በደቡብ ክልል በርካታ የብሄረሰብ ሙዚቃዎች እንዳሉ ቢታወቅም በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች አንድም የሙዚቃ ት/ቤት አለመኖሩ ጥናቶችንና ምርምሮችን በስፋት ለማድረግ እንቅፋት መፍጠሩን የዘርፉ ምሁራን ተናገሩ።
የመጀመሪያው የፊላና የባህል ፌስቲቫል በደቡብ ክልል የሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን ዲራሼ ወረዳ ጊዶሌ ከተማ ከጥር 11-13/2011 ዓ.ም ተካሂዷል።
የፌስቲቫሉ ማጠቃለያ ላይ ‘በምስራቅ አፍሪካ የሙዚቃ ሳይንቲስቶች’ በሚል በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ጥናት ያቀረቡት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪው አቶ ፍሬው ተስፋዬ በፊላ ላይ ጥቂት ጥናቶች ተደርገዋል ነገር ግን ተጨማሪ ጥናት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
አቶ ፍሬው በጥናታቸው በፊላ ላይ ሶስት ምርምሮች ቢደረጉም ሶስቱም የተለያዩ ሀሳቦችን ያነሳሉ ስለዚህ ይህንን ቱባ ባህል በጥልቀት ማጥናትና ለአለም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
ከአርባምንጭ መምህራን ኮሌጅ የመጡት መምህር ምስራቄ ፀሀይ ባቀረቡት ፅሁፍ የደቡብ ክልል በርካታ የብሄረሰብ ሙዚቃዎች እንዳሉ ቢታወቅም የደቡብ ዩኒቨርሲቲዎች ግን አንድም የሙዚቃ ት/ቤቶች የላቸውም፤ ይህም የብሄረሰብ ሙዚቃዎችን በሰፊው ለማስተዋወቅና ምርምሮችን ለማድረግ አንዱ እንቅፋት ሆኗል ብለዋል።
ለአብነትም የዲራሼ ህዝቦች ዘርፈ ብዙ መገለጫ የሆነው ፊላን በተመለከተ የተደራጀ ስራ አልተሰራም፤ ጥናቶች ቢደረጉም በፊላ ዙሪያ መጠናት ከነበረበት እጅግ ያነሱ ናቸው ብለዋል።
በፊላ ዙሪያ ጥናቶችን በማድረግ በሰፊው የማስተዋወቅ ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ በውይይቱ ተገልጿል።
በውይይቱ ከፌደራልና ክልል ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት ባለስልጣናት፣ የወረዳው አመራሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የልማት አጋሮች የተገኙ ሲሆን በፊላ ዙሪያ መሰራት ስላለባቸው ስራዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
ፊላ ከ24-29 የሙዚቃ መሳሪያዎች አገልግሎት ላይ የሚውሉበት የትንፋሽ፣ የምትና የእንቅስቃሴ ቅንጅትን በአንድነት አጣምሮ የያዘ የዲራሼዎች ባህላዊ ጨዋታ ሲሆን በአብዛኛው ከጥምቀት በዐል ጋር ተያይዞ በህብረት ይከወናል።
በድልነሳ ምንውየለት