ የምወደውን አባይ ሳሞጋግስ አንድውል አድርጎኛል።
ከቢሮዬ ወጣ ብዬ የህዝቡን ሁኔታ መመልከት ጀመርኩ። በእግሬ ትንሽ እርምጃዎችን ከተራመድኩኝ በኋላ ሰብሰብ ብለው የሚጨዋወቱ የእድሜ ባለፀጎች አጠገብ ደረስኩ። ፈቃዳቸውን ጠይቄ መቅረፀ ድምፄን ወደእነርሱ ጠጋ አደረግኩ።
አቶ ታደሰ ሲሳይ ይባላሉ፤ የ63 ዓመት እድሜ ባለፀጋ ናቸው። ጡረተኛ መሆናቸውን የሚናገሩት አባት የአንድ ወር የጡረታ አበላቸውን አዋጥተው የግድቡን እድገት እንደ ህፃን ልጅ ከስር ከስር ሲከታተሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ።
“ከባልንጀሮቼ ጋር በተገናኘን ቁጥር ግድቡ እንዴት ሆነ? ምን ሰማችሁ? እንባባል ነበር” የሚሉት አቶ ታደሰ” ዛሬ ቀኑ ደርሶ የመጀመሪያውን ውሃ ለመያዝ መቻሉ ከአድዋ የማይተናነስ ድል ነው ብለዋል። እኔ እንኳን ባልደርስበት ለልጅ ልጆቼ የሚተላለፍ ግድብ ላይ አሻራዬን ስላኖርኩ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል።
አቶ ጌታነህ አበባው በአንድ የግል ኮሌጅ ውስጥ በጥበቃ ስራ የሚተዳደሩ አባት ናቸው “ፈጣሪ እድሜ ሰጥቶኝ ይሄን ለማየት በመቻሌ እራሴን እንደ እድለኛ እቆጥረዋለሁ” ብለዋል። “ከኛ እኩል ካላቸው ላይ ቆጥበው ይሄን ቀን ለማየት ሲጓጉ የነበሩ ጓደኞቻችን ዛሬ በህይወት የሉም። እነርሱን ከጎናችን ብናጣቸውም ግን በነበራቸው አቅም ታሪክ ፅፈው እንዳለፉ እያሰብን እንጽናናለን ሲሉ ተናግረዋል።
በውትድርና ሙያ ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የኖሩት አቶ ይደርሳል ብርሃኔ የሀገር ዳር ድንበርን በማስከበር ስራ ላይ ከኖሩበት ጊዜ በላይ የልማት አርበኛ ሆነው የቻሉትን ያህል ገንዘብ አዋጥተው የግድቡን መጠናቀቅ የድል ብስራት የሚጠባበቁበት ጊዜ እንደሚበልጥባቸው ገልፀው፤ በድሉም ወደር የሌለው ደስታ እንደተሰማቸው ይናገራሉ።
ሌላዋ እናት ወይዘሮ ምህረት ልመንህ ይባላሉ፤ የ72 ዓመት የእድሜ ባለፀጋ ናቸው፤ በመንግስት ስራ ላይ ለበርካታ ዓመታት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በጡረታ ጊዜያቸው ሀገርን በአንድ ድምፅ የሚያነጋግር ድል መገኘቱ የማይቆጣጠሩት ደስታ እንደሰጣቸው ተናግረዋል።
ወይዘሮዋ እንደሚሉት ከሚመሩት እድር አባላቶቹን በማስተባበር የአስር ሺ ብር ቦንድ እንደገዙ አስረድተው፤ ህብረተሰቡ ከእለት ጉርሱ ቀንሶ ያዋጣው ገንዘብ ወደ ስራ ተቀይሮ ውጤት ላይ ሲደርስ ከማየት የበለጠ ደስታ የለም ብለዋል።
የእድሜ ባለፀጎቹ በአንድ አይነት ሃሳብ ግድቡ የኛም የአረጋውያኑ መጦሪያ የልጆቻችን ሀብት ማፍሪያ በመሆኑ “ አዎ ግድቡ የኛም ነው” ብለን አስተዋጽኦችንን በህይወት እስካለን እንቀጥላለን ብለዋል።
“አዎ ግድቡ የኔም ያንችም የእነሱም የሁላችንም ነው”።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2012
አስመረት ብስራት