ሀገራችን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ በወሳኝ ወቅት ላይ ትገኛለች፡፡ ግድቡ በዚህ ሐምሌ ወር ውሃ መያዝ እንዲጀምር የተከናወኑ ተግባሮች ዳር ደርሰው አሁን መያዝ መጀመር በሚችልበት ወሳኝ ወቅት ላይ ይገኛል፡፡ የግድቡ ውሃ መያዝ መጀመር ማለት ለከርሞ ከ700 በላይ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ማግኘት ማለት ነው፡፡ እሸቱን የምንቀምስበት ወቅት ደረሰ ማለትም ነው፡፡ በዚህ የኤሌክትሪክ ኃይል መገኘት መጀመር በርካታ አሻጥሮች በሀገር ውስጥ እና በውጭ ኃይሎች ሲፈጸምበትና ግንባታው ለአሰር ዓመታት ሲጓተት የቆየው የህዳሴ ግድብ እውን ሆነ ማለት ነው፡፡ ህዳሴ ግድብ ከዚህ ሁሉ በላይም ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡፡ የሀገር ዳር ድንበር ተደርጎም የሚወሰድ እንደ መሆኑ ህልውናችን ተከበረ እንደ ማለትም ነው፡፡
ከዚህ በአንጻሩ ደግሞ ሀገራችን ወትሮውንም ቢሆን የግድቡን ግንባታ ለማሰናከል ያለ የሌለ ኃይሏን በመጠቀም ላይ በምትገኘው ግብጽና ታላላኪዎቿ ከፍተኛ ሴራ እየተጠነሰሰ ሲተገበርባት ቆይቷል፡፡ ለቁጥር የሚታክቱ ድርድሮችና ውይይቶች በኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን ለመካሄዳቸው ምክንያቷ ግብጽ ናት፡ ፡ ለደግ ከሆነ ድርድሩም ይሁን ውይይቱ ችግር የለውም፡፡ ችግሩ ግን ሌላ ሴራ ጠንስሶ ግንባታውን ለማስቀረት ካልሆነም ለማጓተት ጊዜ መግዣ አድርጋው መውሰዷ ላይ ነው፡፡ ደፋሯ ግብጽ እንደተባለው ግንባታ ቆሞ ድርድር እንዲካሄድ በተደጋጋሚ መጠየቋ ይታወቃል፡፡
ከአብሮ አደግህ አትሰደድ እንዲሉ ታዲያ ኢትዮጵያም ይህን ሴራዋን በሚገባ ትገነዘባለች፡፡ ግንባታዋን አጠናክራ በመቀጠል ነው ድርድር እና ውይይቶቹን ስታካሂድ የቆየችው፡፡ እንደ ግብጽ ሴራማ ቢሆን ግንባታው ፈቀቅም ባላለም ነበር፡፡ ምስጋና ለሀገራችን ልጆችና መንግሥቷ ይሁንና ግንባታው አሁን ውሃ መያዝ ከሚጀመርበት ታላቅ የክንውን ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
ግድቡ ውሃ መያዝ በሚጀምርበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይም ግብጽ አላረፈችም፡፡ ኢትዮጵያ ከኮቪድ 19 ጋር ግብግብ በገጠመችበት፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ መያዝ እንዲጀምር በግንባታው ላይ ርብርብ ላይ ባለችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ግብጽ ይህን ታላቅ የግድቡ ግንባታ ምዕራፍ ለማስተጓጎል እንደ እብድ ውሻ እየተክለፈለፈች ትገኛለች፡፡ የግድቡን ውሃ ሙሌት ለማሰናከል አንዴ አሜሪካ፣ ሌላ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ጸጥታው ምክር ቤት፣ ሌላ ጊዜ አውሮፓ ህብረት ሌላ ጊዜ ደግሞ አረብ ሊግ እያለች የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ሮጣለች፡፡ በቅርቡም ይህን የግብጽ ጉዳይ ለመመልከት በአፍሪካ ህብረት ታዛቢነት ድርድር ሲካሄድ ቢቆይም ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወቃል፡፡
ግብጽ በአንድ ካርታ ብቻ አትጫወትም አንዱ የሚመክን ሲመስላት በአንዱ ትጫወታለች፡፡ ለእዚህ ደግሞ እንዳለፉት
ዘመናቷ ሁሉ ዘንድሮም ኢትዮጵያውያን ተላላኪዎችን ጭምር አፍርታለች፡፡ እነዚህ ተላላኪዎች በሌለ ጠላት መንግሥትን ጠላት ብለው ፈርጀዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በሚል ለግብጽ አድረዋል፡፡ የጉድ ሀገር እንዲሉ እነዚህ ኃይሎች በእዚህ ብቻ ሳይቆጠቡ በታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን እየሆነ መምጣት ቆሽቷ ከደበነው ግብጽ ጋር እስከ ማበር የደረሱበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡
በሀገር ውስጥ በምንም መልኩ አብረው የማይሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የግብጽን ሴራ ለማስፈጸም በሀገሪቱ ላይ ዘመቻ ከፍተዋል፡፡ የዛሬ አስራ አምስት ቀን በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ከተሞች ተቀስቅሶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የነጠቀው፣ ከተሞችንና ነዋሪዎቻቸውን እንዳልነበር ያደረገው የሽብር ድርጊት በእነዚህ አኩራፊ ኃይሎች የተፈጸመ ድርጊት ነው፡፡
ትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማትን፣ ኮሌጆችን ጭምር እንዳልነበሩ ያደረገው ይህ ድርጊት በውጭ ወራሪ ጠላት ቢፈጸም አይደንቅም፡፡ በሀገሪቱ ልጆች ለእዚያውም ለዴሞክራሲ ማበብ ሲባል በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ በተደረጉ ኢትዮጵያውያን በውድቅት ሌሊት መፈጸሙ በእጅጉ ያሳዝናል፤ ያሳፍራልም፡ ፡ ኢትዮጵያ መሰል ከሀዲዎች ሲገጥሟት ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን በማይፈልጉ ኃይሎች ዳረጎት እየተታለሉ ሲወጓት የኖሩ ጥቂት አይደሉም፤ ሀገሪቱ ሴራቸው እየከሸፈ እንጂ በርካታ ጠላቶች እንዳሉባት ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ ግን ይህን ድርጊት የሚያረክሱ ብዙ አለንልሽ የሚሏት ከተፎዎችም ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያውያን ምሁራን -የቁርጥ ቀን ልጆች እንዳሏት እየተመለከትን ነው፡፡ መገናኛ ብዙኃን ከሀገር ውስጥና ከመላው ዓለም እያሰሱ የሚያወጧቸው የኢትዮጵያ የክፉ ቀን ልጆች የግብጽን ማንነትና ኢትዮጵያ መከተል ስለሚኖርባት አቅጣጫ ግንቢ አስተያየታቸውን እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ በሀገር ውስጥ በዩኒቨርሲቲዎች የሚሰሩ ምሁራን፤ በፖለቲካል ሳይንስና ውሃ እንዲሁ በታሪክ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ምሁራን፣ በተለያዩ ተቋማት በግልም ጭምር የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን የግብጽን ሴራ እያጋለጡ ይገኛሉ፡፡ ይህ በጣም የሚያኮራ ተግባር ነው፡፡
የግብጽን ሴራ ለማክሸፍ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ርብርብ እያደረጉ የሚገኙ በመላ ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እዚህ ላይ ሊጠቀሱ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ መገናኛ ብዙኃን በስካይ ፒና በመሳሰሉት እየሰጡ የሚገኘው አስተያየት ለመንግሥት ትልቅ ግብአት ይሆናል፡ ፡ በመላ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለግድቡ ግንባታና ለሀገራቸው አንዲተጉ በማድረግ በኩል ጉልህ ሚና ይኖረዋል፡፡
ሀገሪቱ ጠንካራ ጠንካራ ተደራዳሪዎችም እንዳላት ነው በየመድረኩ ከሚካሄዱ ውይይቶችና መገናኛ ብዙኃን መረዳት የሚቻለው፡፡ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ክብር መስጠት እና እንደ ዓይን ብሌን መጠበቅም ይገባል፡፡ ወቅቱ እነዚህ ምሁራን
እጅግ በርካታ መሆናቸውን በሚገባ አመልክቷል፡፡ ቀጣዩ ጊዜ በዓባይ ላይ በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ እንደመሆኑ አሁንም እነዚህን ምሁራን ማብዛት ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ እነዚህን ምሁራን የሚሳተፉባቸው መድረኮችን በስፋት ማካሄድ ይጠበቅባታል፡፡ የግብጽን የዘመናት ሴራ ከንቱ ማስቀረት የሚቻለው በተደራጀ እና ተቋማዊ በሆነ አግባብ ነውና፡ ፡ ከዚህ አኳያ እንደ መንግሥት እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮች እንዳሉ ሆነው በአባይ ጉዳይ ላይ እውቀቱ ያላቸውን ምሁራን እና ሌሎች ወገኖችን የሚያገናኝ ተቋም መመስረትም ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ተቋም አማካይነት እነዚህ ኢትዮጵያውያን እየተገናኙ በአባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም፣ተፋሰስ ልማትና በመሳሰሉት ላይ ምርምር እንዲያደርጉ ሀሳባቸውን እንዲያጋሩ ማድረግ ይገባል፡፡
በመሆኑም በዓባይ ወንዝ እና በግብጽ የዘመናት የአባይ ወንዝ ላይ ሴራ ላይ እውቀቱ ያላቸው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገሮች ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት እንዲሁም በግል የተለያዩ ሥራዎችን እየሰሩ በዚህ ጉዳይ ላይ ሀሳብ ማካፈል እና መጋራት የሚችሉ ኢትዮጵያውያንን በአንድ ተቋም አሰባስቦ በመምራት ለሀገራቸው እንዲሰሩ ሊደረ ግ ይገባል፡፡
በተረፈ ምስጋና ለኢትዮጵያውያን ምሁራን እና ለመንግሥት አሁን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴን የተመለከቱ ነገሮች በትክክለኛው መስመር ላይ ይገኛሉ፡፡ ግብጽ ግብጽ ናትና አሁንም መክለፍለፏን ቀጥላለች፤ ነገም ሌላ የማታመጣው አይኖርምና ይህን ለመመከት በተደራጀና በተጠና አግባብ ለመመከት ይሰራ፡፡ ለእዚህ ደግሞ በአባይ ወንዝ፣ በዓለም አቀፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት፣ በታሪክ እና በመሳሰሉት ላይ እውቀቱ ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ምሁራን አሰባስቦ መስራት የግድ ነው፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን በጠቅላላ አብይ አጀንዳቸው በሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ የግድቡ ግንባታ በወሳኝ ምዕራፍ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት በሀገር ቤትም በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያውያን ከግብጽ ጋር በተያዘው ግብግብ እና ለግድቡ ግንባታ በቀጣይም ድጋፍን ለማረጋገጥ በሚደረግ ጥረት ውስጥ የነቃ ተሳትፎ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡
ግብጽ አባይ የእኔ ብቻ አንጡራ ሀብት ነው በማለት ለዘመናት ያቀናበረችውን ቴያትር እንዲህ በአጭር ጊዜ ሀሰት መሆኑን ለማስገንዘብ እና የአቋም ለውጥ እንድታመጣ ለማድረግ ብዙ ጊዜና አያሌ ምሁራንን ይፈልጋል፡፡ አሁን የያዝነው የግድቡን ውሃ ሙሌት ለማስተጓጎል የያዘችውን ዘመቻ በድል ለመወጣት ኢትዮጵያውያን ከየአቅጣጫው ከመላው ዓለም ያደረጉት ርብርብ ትልቅ ግምት ይሰጣል፡፡
መንግሥት እነዚህን ኢትዮጵያውያን በሚገባ ሊያስባቸው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ለአባይ ጉዳይ በጥሪ የማይገኙ ነበሩ፤ ጉዳዩ ስላንገበገባቸው ወጥተው የታዩ ናቸው መንግሥት እነዚህን ኢትዮጵያውያን ሊያሰባስባቸውና በቀጣይ በአባይ ጉዳይ መሰራት ባለበት ሥራ ላይ ሊያሳትፋቸው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 14/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል