በዳቮስ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ከትናንት በስቲያ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ለውጥ በመደመር ፍልስፍና ላይ በመመርኮዝ በሶስት ምሰሶዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር አጽንኦት ተሰጥቶ እየተሰራበት መሆኑን አስታውቀዋል።
ከሶስቱ ምሰሶዎች አንዱ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ማሳደግና ማበልጸግ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፤ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት ለማሻሻልና የአገሪቱን ዕድገት ለማፋጠን አዳዲስ አቅጣጫዎችን ተቀይሰው እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ በዚህም ታላላቅ የሀገሪቱን ኩባንያዎች በከፊል ፕራቬታይዝ የማድረግና የፐብሊክ መንግስት ሽርክናን በሥራ ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን በመግለጽ፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ አስተያየታቸውን የሰጡት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ማህበር የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ አቶ አሚን አብደላ እንደተናገሩት፤ በመንግስትና በግሉ ዘርፍ ሽርክናና በፕራይዜታይዜሽን አማካይነት የተመዘገቡ ውጤቶችን ለመገምገም አስር ወር በቂ አይደለም፡፡ ሆኖም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች አበረታች ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ከመንግስት ባለቤትነት ሊላቀቁ አይችሉም የተባሉ ድርጅቶችን ጭምር በሙሉ ወይም በከፊል የማላቀቅ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ በዚህ መሰረት ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውም መልካም የሚባል ነው፡፡ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መሆን ሲጀምሩ የሀገሪቷን ዕድገት በማፋጠን ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማድረስ መሰረት የሚሆኑ ናቸው፡፡
አቶ አሚን አሰራሩ የግሉ ዘርፍና የመንግስት ሽርክናን በተመለከተ የግሉ ዘርፍ ስኬታማ የሚሆንበትን ለግሉ ዘርፍ ለመተውና መንግስት የተሻለ ውጤት ሊያስመዘግብባቸው ይችላሉ ተብለው የተለዩ ዘርፎችን ለመንግስት ለመተው የሚፈቅድ በመሆኑ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገትና ለውጤታማነት ትልቅ እስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡
እንደ አቶ አሚን ማብራሪያ፤ መንግስትና የግሉ ዘርፍ ሽርክና በርካታ ሞዴሎች አሉት፡፡ ከነዚህ ሞዴሎች ውስጥ ለሀገር የሚጠቅመውን ለይቶ ስራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም ለሀገር የሚበጁ ሞዴሎችን የመለየት ጥናቶች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ በመሰረተ ልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ፣ በማዘጋጃ ቤት ፣ የፐብሊክ ፕራይቬት ሽርክናን በስራ ማዋል ይቻላል፡፡
ፕራይዜታይዝ ለማድረግም እንዲሁ የተለያየ አተገባበር መኖሩን የሚያነሱት አቶ አሚን፤ እነዚህም ሙሉ በሙሉና በከፊል ፕራይዜታይዝ መሆናቸውን ያነሳሉ፡፡ ወደ ግል ሲዛወርም እነማን መሳተፍ አለባቸው የሚለውም ታሳቢ መደረግ አለበት፡፡ መሳተፍ ያለባቸውና የውጭና የሀገር ውስጥ ድርጅቶችም መለየት አለባቸው ይላሉ፡፡ በዚህ ሂደት ዝቅተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታም ታሳቢ ሊደረግ ይገባል ይላሉ፡፡
አቶ አሚን የፐብሊክ ፕራይቬታይዝ ሽርክና ሲተገበር ጥንቃቄ የሚፈልጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ የትኛው ዘርፍ በመንግስት መያዝ አለበት፤ የትኛውንስ በግሉ ዘርፍ መያዝ የስፈልጋል በሚለው ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ ከዚህም በመነሳት ሁለቱም የተሻለ አገልግሎት ሊሰጡና ስኬታማ ሊሆኑ የሚችሉ ዘርፎችን ለይተው መያዝ አለባቸው ብለዋል፡፡
የተጀመረው የግሉን ዘርፍና የመንግስት ሽርክናን ፕራይቬታይዝ ማድረግ የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያመጣ ሁለቱም የየድርሻቸውን መጫወት አለባቸው ያሉት አቶ አሚን፤ መንግስት መሰረተ ልማት በመዘርጋት፣ አደናቃፊ ችግሮችን በመፍታት፣ ህጎችን በማውጣት የግሉ ዘርፍ በድፍረት በኢኮኖሚው ላይ እንዲሳተፍ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
ከግሉ ዘርፍ አቅም በላይ በሆኑ ዘርፎች ላይ በመሳተፍ ክፍተት የመሙላት ስራውን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጠቆሙት አቶ አሚን፤ የግሉ ዘርፍና መንግስት መናበብና መመጋገብ ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት የማይተካ ሚና ስላላቸው ሁለቱ መናበብ ከቻሉ ራሳቸውን ከመጥቀም አልፈው ሀገርን ሊያበለጽጉ ይችላሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ኑረዲን ጁሃር፤ በሀገሪቱ የለውጥ እንቅስቃሴ ከጀመረበት ካለፉት ዘጠኝ ወራት ወዲህ ኩባንያዎችን በከፊልና በሙሉ ፕራይቬታይዝ ለማድረግና የግልና የመንግስት ሽርክናን ለመተግበር የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች በመንግስት እንቅስቃሴ ብቻ የሚሳኩ አይደሉም ያሉት አቶ ኑረዲን፤ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቀና ጥረትና ትብብር እንደሚጠይቁና መንግስት ሁኔታዎች ለማመቻቸት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የግሉ ባለሀብትም በአጭር ጊዜ ትርፍ በሚገኝባቸው ዘርፎች ላይ ብቻ መዋዕለ ንዋዩን ከማፍሰስ ይልቅ በረጅም ጊዜ ሀገርንና ህዝብን ተጠቃሚ ሊያደርጉ በሚችሉ ዘርፎች ላይ ከመንግስት ጋር ለመስራት ዝግጁ በመሆን የኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግና ማስመዝገብ እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡
እንደ አቶ ኑረዲን ማብራሪያ፤ የፐብሊክ ፕራይቬት ሽርክናና ፕራይቬታይዜሽን የሚፈለገውን ለውጥ እንዲያስገኝ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ ግንባር ቀደሙ የርዕዮተ ዓለም ጉዳይ ሲሆን፤ የአንድን ሀገር ኢኮኖሚ ለማሳደግም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ወሳኝ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚመነጨው ደግሞ ከርዕዮተ ዓለም በመሆኑ ሀገሪቱ የምትከተለውን ርዕዮተ ዓለም መለየት አለባት፡፡ ይህ ካልሆነ መንግስትና የግሉ ዘርፍ በምን መልኩ መስራት እንዳለባቸው አቅጣጫ ለማስቀመጥ አዳጋች ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 17/2011
በመላኩ ኤሮሴ