ታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር የውሀ ሙሌት መጠናቀቁ ሲበሰር ያልተደሰተ ኢትዮጵያዊ የለም፤ ያልተደሰተ ሰው ነበር ከተባለ እሱ ሰይጣን ብቻ ነው። ምክንያቱም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ይፋ ከሆነበት መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጀምሮ ሁሉም ዜጋ የአቅሙን አስተዋጽኦ እያደረገ መጠናቀቁን በጉጉት ሲጠብቀው ከርሟል። እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን በሚል የተጀመረው ይሄ ፕሮጀክት በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባይጠናቀቅ እና በግንባታ ሂደት ባገጠሙ መደነቃቀፎች ቢዘገይም ግድፈቶቹ ታርመው፣ አዲስ ወኔ ሰንቀን እንደምናጠናቅቀው ግን እርግጠኞች ነበርን፤ ይሄው የመጀመሪያው ዙር የውሀ ሙሌት ለዚህ ምስክር ሆነ።
ኢትዮጵያ ከባድ ልፋትና ትዕግስትን በጠየቀ ድርድርና ውይይት የመጀመሪያ ምዕራፍ ግብ ላይ ደርሳለች። ይሄ ውጤት ሀገራችን በዓለም ፊት ደምቃ እንድትታይ ያደረገ የድል ቀን ጭምር ነው። ኢትዮጵያውያን በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን በልማት ጭምር ያቀድነውን ማሳካት እንደምንችል፤ በሀገራችን የተመዘገበው ለውጥ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን መጀመር ብቻ ሳይሆን መጨረስ እንደሚቻል ማሳያ ጭምር ነው።
በህዝቡ ሁሉን አቀፍ ድጋፍና ሞራል፤ በአመራሩ ቆራጥነት የተገኘው ድልና ውጤት አስደሳች ቢሆንም አሁንም ባገኘው ድል መደሰት ሳይሆን ድሉ የቀጣዩ ስራዎቻችንና ውጤቶቻችን መነሻ እርሾ ሊሆነን ይገባል። ሀገራችን በርካታ ችግሮች ያሉባት ድህነት ደግሞ መታወቂያችን ሆኖ የቆየ ነው። የውጪ ኃይላት ሳይቀሩ ሊጠመዝዙን የሚፈልጉት ይሄንኑ ድህነታችንን መነሻ አድርገው ጥቂት ገንዘብ እያሳዩ ነው። ድህነታችን ለጥንካሬያችን አንድ አካል ሊሆነን እንጂ የሽንፈታችን መነሻ መሆን አይገባንምና ድህነትን ድል መንሻውን አንድነት ይዘን ባገኘነው ድል ተደስተን ግን ደግሞ ሳንኩራራ ለተሻለ ድል፤ ለተሻለ ውጤት መስራትና መሮጥ ከሁላችንም ይጠበቃል።
የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያው ዙር 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሀ ነው የያዘው። ይሄ በቀጣዩ ዓመት ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ ያደርጋል። በቀጣይ ግን የምንሰራቸው ስራዎች ሙሉ ለሙሉ ተርባይኖቹን ስራ የሚያስጀምር፣ አሁን ካገኘው ውጤት በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ነው።
ስለዚህ ዛሬ የገጠሙንን ፈተናዎች ተቋቁመንና ተሻግረን ነገ ከዛሬና ቀደምት ከነበረው በተሻለ ሁለተናዊ ሀገራዊ ለውጥ ለማስመዝገብ መትጋት ፣ ትልልቅ ህልሞች ማቀድ እና ማሳካት ይኖርብናል።ከልምዳችን ተምረናል በፈተና ውስጥ የሚመጣ ውጤት በራስ ለመቆም የሚያስችል ጠንካራ ምሶሶ ነውና በፈተናችን ውስጥ መዘንጋት የሌለብን ሀገራዊ ግባችን በአንድነት የሀገራችንን ልማቶች ወደፊት ማስቀጠል ነው።
የሀገራችን ሀብት ከዜጎች አቅም፣ አንድነት እና ቁርጠኝነት ጋር እስከተቀናጀ ድረስ ምንም የማይቻለን ነገር አይኖርም። ከተባበርን ለአንድ ዓላማ ከቆምን የሚያደነቃቅፍ ያጋጥመን ይሆናል እንጂ የሚያቆመን ነገር አይኖርም። እስካሁን በሄድንባቸው መንገዶችም ጠመዝማዛ ፣ ወጣ ገባ ችግሮች አጋጥመዋል፤ አልፈናቸዋል። ወደፊትም ያጋጥማሉ ፤ እንቅፋቶችን በጥበብ፣ በማስተዋልና በብልሀት በማለፍ በቆራጥነትና አንድነት በውጤት እናጠናቅቀዋለን። ያሰብነውን ለማሳካት፣ ያቀድነውን ለማጠናቀቅ፣ ባጠናቀቅነው ለመጠቀም አሁንም ወሳኝ ዳገቶች መውጣት ይጠበቅብናል። አንዱ በቃላችን መሰረት መገኘት ነው፤ እንደጀመርን እንጨርሰዋለን ብለን የገባነውን ቃል በድጋሚ አድሰን ቦንድ በመግዛት፣ በእውቀትና በሞራል በመደገፍ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ነው።
ሌላው ደግሞ ልማት ጠል የሆኑ ከውስጥም ከውጪም የሚያጋጥሙ ሀይሎችን በጋራ ክንዳችን መመከት መቻል ነው። በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መወጣት ያለብንን ትናንት እንዳሳየነው በመላው ዓለም የሚገኝ ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሁንም በእውነትና በምክንያት ላይ የተመሰረተውን የዲፕሎማሲ ጥረት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል። በሀገር ውስጥ የውስጥ ሰላምና አንድነትን በማጠናከር ድል አድራጊነታችንን ተባብረን ልንወጣ ይገባል። ይሁንና ያገኘነው ድል የሚያስደስት ቢሆንም የሚያኩራራና የሚያዘናጋን መሆን ስለሌለበት ለተጨማሪ ድል የሚያነሳሳን መሆን አለበት። ስለሆነም በተገኘው ድል ሳንኩራራ ለቀጣዩ ድል እጅ ለእጅ ተያይዘን እንስራ!
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19 ቀን 2012 ዓ.ም