የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የስምንት ሀገራት አምባሳደሮችን የሹመት ደብዳቤ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው እንደገለፁት በዛሬው ዕለት የስምንት ሀገራት አምባሳደሮች የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል፡፡
ከስምንቱ መካከል ስድስቱ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ያደረጉ ሀገራት ናቸው ያሉት አቶ ነብያት ሁለቱ ደግሞ በጎረቤት ሀገሮች ኢትዮጵያን ሸፍነው የሚሰሩ ናቸው ብለዋል፡፡
አምባሳደሮቹ በአገራቸውና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስፋፋት ዝግጁነታቸውን ገልፀዋል፡፡
በአገራቸውና በኢትዮጵያ መካከል በንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ በቱሪዝም እንዲሁም የሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደሮቹ በአገራችን እየተካሄደ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ በቅርበት እንደሚከታተሉትና የአገሮቻቸው ሙሉ ድጋፍ እንዳለ ገልፀው በቀጣይም አብሮ ለመሥራት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው እነዚህ አምባሳደሮች በቆይታቸው የሚወክሉት አገርና ከአገራችን ጋር ያለው ግኙነት ይበልጥ እንዲጠናከር የመንግስት ሙሉ ድጋፍ አንደማይለያቸው አረጋግጠውላቸዋል፡፡
የሹመት ደብዳቤያቸውን ያቀረቡት የካናዳ አምባሳደር አንቶኒ ቼቭረኤር ፤የቱርክ አምባሳደር ያፕራክ አልፕ፤ የሴራሊዮኑ አምባሳደር ዶክተር ብሪማ ፓትሪክ ካፑዋ፤ የኢካቶሪያል ጊኒ ክሪስአንቶስ ኦባማ ኦንዶ፤ የስሎቫክ አምባሳደር ድራሆሚር ስቶስ፤ የሰርቢያ አምባሳደር አሌክሳንደር ሪስ ቲች፤የኮሎምቢያ አምባሳደር ኤልዛቤት ኢንስ ቴይለር ጃይ እና የማልታ አምባሳደር ሮናልድ ሚካሌፍ ናቸው፡፡
በማዕረግ ገ/እግዚአብሄር