አዲስ አበባ፡- የካቲት 6 እና 7 ቀን 2011 የሚከበረው የመከላከያ ሠራዊት ቀን አገሪቱ በአጭር ጊዜ ሙሉ በሙሉ ወደ አስተማማኝ ሠላም እንድትገባ ለመስራት ሠራዊቱ ቃሉን የሚያድስበት እንደሚሆን መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዕለቱን አስመልክቶ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለፀው፤ ዘንድሮ ለሰባተኛ ጊዜ በዓል በኢፌዴሪ አየር ኃይልና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በአዳማ ከተማ ‹‹ሕገ-መንግስታዊ ታማኝነታችንና ሕዝባዊ ባህሪያችንን ጠብቀን የተጀመረውን ለውጥ እናስቀጥላለን!›› የሚል መሪ ቃልን ይከበራል፡፡
በሚኒስቴሩ የመከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሠማ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ አስተማማኝ ሰላም መኖር አለበት፡፡ ምንም እንኳ የለውጥና የተሃድሶ ሂደቱን ማካሄድ የሚያስችል የተመቻቸ የፀጥታ ሁኔታ ቢኖርም በየአካባቢው የሚነሱ ግጭቶችና የፀጥታ ችግሮች ግን ከፍተኛ ተግዳሮት ሆነዋል፡፡ እነዚህንም በየደረጃው ካሉ የመንግስት አካላትና የክልል ፀጥታ ኃይሎች ጋር የአካባቢዎቹን ሠላም፣ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ለማስጠበቅ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፤ ሠራዊቱ በዓሉ ሲከበር በመሪ ቃሉ መሠረት ዳግም ቃሉን የሚያድስበትና ለበለጠ ግዳጅ ራሱን የሚያዘጋጅበት ይሆናል፡፡ የበዓሉ ዓላማም ሠራዊቱ በሕገ-መንግስቱ የተሰጡትን ተልዕኮዎች መፈፀም የሚያስችል አቅም ዝግጁነት እንዳለው ማሳያ፣ ከሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት ይበልጥ የሚጠናከርበት ብሎም ለሕገ-መንግስታዊ ስርዓት ደህንነት ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን የከፈሉ ሠማዕታት የሚዘከሩበት ነው፡፡
በበዓሉ የሚከናወኑ ተግባራትም ክፍተቶችን ለመሙላት ምን ማድረግ እንዳለበት በስፋት ገምግሞ ተልዕኮውን ለመወጣት ዋናው መሠረት የሆኑት ሕዝባዊ ባህሪያትና እሴቶች ይበልጥ አጠንክሮ ለቀጣይ ግዳጅ ራሱን በተሟላ መልኩ አዘጋጅቶ ወደ ሥራ የሚገባበት ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡ በዚህም ሠራዊቱ በየደረጃው በአደረጃጀቱ የሚወያይበትና በግዳጅ አፈፃፀሙ የነበሩ ጠንካራ ጎኖናችና ክፍተቶች እንደሚለዩበት አመልክተዋል፡፡
በበዓሉ ከሻለቃ እስከ ዕዝ ባሉ የጦር ክፍሎች የሚደረጉ የተለያዩ የስፖርት ፌስቲቫሎች የእርስ በእርስ ወዳጅነትን በማጠናከር የበለጠ መግባባትን እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል፡፡ በሁሉም የክልል ከተሞች ርዕሰ መስተዳደሮች እንደሚመሩት የሚጠበቅ የፓናል ውይይቶች ላይም ከፍተኛ የሠራዊቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ለዚህ የሚረዱ ሰነዶች ዝግጅትም የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ከዛሬ ጀምሮ ስርጭቱ ይጀመራል ብለዋል፡፡
በመድረኮቹ አገራዊ ለውጥ እንቅስቃሴን ተከትሎ በተቋሙ እየተካሄደ ያለውን የሪፎርም እንቅስቃሴ ሠራዊቱና ሕዝቡ እንዲገነዘቡ በማድረግ ሕዝቡ ከሠራዊቱ ጎን እንዲቆም የሚያስችሉም ይሆናሉ ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በሕዝባዊ መሰረት ላይ የተገነባው ሠራዊቱ ሕገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን እየተወጣ የሚገኝ፣ ወደፊትም ግዳጁን በሚገባ መወጣት የሚያስችለው አቅም ያለው ነውና ከሌሎች አገራዊ አቅሞች ጋር ተደማምሮ አገሪቱን ከማንኛውም ጥቃት መከላከል የሚያስችል ቁመና ላይ መኖሩንም በግልጽ ለማሳየት የሚረዱ ዋና ዋና መልዕክቶች እንደሚተላለፉበት ሜጀር ጀነራል መሐመድ አስታውቀዋል፡፡
በ2007 ዓ.ም በምዕራብ ዕዝና በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት በባህር ዳር ከተማ ተካሂዶ ነበር፡፡ ሠራዊቱም ከሕዝቡ ገንቢ ሃሳቦችን ያገኘበት በመሆኑ ከበዓሉ መከበር ማግስት ጀምሮ በእያንዳንዱ የተግባር እንቅስቃሴው በማካተት ግዳጁን ሲወጣ ቆይቷል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 16/2011
በፍዮሪ ተወልደ