የሰው ልጅ ምድር ላይ ሲኖር የገጠመውን ፈተና በድል ተወጥቶ ታላላቅ ድሎችን ማስመዝገብ ሲችል የግለሰቡ ጥንካሬ የትልቅነት ማሳያ መሆን ያስችላል።የአመለካከት ልዕልና ላይ የደረሰ፣ የላቀን ስብዕና የተላበሰ፣ እራሱን በላቀ ለዋጭ አስተሳሰብ ያበቃ ሰው አካሉ ቢያዝ ብልህ አዕምሮውን ተጠቅሞ ያሰበውን ማሳካት ይችላል።በዚህም የሰው ልጅ በለውጥ ሀሳብ ውስጥ እራሱን ካራመደና እችላለው ብሎ ከተነሳ መቻሉን ያሳያል።የሚፈልገውን ያደርጋል። ካሰበው የሚያስቆመው ምንም ሀይል አይኖርም።
የሰው ልጅ በተቃና አመለካከቱ፣ በተገራ ማንነቱና እሳቤው አስውቦ ዓለምን ይሰራታል።አልያም ደግሞ ቀና ባልሆነ እይታው ምክንያት ለራሱም ሆነ ለሌላው መኖሪያ ከመሆን ይልቅ ሲኦል አድርጎ ያንፃታል፤ያፈርሳታልም።አሁን ላይ ያለ ትውልድ በእጁ ያለችውን አለም ለቀጣዩ ትውልድ ባሻው መንገድ ማሸጋገር የሚችል ባለ መብት መሆኑ እሙን ነው።ይህ ደግሞ በእውን ያሳየ ታላቅ ሰው በዛሬው የዝነኞች አምድ እንግዳችን አድርገን ይዘንላችሁ ቀረብን።በታላላቅ የስዕል አውደ ርዕዮች ስራዎቹን ለህዝብ በማቅረብ አድናቆትን አትርፏል።ለየት ባለ የአሳሳል ጥበቡ ብዙዎች ለሱ ያላቸው አክብሮት የተለየ ያደርገዋል።
በፅናት ወደ ስኬት መመለስ
በጥረቱ ውስጥ የገጠመውን ትልቅ ፈተና በድል የተወጣ ወጣት ነው ሰዓሊ ብሩክ የሺጥላ።ዓለምን በበጎ ከሚገነቡ ለሰው ልጆች ብሩህ ሆና እንድትቀጥል የራሳቸውን በጎ ተፅዕኖ ከሚፈጥሩ የጥበብ ባለሙያዎች አንዱ ነው። ብርታቱ በንግግሩ ውስጥ ጎልቶ ይሰማል።በጥበቡ ቀለምን ከብሩሽ ጋር አዋዶ ሸራ ላይ በስዕል ህይወት ዘርቷል።የዓለም ልዩ ልዩ ምልከታዎችን፣ የሰው ልጅ ምስጢራትንና ስልጣኔን፣ የህይወት ልዩ ዕይታና ትርጓሜ፣ ፍቅር፣ አብሮነትንና ህብረትን፣ ጥልቅ እይታና ተፈጥሯዊ ውበትን ብሩህ አድርጎ ማሳየት ተክኖበታል፡፡በስራዎቹ ከአገር አልፎ አህጉር ብሎም ዓለም አቀፍ እውቅናን አትርፏል።ዝነኛው የስዕል ጥበብ ባለሙያው ብሩክ ።
የሰባት አመት ልጅ ሳለ እናቱ ከባህር ማዶ ያመጡለት የስዕል መሳያ ቁስ ዛሬ ለደረሰበት አለም አቀፍ እውቅና ትልቅ ምክንያት ሆነው።በትምህርት ቤት ቆይታው በስዕል ጥበብ ያለውን ልዩ ክህሎት የተመለከቱት መምህሩ ደግሞ የቤተሰብ ልዩ ድጋፍ እንዲያገኝ አደረጉ።ይህም ወደ ስዕል ጥበብ ባለሙያነት አስጠጋው። አብዛኛው ሰዓቱ የህይወትን ልዩ ልዩ መልክና የተፈጥሮን ልዩ ገፅታ በስዕል በመግለፅ ማሳለፍ ሆነ።
አካሉ ላይ የደረሰን ህመም ችሎ፤ ብሩህ አዕምሮውን በመጠቀም “የሰው ልጅ በተወሰነ ቦታ ያልተወሰነ መሆንን ያስችለዋል፡፡”በሚል መፈክሩ ከራሱ አልፎ ለሌሎች ተምሳሌት የሆነ ስኬት ላይ የደረሰ ትጉህ ሰዓሊ ነው።ማድረግ ከሚገባው በላይ ሆኖ የተገኘ ሰው ነው ብሩክ የሺጥላ።
የዝነኛው እረፍት ጊዜ
የእረፍት ጊዜውን አነቃቂ ጽሁፎችን አብዝቶ ማንበብን ይመርጣል።የተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎች ግለ ታሪክ ማንበብ የአለምን የተለየያዩ ሁነቶች መከታተል፣ተከታታይ ፊልሞችን መመልከት እና ስለ ማህበራዊ ጉዳይ መወያየት ያስደስተዋል።በተለይ ታሪክ ተኮር የሆኑ ፊልሞች አረፍ ሲል መማሪያም መዝናኛዎቹም ናቸው።
ከቤተሰብና ከጓደኞቹ ጋር ስለ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች እያነሱ ማውጋት ስለ ሀገራዊ ጉዳይ መወያየትና በልዩ ልዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ሃሳቦችን መለዋወጥ የሰዓሊ ብሩክ ዘወትራዊ ተግባሩ ነው።የምወደስ የስዕል ስራው እንደ መዝናኛም እረፍትም የሚሆነው ወዶ የሚያዘወትረው ሌላኛው የህይወት ጣዕሙን ከፍ የሚያደርግለት ድርጊቱ ነው፡፡
ከምግቦች ሁሉ በተለየ መልኩ ፍቅር ያለው ለእንቁላል ሲሆን፤ ከእንቁላል ጋር በተያያዘ የራሱ ፍልስፍና ስላለው በስዕሎቹ ደጋግሞ የሚያንፀባርቀው የእንቁላል ቅርፅን ነው።ድጋሚ ህይወት መዝራት እንደአዲስ መጀመርና የተለየ የህይወት ኡደትን በዚያ ውስጥ ማየት እንደሚያስችለውም ይናገራል።
በሌላው ዓለም ትልቅ ቦታ ያለውና እድገቱም አስገራሚ በመሆኑ የስዕል ጥበብ በአገራችን የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እንደሚችል የስዕል ባለሙያው ያላሰለሰ ጥረትና የመንግስት ለዘርፉ የሚሰጠውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል የሚኖርበት መሆኑን ያስረዳል። ያኔ ስዕልና ሰዓሊው የተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛሉ በማለት አስተያየቱን ይሰጣል።
የዝነኛው መልዕክት
“ከሌላው አገር ለአገር የሚበጅ መልካሙን ነገር ወስደን እኛ ጋር ያለውን መልካም ነገር አጎልብተን ለአገራዊ ሁለንተናዊ ለውጥ እንትጋ።አንዲት አገር ብቻ ነው ያለችን።እስዋ ውስጥ ደግሞ ያለው በመተሳሰብ ከተጠቀምን ለሁላችንም በቂ ነው።ኢትዮጵያን መልካም ሊያደርጋት የሚችል ነገርን ሁሉ እንስራ።ወጣቶች ከሁሉ ነገር በላይ አገራቸውን አስቀድመው እንደ አገር ትልቅ እንድንሆን የሚያስችሉንን ጉዳዮች የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ ይኖርባቸዋል።አንድነትና ፍቅርን ከሚሰብኩት ጋር በመቆም የጸናችና የበለፀገች ሀገርን ለቀጣይ ትውልድ እናስረክብ።“ በማለት አገራዊ ታላቅ ምክሩን ለወገኖቹ እንካችሁ ብሏል።እኛም ብርታቱ በሆነው ጥረቱና የመንፈስ ጥንካሬው ለብዙዎች ምሳሌ ይሆናል ብለን ያዘጋጀነውን ፅሁፍ በዚሁ አበቃን፤ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን ሀምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም
በተገኝ ብሩ