ደኖች የአየር ንብረት ለውጥ የተረጋጋ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ :: በደን መጨፍጨፍ ምክንያት ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን የሙቀት አማቂ ጋዝ የክምችት መጠን እንዲቀንስ በማድረግ ሊያስከትል የሚችለውን ተጽዕኖ መቋቋም የሚችሉም ናቸው::
የደን ሀብትን ማልማት የአየር ንብረት ለውጥ እያሳደረ ያለውን ተጽፅኖ በመቀነስ ምቹ የአየር ንብረት እንዲኖር የሚያደርግ ቢሆንም ፤ ለዘርፉ ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል:: ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ሊከሰት የሚችለውን ችግር በዘላቂነት ለመመከት የሚያስችል መሆኑ በእጅጉ ታምኖበታል::
ስለሆነም የአየር ንብረት ለውጥና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ከወዲሁ ማስተካከል ለአሁኑም ሆነ ለመጪው ትውልድ ደህንነት እጅግ አስፈላጊ ነው:: ለዚህም ለደን ልማት ትኩረት በመስጠት እየተከሰተ ያለውን የውሃ እጥረት፤ የምርታማነት መቀነስ፣ የጤና ችግሮች እና የሙቀት መጨመረን በመከላከል ይገባል:: ዛፎችን በመትከል፤ ደኖችን በመንከባከብ ፤ አካባቢን ከብክለት በመጠበቅ ረገድ ሌት ተቀን ለመስራትም የሁሉንም የህብረተሰብ ርብርብ የሚጠይቅ ነው::
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአካባቢና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዙሪያ እንደ አገር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ክልሎችም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዘርፈ ብዙ በተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚሁ ዙሪያ ሀሳባቸውን ያካፈሉን የድሬዳዋ አስተዳደር የአካባቢ ፣የደንና አየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ አብዱመሐመድ አባመጋል፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያከናወነ ነው ይላሉ::
አቶ አብዱመሐመድ አባመጋል እንደሚናገሩት ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዋናነት ሁለት ዋና ዋና ተግባራት አሉት:: እነዚህም የሬጉላቶሪ ዘርፍ አብዛኛው ከህግ ተጠያቂነት ጋር ተያያዥ የሆኑ ስራዎች የሚሰሩበት ሲሆን፤ የደን ጥበቃና ልማት ዘርፉ ደግሞ ደን ከማልማትና ከመጠበቅ ጋር ተያያዥ የሆኑ ስራዎች የሚያካትት ነው::
በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ከብክለት ቁጥጥር ፤ ከአካባቢ ማህበራዊ ተጽፅኖ ግምገማ ጋር በተያያዘ የቁጥጥር ስራዎች የሚሰሩበት መሆኑን ጠቁመው፤ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ጋር ተያይዞ ከሰባት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ጋር በመሆኑ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ነው ሥራ አስኪያጁ ጨምረው የሚገልጹት::
ደንን በማልማት ረገድ ያሉትን የተወሰኑ ጥብቅና የተፈጥሮ ደኖችን የመንከባከብና የመጠበቅ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ:: አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ 5 ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ድርሻም 0.02 ፐርሰንት መሆኑን አመልክተው፤ ለድሬዳዋ አንድ ሚሊየን ችግኞችን መትከል የሚያስችል ኮታ ተሰጥቷል:: በዚህ መሠረት ከተሰጠው ኮታ በላይ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል እቅድ በመያዝ ችግኞችን አፍልተው የመትከሉ ሂደት የተጀመረ መሆኑን ይናገራሉ::
በአዲስ በተቀየረው የደን ትርጉም መሠረት አሁን ያለው የክልሉ የደን ሽፋን 9.2 ፐርሰንት አካባቢ እንደሆነ ይገመታል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ የተቋሙን የ10 ዓመት መሪ እቅድ በማዘጋጀት በሬጉላቶሪም ሆነ በደኑ ዘርፍ ከየት ተነስተን የት መድረስ እንዳለበት ግብ ተቀምጦ እየተሰራ ነው ሲሉ ተናግረዋል::
‹‹ድሬዳዋ የምስራቅ ኢትዮጵያ የንግድና የኢንዱስትሪ ኮርደር ብቻ ሳትሆን ፤ የአገሪቷ ገቢና ወጪ ንግድ ኮሪደር ሆና የምታገለግል በመሆኗ በርካታ ፋብሪካዎች አላት ›› ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ አሁንም ወደ ድሬዳዋ በርካታ ፋብሪካዎች እየመጡ ይገኛሉ:: ፋብሪካዎች በበዙ ቁጥር ደግሞ የአካባቢ ብክለት መጠኑም በዚያው ልክ እንደሚጨምር ጠቁመው፤ የህንን ለመከላከልም የተጠናከረ የህግ ማስከበር ስራ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ::
እንደ ስራ አስኪያጁ ገለጻ፤ ወደ ድሬዳዋ የሚመጡ አዳዲስ ፋብሪካዎችም ሆነ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከኢንቨስትመንት ቢሮ ፍቃድ ከወሰዱ በኋላ ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ይመጣሉ:: በዚህም ጊዜ ፕሮጀክቶቹ በአካባቢ ላይ ሊያስከትሉት የሚችለው አሉታዊ ተጽዕኖ ምንድነው? የሚለውን የመፈተሽ ስራ ይስራል:: ፕሮጀክቱ የአካባቢና ማህበራዊ ተጽዕኖ ግምገማ ያስፈልገዋል ወይስ አይስፈልገውም የሚል ውሳኔም ይሰጣል ይላሉ:: ፕሮጀክቱ በአካባቢ ላይ የጎላ ተጽዕኖ ሊያስከትላል ይችላል ተብሎ ሲታመን ሙሉ የአካባቢ ተጽፅኖ ግምገማ እንዲካሄድ ይደረጋል:: መለስተኛ የሆነ ጉዳት በአካባቢ ላይ የሚያደርስ ከሆነ ደግሞ በከፈል የአካባቢ ተጽፅኖ ግምገማ ጥናት እንዲካሄድ የሚወሰን መሆኑን ጠቁመው፤ በፕሮጀክቱ የአካባቢና የማህበራዊ ግምገማ ጥናት የማያስፈልገው ከሆነ በቀጥታ እንዲያልፍ የሚደረግ መሆኑን ያብራራሉ ::
በተመሳሳይ የፕሮጀክቶቹ ባለቤቶች በራሳቸው ማህበራዊ አማካሪ በኩል ጥናት የሚያስጠኑ ከሆነም ፤ የተጠናውን ጥናት በመፈተሽ አስተያየቶች የመስጠትና መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች ካሉም እንዲስተካከሉ የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል:: በመቀጠልም ወደ ስራ የገቡ ፋብሪካዎችም ሆኑ ሌሎች በገቡት ግዴታ መሠረት እየሰሩ መሆኑን ለማረጋገጥ የቁጥጥርና ግምገማ ስራ ይሰራል ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ በተጨማሪም በድንገት በሚደረግ ፍተሻና ቁጥጥር የላቦራቶሪ ናሙናዎችን በመውሰድ ፋብሪካዎቹ የሚለቁት ሙቀት አማቂ ጋዝ ወይም ፍሳሽ እንዲመረምር ይደረጋል:: እያንዳንዱ ፋብሪካ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀው ሙቀት አማቂ ጋዝም ሆነ ፍሳሽ ስታንደርድ ያለው መሆኑን ገልጸው፤ ፋብሪካዎቹ የሚጠቀሙት ከተቀመጠው ስታንዳርዱ በላይ ከሆነ እንዲያስተካክሉ ያደርጋል፤ የማያስተካክሉ ካሉም እስከ መዝጋት የሚደርስ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ጠቅሰዋል::
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ማያ የማካሮኒ ፋብሪካ ከፍተኛ የሆነ ፍሳሽ በመልቀቅ የአካባቢ ብክለት ሲያስከትል በመገኘቱ እርምጃ ተወሰዶበት፤ ስህተቱን በማረሙ ወደ ስራ ተመልሷል :: ከህዝብ በቀረበ ቅሬታና በተደረገው ቁጥጥር እንዲዘጉ ከተደረጉት መካካል የድሮ የድሬዳዋ ሲሚንቶ ፋብሪካና አንድ የከረሜላ ፋብሪካም ተጠቃሽ ናቸው:: ‹‹ ከተቋሙ ስራ አንዱ ልማቱን በመደገፍ መለወጥ፤ መልማትና ማደግ ነው›› ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ከልማት ስራው ጎን ለጎን ቅድሚያ ለሰው ጤና በመስጠት አከባቢ ከብክለት መጠበቅ ያስፈልጋል :: ልማቱንና የአካባቢ ጥበቃን ሁለቱን አንድ ላይ አጣጥሞ ማስኬድ ላይ ተግዳሮቶች የሚያጋጥሙ መሆኑን ጠቅሰው፤ ምንም ይሁን ምን ከህዝብ ጤና በላይ የሚቀድም ነገር የለምና ልማት እንደተጠበቀ ሆኖ አካባቢ ላይ ብክለት የሚያደርሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ያስረዳሉ ::
ከአካባቢ ብክለት ጋር ተያይዞ ብዙ የብክለት አይነቶች አሉ የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ የአፈር ፡ የአየር፤ የውሃ ፤ የድምፅ ብክለቶች ይጠቅሳሉ:: በድሬዳዋ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ የድምፅና የአየር ብክለት ለማወቅ ጥናት መካሄድን ጠቁመው:: ከሃይማኖት ተቋማት የሚወጡ ጽምጾች ጨምሮ ሁሉም ጽምጾች ሰውን በማይረብሽ መልኩ መካሄድ ስላለባቸው ለሃይማኖት አባቶችና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት ትምህርት ተሰጥቷል:: በተለይም ከተማ ውስጥ በሞንታርቦ የሚደረገው ቅስቀሳ ከባለስልጣኑ እውቅና ውጪ ማድረግ የማይቻል ነው ሲሉ ተናግረዋል ::
የጽምፅ ብክለትን በመቆጣጠር ረገድ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት የተሰራ መሆኑን የሚገልጹት ስራ አስኪያጁ ፤ በተለይ ለትራፊክ ፖሊሲ ስልጠናና የድምጽ መለኪያ መሳሪያዎችን በመስጠት በተቀመጠ ስታንዳርድ መሠረት የድምጽ ብክለት የመለካት ስራ እየተሰራ ነው:: በተመሳሳይ የባለስልጣኑ ባለሙያዎች በአካል በመገኘትና በመሳሪያ በመጠቀም በሚያደርጉት ምልከታ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት የመቆጣጠሩ ስራ እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ ::
በመኖሪያ፣ በኢንዱስትሪዎች እና በንግድ ተቋማት አካባቢ በቀን እና በማታ ምን ያህል የጽምፅ መጠን መጠቀም እንደሚፈቀድ የተቀመጠ የድምፅ ደረጃ ስታንዳርድ አለ:: ከተፈቀደው የድምፅ ደረጃ ውጪ የሚጠቀሙ አካላት ካሉ እርምጃ የሚወሰድ ይሆናል ያሉት ስራ አስኪያጁ ፤ አሁን ላይ በአብላጫው ማስተማሩ ላይ ትኩረት መስራቱን ጠቅሰዋል:: ‹‹የሰውን አእምሮ በመቀየር ለውጥ ማምጣት የሚቻለው በማስተማር እንጂ፤ በቅጣት አይደለም፤ በአካባቢ ላይ ያለው ድምፅ ለሰው ጆሮ የሚመጥን መሆን አለበት፤ ከዚህ በላይ ከሆነ ለጤናም ችግር ነው›› ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ የማስተማሩ ስራ ላይ ትኩረት በመስጠት በኦሮምኛ፤ በአማርኛና በሶማሊኛ ቋንቋዎች በመጠቀም ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን አመልክተዋል:: በተመሳሳይ ሚዲያዎችን በመጠቀምም በድሬ ቴሌቪዝንና ሬድዮ ፤ በሬድዮ ፋና ሃረማያ ቅርንጫፍ እንዲሁም በህትመት ሚዲያውም የማስተማሩ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ያብራራሉ::
የኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ለማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ሰባት ዘርፎች ላይ የሚያነጣጥር መሆኑን ጠቁመው፤ ከእነዚህም ውስጥ ኢንዱስትሪ ፤ ትራንስፖርት፤ ደን ፤ ግብርና ወዘተ ተጠቃሾች ናቸው:: በፌዴራል ደረጃ ጥናቱ ሲጠና እያንዳንዱ ዘርፍ ምን ያህል ሙቀት አማቂ ጋዝ ይለቃል የሚለውን የሚያካትት ሲሆን፤ ለምሳሌ ግብርና 50 በመቶ፤ የደኑ ዘርፍ 37 በመቶ እያለ የሁሉንም በዝርዝር ከፍፍሎ የሚያሳይ ነው:: ክልሎች ያላቸውን ድርሻ ምንያህል ነው የሚለውን የሚያሳይ አይደለም ይላሉ::
የሙቀት አማቂ ጋዝ ለመቀነስ መነሻው ማወቅ አለብን የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ በ2015 እኤአ የድሬዳዋ የሙቀት አማቂ ጋዞች ምን ያህል ነው የሚለው በሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ አማካይነት ጥናት ተጠንቶ ፤ የሰባቱን ሴክተሮች መነሻ መለየት ተችሏል:: በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽ እቅድ ላይ እያንዳንዳቸው ሴክተሮች ምን ያህል ሙቀት አማቂ ጋዞች መልቀቅ እንዲሚችሉ የሚያሳይ የመግባቢያ ስምምነት ሰነድ በመፈራረም እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር የሙቀት አማቂ ጋዞች ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረት ለውጥ ለማይበገር የአረንጓዴ ልማት የሚል የትግበራ ሰነድ በማዘጋጀት ለሰባቱ ሴክተሮች በመስጠት ስራ ላይ መዋላቸውን ይገልጻሉ::
አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስንል ሙቀት አማቂ ጋዞች መቋቋሚያ እርምጃዎችንና ተጋላጭነትን ሊቀንሱ የሚችሉ ሙቀት አማቂ ጋዞች አሉ ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ ሙቀት አማቂ ጋዞችን ለመለካት እውቀት ይፈልጋል:: በመሆኑም ሙቀት አማቂ ጋዞች እንዴት ወደ ከባቢ አየር ይለቀቃሉ? እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? እንዴት ሪፖርት ይደረጋል? የሚለውን ለማወቅ የሚያስችል ስልጠና ለእያንዳንዱ ሴክተር ተሰጥቷል:: ከእነዚህ ሴክተር የሚለቀቁ የሙቀት አማቂ ጋዞች ለመለካት እንዲችሉ አይፒሲሲ የተሰኘ ሶፍት ዌር በመጠቀም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል ::
‹‹ አርሶ አደሩ ዛፍ መቁረጥ ችግር እንዳለበት ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም የሚቆርጠው፤ ሲቸገር የሚያየው አካባቢ ያለውን ደን ነው፤ እዚህ ላይ ከፍተኛ ተግዳሮች አሉ›› የሚሉት ስራ አስኪያጁ ፤የደን ቁጥጥርና የመከላከል ስራ ደኑ ሳይቆረጥ በፊት መሆን አለበት ፤ አርባና ሃምሳ አመት የቆየ ደን ከተቆረጠ በኋላ መቆጣጣር እጅግ አዳጋች ነው ሲሉም አክለው ይገልጻሉ::
ይሁን እንጂ እንደ ድሬዳዋ ለየት የሚያደርገው መጤ ወራሪ ዛፍ አለ:: ይህም በድሬዳዋ አካባቢ የፈረንጅ ዛፍ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ በአብዛኛው የማገዶ አገልግሎትን የሚሸፍነው ይህ ዛፍ ነው፤ ዛፉ የራሱ አሉታዊ ተጽፅኖ ቢኖረውም በነባር እጽዋት ላይ ያለው ተጽፅኖ በመቀነሱ 92 በመቶ በምዕራብ በኩል ወደ ድሬዳዋ ከተማ ከሚገባው የማገዶ እንጨት አብዛኛውን የሚሸፍን መሆኑን ተናግረዋል ::
የአካባቢ ጥበቃ ስራ የአንድ ተቋም ስራ መሆን የለበትም የሚሉት ስራ አስኪያጁ ፤ በየደረጃው ያለን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ስራ የሚጠይቅ ነው:: አሁን ላይ ያለው የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መዋቅር በከተማ አስተዳደር ብቻ ተንጠልጥሎ የቀረ መሆኑን ጠቁመው፤ በድሬዳዋ 36 የገጠር ገበሬ ማህበርና 9 ክፍለ ከተማ መሆን የሚችሉ የከተማ ቀበሌዎች በመኖራቸው መዋቅሩ እስከታች ድረስ መድረስ አለበት ብለዋል::
ለአካባቢ ጥበቃ መስሪያ ቤት የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ መሆኑን የሚገልጹት ስራ አስኪያጁ ፤ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዝ የተወሰነ ድጋፍ ከውጪ ይደረጋል:: ከዚህ በስተቀር ከስራው ጋር ተያይዞ እንደተቋም የተሟላ የግብዓት አቅርቦት እንኳን የለም ስለሆነም ይህ ሊታሰብበትና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲል ሀሳባቸውን አጠቃለዋል::
አዲስ ዘመን ሰኔ 22/2012
ወርቅነሽ ደምሰው