የቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግስት ርእሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሀሰን የተወለዱት በአሶሳ ዞን ልዩ ስሙ ኦዳ ቡልዲጊዱ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ነው፡፡ የተማሩት በአሶሳ ዞን ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ፤ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን አግኝተዋል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት ናቸው፡፡ አቶ አሻዲሊ በወረዳ ደረጃ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ ፤ በዞን ደረጃ የአሶሳ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አማካሪና የውሃ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በቤኒሻንጉል ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ የፖለቲካ ጉዳዮች አማካሪ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ለቤተሰባቸው ዘጠነኛ ልጅ ናቸው፡፡ በክልሉ ወቅታዊና ሌሎች አነጋጋሪ ጉዳዮች ላይ ልዩ ቃለ ምልልስ አድርገናል፡፡ ይከታተሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ካማሺ ዞን የተፈጠረው ግጭት መንስኤው ምንድን ነበር? በግጭቱ የተሣተፉ ሕገወጥ ታጣቂዎች እንደነበሩ ይሰማል፡፡ ማንነታቸው አልታወ ቀም? ማን ነው ጥቃቱን የፈጸመው?
አቶ አሻድሊ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ካማሺ ዞን የተከሰተው ግጭት ዋናው መነሻ የነበረው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አመራር በጸጥታ ጉዳይ የነበራቸውን ውይይትና ስራቸውን ጨርሰው ወደ ካማሺ ሲመለሱ በጸረ ሰላም ኃይሎች መንገድ ላይ በደረሰባቸው ጥቃት አራት አመራሮች ሕይወታቸው ማለፉ ነው፡፡ ይህን ጥቃት የፈጸሙት የተደራጁ የጸረ ሰላም ኃይሎች የኢትዮጵያን፣ የኦሮሚያንና የቤኒሻንጉል ጉሙዝን ልማት የማይፈልጉ ናቸው፡፡
በዚህም የተለያዩ ጥቃቶች በመፈጸም በርካታ ንጹሃን ዜጎች እንዲጎዱ፣አርሶ አደሮች እንዲፈናቀሉና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል፡፡ በሰው ሕይወትም ላይ አደጋ ደርሷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ጉዳት ደረሰ? ምን ያህል የሰው ሕይወት ጠፋ?
አቶ አሻድሊ፡- እስከ አሁን ድረስ ምን ያህል ሰው እንደሞተ መረጃ የለንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- እንዴት ፤ግርድፍ የሆነም ቢሆን?
አቶ አሻድሊ፡-አ ልተጣራም፡፡ ስምንት ወይም ዘጠኝ ሰዎች ሞተዋል የሚል መረጃ አለ፡፡ በትክክል ለማወቅ ተጨባጭ ስራ እየተሰራ ነው ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በእናንተ ግምት ማነው ጥፋቱን ያደረሰው? ከየት የመጡና እነማን ናቸው?
አቶ አሻድሊ፡- ይሄን ጥቃት ያደረሱ አካላት የኦነግ አፈንጋጭ ቡድን ሽኔ የሚባሉት አካላት ናቸው፡፡ እዚያ ገብተው ይሄን ጥቃት የፈጸሙት፡፡
አዲስ ዘመን፡- በወቅቱ የመንግስት አካላት ለመከላከል እርምጃ አልወሰዱም? በእናንተ በኩልስ ምን ተደረገ ?
አቶ አሻድሊ፡- በወቅቱ በእኛ በኩል የተወሰደ እርምጃ የለም፡፡ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ እዚያ ያለውን ንጹሃን ሰዎችን መግደል ነው ያጋጠመው፡፡ ጥቃቱ ሁከት በፈጠሩት ላይ ቢፈጸም ኖሮ ጥሩ ይሆን ነበር፡፡ ግን በንጹሃን ዜጎች ላይ ነው የተፈጸመው ትክክለኛ ያልሆነውም ነገር ይሄ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጸጥታ ችግሩን ለማስወገድ የተቋቋመው ወታደራዊ ኮማንድ ፖስት (የእዝ ጣቢያው) ምን ውጤት አስገኘ ? ምን ሥራ እየተሰራ ነው ያለው?
አቶ አሻዲሊ፡- ኮማንድ ፖስቱ አጎራባች በሚል ነው በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መካከል ለሚፈጠሩ ችግሮች የተቋቋመው፡፡ አሁን ከቀደመው ጊዜ የተሻለ አንጻራዊ ሰላም አለ፡፡ ኮማንድ ፖስቱን በተመለከተ ራሱን የቻለ መረጃ ሰጪ አካል ያለው በመሆኑ እኔ መስጠት አልችልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተፈጠረው ግጭትና ቀውስ በአጠቃላይ ምን ያህል ሰው ተፈናቅሏል? ምን ያህል ሰው ሞቷል?
አቶ አሻዲሊ፡- ካማሺ ዞን ላይ መንገድ ተዘግቶ በመቆየቱ የተነሳ ተጨባጭ የተሟላ መረጃ ማግኘት አልቻልንም፡፡ አሁን በቅርቡ መንገድ ስለተከፈተ ሰው በማስገባት መረጃ ማጠናከር ጀምረናል፡፡ በአብዛኛው የተፈናቀለው ግን በኦሮሚያ በኩል ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በግምት ምን ያህል ይሆናል? የተለያዩ ሚዲያዎች የተለያየ ቁጥር ሲጠቅሱ ይሰማል፡፡
አቶ አሻዲሊ፡- አሁን በቅርቡ ያለን መረጃ ወደ 129 ሺ የሚደርስ ሕዝብ መፈናቀሉን ነው የሚያሳየው ከእነዚህም 60 በመቶው ከኦሮሚያ ነው የተፈናቀሉት። ከቤኒሻንጉል ክልል የተፈናቀሉት ወደ 60 ሺ ይሆናሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡-ለተፈናቃዮች ምን ድጋፍ እያደረጋችሁ ነው ?
አቶ አሻድሊ፡- ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው ያለው፡፡ ካማሺ ዞን ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት በየደረጃው ያለው አመራር እንቅስቃሴ እያደረገና ሕዝብን እያወያየ ነው፡፡ ሕዝቡ እያነሳ ያለው ጉዳይ እነዚህን ሰዎች ወደ ካማሽ መመለስ አለባችሁ የሚል ነው፡፡ እኛም ሕዝቡን ስናወያይ የሕዝቡን መሰረታዊ ጥያቄ ወደነበሩበት ይመለሱ የሚለውን መሰረት በማድረግ ቢመለሱ ይሻላል የሚለውን ሃሳብ ተግባራዊ ለማድረግ እየሰራን እንገኛለን፡፡ በኦሮሚያ በኩልም እርዳታ እየቀረበላቸው ነው ያለው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህን ግጭት የሚቀሰቅሰው ሃይል ሰርጎ የገባና የተደራጀ ኃይል ነው የሚባለውን አስተያየት እንዴት ያዩታል ?
አቶ አሻድሊ፡- በተለያየ ሚዲያዎች የሚራገቡ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ የተደራጀ ኃይል ነው ጦርነት እየከፈተ ያለው የሚባለው ነገር ትክክል አይደለም፡፡ መነሻውን አስቀድሜ ገልጬያለሁ፡፡ እዛ ያለው አርሶ አደር የእኔ ልጅ ተነካ ብሎ አንዳንድ ነገር የማድረግ ሁኔታ ካልሆነ በስተቀር በኦሮሚያም ይሁን በቤኒሻንጉል የተደራጀ ቡድን ጦር ገጥሟል የሚባል ነገር የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተወሰኑ ሰዎች ግጭት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ይሆናሉ ማለትዎ ነው ?
አቶ አሻድሊ፡- አይጠፉም በግለሰብ ደረጃ ሰርገው የሚንቀሳቀሱ ይኖራሉ፡፡ የሚቀሰቅሱም አደገኛ ሰዎች አሉ፡፡ ይሄን ጉዳይ እየሄድንበት ነው፡፡ በርካታ ሰዎች ላይ መረጃ ሰብስበን የጠየቅናቸውና ያስጠየቅናቸው ሰዎች አሉ፡፡ በግጭቱ ዙሪያ እጃቸው አለበት ቀስቃሽ ነበሩ የተባሉ በርካታ ሰዎች በማረሚያ ቤት ነው ያሉት፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከካማሺ ግጭት ጋር ተያይዞ በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ተፈናቅለው እንደነበር ይታወቃል፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው፤በቅርቡም የካማሺ ዞን ሲቪል ሰርቪስ ሰብስቦ እንደሚከፍላቸው አሳውቆአል፡፡ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል ?
አቶ አሻዲሊ፡- ካማሺ አካባቢ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመንግስት ሰራተኞችና አርሶ አደሮች ተፈናቅለዋል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ከኦሮሚያ እና አማራ ክልል ወደ አሶሳ ከተማ በርካታ ቁጥር ያላቸው የመንግስት ሰራተኞችና አርሶ አደሮች ገብተዋል፡፡ ሥራዎች በተወሰነ ደረጃ ተስተጓጉለዋል፡፡ በቅርቡ መንግስት ባደረገው ጥረት ጥሪ ተላልፎ የመንግስት ሰራተኞችን ለማወያየት ሞክረናል፡፡ አሁን አንጻራዊ ሰላም ስላለ ወደ መደበኛ ስራችሁ እንድትመለሱ በሚል ጥያቄ አቅርበን ተስማምተዋል፡፡ እስካሁን ድረስ የሁለት ሶስትና አራት ወር ደመወዝ ያልተከፈላቸው አሉ፡፡ እንደ መንግስትም ተወያይተንበታል፡፡ እንደሚከፈላቸውም ተስማምተናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ በሚመሩት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢ ከአልጣሽ ፓርክ የተወሰደ አውጀሚስ የሚባል ቦታ አለ፡፡ እዚያ አካባቢ ሕገ ወጥ የሆነ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ቦታዎች መኖራቸው ይሰማል፡፡ ሰራዊት ይሰለጥናል ነው የሚባለው፤ ይሄንን እንዴት ነው የሚያዩት ?
አቶ አሻዲሊ፡- እኛ ጋ ከአልጣሽ ፓርክ ጋር የሚዋሰን አውጀሚስ የሚባል ፓርክ አለ፡፡ እዚያ አካባቢ በጣም ሰፊ መሬት አለ፡፡ ደኑም በተመሳሳይ ሰፊ ነው፡፡ በእኛ በኩል ሰው እየሰለጠነ ነው የሚል ተጨባጭ መረጃ የለንም፡፡ ነገር ግን ሕገ ወጦችና በሕገወጥነት ገብተው የማረስ ሁኔታዎች አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እኛም እኮ ያልታወቁ ሕገ ወጦች ተሰባስበው ወታደራዊ ስልጠና ይወስዳሉ በአካባቢው ይንቀሳቀሳሉ የሚል መረጃ ነው ያለን፡፡
አቶ አሻዲሊ፡- ሕገወጥ ሥልጠና ሳይሆን በሕገ ወጥ መንገድ ገብተው እርሻ የማረስ ሁኔታዎች አሉ ነው ያልኩት፡፡ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ማለቴ አይደለም፡፡ ምናልባት እዚያ አካባቢ ያለው ሰው ሕገ ወጥ መሳሪያ ይዞ ሊንቀሳቀስ ይችላል እንጂ ሰው እየሰለጠነ ነው የሚል ተጨባጭ መረጃ የለንም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአንድ ወቅት መንግስት የማያውቃቸው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ሕገወጥ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች መኖራቸ ውንና ሥልጠና ይወስዱ ነበር የሚል በክልሉ በኩል በመገናኛ ብዙሃን ተገልጾ ነበር፡፡ ይሄን ቢያብራሩልን ?
አቶ አሻድሊ፡- ይሄ በሌላ አቅጣጫ በኩል ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ ከአገራዊ ለውጡ ጋር በተያያዘ ሌሎችም አካላት ነበሩ፡፡ የተወሰኑ ሰዎች ወጣቶችን መልምለው ወደ ጫካ በመውሰድ የማሰልጠን ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ በእነዚህ ላይ መንግስት እርምጃ ወስዷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነማን ናቸው የሚያሰ ለጥኑት ለምን አላማ ?
አቶ አሻድሊ፡- ሕገ ወጥ ሰዎች ናቸው ይሄን የሚያደርጉት፡፡ ሰው ከዚያ አካባቢ ተውጣጥቶ ነው፡፡ በእከሌ ሥም በእከሌ ሥም የሚባል ነገር የለውም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚሁ አካባቢ ካዋራጅ የሚባል ኢስላማዊ አክራሪነትን የሚያራምድ፣ በትጥቅና በኃይል የተደራጀ አካል ነበር፡፡ በወቅቱ እርምጃ ተወስዶ እንቅስቃሴው እንዲገታ ተደርጎ ነበር፡፡ አሁንም ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎች አሉ ይባላል፡፡ ይሄን እንዴት ያዩታል?
አቶ አሻዲሊ፡- መረጃው አለኝ፡፡ ከዚህ በፊት እንቅስቃሴ ነበረ፡፡ መንግስት እርምጃ ወስዷል፡፡ አሁንም በውስን ቦታዎች ላይ እንዲህ አይነት እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ፡፡ ያን ያህል ግን የገዘፈ አይደለም፡፡ እንደድሮው የገዘፈ ሳይሆን በማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ከሚንጊጋር በሚዋሰነው አካባቢዎች ምልክቶቹና እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ከዚህ በፊት እንደነበረው ግን አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል ጀምሮም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአማራ ተወላጆችን የማፈናቀል ሥራዎች መሰራታቸው ሲዘገብ ነበር፡፡ እንደውም የአማራ ኬላ የሚባልም አለ ይባላል፡፡ በእዚያ ኬላ የአማራ ተወላጆች እንዳያልፉ የሚያደርግ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የትናንቱንም ሆነ የዛሬውን ችግር ለማረምና ለማስተካከል በእናንተ በኩል እየተወሰደ ያለው እርምጃ ምንድን ነው?
አቶ አሻዲሊ፡- የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች በጋራ የሚኖሩበት ሲሆን የሚታወቀው በመቻቻል፣አብሮ በመስራት ነው፡፡ ይህ ጉዳይ አሁን የተጀመረ ሳይሆን ቀደም ብሎ የኖረና ያለ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት አልፎ አልፎ ከመሬት ጋር በተያያዘ በክልሉ የሚታዩ ነገሮች ፣ በግለሰቦች በሚፈጠር ጠብ አማካኝነት የሚነሱ ግጭቶችና የሰዎች መፈናቀሎች ይታያሉ፡፡ ይህ ነገር በተለይ ጎልቶ የሚታየው ካማሺ ዞን ውስጥ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ትክክል እንዳልሆነ በመግለጽ በተደጋጋሚ ስንሰራበት ነበር፡፡ አንዱ የሰራነው የሕግ የበላይነትን የማስከበር ስራ ነው፡፡ በግለሰቦች ምክንያት በተነሳ ግጭት ሰው ማፈናቀልና የሰው ሕይወት ማጥፋት ተገቢ አይደለም፡፡ ሁለተኛው በየደረጃው ያለውን አመራር በመፈተሽ በጥፋተኞች ላይ አስተዳደራዊና ሕጋዊ የማስተካከያ እርምጃዎችን ወስደናል፤ተጠያቂም አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል እርምጃ ወስዳችኋል?
አቶ አሻዲሊ፡- እስከ ከፍተኛ አመራር ዞን አስተዳዳሪ ድረስ ርምጃ ተወስዷል፡፡ ሌሎች እጃቸው አለበት የተባሉ አካላትም ተጠያቂ ተደርገዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአብዛኛው ችግሩን የሚፈጥረው የአመራሮች የአስተሳሰብ ችግር እንደሆነ ስለሚታይ በተጨባጭ ምን ያህል ቁልፍ ሰዎች ላይ በዞን ፤ በክልል እርምጃ ተወስዷል?
አቶ አሻዲሊ፡- ቁጥሩ ይሄን ያህል ባይባልም በቁልፍ አመራር ደረጃ የነበሩትን ተጠያቂ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እስኪ ወደኋላ ልመልስዎትና ባለፈው ሰኔ ወር ላይ በክልሉ በተለይ በአሶሳ ግጭት ተፈጥሮ በነበረበት ወቅት የተያዙ ሰዎች አሉ፡፡ ምን እርምጃ ተወሰደ ቢገልጹልን?
አቶ አሻዲሊ፡- ሰኔ አካባቢ በአሶሳ በርካታ ሰዎች ተይዘዋል፡፡ ያሉት ማረሚያ ቤት ነው፡፡
ጉዳያቸው እየተጣራ ወደ ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ እየተመሰረተባቸው ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምን ያህል ሰዎች ናቸው?
አቶ አሻዲሊ፡- 59 ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነዚህም በቂ መረጃ ያልተገኘባቸውና የተለቀቁ አሉ፡፡ ነገር ግን ሃምሳ ዘጠኙ ሰዎች ክስ ደርሷቸዋል፡፡ በመደበኛ ፍርድ ቤት ቀርቦ ጉዳያቸው በቀጠሮ እየታየ ይገኛል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከፍተኛ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በክልላችሁ መኖሩ ይሰማል፡፡ ከቀላል እስከ ከባድ የጦር መሳሪያ ድረስ በስፋት ይዘዋወራል የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ ይሄንን እንዴት ያዩታል?
አቶ አሻዲሊ፡- የጦር መሣሪያ ዝውውርን በተመለከተ እንደ ሀገር በጣም በከፍተኛ ችግር ውስጥ ነው ያለነው፡፡ በስፋት እየተካሄደ ነው፡፡ ቤኒሻንጉል ክልል ደግሞ እንደሚታወቀው ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን ጋር ይዋሰናል፡፡ እነዚህ ቦታዎች ለጦር መሣሪያ ዝውውር ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል፡፡ በክልሉ ይህን ጉዳይ ለመቆጣጠር ሰፊ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ መጠን ያላቸው መሣሪያዎች እየያዝን ነው ያለነው፡፡ ቁጥጥሩ አለ፡፡ ነገር ግን አምልጠው ወደ መሃል አገር የሚገቡም አሉ፡፡ ከኬላ ውጭ በሆነ መንገድ ነው የሚያሳልፉት፡፡ ስለዚህ የህዝቡን ትብብር በከፍተኛ ደረጃ የሚጠይቅ በመሆኑ ግንዛቤ እየፈጠርን ነው፡፡ በኬላና በፖሊስ ብቻ ድርጊቱን ማስቆም አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሕገ ወጥ መሣሪያ ዝውውሩ የመንግስትን መዋቅር ጭምር በመጠቀም የሚፈጸም ነው የሚሉ መረጃዎች አሉ፡፡ በእናንተም ክልል የመንግስትን መዋቅር ተጠቅመው የሚያዘዋውሩ አሉ ይባላል፡፡ ያገኛችሁት ተጨባጭ ጉዳይ አለ?
አቶ አሻዲሊ፡- በመረጃ ደረጃ እንዲህ ነው ሲባል ይሰማል፡፡ በተጨባጭ የተደረሰበትና የተያዘ ግን እስካሁን የለም፡፡ የማያቋርጥ ክትትልና ቁጥጥር እናደርጋለን፡፡ የክልሉን ሰላምና ደህንነት የሕዝቡንም ሰላምና መረጋጋት አስተማማኝ ለማድረግ እየሰራን ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ከተለያዩ አጎራባች ክልሎች ጋር በተያያዘ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ በአንድ ወቅት አቶ ያረጋል አይሸሹም ድንበራችን እስከ ወልቃይት ነው ብለው የሽግግር ቻርተሩን ጠቅሰው ተናግረው ነበር፡፡ ይሄን ሁኔታ አሁን ላይ እንዴት እያያችሁት ነው?
አቶ አሻዲሊ፡- ወሰንን በተመለከተ እኔ ብዙ መረጃ መስጠት አልችልም፡፡ እንደ አገር የወሰን ጥያቄዎች በርካታ ቦታዎች ላይ ይነሳሉ፡፡ በእኛ ክልል በኩል የጎላ ነገር የለም፡፡ ጥያቄዎች ግን አሉ፡፡ አሁን መንግስት በጀመረው አደረጃጀት መሰረት እልባት የሚያገኝ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው ወልቃይት፤ መተማ… እንዲህ እንዲህ ሊባል ይችላል፡፡ የአስተዳደር ወሰን የቤኒሻንጉል ክልል ይሄ ነው… የእከሌ ይሄ ነው ተብሎ ተካልሏል፡፡ ስለዚህ አዲስ ጥያቄዎች ካሉ እንደ ሀገር የሚመለሱ ናቸው ብዬ ነው የማስበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቤኒሻንጉል ክልል በአገሪቱ ለም ከሚባሉና በተፈጥሮ ሀብት ከበለጸጉት አንዱ ነው፡፡ መንግስታዊ አሰራርና መዋቅሩን እንደ ሽፋን በመጠቀም በክልሉ ከፍተኛ የመሬት ዘረፋና ቅርምት ፈጽሟል ይባላል፡፡ ይሄንን ጉዳይ ተከታትላችሁ የወሰዳችሁት እርምጃ ካለ ቢገልጹልን ?
አቶ አሻዲሊ፡- ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚታወቀው በተፈጥሮ ሀብቱ ነው፡፡ ዋናው ደግሞ የመሬት ጉዳይ ነው፡፡ ለም የሆነ ሰፊ መሬት አለ፡፡ በተገቢው መንገድ ቢሰራበት ክልሉ ለድፍን ኢትዮጵያ የሚተርፍ ነው፡፡ ቀደም ሲል ባነሳኸው ሁኔታ አሰራሩ ልቅ ስለነበረ በርካታ ሰዎች ክልሉ ውስጥ ገብተው መሬት ዘርፈዋል፡፡ መሬት በስፋት የመዝረፉ ጉዳይ እኔ ባለኝ መረጃ መሰረት በእርሻ ላይ ብቻ ከ600 በላይ የሚሆኑ ኢንቨስተሮች የተባሉ መሬት ወስደዋል፡፡ ከዚያ ውስጥ 20 በመቶ የሚሆኑት እንኳን መሬቱን አላለሙም፡፡ ስለዚህ ዘረፋ ነው የተካሄደው፡፡ በዚህ ላይ በስፋት ጥናት አድርገን እርምጃ ወስደናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የዘረፈዎቹ መገለጫ ምን መልክ ነበረው?
አቶ አሻዲሊ፡- የዘረፋው ስልት የመጀመ ሪያው መሬቱን ተረክበው የባለቤትነት ካርታ ያወጣሉ፡፡ ካርታውን በማስያዝ ከባንክ ከፍተኛ የገንዘብ ብድር ይወስዱበታል፡፡ ይሁንና እናለማለን እንሰራለን ካሉት ነገር ምንም አልሰሩም፡፡ ስለዚህ መሬቱን ዘርፈዋል ከማለት ውጪ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡ ደኖች መመንጠርና ሌሎች ሌሎች ተግባራትም ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ 600 በኢንቨስተር ስም የተመዘገቡትና መሬት የወሰዱት በምን በምን መስኮች ላይ ነበር ለመሰማራት ፈቃድ ያገኙት?
አቶ አሻዲሊ፡- እነዚህ በመሬት ወረራ ብቻ የተሰማሩ በእርሻ ስም ብቻ የወሰዱ ናቸው፡፡ ማዕድናትና በመሳሰሉት ሌሎች ዘርፎችም አሉ፡፡ ይሄን ያለአግባብ በዘረፋ የተወሰደ መሬት ለማስመለስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርገናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ማዕድናቱስ እልተዘረፉም ?
አቶ አሻዲሊ፡- ማዕድናቱም በከፍተኛ መጠን ባክነዋል፡፡ የተሰጠው ለእርሻ መሬት ነው፡፡ አምስት መቶ ሄክታር፣ አንድ ሺህ ሄክታር እየተደረገ ነው የተሰጠው፡፡ እብነ በረድ ነው፡፡ ሌሎች እንደ ወርቅ አይነቶች ሲሰሩ የነበረው በሕገ ወጥነት ነው፡፡ ፈቃድ ወስደው በመስራት በኩል ብዙም አልተሄደበትም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቤኒሻንጉል ክልል በተሰሩ ቀደምት ጥናቶች የተፈጥሮ የነዳጅ ዘይት አለ ይባላል፡፡ በኢንቨስትርነት ይሄን ለመስራት የገባ አካል አለን?
አቶ አሻዲሊ፡- እስካሁን ድረስ የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በእናንተ በኩል በተገለጸ መረጃ 162 ባለሀብቶች መሬት ተነጥቀዋል፡፡ 164 ባለሀብቶች ማስጠንቀቂያ ተሠጥ ቷቸዋል፡፡ ምክንያቱን ቢገልጹልን?
አቶ አሻዲሊ፡- ያደረግነው ዝርዝር ጥናት ነው፡፡ ወደ ሥራ ያልገቡ ናቸው ያልነውም ዝም ብለን ሳይሆን ጥናት አድርገን ነው፡፡ ፈጽሞ ወደ ስራ ውስጥ ያልገቡ 102 ኢንቨስተሮች የወሰዱት መሬት ተነጥቆ ወደ መንግስት እንዲገባ የነበራቸው ካርታም እንዲከስም እንዲሰረዝ ተደርጓል፡፡164 ሰዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷ ቸዋል፡፡ በሚቀጥለው የምርት ዘመን አሰራራቸውን ካላሻሻሉ መሬቱ የሚነጠቅ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የተመለሰው መሬት ለአልሚ ባለሀብቶች፣ ለወጣቶች እንዲሰጥና የልማት ስራ እንዲሰራ ሰፊ የስራ እድል እንዲከፍት የሚደረግበትን ሥርዓት ነድፈን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- ክልሉ ኢንቨስተሮች ለተባሉት መሬት በገፍ ሲሰጥ የአሰራር ክፍተት አልነበረበትም? በቂ መረጃ ሳይመዘግብ፤ የባንክ ስቴትመንቶች ሳያጣራ መሬት መስጠት ከሙስና ጋር የሚያያዝ መሆኑ ይሰማል፡፡ በክልሉ ያለው እውነታ ምን ይመስላል? የተወሰደ እርምጃ ካለ ቢገልጹልን ?
አቶ አሻዲሊ፡-ከዚህ በፊት የነበረው የመሬት አሰጣጥ በጣም ከፍተኛ ችግር ነበረበት፡፡ ዘመናዊ መለኪያ የለውም፡፡ ከዚህ ተራራ እስከ እዚያኛው ተራራ ድረስ በሚል ነው መሬት ሲሰጥ የነበረው፡፡ ሰው የወሰደው መሬት አንድ ሺህ ሄክታር ነው ተብሎ በተጨባጭ ሲለካ አምስት መቶ ሄክታር የሚሆንበት፤ አምስት መቶ ሄክታር ተብሎ የወሰደው ደግሞ ሁለት ሺ ሆኖ የሚገኝበት አይነት ችግሮች ነበሩ፡፡ እውቀት ባለው ባለሙያ የሚመራ የመሬት አሰጣጥ አልነበረም፡፡ በመንግስት በኩል ችግር አልነበረም ተብሎ የሚወስድ አልነበረም ማለት ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም የባንክ ስቴትመንት ያመጣሉ፡፡ ነገር ግን ባንክም ችግር አለበት፡፡ ሁሉን የባንክ ሰነድ አሟልቶም ወደ ሥራ ግባ ማሽን አምጣ ሲባል ምንም የለም፡፡ ካርታውን ወስዷል፡፡ ይሸጠዋል ወይም ከባንክ ብድር ይወስድበታል፡፡ የነበረው ሂደት ይሄን ይመስላል፡፡ በክልሉ መንግስት በኩል ሁኔታውን ለማረምና ለማስተካከል በርካታ እርምጃዎች ወስደናል፡፡ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ ለረዥም ዓመታት ከመሬት አሰጣጥና ከኢንቨስትመንት ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከወረዳ እስከ ክልል አመራሮች ድረስ ፈትሸን አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃ ወስደናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የመሬቱን ካርታ ከማም ከንና ማስመለስ ውጪ ሌላ እርምጃም ወስዳችኋል?
አቶ አሻዲሊ፡- አዎ፡፡ አስመልሰናል፡፡ ማስመለስ ብቻ ሳይሆን እነዚህ ኢንቨስተር ነን የሚሉ ግለሰቦች ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ከመንግስት በተፈቀደው መሰረት ከቀረጥ ነጻ የሆኑ የተለያዩ እቃዎች የሚያስገቡበት ሁኔታም ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተገቢውን አሰራር እንዲከተል በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በክልሉ ከዜጎች መፈና ቀልና ከረብሻዎቹ ጋር ተያይዞ ከበስተጀርባ ባለሀብቶች እጃቸው አለበት የሚባለውስ ምን ያህል እውነት ነው ?
አቶ አሻዲሊ፡- አዎ፡፡ በተጨባጭ ለመግለጽ ቢከብደኝም እጃቸው የለበትም ብሎ መደምደም ግን አይቻልም፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተደረሰባቸው የሉም?
አቶ አሻዲሊ፡- በጥርጣሬ ደረጃ በመጣው ጥቆማ መሰረት ስምንት ሰዎች በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው የሚገኙ አሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በነበረው ሁኔታ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ አመራሮች በስውር በሌሎች አመራሮች ጣልቃ ገብነት ይመሩ ነበር፤ራሳቸውን ችለው ያልቆሙ ናቸው፤ ክልሉንም የክልሉንም ሕዝብ መጠቀሚያ አድርገውት ኖረዋል የሚሉ ሰፊ ትችቶች ይሰማሉ ምን ያህል እውነት ነው ?
አቶ አሻዲሊ፡- ምናልባት የቀድሞዎቹም ሲገልጹት የነበረ ይመስለኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል እንደ አጋርም ሆነ እንደ ታዳጊ ክልል አመራሩ በቀድሞው ጊዜ ሙሉ እምነት ኖሮት፣ በክልሉ ጉዳዮች ላይ ነጻ ሁኖ ወስኗል ብሎ መውሰድ ይቸግራል፡፡ ችግሮች ነበሩበት፡፡ እኛም ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ደርሰንበታል፡፡ ስለዚህ የተነሳው ጉዳይ ውሸት ነው ተብሎ የሚወሰድ አይደለም፡፡ ትክክል ነው፡፡ በተለያየ መንገድ ተሂዶ ውሳኔዎችን በጋራ ወይም በጫና ለማስወሰን መሯሯጦች ነበሩ ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሌሎች አካላት ጣልቃ ገብነት ምን አይነት ውሳኔዎች በጫና ይወሰኑ ነበር?
አቶ አሻዲሊ፡- ቅድም ባነሳሁት የመሬት ጉዳይ ብዙ ነገር ማንሳት ይቻላል፡፡ በትእዛዝ ለእነ እከሌ እከሌ ስጥ ትባላለህ፡፡ እንግዲህ ለእነዛ ካልሰጠህ ሌላ ነገር ነው የሚሆነው፡፡ ከዚያ ውጭ በሌሎችም በመሰረተ ልማቶች፣ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ጉዳይም ቢሆን ፓርቲው ነጻ ሆኖ እየሰራ አልነበረም፡፡ አመራርን የመመደብ ሁኔታዎችም ከጣልቃ ገብነት ነጻ አልነበሩም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ምደባው በምን መልክ ነው? በአማካሪ ደረጃ ነው ወይስ በሌላም?
አቶ አሻዲሊ፡- እኔ ታች በነበርኩበት ጊዜ በነበረኝ ምልከታ እንደታዘብኩት አማካሪዎችን በመመደብ ሊሆን ይችላል፡፡ የፖለቲካ አማካሪዎች ይመደባሉ፡፡ የሚሰሩት በጋራ ነው፡፡ ነጻ ሆነው ቢሰሩ ኖሮ ችግር የለውም ነበር፡፡ ለአገራዊ የጋራ እድገት ከሆነ ማለት ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮች በስፋት ነበሩ፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁንስ ምን ያህል ነጻ ሆነዋል?
አቶ አሻዲሊ፡- አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በሙሉ እምነት መናገር ይቻላል፡፡ አሁን ነጻ የወጣንበት ወቅት ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ በፊት የተመደቡት አማካሪዎች አሁን የሉም?
አቶ አሻዲሊ፡- አማካሪዎች መኖር አለባቸው የሚል እምነት አለን፡፡ አማካሪዎች ቢኖሩም ጣልቃ አይገቡም፡፡ ክልሉ በታሪክ አጋጣሚ ታዳጊ ነው፡፡ አንድ ላይ ሁነን አብረን ማደግ አለብን፡፡ ነገር ግን እንደ ክልል መንግስት በምንወስናቸው ውሳኔዎች ደግሞ ገለልተኛ ሆኖ፣ ክልሉ በራሱ እየወሰነ እንዲሄድ ማድረግ ይገባል፡፡ አሁን ባለው ለውጥ ነጻ ሆኖ ክልሉን ወደ ልማት ጎዳና እንዲገሰግስ ማድረግ ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ ክልሉ ግምገማ አድርጎ የአመራር ለውጥ አድርጓል፡፡ ቀድሞ የነበሩት አመራሮች ላይ የተገኙት ጉድለቶችና ይዘታቸውስ ምን ነበር?
አቶ አሻዲሊ፡- በቅርብ ጊዜ በድርጅታችን ውስጥ ጥልቀት ያለው ግምገማ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ግምገማው በጣም የተሻለ ነበር፡፡ በተለይ በአመራሩ ውስጥ የአስተሳሰብና የተግባር አንድነት ለመፍጠር ትኩረት አድርገን ነው የገመገምነው፡፡ ከዚህ አኳያ ከክልል ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በርካታ አመራሮች ከኃላፊነት እንዲነሱ አድርገናል፡፡ አንዳንዶቹን ከውጤታማነት አኳያና ሁለተኛው ደግሞ ከኪራይ ሰብሳቢነት ጋር በተያያዘ የገመገምናቸው አመራሮች አሉ፡፡ በተለያየ መንገድ ቡድን ፈጥረው አመራሩን ለመጠላለፍ የሚሞክሩ የነበሩበት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ እነዚህን መሰረት አድርገን እርምጃዎች ወስደናል፡፡
አዲስ ዘመን፡-በቁጥር መጥቀስ ይቻላል?
አቶ አሻዲሊ፡- 59 የሚሆኑ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡ የታችኛውን መዋቅር ሳይጨምር፡፡
አዲስ ዘመን፡- አጋር ድርጅቶች እስከ መቼ ድረስ ነው አጋር የሚሆኑት የሚል ሃሳብ በስፋት ሲንሸራሸር አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በቅርቡ በተደረገው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባዎች መሳተፍ ጀምራችኋል፡፡ በእናንተ በኩል እንዴት አያችሁት? መሳተፋችሁ ምን አስገኝቶላችኋል?
አቶ አሻዲሊ፡- አሁን ከለውጡ ጋር በተያያዘ ባለው ሂደት በጣም ትልቅ እመርታ የታየበት ነው፡፡ ያነሳኸው ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለል የነበረ የፓርቲዎቹ ብቻ ሳይሆን የህዝብም ጥያቄ ነበር፡፡ አንድ ሀገር ሆነን ለምንድን ነው አጋር የምንባለው የሚል፡፡ አሁን የፓርቲ ሊቀመንበርና ምክትሉ በኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ ላይ ተሳትፈናል፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ የክልሉን አጠቃላይ ፖለቲካዊና የልማት እንቅስቃሴ የአገሪቱ ቁልፍ አመራሮች ባሉበት ማንጸባረቅ፣ትኩረት እንዲያገኝ የማድረግ ጉዳይ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተጀመረው እንቅስቃሴ በእኛ በኩል ወደ አንድነት ለማምጣት ትልቅ መንገድ ይከፍታል በሚል ነው የምንወስደው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ወደ አገር ውስጥ የገባው የቤሕነን ኃይል በምን ደረጃ ላይ ይገኛል፤ሰራዊትስ ነበረው ወይ? ከነበረውስ ትጥቅ ፈትቶ ገብቷል ወይ? ከእናንተስ ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል?
አቶ አሻዲሊ፡- ከዚህ በፊት በ2005 ዓ.ም ላይ የተወሰኑ ውጭ የሚገኙ የቤሕነን ንቅናቄ ሰራዊትና አመራሮች ለማስገባት ሞክረን ነበር፡፡ በዚያ ሁኔታ በ2007 ዓ.ም.በተካሄደው ምርጫ በተቃዋሚዎች የተነሳ የተለያየ ሁከትና ብጥብጥ ተነስቷል፡፡ የሰው ሕይወትም ጠፍቷል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ ከዚህም ጋር ተያይዞ እንዲታሰሩ እና በፈጸሙት ጥፋት ወደ ህግ እንዲቀርቡ ተደርጓል፡፡ በአብዛኛው ግን ወደ ሱዳን ተመልሰው ሄደዋል፡፡
በ2009 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ይመስለኛል ውጪ የነበሩና በተለይም ኤርትራን ማዕከል ያደረጉና በየጊዜው የሰው ኃይል አደራጅተው እየገቡ በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አካላትን ተደራድረን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ አድርገናል፡፡ 112 የሚሆኑ ታጣቂዎች ገብተዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በየት አድርገው ነው የገቡት ?
አቶ አሻዲሊ፡- በመተማ በኩል ነው ያስገባናቸው፡፡ ከአገር መከላከያ የምዕራብ እዝ ጋር በመነጋገር ትጥቅ ፈትተው ነው የገቡት፡፡ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ህገ መንግስታዊ ሥልጠና ሰጥተን ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ አድርገናል፡፡ አሁን ከህዝቡ ጋር ተቀላቅለው በሰላም እየኖሩ ነው፡፡ ክትትልም እናደርጋለን፡፡ ከተመላሾች ጋር ተያይዞ የገጠመን ችግር የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሕይወታቸውን የሚያሻሽልና የሚለውጥ ምን ምቹ ሁኔታ ፈጠራችሁላቸው?
አቶ አሻዲሊ፡- የሰራነው ብዙ ነው ባይባልም በፍላጎታቸው መሰረት ምን ላይ መሰማራት ትፈልጋላችሁ በሚል ተጠይቀው የእርሻ መሬት የሚፈልግ ካለ መሬት እንዲመቻችላቸው አድርገናል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ያደራጀናቸውም አሉ፡፡ ብድር ወስደው በንግድ ዘርፍና በሌሎችም መስኮች ተሰማርተው እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- የተመለሱ የቤህነን ሰራዊት አባላትን ለማደራጀት በሚል በክልሉ ካቢኔ ውሳኔ ወደ ሦስት ሚሊዮን ሰባ አምስት ሺ ብር አካባቢ ተሰጥቷቸው ለቤት መስሪያና ለመቋቋሚያ በሚል እንደተሰጠ በማንሳት ከጉዳዩ ተገቢነት ጋር ተያይዞ ጥያቄ ይነሳል፡፡ በዚህ ላይ ምን የሚሉት ነገር አለ?
አቶ አሻዲሊ፡- የቤህኔን አባላት ሲመለሱ ብዙ ነገር ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ከአቅም አኳያ ችግር ነበር፡፡ የመጀመሪያው ከመሬት ጋር ተያይዞ ነው። ለተወሰኑት አሶሳ ላይ መሬት ሰጥተናል፡፡ ለቆርቆሮ መግዣ የሚሆን ከፌዴራልም የተወሰነ ድጋፍም ተደርጎልናል፡፡ በግለሰብ ደረጃ 40 ሺ ብር ሰጥተናል፡፡ ስለዚህ የሚሰማው የተዛባ አስተያየት ተቀባይነት የለውም፡፡ ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ተረጋግተው እንዲኖሩ ልማቱን እንዲያግዙ ማቋቋም ተገቢ ነው፡፡ ትክክለኛ እርምጃም ነው የወሰድነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከለውጡ ወዲህ የታዩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ምንድን ናቸው?
አቶ አሻዲሊ፡- ከለውጡ ወዲህ በርካታ ጠንካራ ጎኖች አሉ፡፡ ቅድም እንዳነሳሁት፡፡ እንደ አመራር ስናይ በእጅ አዙር የሚመጡ የተለያዩ ጉዳዮች ነበሩ፡፡ ለውጡ ከመጣ በኋላ ነጻ ሆኖ የመወሰን፣ ነጻ ሆኖ የመስራት እና እንደ ድርጅትም በክልሉ ጉዳይ ላይ ጠንካራ ሆኖ የመስራት ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ ይሄ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ በጥንካሬ ደረጃ በጠንካራ ጎን የሚነሳ ነው፡፡
በድክመት የሚነሱት ለውጡን ለመቀልበስ የሚፈልጉ ሃይሎች በየቦታው እየገቡ ህዝቡን የማደናገር ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡ የመጣውን ለውጥ ህዝቡ እንዲጠራጠር የሚሰሩ አሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ህዝቡን አደናግሮ ወደ ግጭት እንዲገባ የሚቆሰቁሱ ናቸው፡፡ እነዚህን በተገቢው አጥርቶ ማስወገድ አለመቻሉ በድክመት የሚታይ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ችግሩ እየተቀረፈ በመሄድ ላይ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የጣና በለስ ስኳር ልማት ፕሮጀክት በሚል ከቀያቸው የተነሱ ዜጎችን በተመለከተ ተገቢው ካሣ፣ምትክ ቦታ ተገምቶ ስላልተሰጣቸው ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸዋል ይነሳል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አስተዳደር ምን እየሰራ ነው? ምን እርምጃ ወሰዳችሁ?
አቶ አሻዲሊ፡- ተነሽዎቹ የሚታዩት በሁለት መንገድ ነው፡፡ ከፊሉ የአማራ ክልል ሲሆን ከፊሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ነው፡፡ በስኳር ተነሺዎቹ አካባቢ በእውነቱ ጥሩ የሚባል ሥራ ሰርተናል፡፡ ለተነሽዎቹ ምትክ መሬት ከመስጠት አንስቶ የሚያስፈልጋቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት ከነውስንነቱም ቢሆን ለመገንባት ሞክረናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሳው አንዱ ችግር ቀድሞ ከነበሩበት ቦታ ወደ እዚህ ሲመጡ ከነበራቸው የመሬት መጠን የተወሰነ የቀነሰባቸው ሰዎች አሉ፡፡ በዚህ ቅሬታ ያነሱ ሰዎች አሉ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከተሰጠው መሬት የተወሰነው በሚፈለገው ደረጃ ምርት የሚሰጥ አለመሆኑን አይተናል፡፡ ይሄን ከአምና ጀምሮ በክልል ደረጃ እየተነጋገርንበት እንገኛለን፡፡ መሬት አፈላልገን ለእነዚህ አካላት ለመስጠት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ዘንድሮ ይሄን ቅሬታ እንፈታለን ብለን እናስባለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- የልማት ተነሽዎችን በተመለከተ የተዋቀረው ኮሚቴ ጥናቶች አድርጎ ሁለት ሺ ሄክታር መሬት ለተነሽዎች እንዲዘጋጅ ለእናንተ ሀሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ ይሄን ጉዳይ እርስዎ ያውቁታል? ውሳኔስ ሰጥተውበታል ?
አቶ አሻዲሊ፡- አንተ እንዳነሳኸው ያን የሚመለከት ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ ሁለት ቦታዎች ላይ መሬት ለይቷል፡፡ አንዱን በርቀቱ አማካኝነት አርሶ አደሮቹ አልተቀበሉም፡፡ ሌላው የተለየው ጉዳይ ደግሞ ከግለሰቦች ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይሄን ችግር ለመፍታት በደንብ ካልተሰራ በመንግስት በኩል ግልጽ ሳይደረግ መስጠቱ ሌላ ጭቅጭቅ ይፈጥራል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እናስ ሌላ ምን አማራጭ ምን አሰባችሁ?
አቶ አሻዲሊ፡- እያሰብን ያለው አማራጭ ከእነሱ ጋር ተወያይተን የሩቁን ቦታ ተመላልሰው አርሰው የሚኖሩ ከሆነ የእርሻ መሬት መስጠት ይቻላል፡፡ በአብዛኛው መሬት ለማቅረብ ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ካላግባባን ደግሞ ቅርብ የሆነ መሬት ፈልገን ዘንድሮ ችግሩን እንፈታለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- የሕዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ትልቅ ፕሮጀክት ነው፡፡ አንዳንድ ሥራዎችን በተመለከተ ውል ፈጽመው የጠፉ ተቋራጮች ጉዳይ አለ፡፡ የግድቡ ውሃ በሚተኛበት አካባቢ ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስነሳት መልሶ የማስፈር ሥራ በክልሉ እየተሰራ ነው፡፡ አሁን ያለበት ደረጃ ምን ይመስላል፡፡ የሚፈናቀሉትስ ምን ያህል ሰዎች ናቸው? እስከአሁን ምን ተሰርቷል?
አቶ አሻዲሊ፡- ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ወደ ሃያ ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከቀያቸው ተነስተዋል፡፡ በተዘጋጁላቸውም ቦታዎች አስፍረናቸዋል፡፡ የሚያስፈልጓቸውን የአገልግሎት መስጫ ተቋማትም ለመገንባት ሞክረናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ እናመሰግናለን፡
አቶ አሻድሊ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
ወንደሰን መኮንን