አዳም ክፉንና ደጉን ከሚያስታውቀው ከዚህ ዛፍ አትብላ ተብሎ ከፈጣሪው የተሰጠውን ትዕዛዝ ተላልፎ በሰራው ኃጢያት ወደዚች ምድር ከመጣ ጊዜ አንስቶ እንኳ ብናሰላው ህክምና የባህሉን ጨምሮ እልፍ አዕላፍ ዓመታትን አስቆጥሯል።የሕክምና አባት በመባል ከሚታወቀው የቆሱ ሂፓቅራጠስ / ታላቁ ሂፓቅራጠስ / እንኳ ብንነሳ” ዘመናዊ “ህክምና ቢያንስ 2ሺህ ዓመት እና ከዚያ በላይ ሆኖታል።ዳሩ ግን ዛሬም ራስ ምታትን በቅጡ መፈወስ አልቻለም።ይህ ሲባል ህክምና በአድናቆት እጅን በአፍ የሚያስጭኑ እንደ ጂኖምና ክሎን ያሉ ግኝቶችና ስኬቶች የሉትም ማለት አይደለም።ስኬቶቹ ካንሰርን ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስን ፣ የአእምሮ ዝግመትን ፣ ሽባነትን ፣ አምኔዥያን ፣ ዲሜንሽያን ፣ የአእምሮ ዝግመትንና እንደ ስኳር ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ፈዋሽ ህክምናም ሆነ መድሀኒት አለማግኘቱን ለማውሳት ተፈልጎ እንጂ።
የህክምና ዘርፉን እጀ ሰባራ ያደረጉት ምክንያቶች በቀጥታ ረቂቅና ሚስጥራዊ ከሆነ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ጋር የተያያዘ መሆኑ፤ የመድሀኒትም ሆነ የህክምና ሙከራው እንደ ሌሎች የሳይንስ ዘርፎች በግኡዝ ነገሮች ሳይሆን በሰው ላይ የሚካሄዱ ስለሆነ እጅግ ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑ እና በጤና ዘርፍ የሚደረጉ ምርምሮች የተመራማሪውን ህይወት አደጋ ላይ ሊጥሉ ስለሚችል ልዩ ጥንቃቄ የሚጠይቅ መሆኑ እንደ ሌሎች የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ማደግ አለመቻሉን በጥቁር አንበሳ የህክምና ኮሌጅ መምህርና የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶክተር አምሳሉ ቢተው ይገልጻሉ።ከህክምና ውጭ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ባሉ ግኝቶችና ፈጠራዎች መታገዝ ባይችል ኖሮ ኋላ ቀርነቱ ከዚህ የባሰ ሊሆን እንደሚችል ዶ/ር አምሳሉ ያወሳሉ፡፡
ከሰሞነኛ የሀሳብ ሰበዞቼ ህክምናን የመዘዝሁት ኋላ ቀርነቱ የኮቪድ19 በተከሰተባቸው የመጀመሪያ ሁለት ወራት የፈጠረው ድንጋሬ ወረርሽኙ ድምጹን አጥፍቶ በስፋት እንዲሰራጭ ያደረገውን ክፍተት ከተነባቢው “ዘ ኒውዮርክ ታይምስ “ በመመልከቴና ከአራት ወራት በኋላም በሀገራችን ቫይረሱ ኖሮባቸው የሕመም ምልክት የማያሳዩ ኮቪድ 19 እንደሚያስተላልፉ የጠራ ግንዛቤ ስለመኖሩ እርግጠኛ ስላልሆንሁ ነው፡፡
“ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ “ ሰሞኑን ከደርዘን በላይ ሀኪሞችንና የጤና ባለሙያዎችን ቃለ መጠይቅ አድርጎ ይፋ ባወጣው ሪፓርታዥ ፤ ኮቪድ 19 በተከሰተባቸው የመጀመሪያ ሁለት ወራት በቫይረሱ ተይዘው የህመም ምልክት ያልታየባቸው / ሲፕተምለስ / ሰዎች ቫይረሱን ወደ ሌላ ሰው እንደሚያጋቡ በቂ ሳይንሳዊ መረጃዎች ቢኖሩም የምዕራባውያን የጤና ባለሙያዎች እውነታውን ለመቀበል ማመንታታቸውና መካዳቸው ወረርሽኙ በስፋት ድምጹን አጥፍቶ እንዲዛመት ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል፡፡
የሚያሳዝነው ታዋቂ አለማቀፋዊና ቀጣናዊ የጤና ተቋማት ማለትም የዓለም የጤና ድርጅትንና የአውሮፓ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከል ማዕከል ሳይቀሩ ምልክቱ ያልተየባቸው ሰዎች ወረርሽኙን እንደሚያስተላልፋ አበክረው ማስጠንቀቅ ሲገባቸው እርስ በርሳቸው የሚጣረሱ መረጃዎችንና ምክሮችን በመስጠት ግራ ሲያጋቡና ሲያዘናጉ መኖራቸው ነው።የህመም ምልክት የማያሳይ ሰው ወረርሽኙን ያስተላልፋል ወይስ አያስተላልፍም የሚለውን ብዥታ አጥርቶ እልባት ከመስጠት ይልቅ ሀኪሞቹም ሆኑ የጤና ባለሙያዎች በወረርሽኙ የተያዘ ነገር ግን ምልክት የማይታይበትን ሰው ምን እንበለው በሚል የቃል ትርጉም ሲጨቃጨቁ ኮቪድ 19 ድምጹን አጥፍቶ ይዛመት ነበር፡፡
ለሁለት ወር በዘለቀው መዘግየት የተፈጠረው በተሳሳተ ሳይንሳዊ ግምት ፣ በምሁራን አለመግባባት እና ከሁሉም በላይ ወረርሽኙን መግታት በቀጣይ ስር ነቀል እርምጃ ለመውሰድ ያግዝ እንደነበር በውል ባለመገንዘብ ነው።በወቅቱ የሕመም ምልክት የማይታይባቸው ሰዎች ቫይረሱን ወደ ጤነኛ ሰው ያጋቡ እንደነበረ በርካታ ሳይንሳዊ ማስረጃዎች ቢኖሩም ዓለም በዚህ ተመስርቶ እርምጃ ለመውሰድ ዳተኛ መሆኑ ኮቪድ 19 በስፋት እንዲዛመት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።በዚህ የተነሳ አበክሮ መከላከል ላይ በተፈጠረ መዘናጋት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማዳን አልተቻለም።ይሁንና ሲንጋፖርና ካናዳ የሕመም ምልክት ባልታየባቸው ላይ ሳይቀር በስፋት ምርመራ ፣ ግንኙነታቸውንን ተከታትሎ የመለየትና ለይቶ የማቆየት ስራ በማከናወናቸው ሊከተል፣ የሚችለውን ጉዳት በእጅጉ መቀነስ ችለዋል። በቻይና በጣሊያን ፣ በፈረንሳይ ፣ በእንግሊዝ ፣ በአሜሪካ ፣ በብራዚል ፣ በሕንድ ወዘተረፈ ያ ሁሉ ጉዳት የደረሰውና እየደረሰ ያለው የሕመም ምልክት ያላሳዩ ሰዎች ቫይረሱን እንደሚያስተላልፉ ተገንዝቦ አስፈላጊውን የመከላከል ስራ ባለመስራቱ ነው። በሆንግኮንግ፣ ሲንጋፖርና በቻይና የተደረጉ ጥናቶች የሕመም ምልክት ያልታየባቸው ሰዎች ለኮቪድ 19 መዛመት ከ30 እስከ 60 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ጥናቶች አረጋግጠዋል፡፡
ኮቪድ 19 እንደ ሰደድ እሳት በመዛመት በዓለማችን ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ያጠቃ፤ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ቢሆንም ያልተፈታ እንቆቅልሽ እንደሆነ ቀጥሏል።ክፉው ቀን ስለማለፍም ሆነ ሁለተኛው የኮቪድ 19 ማዕበል ስለመምጣቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም።ጀርመን የሕመም ምልክት የማይታይባቸው ሰዎች ቫይረሱን እንደሚያስተላልፉ ቀድማ የደወለችው የማንቂያ ደወል ሰሚ ቢያገኝ ኖሮ በጣሊያንም ሆነ በሌሎች ሀገራት ያን ያህል ሕዝብ እንደ ቅጥል ባረገፈ።እንደ ኮቪድ 19 ያሉ ወረርሽኞችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ጊዜ ምን ያህል የማይተካ ሚና እንዳለው አሜሪካና ብራዚል ጥሩ ማሳያ ናቸው።ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወረርሽኙን ቀላል ጉንፋን ነው እያሉ ከወር በላይ ማቃለላቸው ከ120ሺህ በላይ አሜሪካውያንን ህይወት እንዲነጥቅ፤ ከሦስት ሚሊዮን
በላይ የሚሆኑትን እንዲያዙ አድርጓል።ትራምፕ ለፓለቲካዊ ጥቅም ሲሉ በየግዛቶች የእንቅስቃሴ ገደቡ በጥድፊያ እንዲላላ በማድረጋቸው ወረርሽኙ በስፋት እየተዛመተ ነው።የብራዚል ፕሬዚዳንትም የኮቪድ 19ን አደገኛነት በማቅለላቸው ሕዝባቸው እያለቀ ከመሆኑ ባሻገር ነሐሴ ላይ በቫይረሱ የሚሞቱም ሆነ የሚያዙ ብራዚላዊያን ቁጥር ከአሜሪካውያኑ እንደሚበልጥ ከወዲሁ እየተጠቆመ ነው፡፡
የCNNኑ ፋሪድ ዘካርያ ምንጭ ጠቅሶ በተጠቀመበት ቀመር፤ ታይዋን የተጠናከረ ምርመራ እና የእንቅስቃሴ እቀባ ባታደርግ ኖሮ በወረርሽኙ የሚያዘው ሰው ከ400 በ67 እጥፍ አሻቅቦ 26 ሺህ 800 ይደርስ ነበር።እንዲሁም የምርመራና የእቀባ ስራዋን ከጀመረችበት ቀን አንድ ሳምንት ቀድማ ማካሄድ ብትጀምር ኖሮ ደግሞ በወረርሽኙ የተያዘውን ዜጋ ቁጥር ከ400 በ66 በመቶ ቀንሶ ማለትም በ264 ቀንሶ ወደ 136 ማውረድ ትችል ነበር።ሀገራችን ወረርሽኙን በተመለከተ የወሰነችውን ውሳኔ ከአንድ ሳምንት ቀድማ ብታደርገው ኖሮ ዛሬ የተሻለ ውጤት ባስመዘገበች።እዚህ ላይ የታይዋን መንግሥት ፈጥኖ መንቀሳቀስ መቻሉ በወረርሽኙ ይጠቃ የነበረን 26ሺህ 400 ሰው መታደግ ችሏል።
ኢኮኖሚያችን፣ ግንዛቤያችንና የስነ ልቦና ውቅራችን የተለያየ ቢሆንም ሕዝባችን ወረርሽኙን ለመከላከል ንቁ ተሳታፊ ቢሆን ኖሮ እንደ ታይዋን ውጤታማ መሆን በተቻለ።በሀገራችን እየሆነ ያለው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው።አይደለም በራስ ተነሳሽነት የመከላከል ጥረቱን መቀላቀል መንግሥት ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት እያደናቀፈ ነው ማለት ይቻላል።የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁንም በቅጡ እያከበረ አይደለም።ሕዝብ መንግሥት የሚለውን አድምጦ ተባባሪና የመከላከል ጥረቱ አካል መሆን ካልቻለ በአንድ እጅ እንደ ማጨብጨብ ነው።
መንግሥት ምንም ያህል ከላይ እስከታች የተቀናጀና የተናበበ ጥረት ቢያደርግ ብቻውን ውጤታማ ሊሆን አይችልም። ለዚህ ነዉ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 8ሺህን የተሻገረውና የሟቾች ቁጥርም 146 የደረሰው።ይሁንና ዛሬም አልረፈደምና ሕዝብ በተቻለ አቅም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።የመከላከሉ ጥረት አካል ለመሆን የግድ ከእልቂትና ከሞት ጋር ፊት ለፊት መጋፈጥ አያስፈልግም።እንደ አሜሪካ ፣ ጣሊያን ፣ ስፔን ሕዝብ ማለቅ የለበትም።እንደ አሜሪካ በአንድ ቀን 140ሺህ ሰው በቫይረሱ መጠቃት የለበትም።ቫይረሱ ያለባቸው ነገር ግን የሕመም ምልክት የማያሳዩ ቫይረሱን ስለሚያስተላልፉ የህክምና ባለሙያዎችን ምክር በመስማት እርቀትን መጠ በቅ፣ ጭምብል ማረግ፣ሲያስነጥሱም ሆነ ሲስሉ በክርን መሸፈንና እጅን ደጋግሞ በመታጠብ ራስንም ወገንንም በቀላሉ መከላከል ይቻላል።
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ !!! አሜን ፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com