ኢትዮጵያ በተፈጥሮና በደን ሀብቶቿ የታደለች ለምለም ሀገር ብትሆንም ባለፉት አሥርት ዓመታት ደኖች በከፍተኛ ሁኔታ መመናመናቸው ደግሞ እውነት ነው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የነበረው የደን ሽፋን 40 በመቶ ቢሆንም አሁን ወደ 15 በመቶ አሽቆልቁሏል። ወደዚህም ደረጃ የተደረሰው በተሰሩ በርካታ ሥራዎች ነው እንጂ ሽፋኑ ወደ 3 በመቶ ዝቅ ብሎ እንደነበርም ሲገለጽ ቆይቷል። የተመናመኑ የደን ሀብቶች ወደ ነበረበት ለመመለስ እንኳን ባይቻልም መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ በርካታ ሥራዎችን የሚጠይቅ ነው።
ደኖች ከመሬት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን በካይ ጋዝ አምቀው በመያዝ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም በመስጠት ፤ እርጥበታማ አፈር በመያዝና የከርሰምድርና የገጸ ምድር ውሃ እንዲጠራቀም የሚያደርጉ ናቸው። እነዚህን ደኖች ማልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም ዘላቂና ፈጣን ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል በመሆኑ በአፈር ለምነትና ጥበቃ፣ በገፀ ምድርና ከርሰ ምድር ውሃ ሃብት፣ በእፅዋትና በደን ልማት ላይ በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጥናቶች ያረጋግጣሉ ።
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ሊያጋጥሟት ይችላሉ ተብለው ለሚገመቱት ያልታሰቡ የድርቅ አደጋዎች የአካባቢ ጥበቃና የተፋሰስ ልማት ላይ የሚሰሩ የልማት ሥራዎች ፍቱን መፍትሔ የሚሰጡ ናቸው። በእነዚህ የልማት ሥራዎች ላይ አርሶ አደሩን በማሳተፍ የአፈርና ውሃ እቀባ ሥራዎች ማከናወን የአካባቢው ልምላሜ ከመመለስ ባሻገር ደርቀው የነበሩ ምንጮች ውሃ እንዲያፈልቁ እርጥበታማ አየር እንዲኖር ያደርጋሉ።
በተለይ በሀገሪቱ በአንዳንድ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የተቀናጁ የተፋሰስ ልማት ሥራዎች የተራቆቱ መሬቶች መልስ እንዲያገግሙ በማድረግ ለአረንጓዴ ልማት መሠረት የሆኑና ከፍ ሲልም በዘላቂነት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዙና የህብረተሰብ አቀፍ ንቅናቄን የሚያጠናክሩ ናቸው። ከዚህም ባሻገር የተፋሰስ ልማት ሥራዎች ድርቅን ከመቋቋም አልፈው ለገጠር ወጣቶች የሥራ እድል የሚፈጥሩ ፤ የስነ-ህይወታዊ ዘዴን የሚያጠናክሩ፤ ለእንስሳት ሀብት ልማት፣ ለአትክልት፣ ለፍራፍሬና ለደን ልማት የሚውሉ መሆናቸውን በተጠናከረ መንገድ ሊሰራባቸው የሚገቡ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ይነገራል ።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ አረንጓዴ ልማትን በተፋሰስ ልማት ላይ በማልማት እንቅስቃሴዎች በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑ ይታወቃል። ሀዋሳ ከተማና አካባቢ የሚገኙ አረንጓዴ ልማትን በተፋሰስ ሥራዎች ላይ በማልማት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ከሚገኝባቸው ቦታዎች በመሆኑ ተጠቃሽ ነው። ይቺ ችግኝ ተከላ የተጀመረባት ውብ አረንጓዴ ልምላሜን የተላበሰችዋ ሀዋሳ በባለፈው ዓመት የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብም ሆነ በተፋሰሶች ላይ የጀመረችው የአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ይበል የሚያሰኙ ናቸው።
የተፋሰስ ልማቶች ሥራዎቹ የተራቆቱ አካባቢዎችን መልሶ በማልማት በርካታ ሥራዎች እየተሰራባቸው መሆኑን አስመልክቶ የሀዋሳ ከተማ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቅረ እየሱስ አሸናፊ እንደሚናገሩት፤ እነዚህ በሀዋሳ ከተማና አካባቢ እየተሰሩ የሚገኙ የተፋሰስ ልማቶች አበረታች ውጤት እያስገኙ ያሉ ለአረንጓዴ ልማት ተስፋ ሰጪ ምልክቶች ናቸው።
አቶ ፍቅረ እየሱስ አሸናፊ እንደሚገልጹት፡- በዘንድሮ ዓመት በሃዋሳ ከተማና ዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች በአረንጓዴ ልማት 3ሚሊዮን ችግኞች ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው። የሃዋሳ ከተማ አሥራ ሁለት የገጠር ቀበሌዎች ወይም አንድ ክፍለከተማ ያላት ሲሆን ፤ በእነዚህ የገጠር ቀበሌዎች 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ችግኞችን፤ በከተማ ደግሞ አራት መቶ ሺህ ችግኞች በአጠቃላይ 3 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ ነው ።
በገጠር በሚገኙ 18 ተፋሰሶች ላይ ኤክስዋይ ኮርድኔት በመውሰድ እንዲሁም በከተማ በሚገኙ ታቦርና አላሞራ ተራራ በሚል ስያሜ በሚታወቁ ሁለት ቦታዎች ላይ ሁለት ኮርድኔት በመውሰድ በአጠቃላይ 20 ተፋሰሶች ላይ የአረንጓዴ ልማት ሥራ እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል ።
በተፋሰሶች ውስጥ የሚገኝ 200 መቶ ሄክታር መሬት ተለይቶ ዛፍ እንዲተከልበት ተደርጓል። ከዚህ
በተጨማሪም የከተማ ዙሪያ እንደመሆኑ መጠን ሰፊ መሬት ባይኖርም በእያንዳንዱ አርሶ አደሩ በጓሮው 50 ችግኞችን በነፍሰ ወከፍ እንዲተክል እንዲሁም እያንዳንዱ የከተማ ነዋሪ ደግሞ በግቢውና በበሩ ላይ አራት ችግኞች መትከል እንዲችል ለማድረግ የተለያየ ስልት ተቀይሶ ወደ ሥራ የተገባ መሆኑን ይናገራሉ።
እንደነዚህ አይነቱን ስልቶችን በመቀየስ የዘንድሮውን የአረንጓዴ ልማት ሥራ ቀደም ብሎ በሚያዚያ ወር በመጀመሪያ አካባቢ 850ሺ ችግኞችን በመትከል የተጀመሩ መሆኑን የሚገልጹት ኃላፊው፤ በሀገር አቀፍ ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በግንቦት ወር በሀዋሳ ታቦር ተራራ ላይ ባስጀመሩት የችግኝ መክፈቻ ፕሮግራም መከናወኑን አስታውሰው፤ በከተማው በሚገኙ ሁሉም መምሪያዎች ሁሉም የልማት ተቋማት ፤ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማትና የመንግሥት ሠራተኞች በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ተከላ እያካሄዱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ተጠናክሮ በቀጠለው የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እስካአሁን ድረስ 2 ሚሊዮን 200 መቶ ሺህ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን ቀሪ 800 መቶ ሺህ ችግኞችን በ15 ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል። በሚቀጥለው ሳምንትም የማጠቃለያ ምዕራፍ ሥራዎች በመስራት በዘንድሮ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ሥራ ያልተሸፈኑ ክፍት የሆኑ ሁሉም ቦታዎች በመሸፈን የሚጠቃለል መሆኑን ገልጸዋል። ለተከላው ከሚውሉ ችግኞች ውስጥ 30ሺ ዘርፈ ብዙ የሚሆኑን ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ሲሆን 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች በአረንጓዴ ልማት የመኖ ቁርጥራጭና ግንጣይ በተራሮችና በጋራዎች ላይ ተተክለው የሚለሙትን የሚያካትት መሆኑን አመልክተዋል።
የተፋሰስ ልማቱ 1ሺህ 80 ሄክታር መሬት ላይ ያሉ ተፋሰሶች የሚያካትት ነው የሚሉት ኃላፊው፤ የተፋሰስ ልማቶቹ በ2011 በጀት ዓመት የተለዩ ሲሆኑ ዘንድሮም እነዚሁ እንዲቀጥሉ የተደረገ እንጂ ሌላ አዲስ ተፋሰስ ልማት ዲዛይን ያልተደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ። በተፋሰሶቹ ላይ የሚሰሩ ሥራዎች አንድ ጊዜ ከተጀመረ ተከላው እዚያ ላይ እየተጠናቀቀ የሚሄድ ሆኖ በተፋሰሱ ላይ የዛፍ ተከላ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፈርና የውሃ እቀባ ፊዚካል ሥራዎች በቁፋሮ የሚሰሩ መኖራቸውን ይገልጻሉ ።
በተፋሰስ ልማት ሥራዎች አካባቢ የእንስሳት መኖ ልማት እርባታ እጅግ ጠንካራ በመሆኑ ለእንስሳት መኖ የሚሆኑ ዛፎች ይለማሉ ያሉት ኃላፊው፤ ይህ የእንስሳት መኖ ልማት አፈርን ከጎርፍ ለመከላከል ሥራ የሚውል ሆኖ በሚደርስበት ወቅት ደግሞ ማህበረሰቡ በጋራ እያጨደ የሚጠቀምበትና ለእንስሳት መኖነት የሚገለገልበት መሆኑን ይናገራሉ።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፈር ዞን በመባል በሚጠራው በሀዋሳ ሀይቅ ዙሪያ በሚገኘውና በሌሎችም በፈር ዞኖች ላይ የሙዝና የመኖ ተክሎች በመትከል አፈር ወደ ሀይቁ ዙሪያ እንዳይገባ የመከላከል ሥራ እየተሰራ ነው የሚሉት ኃላፊው፤ ኃይቅን ወይም ወንዝን ተከትሎ ምንም የማይሰራበትና ከንክኪ ነጻ የሚሆን ቦታ በፈር ዞን ይባላል። ሳይንሱ እንደሚመክረው ለምሳሌ ከሀዋሳ ሀይቅ 200 ሜትር ወጣ ብሎ ሌሎች ነገሮች መትከል እንደማይቻል ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ ሳይንሱ ተግባራዊ ሲደረግ አይታይም። በፈር ዞን አካባቢ የሙዝና የመኖ ተክሎች በሚተከሉበት ጊዜ ከላይ የሚመጣውን ጎርፍ በመከላከልና አፈሩን ይዞ በማስቀረት የተጣራ ንጹህ ውሃ ወደ ሀይቁ እና ውሃ መፍሰሻ ቦታዎች የሚገባ መሆኑን ጠቁመው ፤ በዘንድሮ የአረንጓዴ ዘመቻ ሁለት ሺህ የሙዝና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን የመኖ ቁርጥራጭና ግንጣይ በመትከል አብሮ እየተሰራ ያለበት ሁኔታንም አመልክተዋል ። ይህም በዚህ አሥራ አምስት ቀናት ውስጥ የሚጠናቀቅና አፈጻጸሙም በዚሁ በ2012 በጀት ዓመት የሚጠናቀቅ መሆኑን ያብራራሉ።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ አሞራ ተራራ ላይ ካቻምና፣ አምናና ዘንድሮም የተተከሉ ችግኞች በየዓመቱ እያሳዩ ያለው የእድገት ደረጃ በጣም ጥሩ ነው። አሁን ላይ ባሉ ተፋሰሶችም እየተተከሉ ያለው ችግኞች በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሲሆን የሀዋሳ ከተማ በአረንጓዴ ልማት የማትታማ በመሆኗ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ይገልጻሉ። በተፋሰሱ ዙሪያ ላሉ አርሶ አደሮች ተፋሰሶችን የመንከባከብና የጥበቃ ሥራዎች እንዲሰሩ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የተፋሰሱ የደን ጥበቃ ዙሪያ የሚገኙበት ቦታ በከተማ ዙሪያ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን ሳይንሱ እንደሚለው ማህበረሰቡ እራሱ ነው መጠበቅ ያለበት። ነገር ግን የማህበረሰቡ አስተሳሰብን በማጎልበት የሚፈለገው ደረጃ እስከሚደርስ ድረስ እዚያ አካባቢ ያሉ በመስሪያ ቤቱ የሚደጎሙ የጥበቃ ሥራዎች የሚሰሩ መሆናቸውን አመልክተዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ማህበረሰቡን በጋራ በማቀናጀት ሙሉ ለሙሉ በእኔነት ስሜት ተቀብሎ እንዲጠብቅ በማድረግ የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ይጠቁማሉ።
በተፋሰስ ልማት ዙሪያ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች አንዳንድ ህገ ወጥ ሰዎች ዛፎች ቆርጠው በመውሰድ ፤ እንዲሁም ልቅ በሆነ ሁኔታ ከብቶችን በመልቀቅ ችግኞችን እንዲጎዱ የሚያደርጉበት ሁኔታዎች መኖራቸውን የሚገልጹት ኃላፊው፤ እነዚህ ከንክኪ የሚከለሉ ቦታዎች እንስሳትና ሌሎች አካላት በሚነኳቸው ጊዜ ቶሎ እንደሚጎዱ ይናገራሉ። በሌላ በኩል አመቺ ያልሆኑ የአየር ንብረት ሁኔታዎች በአንዳንድ ቦታዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ለምሳሌ አሸዋማና ቆላ ነክ የሆኑ ቦታዎች የሚተከሉ ችግኞች በበጋ ወቅት አየሩን ለመቋቋም
የሚያስቸገሩበት ሁኔታዎች መኖራቸውን ይገልጻሉ። በተለይም ጋራና ተራራማ አካባቢዎች ችግኞች በጋን ለመቋቋም እንቅፋት ይገጥማቸዋል። ይህንን ችግር ለመቅረፍም በተለይ ዘንድሮ ትኩረት በመስጠት የአየር ንብረቱንና በጋን የመቋቋም ችሎታ ያላቸውን እንደ ግራር አይነት ችግኞችን ወደ ጋራና ተራራማ ቦታዎች በማምጣት እየተሰራበት መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ይህን ስልት በማስቀጠል የልማቱን ሥራ ውጤታማ ለማድረግ የሚሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
እንዳ ኃላፊው፤ የሲዳማ ክልል ለየት የሚያደርገው ነገር በአግሮ ፎረስተሪ የግብርና ሥርዓት የሚበዙበት መሆኑ ነው። አግሮ ፎረስተሪ ሥርዓት ደግሞ ለየት የሚያደርገው ስነምህዳር ለመጠበቅ የደኖች፤ ዛፎችና ሰብሎች እንዲሁም የእንስሳት እርባታው በእኩል መኖራቸው ነው። ሌላው አግሮ ፎረስተሪ ሥርዓት ውስጥ ሆኖ ቡናንም የሚያለማ አካባቢ መሆኑ፤ ቡና እራሱን የቻለ እንደ አንድ ደን የሚታይ ሲሆን ይህም ከሃዋሳ ዙሪያ ወጣ ብሎ የሚገኝ ነው። የቡና አቅራቢ በመሆን ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከሚያስገኙት ውስጥ ሲዳማ ብሔራዊ ክልል አንዱ መሆኑን የሚጠቁሙት ኃላፊው፤ የህብረተሰቡ ማህበራዊ ኢኮኖሚ በአግሮ ፎረስተሪ ሥርዓት ላይ የተመሰረተ መሆኑን ይናገራሉ። እነዚህ በአንድ ላይ ተያይዘው ሲታዩ የእንስሳት እርባታውንም ቋሚ ተክሎችንና ዓመታዊ ሰብሎችንም አንድ ላይ አድርጎ የሚይዝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሀገራችንን ቀጣይነት ያለውን አረንጓዴ ልማት መነሻ በማድረግ ወደ ፊት እየተጓዘች ነው የምትገኘው የሚሉት ኃላፊው፤ የተረጋጋ ስነምህዳር ለመፍጠር ይህንን ግንዛቤ ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መድረስ አለበት። መንግሥትም በቂ ሀብትና ፋይናንስ በማፍሰስ ሥርዓት እየዘረጋ ዘርፉን እያስፋፋ ቢሄድ የበለጠ የሚያጎልበተው መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት የሚባልበት ምክንያትም አየር ንብረቱ ካልተረጋጋ ምንም ለውጥ ማምጣት የማይቻልበት ሁኔታ የሚፈጠር በመሆኑ ነው። ስለምህዳሩ ባልተረጋጋ ቦታ ላይ ደግሞ ትክክለኛ የሆነ የወቅቶች መፈራረቅ አይኖርም፤ ትክክለኛ የሆነ የወቅቶች መፈራረቅ ከሌለ ደግሞ ሌሎችም የተለያዩ ችግሮች ሊከሰቱ ይችላሉ ብለዋል።
በሀገራችን እስካአሁን እንደሚታወቀው በአብዛኛው የግብርና ልማቱ የዝናብ ውሃ በመጠቀም የሚከናወን ሲሆን ፤ ከዚህ ተላቀን ወደ መስኖ ልማት መሸጋገር እስከምንችል ድረስ የአረንጓዴ ልማቱን ለማስቀጠል የሁሉም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአረንጓዴ ልማት የህልውና መሠረት በመሆኑ ሁሉም በሀገር ውስጥ ያለም ሆነ በውጭ ያለ ዜጋ ትኩረት በመስጠት በዘመቻው ላይ በመሳተፍ የራሱን አሻራ ማሳረፍ አለበት ሲሉ ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 13/2012
ወርቅነሽ ደምሰው