የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሥራ አስፈጻሚ በቅርቡ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ሰላምን፣ የህግ የበላይነትንና ፍትህን ማረጋገጥ በተለይም ኢኮኖሚው እንዲያንሰራራ ማድረግ የቀጣይ ቁልፍ ተልዕኮው መሆኑን በመግለጫው አስታውቋል።
ማንኛውም ለግጭት እና አለመረጋጋት የሚዳርጉ ሁኔታዎች በግልጽ ተለይተው በአስቸኳይ መታረም እንዳለባቸውና ሁሉም የግንባሩ አባል ድርጅቶች በዝርዝር ተገምግሞ የጋራ በተደረገው ስምምነት መሰረት በተግባር እንዲመሩና መንግሥትም ህግን የማስከበር ቁልፍ ኃላፊነቱን በጥብቅ መወጣት እንደሚገባው፤ እንዲሁም ከዚህ በፊት ይስተዋሉ የነበሩ ሌብነትና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ፈፅሞ እንዳይደገሙ በቂ ክትትል ማድረግና ለዚህ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ዝንባሌዎችን በሁሉም የሥራ መስክ እየፈተሹ መጓዝ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ለአዲስ ዘመን አስተያየት የሰጡ ፖለቲከኞች ግን ግንባሩ ያወጣው መግለጫ ይዘትና ተግባሩ አንድ ዓይነት አቋም አለመያዙን ያሳያል ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ይህ ሁኔታ በሀገሪቷ የህግ የበላይነት ላይ ተጽእኖ ከማሳደሩ በተጨማሪ አደገኛና ወደ እርስ በርስ ጦርነት የሚያመራ አዝማሚያ ሊኖረው እንደሚችልም ያመለክታሉ፡፡
በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ሀብቶም ካህሳይ እንደሚሉት፣የህግ የበላይነት ላይ ስምምነት ካልተደረሰ ሀገሪቷ ወደፊት የከፋ ሁኔታ ይገጥማታል፡፡ አራቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የሚንቀሳቀሱት በየራሳቸው ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት አካል ሳይሆን የኮንፌዴሬሽን አባል ነው የሚመስሉት፡፡ ልክ እንደ ኢጋድ አባል ሀገራት፡፡ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርም የአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ጠቅላይ ሚኒስትር እስኪመስሉ ድረስ ነው ልዩነት የሚስተዋለው፡፡
እንደ አቶ ሀብቶም ገለጻ፣ኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሠረታዊ በሆኑ ነገሮች መግባባት፣ በፌዴራሊዝም ሥርዓቱና በህገመንግሥቱ ማመን ይኖርባቸዋል፡፡ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች ካሉም በጋራ አቅጣጫ ማስቀመጥ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ በሌለበት የአስተሳሰብ አንድነትም ሆነ የህግ የበላይነት ይከበራል ለማለት አያስደፍርም፡፡ አራቱ ድርጅቶች እንደ አንድ ድርጅት ሆነው መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡እነርሱ አንድ ሲሆኑ ነው ማህበረሰቡ በእነርሱ ላይ አመኔታ የሚኖረውና ተግባብቶ የሚሠራው፡፡
የኢትዮጵያውያን ሀገርአቀፍ ንቅናቄ(ኢሀን) ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት በበኩላቸው፣ የህግ የበላይነት እንዲከበር የጋራ አቋም መያዛቸውን የሚያሳይ ነገር በውይይታቸው አለመታየቱ አደገኛ ነው፡፡ የለየለት የእርስ በርስ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል፡፡ የሥርዓቱንም ተቀባይነት ያሳጣዋል፡፡ ‹‹በስልጣን ላይ የነበሩት አብዛኛው የህወሓት አባል በመሆናቸው በሙስናም ሆነ በሰብዓዊ መብት ረገጣ ቢጠረጠሩ አይገርምም›› ያሉት ኢንጂነር ይልቃል ህግ ከማስከበር ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘቱ እያመዘነ ነው ብለዋል፡፡
የድርጅቱን መግለጫ መከታተላቸውን የገለጹት የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው፣በውይይቱ በምን ጉዳይ ላይ እንደተነጋገሩ፣ውይይታቸው ምን ያክል ግልጽነት እንደነበረውም ከመግለጫው መረዳት እንዳልቻሉና መግለጫው ግልጽ እንዳልሆነም ይናገራሉ፡፡ የህግ የበላይነት ማስከበርም የመንግሥት የዕለት ተዕለት ተግባር እንጂ ደርጅቱ በውይይት ውሳኔ ሚያሳልፍበት እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡
የወደፊት የመፍትሔ አቅጣጫ ላይ አቶ ሀብቶም እንዳስረዱት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከማንም በላይ የሀገር አንድነትን አስቀድመው በመካከላቸው ያለውን ሽኩቻ ማቆም ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ከሲቪልና ኢህአዴግን ጨምሮ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የተውጣጣ የጋራ ኮሚሽን በማቋቋም ወይንም ደግሞ ምርጫው እስኪጠናቀቅ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ የህዝብ አመኔታን ለማግኘትም ይረዳቸዋል፡፡
ለሀገር ህልውና ሲባል ሁሉም ተሳታፊ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወጣቱ ከስሜታዊነት ወጥቶ በሰከነ መንፈስና በምክንያታዊ ሆኖ ነገሮችን ማየት ይኖርበታል፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ችግሮችን ከማጉላትና ከማስፋት ማጥበብ ላይ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም የህዝብ ወገኝተኛ ሆነው የህዝብ ተደራሽነታቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል ሲሉ አቶ ሀብቶም አሳስበዋል፡፡
ኢንጂነር ይልቃል ኢህአዴግ ሁሉን ነገር በማዕከላዊነት ጨፍልቆ ከመያዝ መውጣት ይኖርበታል፡፡ በትግራይና በአማራ፣በኢሣና በአፋር፣በኦሮሚያና በሱማሌ፣በደቡብና በኦሮሚያ በአጠቃላይ በብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል ያለውን አለመግባባትና አለመተማመን ቶሎ መፍትሔ እንዲያገኝ በህግም በአሠራርም መፍታት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ረገድ ችግሮቹን ለመፍታት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አቅም ባይኖራቸውም የችግሩን አሳሳቢነት መረዳትና በጥሞና በማየት የመፍትሔው አካል መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡
ኢንጂነር ይልቃል ‹‹የፌዴራል መንግሥት ህግ ለማክበር በሙስና የተጠረጠሩና ከፍተኛ ሰብዓዊ መብት የጣሱትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት ሲያደርግ፣ በህወሓት በኩል ደግሞ እኛ ላይ ያነጣጠረ ነው ብለው በአደባባይ ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድም ተውኩት ቢሉ በህዝብ ያላቸው አመኔታና በህግ የበላይነት ላይ ያላቸው አቋም ይሸረሸራል፤ ይህ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎችን ለህግ ካቀረቡ በኋላ በይቅርታ መፍታት ሌላ አማራጭ መፍትሔ ሊሆን ይችላል» ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
ፕሮፌሰር በየነ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀባይነት አለማግኘታቸው እንጂ በአቅማቸው አማራጭ መፍትሔዎችን ከመስጠት እንዳልተቆጠቡና እንደማያቋርጡም ይገልጻሉ፡፡ «እስከመጪው ምርጫ ድረስ የህዝቡን ሰላም በመጠበቅ በኩል በስልጣን ላይ ካለው መንግሥት ከፍተኛ ሥራ ይጠበቅበታል፡፡ ሁሉም የሚንቀሳቀሰው በህገ መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ስለሆነ ኢህአዴግና አባል ድርጅቶቹን ጨምሮ የህግ የበላይነትን አክብረው ከተንቀሳቀሱ መረጋጋት ይፈጠራል፤ ሁሉም ለመፍትሔ የየራሱን ለመወጣት ጥረት ካላደረገ የህግ የበላይነት አደጋ ላይ ይወድቃል» ሲሉ ይገልጻሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2011
በለምለም መንግሥቱ