ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ከምትታወቅባቸው የድልና የአርበኝነት ታሪኮች አንዱ ነፃነቷን አስከብራ የቆየች አገር መሆኗ ነው። ዓለም በቅኝ ገዢዎች ፉክክር በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በገባችበት በ19ኛው ክ/ዘመን ኢትዮጵያ ነፃነቷን አስከብራ የኖረች ብቸኛ የአፍሪካ አገር መሆኗ በጉልህ ይነሳል። በተለይ ለውጭ ወራሪ ኃይል መገዛት የኢትዮጵያውያን መገለጫ እንዳልሆነ ብዙዎች የሚመሰክሩት ሃቅ ነው። ኢትዮጵያውያን ለበርካታ ጊዜያትም ድንበር ተሻግረው የመጡ የውጭ ጠላቶችን አሳፍሮ በመመለስ ታሪክ መስራት ችለዋል።
በወቅቱ ከነዚህ እብሪተኛ የወራሪ ኃይሎች ጋር ከመዋጋት ውጪ አማራጭ አልነበረምና እነዚያ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው ሀገራቸውን ከወራሪ ኃይልና ከአምባገነን ሥርዓቶች በመታደግ ታሪክ ሰርተው አልፈዋል። ሀገራቸውንም ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላት ጠብቀው በማቆየታቸው ዛሬ ላይ ነፃነቷን የጠበቀችና የራሷ ማንነትና ታሪክ ያላት አገር እንድንወርስ አድርገውናል።
በወቅቱ እነዚህ ጀግኖች አባቶቻችን የዚህ ዓይነት መስዋዕትነት ባይከፍሉ ዛሬ ላይ የምናገኛት ኢትዮጵያ የዚህ ዓይነት ቅርፅ እና ታሪክ ላይኖራት እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ነፃነት ምን እንደሆነ ላጣጣመ ትውልድ አባቶቻችን የከፈሉት መስዋዕትነት ትርጉሙ ምን ማለት እንደሆነ መገንዘብ አይከብድም። መስዋዕትነቱ ክቡር የሆነውን ሕይወት የሚጠይቅ ነውና።
በሌላ በኩል አሁን ላይ ያለን ኢትዮጵያውያንም የዚሁ ትውልድ አካሎች ነን። ምንም እንኳን የትውልድ እና የዘመን ልዩነት ቢኖርም ሀገራችንን አሁን እንድናገኛት ያደረጉት ዜጎች አያት ቅድመ አያቶቻችን በመሆናቸው ያደረጉትን አስተዋፅኦ ከግምት ውስጥ አስገብተን እኛም በተራችን ለመጪው ትውልድ ታሪክ ያላት አገር ማውረስ እንዳለብን መረዳት ይጠበቅብናል።
ታሪክ መስራት ማለት ምን ማለት ነው? ታሪክስ እንዴት ይሰራል? ባለታሪኮችስ እነማናቸው? ለሚለው ጥያቄ በርካታ መልሶች ሊሰጡ ይችላሉ። ጀግንነትም እንደዘመኑ ትርጓሜው ሊለያይ ይችላል።
ያም ሆነ ይህ ግን ታሪክ መስራት ማለት በጦርነት ማሸነፍ ማለት ብቻ አይደለም። ታሪክ በተለያዩ መስኮች ይሰራል፤ ባለታሪኮችም በየዘርፉ ይፈጠራሉ፤ ጀግኖችም እንዲሁ። ዋናው ጉዳይ ለራስም ሆነ ለሀገር የሚጠቅምና ለመጪው ትውልድ ረብ ያለው ቁምነገር ሰርቶ ማለፍ ነው። ትውልድ የሚዘክረው ታሪክ መጻፍ/መስራት ማለት ነው።
ሀገራችን አሁን ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት በአንድ በኩል በውስጥና በውጭ ኃይሎች ሴራ አገርን የማተራመስና ብሎም የማፍረስ ጥረት ከመቼውም ጊዜ በላይ የታየበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ጋር ከፍተኛ ግብግብ ውስጥ የተገባበት ነው። በዚህ ወቅት አገርን ከዚህ ፈተና መታደግና የበለጸገችና ለዜጎቿ ምቹ የሆነች አገር ለቀጣዩ ትውልድ ማስረከብ ወቅቱ የሚጠይቀው አርበኝነት ነው።
ድህነት የሁሉ ነገር እንቅፋት ነው። ድህነት ካለ ሰላም አይኖርም፣ ድህነት ካለ የተሟላ ነፃነት አይኖርም፣ በዚህ ዘመን ድንበርን ተሻግሮ ወረራ የሚያካሂድ ጠላት ብዙም አይጠበቅም። ከዚያ ይልቅ በሴራ ሰላም እንዳይኖር የማተራመስና ከድህነት እንዳይላቀቁ ማድረግ የዘመኑ የጦርነት ስልት ነው። በአሁኑ ዘመን ጦርነት ከድህነትና ከሀብት ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት ፈጥሯል።
ዛሬ በደረስንበት ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ዘመን ድንበር ተሻግሮ የሚመጣን ኃይልም ቢሆን እንደከዚህ ቀደሙ በጦርና በጎራዴ ለማሸነፍ ጊዜው የሚፈቅድበት ወቅት ላይ አይደለንም። እነ አሜሪካና ሌሎች የሰለጠኑ አገራት ዛሬ ላይ ሰው አልባ አውሮፕላንን በመላክ እስከመዋጋት ደርሰዋል። እናም የዛሬ ውጊያ ከሰው ጋር ሳይሆን ከድህነት ጋር ነው።
ከዚህ በኋላ በኢኮኖሚም ሆነ በቴክኖሎጂ ሌሎች አገሮች የደረሱበትን እየተከተሉ አብሮ ማደግ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው። ድህነት ለተጠቂነት የሚያጋልጥ ክፉ በሽታ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ ከዚህ የበለጠ ጠላት አለመኖሩን መገንዘብ ተገቢ ነው። ድህነትን ለማሸነፍ መትጋት የሁላችንም ድርሻ ሊሆን ይገባል። የዘመኑ የአርበኝነት ተጋድሎ ድህነትን ታሪክ ማድረግና አባቶች ያስረከቡንን ነፃነት ሙሉ ትርጉም እንዲኖረው ማድረግ ነው። ለመጪው ትውልድ ነፃና የበለጸገች ሀገር ማስረከብ ነው።
በአሁኑ ወቅት አገራችን ይህንን በመገንዘብ ከድህነት ለመውጣት ዘርፈብዙ ጥረቶችን እያደረገች ነው። የሰሞኑ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌትም ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የጀመርነው የብልፅግና ጉዞ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
መንግሥት በአንድ በኩል ሰላምን ለማደፍረስ የሚጥሩ ኃይሎችን ሴራ እያከሸፈ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ የሚያስችሉ ትላልቅ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል። ይህንን ባለሁለት ሰይፍ የልማት መንገድ በድል ለመወጣት የእያንዳንዱን ዜጋ ተሳትፎ የሚጠይቅ ታሪካዊ ኃላፊነት ነው።
ከዚህ አንጻር ቀደምት አባቶቻንና እናቶቻችን ያቆዩልንን ሀገር በተሻለ እድገት ለማስቀጠል ቆም ብሎ ማሰብን የሚጠይቅበት ወቅት ነው። በተለይ ድህነት ዋነኛ የሕዝባችን ጠላት በሆነበት በዚህ ዘመን ዋነኛው ክንዳችን ማረፍ ያለበት በድህነት ላይ ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚነሱትን ቅሬታዎች መሠረት በማድረግ ያለችውን የልማት ሥራ ማውደም ደግሞ ድህነትን ማባባስ በመሆኑ ሊታሰብብት ይገባል። በሀገር ላይ የሚፈጸም ወንጀል መሆኑም በአግባቡ ሊታወቅ ይገባል።
እኛ ኢትዮጵያውያን የአንድ ሀገር ሕዝቦች ነን። ኢትዮጵያ ውስጥ ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቢኖሩም እነዚህን ሕዝቦች ግን ሊነጣጥል የሚችል አንዳችም ኃይል አይኖርም። በኢትዮጵያ ውስጥ አንዱ ከሌላው ጋር የተዋለደና የተጋመደ ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች ኅብረተሰቡ በደምና በስጋ እንዲሁም በመንፈስ ውህደት ፈጥሯል። በዚህ ዘመን ዘርን መሠረት እያደረጉ የግጭትና የብጥብጥ መነሻ በማድረግ ሀገርን ለመበታተን ጥረት ማድረግ ለሁላችንም አይበጅም። በትውልዶች ተስፋ ላይ የሚደረግ ወንጀል ነው።
እኛ ኢትዮጵያውያን የምንታወቀው በአንድነታችንና በህብረታችን ነው። የአድዋ ድል ስኬታማ የሆነው በመላ ኢትዮጵያውያን የአንድነት መንፈስ ነው። የእኛ ህብረት ለጦርነት ዘመቻ ብቻ መሆን የለበትም። ጦርነት አንጻራዊ ነው። ለልማት የሚደረግ ጦርነትም ከጦርነቶች ሁሉ የማይተናነስ ይልቁንም ለነገው ትውልድ ቅርስ ትቶ ለማለፍ የሚያስችል አቅም የሚፈጠርበት ቅዱስ ጦርነት ነው።
በተሰማራንበት የሥራ መስክ ስኬታማ ለመሆን በወኔና በአንድነት መንፈስ መስራትና ስኬት ማምጣት ደግሞ ጀግንነት ነው። ከዚህ በላይ ጀግንነት፤ ከዚህ በላይ ድል የለም። አገራችንን ለማልማት፣ ድህነትን ታሪክ ለማድረግ ራሳችንን ከብጥብጥና ከሁከት በማራቅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በሰለጠነ መንገድ ሰላማዊ የትግል ስልት በመከተል ልማታችንን ማፋጠን ይጠበቅብናል። ከብጥብጥ፣ ከጦርነትና ከርስ በርስ ግጭት አንድም ትርፍ አይገኝም። ከሰላማችን እና ከልማታችን ተጠቃሚዎች የምንሆነው በቅድሚያ እኛና እኛ ብቻ መሆናችንን ልናስተውል ይገባል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 17/2012
ውቤ ከልደታ