ባለፉት 27 ዓመታት ሀገራችን ያስመዘገበችው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ብዙ የተወራለት ቢሆንም የፍትሃዊነት ችግር ስለነበረበትና በሰብዓዊና ዴሞክራሲዊ መብቶች መጠናከር ስላልታጀበ ቅሬታን ወልዶ ሀገራችን በአመጽና አለመረጋጋት ስትናጥ ቆይታለች። እያደገ ከመጣው ወጣት ቁጥር አንጻር የተፈጠሩት የሥራ ዕድሎች እጅግ አናሳ ስለነበሩና የሰፈነው ዴሞክራሲም ዘመኑን የማይመጥንና የይስሙላ በመሆኑ በተለይም ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍልን የትግልና የአመጹ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆን አድርጎት ቆይቷል።
ከህዝባዊ እምቢተኝነቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠሩ ችግሮች የበርካታ ለጋ ወጣቶች ህይወት ተቀጥፏል፣ ንብረት ወድሟል፣ ሰላም ተናግቶ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በከፍተኛ መጠን ተሽመድምዶም ቆይቷል። በወቅቱ የተፈጠረው ችግር ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግን ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ጥሎት ጊዜያዊ የማስተንፈሻ እርምጃዎችን ቢወስድም መድሃኒቱ ፍቱንና ተመጣጣኝ አልነበረምና ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት የፈየደው ነገር አልነበረም።
ይሁንና የህዝቡ ጥያቄና አመጽ እየሰፋ ሲመጣና የሀገሪቱን ህልውና መፈታተን ሲጀምር ፓርቲው ስር ነቀል ለውጥ እንዲያመጣና እስካሁን ሲሄድበት የነበረው መንገድ እንደማያዛልቀው ሊረዳ ችሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ድርጅቱ በሀገሪቱ ለተፈጠሩ ችግሮች ሃላፊነቱን በመውሰድና ህዝብን ይቅርታ በመጠየቅ ሊቀመንበሩን እስከ መለወጥ የደረሰ እርምጃ ለመወሰድ በቅቷል። ከዚህም በኋላ የሀገሪቱ ችግሮች የሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግር፣ ዴሞክራሲ በሚፈለገው መጠን አለመስፈን፣ ኢኮኖሚው በሚፈለገው ደረጃ አለማደግና ከዚህም ጋር ተያይዞ የኅብረተሰቡ ኑሮ በሚፈለገው መጠን አለማደግና የስራ አጥነት ችግር እየከፋ መሄዱ መሆኑን በግልጽ አስቀምጦ ለመፍትሄው ህዝብን በማስተባበር እንደሚሰራ አቅጣጫ አስቀምጧል።
ትናንት በዳቡስ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ፎረም ንግግር ያደረገት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ለውጥ በመደመር ፍልስፍና ላይ የተመረኮዘና በሶስት ምሰሶዎች ላይ አተኩሮ ሀገሪቱን ወደተሻለ ደረጃ ለማራመድ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል። ከምሰሶዎቹም የመጀመሪያው ምሶሶ ዴሞክራሲውን ማስፋት፣ ዘላቂና አስተማማኝ ማድረግ መሆኑን አውስተው፣ ይህንንም ዕውን ለማድረግ ሚዲያ በነጻነት የሚሰራበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ አፋኝ ህጎችን የማሻሻል የፖለቲካ እስረኞችን የመፍታት ስራ በስፋት መከናወኑን አብራርተዋል።
ከህዝቦቿ ግማሽ የሆኑትን ሴቶች ሳያሳትፉ የሚመጣ ለውጥ ስሌለም የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ታላላቅ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው አውስተው በዚህም መሰረት የአገሪቱ መከላከያ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ፣ አዲስ የተቋቋመው የሰላም፣ የከፍተኛ ትምህርት፣ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮች እንዲሁም የአገሪቱ ፕሬዚዳንትና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሴቶች እንዲሆኑ ተደርጓል ብለዋል።
ሁለተኛው ምሰሶ ደግሞ ኢኮኖሚውን ማሳደግና ማበልጸግ ነው፡፡ የአገሪቱን ኢኮኖሚ በፍጥነት ለማሻሻልና የአገሪቱን ዕደገት ለማፋጠንም አዳዲስ አቅጣጫዎችን በመቀየስ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም ታላላቅ የሀገሪቱን ኩባንያዎች በከፊል ፕራቬታይዝ የማድረግና የፐብሊክ መንግስት ሽርክናን በሥራ ላይ ለማዋል እየተሰራ ነው ብለዋል። ይህንንም በማድረግ የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በልዩ ሀኔታ ርብርብ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
ሶስተኛው ምሰሶ ቀጣናዊ ውህደትን ማምጣት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ውህደቱ ለልማትና እድገት ብቻ ሳይሆን ሰላምን ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግና ውህደቱ ለቀጣናው ብሎም ለአፍሪካ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።
በአጠቃላይ የሀገሪቱን ገጽታ የሚለውጡና ዕድገቷን በማፋጠን ወደተሻለ የዕድገት ደረጃ ለማራመድ የተሰሩ ሥራዎች ተስፋ ሰጪና ለሀገሪቱም ችግር ሁነኛ መድሃኒቶች መሆናቸው እሙን ነው። የሀገሪቱ ዕድገት ምሰሶዎች የተባሉት የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት አያያዝን ማሻሻል፣ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማፋጠን፣ የሴቶች ተሳትፎን ማሳደግና ማጎልበት፣ የፍትህ ስርዓቱን ማሻሻልና አሳሪ ህጎችን መለወጥ ከተዘፈቅንበት ችግር በማላቀቅ በዕድገት ጎዳና ለመገስገስ ምቹ መደላድሎች መሆናቸውም አይካድም።
ይሁንና እነዚህ ምሰሶዎችን መሰረት አድርጎ እየተሰራ ያለው ሥራ ገና በእንጭጭ ደረጃ ላይ ያለና ለማጠናከርና ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረትና ልፋትን የሚጠይቁ መሆናቸው መዘንጋት አይኖርበትም። ውጥኖቹና ጅምር ተግባራቱም በመንግስት ብቻ የሚፈጸሙ ሳይሆኑ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቀና ጥረትና ትብብር እንደሚጠይቁም ሊዘነጋ አይገባውም። ስለሆነም የህግ የበላይነት በማክበርና በማስከበር፣ ለዕድገት በመታተርና አደናቃፊ ተግባራትን በጋራ በመታገል ዜግነታዊ ግዴታችንን ልንወጣና የበለጸገች አገር ለመፍጠር በጋራ መንቀሳቀስ ይገባል እንላለን!
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011