አዳማ ፡- የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር ለማድረስ አመራሩ ግንባር ቀደም ሚናውን መወጣት እንዳለበት የክልሉ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ አመለከቱ ። ጨፌ ኦሮሚያ በአምስተኛው ዙር የስራ ዘመኑ አምስተኛ ዓመት ጉባኤ የባለስልጣናትን ሹመት በማጽደቅ ተጠናቋል።
የክልሉ አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሎሚ ትናንትና ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር፣ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ ከዳር በማድረስ የክልሉንና የሀገሪቱ እድገት ማረጋገጥ የሚቻለው አመራሩ በትጋትና በቁርጠኝነት ሲሰራ እንደሆነ አመልክተዋል።
በአሰራር ላይ እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን አስቀድሞ በመለየት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አፈ ጉባኤ፣ በተለይም የክልሉን ሰላምና ጸጥታ በማስከበር ምቹ የስራ ሁኔታ መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ጨፌው በትናንትና ውሎው የክልሉን ጠቅላይ ኦዲት መስሪያ ቤት፣ ፍርድ ቤት እና የጨፌውን የ2012 ዓ.ም አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም አድምጧል። የጨፌው አባላት በኦዲት የተገኙ ውጤቶች የክልሉን እንቅስቃሴና እድገት የጎዱ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህን በተመለከተ የተወሰዱ ርምጃዎች አለመጠቀሳቸው ሪፖርቱ ሙሉዕ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል።
በወቅቱም ፍርድ ቤቶች የህግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ እና ፍትህን እንዲያረጋግጡ በርካታ ሀሳቦች ተንጸባርቀዋል። በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶች፣ የፍትህ ስርዓቱን በጥቅም ለማዛባት የሚሞክሩ የውጭ ደላሎችና የውስጥ ጉዳይ አስፈጻሚዎችን አደብ ማስገዛት እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።
ጨፌው ለ2013 ዓ.ም በረቂቅ ደረጃ የቀረበውን የ 90 ቢሊዮን ብር በጀት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። ከዚህ ውስጥ 61 ነጥብ 2 ቢሊዮኑ ብር ከፌዴራል መንግስት የሚሰጥ ሲሆን 28 ነጥብ 8 ቢሊዮኑ ደግሞ ከክልሉ ገቢ የሚሰበሰብ መሆኑ ተገልጧል።
በተጨማሪም ጨፌው የክልሉን የመጠጥ የውሃ ሃብት አጠቃቀም በተመለከተ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አጽድቋል እንዲሁም የ2012 ዓ.ም ተጨማሪ በጀት ረቂቅ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አጽድቀዋል።
ከቅዳሜ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ይህ ስብሰባ አስራ አንድ የሚደርሱ አጀንዳዎች የዳሰሰ ሲሆን፣ ትናንት ማምሻውን የባለስልጣናትን ሹመት በማጽደቅ ተጠናቋል።
በዚሁ መሰረት፤ ዶክተር መንግስቱ ሁሪሳ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ሃላፊ፣ አቶ ታረቀኝ ቡልቻ የመሬት አስተዳደር ሃላፊ፤ ወይዘሮ መስከረም ደበበ የኦሮሚያ ገቢዎች ባልስልጣን ሃላፊ፣ አቶ አህመድ ሰይድ ኢብራሂም የህብረት ሥራ ኤጀንሲዎች ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ በመሆን ተሹመዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2012
በኢያሱ መሰለ
ፎቶ በጸሀይ ንጉሤ