የጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ የአዕምሮ ሀኪም፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ፋክሊቲ መምህርና የጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ናቸው።ትሁት፣ ታታሪ እና ህዝብ አገልጋይነታቸው መታወቂያቸው ነው።ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ የግል ሆስፒታሎችን የማያዳርሱ፣ለቆሙለት ሙያና ለገቡት ቃልኪዳን በታማኝነት የሚያገለግሉ ባለሙያ ናቸው። ከህክምና ዘርፉ አለፍ ሲሉ ‹‹አለመኖር›› በሚል ርእስ ባሳተሙት መፅሃፋቸው ብዙዎች ያውቋቸዋል። ከአዲስ አበባ እስከ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ ፤ በውጭ አገር ካናዳ ድረስ በመሄድ በዘርፉ አገልግለዋል። በመምህርነት አሻራቸውን በማሳረፍ በርካታ ባለሙያዎችን አፍርተው ለአገራቸው እንዲተርፉ አድርገዋል። ከህይወት ተሞክሯቸው ብዙዎች እንማር ዘንድ የዛሬ ‹‹ የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን አድርገናቸዋል። እኚህ ሰው ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ ይባላሉ። መልካም የንባብ ቆይታ! ልጅነት
እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ልጅ ጎረቤት በስነምግባር ታንፀው እንዲያድጉ እየቆነጠጣቸውና ከአቻ ጓደኞቻቸው ጋር እየተጫወቱ በአዲስ አበባ ከተማ አዲሱ ገበያ አካባቢ ነው ያደጉት። የመጨረሻና ብቸኛ ወንድ ሲሆኑ፤ እናታቸው ብቻቸውን ነው ያሳደጓቸው። ወላጃቸውም ሆኑ እህቶቻቸው ለቁምነገር እንዲበቁላቸው በብዙ ጥረዋል። ይህ ደግሞ የቤተሰብ ኃላፊነት እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል።
በልጅነታቸው ቀስት ማስወንጨፍና እግር ኳስ የሚያስደስታቸው ጨዋታ ነበር። የማይረሳው ሌላው ትዝታቸው ደግሞ በጭቃ የሚሰሩት ግድብ ነበር። ከአካባቢው ልጆች ጋር ታላላቅ ወንዞችን ስያሜ እየሰጡ ለጨዋታ በጭቃ ገድበዋል። ድርጊታቸው ደግሞ እያንዳንዱን በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ግድቦች እንዲያውቁ አግዟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ ። በልጅነታቸው ባለ ራእይ እንደነበሩ ይናገራሉ። አባይ ጭምር በእነርሱ የጭቃ ግንባታ ተገድቦ እንደሚያውቅ ሲያስታውሱና አሁን ይሄ ህልማቸው እውን ሆኖ ማየታቸው እጅጉን ያስደስታቸዋል።
‹‹አዲሱ ገበያ አሁንም ድረስ እግዚአብሔርን የሚፈራ ያለበት፤ እርስ በእርስ መዋደድ እንጂ ጥላቻ የማይታወቅበት፣ ትልቅ ትንሹ የሚከባበርበት፣ ቆንጥጦ አሳዳጊ የሞላበት፣ እኔም አድጌ ሌሎችን መቆጣት የቻልኩበት ነው። ጥቅጥቅ ያለ ጫካ ስለነበረም ብዙ ትዝታዎች እንዲኖሩኝ ያደረገኝ ነው›› ይላሉ የልጅነት ትዝታቸውን መለስ ብለው እያስታወሱ፤ ከትውስታቸው እየጨለፉ እያጋሩን።
አስተዳደጋቸው ከጨዋታም ባሻገር የቤተክ ርስቲያን አገልግሎት የታከለበት ነበር። የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪና ዲያቆን በመሆናቸው ከጨዋታ መልስ በቤተክርስቲያን ያገለግላሉ። ከፍተኛ ደስታ የመንፈስ እርጋታም ነበራቸው። ግጭት በተለይ ደግሞ አካላዊ ድብደባ በፍጹም አይወዱም። ጨዋታ እንኳን ሲመርጡ የተረጋጉትንና ግጭት የማይፈጠርባቸውን ነው። ከሰዎች ጋር በህብረት መስራትና ተሰባስቦ ሰዎችን መርዳት ያስደስታቸዋል። የማስተባበርና የመምራት ተሰጦ እንዳላቸው ይናገራሉ።
‹‹አንድ ሰው ስኬታማ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው በሚል ራሳችንን ብዙ ጊዜ እናሳምናለን ፤ እንፈርጃለን ።ይሄ ከአጋጣሚ በላይ የሚወሰድ አይደለም። እኔ ተምሬ ለዚህ ደረጃ የበቃሁት እድል ገጥሞኝ ነው። ልዩ ተፈጥሮ፣ ድጋፍና ችሎታ ስላለኝ አይደለም›› የሚሉት እንግዳችን፤ ማናችንም ከማናችንም የሚለያየን ተፈጥሮ የለም የሚል እምነት አላቸው። ነገር ግን እድል ቀንቷቸው የመጨረሻ ልጅ በመሆናቸው ምንም እንዳልጎደለባቸውና በነጻነት ማደግ እንደቻሉ ያነሳሉ።
ቤተሰቡን የሚያግዙበት ሁኔታ እንብዛም ባይሆንም በልጅነታቸው ቤተሰብን ከማገዝ አላመለ ጡም ። እንጨት ማምጣት፣ መላላክ፣ የእናታቸውን የተለያየ ቦታ እድር ክፍያ መፈፀምና ወፍጮ ቤት እህል አስፈጭቶ ተሸክሞ መምጣት ተደጋጋሚ ሥራቸው ነበሩ። ይሄ ተግባር የእድሜ እኩዮቻቸውም በየቤታቸው የሚከውኑት ጭምር እንደነበር ያስታውሳሉ።
በልጅነታቸው በጣም ከሚጠሉት ነገር የጓሮ አትክልት መትከልና መንከባከብ ሲሆን፤ ቤት ውስጥም ይህንን እንዲያደርጉ ሲታዘዙ በጣም ይናደዱ እንደነበር አይረሱትም። ዛሬ ይህ ተቀይሮ መስራቱን አጥብቀው
ይወዱታል። የአትክልት ምርት ተጠቃሚ ናቸው።
‹‹ለእኔ የልጅነቴ ትልቁ ስጦታ ነጻነቴ ነው። ቤተሰቦቼ አንድም ቀን ይህ ልክ አይደለም ብለውኝ አያውቁም። አጋጣሚው ስህተቴን በራሴ ጥረት እንድረዳ አድርጎኛል›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ ከጎረቤታ ቸውም ተጨማሪ እህት ወንድም፣ አባት እናት የሚሆኑ ማግኘታቸውም የልጅነታቸው ስጦታ እንደሆነ ያምናሉ።
ወላጅ እናታቸውና እህቶቻቸው ልጃቸው አድጎ ተምሮ ተግባረዕድ በመግባት መካኒክ እንዲሆኑ ይመኙ ነበር ። እሳቸውም ለቤተሰቦቼ ልድረስ በሚል ጭንቀት ሳይሆን ጥሩ እንደተመኙላቸው በማመን መካኒክ መሆንን አምነው ይማሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። እየበሰሉና ሁሉን ነገር ማገናዘብ ሲችሉ ብዙ ነገሮችን በራሳቸው እንዲወስኑ ስለተተዉና በጊዜው አውሮፕላን ማብረር ብርቅ ስለነበር ፓይለት መሆንን ምኞታቸው አደረጉ።
ከአዲስ አበባ እስከ ቶሮንቶ
ፊደልን መቁጠር የጀመሩት ቤተክርስቲያን በሚያገለግሉበት ጊዜ ነበር። ዘመናዊ ትምህርትን መቁጠር የጀመሩት ደግሞ ላዛሪስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። እስከ ስምንተኛ ክፍልም በዚያው ቆዩ። ቀጥሎ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የዛሬው ቀለመወርቅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ተከታትለዋል። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በስኬት አጠናቀው ከፍተኛ ውጤት በማምጣታቸውም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታልን ተቀላቅለዋል።
ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ ግን የፖለቲካ ሳይንስ፣ ህግና ማህበራዊ ሳይንስን መማር ይፈልጉ ነበር። ምክንያታቸው ደግሞ በዘርፉ ልዩ ተሰጦ አለኝ ብለው በማመናቸው ነበር። ለዚህ ነበር ምርጫቸው እንዲሳካ አስረኛ ክፍል እያሉ ምርጫቸውን አርት አድርገው መማር የጀመሩት። እድል ግን 11ኛ ክፍል ሲደርሱ ነገሮችን ቀየረች። በትምህርታቸው ጎበዝ በመሆናቸው ልዩ / ስፔሻል/ ክፍል እንዲገቡ ተደረገ። ወቅቱ የሚፈልገውን የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርት እንዲማሩ ሆኑ። ይሄ ምክንያት ህክምና እንዲያጠኑ መንገድ ከፈተላቸው። ዛሬም ድረስ ‹‹ዶክተር›› በሚለው የሙያ ማዕረጋቸው ሲጠሩ እንደሚገረሙ አጫውተውናል።
ህክምናን አጥንተው ጥቂት እንደሰሩ ሌላ የትምህርት እድል አገኙ። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በተማሩበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ዳግም በአዕምሮ ህክምና ስፒሻላይዝድ አድርገዋል። ወደ ስኮትላንድ በማቅናትም በኤደንብራ ዩኒቨርሲቲ በሶሻልና ፓፕሊክ ፖሊሲ የትምህርት መስክ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
ትምህርት በቃኝ አያውቁምና አሁንም ለመማር ወደ ካናዳ ሄደው ተመለሱ። የአዕምሮ ህክምና ማለትም የንግግር ህክምናን በቶሮንቶ ኢኒሲሶርስ ሳይኮ አናሊስስ ትምህርት ቤት አጥንተዋል። ቀጥለው ደግሞ ሳይኮ ቴራፒ የሚባል ትምህርትም በዚያው ተምረዋል። ከዚህም በላይ የተማሯቸው ትምህርቶች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ።
በእርሳቸው ምልከታ ‹‹ ትምህርት የሰውን እኩልነት ማረጋገጫ እንጂ የሰውን ልዩነት ማስረገጫ አይደለም። መኮፈሻ፣ ለህዝብ ጥቅም ዝቅ የማይባልበት፣ በስሙ ክብር እንጂ ሥራ የማይሰራበት፣ የፈሰሰ ውሃን ማቅናት አይመጥነኝም የሚባልበት አይደለም። ይልቁንም ምጡቅ የሆነ አዕምሮ ባለቤት መሆን፤ ጠያቂ መሆን፤ የነገሮችን ስረ መሰረት መረዳት፤ ከሌሎች ጋር መኖር መቻል ነው።››
ከቤንች ማጂ እስከ ካናዳ
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከተመረቁ በኋላ የገጠሪቱን
ኢትዮጵያ በሙያቸው አገልግለዋል። እንዳውም ህይወትን ያጣጣሙት ቤንች ማጂ በሄዱበት ወቅት እንደነበር ይናገራሉ። የመጀመሪያ ሥራቸው በአማን ሆስፒታል ነበር። ቀጥሎ ወደ ዲላ አመሩና የወቅቱ ደቡብ ዩኒቨርሲቲ በማስተማርና በማከም ማገልገል ተያያዙ። ብዙም ሳይቆዩ ወደ ሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በማምራት የሥራ ቦታቸው በዚያ ሆነ።
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት እንዲጀመር ካደረጉት መካከል ስለነበሩም በዩኒቨርሲቲው በማስተ ማርና በማከም አገልግለዋል። በመካከል የትምህርት እድል በማግኘታቸው ሥራውን አቋርጠው ቢቆዩም ዳግም ግን እዛው በመመለስ የነበሩበትን የማስተማርና የማከም ተግባራቸውን ቀጥለው እንደነበር ያወሳሉ።
በጆን ኦፍ ኪንግ ግል ሆስፒታል ለጥቂት ጊዜያት እንደሰሩ የሚናገሩት ዶክተር ዳዊት፤ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ብዙ ነገሮች ምቹ በመሆናቸው በማስተማርና በህክምና ለማገልገል መጡ።
እንግዳችን በትምህርት ላይ እያሉ ሳይቀር የተለያዩ ኃላፊነቶች በመውሰድ ሰርተዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ለሰባት ዓመታት በቆዩበት ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች መማክርት ፕሬዚዳንት መሆናቸው ነው። በሌላ በኩል ከትምህርት በኋላ ደግሞ የአዕምሮ ህክምና ክፍልን በረዳት ፕሮፌሰርነት መርተዋል። ተባባሪ ፕሮፌሰር ሆነውም አስተዳድረዋል። የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ክፍሉ በተወሰነ ደረጃ ጳውሎስ ሆስፒታል ይሰራ
ነበርና ይህንንም ክፍል በኃላፊነት የመምራት እድሉ ነበራቸው። በጥቁር አንበሳ ትምህርቱ እንዲከፈት ካደረጉ በኋላ ደግሞ ከጳውሎስ ወደ ተማሩበት ትምህርት ቤት በመመለስ ክፍሉን በኃላፊነት መርተዋል።
እንግዳችን፤ የጤና ሳይንስ ኮሌጁን ማለትም በግቢው ውስጥ የሚሰጡ የትምህርት ክፍሎችን እንዲሁ በተባባሪ ዲንነት መምራት ችለዋል። የኮሌጁ ድህረ ምረቃ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ነበሩ። ቀጥለው ደግሞ በትምህርት ምክንያት በሄዱበት በካናዳ ክሊኒካል ፕሮፌሰር ሆነው ሰርተዋል። የጭንቀትና የድብርት ህክምና አማካሪም በመሆን በካናዳ መስራታቸውን ይናገራሉ ።
ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ደግሞ አሁንም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ትምህርት ክፍሉ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። የኮሌጁ ዳይሬክተርም ነበሩ። አሁን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ማዕረግ የሆስፒታሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።
በርካታ ተቋማትን በኃላፊነት በመምራት የብዙ ዓመት የሥራ ልምድ ቢያዳብሩም በግል ሆስፒታሎች ውስጥ መስራትን ግን በፍጹም አይፈልጉም። ምክንያታቸው ደግሞ አንድና አንድ ሲሆን፤ ሙሉ ጊዜያቸውን በውጤታማ ሥራ ማሳለፍን ስለሚፈልጉ ነው። ይህን ካደረጉ ለታካሚውም ሆነ ለራሳቸው የሚያጎሉት ነገር እንዳለ ስለሚያምኑ በውሳኔያቸው እስካሁን ፀንተው እንደቆዩ ይናገራሉ።
‹‹ሀኪም መሆን መመረጥ ነው። ለዚህም ማሳያው ብዙ የማያውቅሽ ሰው ሲያምንሽ ታያለሽ።›› የሚሉት ዶክተር ዳዊት፤ በቅርቡ ማታ ስራ ላይ እያሉ የገጠማቸውን ለአብነት ያነሳሉ። ሁለት ባልና ሚስት የአራት ዓመት ከስድስት ወር ልጃቸውን ለማሳከም ይመጣሉ። ድንገት ለሁሉም በተደረገላቸው ምርመራ እናትና አባት በኮሮና ተይዘዋል። ህጻኗ ግን ነጻ ነች። ስለዚህ እናትና አባት ወደ ማቆያ ሲላኩ ህጻኗ በአደራነት የተሰጠው ለእኛ ነበር። ሰዎቹ ከገጠር የመጡ በመሆናቸው ጭንቀቱ የበለጠ ጨመረባቸው ፤ ሆኖም ግን እነርሱንም እርሷንም የማዳን ግዴታ ስላለብን ወላጆቿን ወደ ማቆያ በመላክ ልጅቱን መንከባከብና ማዳን ላይ ተረባረብን ሲሉ አጫውተውናል።
ሙያው በስም እንኳን ለማያውቅ ሰው ልጅን ያህል አምኖ እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው ። ለአመኔታ እንዲታጭ የሚያደርግ ነው። አባት፣ እናት መሆን የሚቻልበት ነው፤ ይሄን በሁለት መንገድም ይገልጹታል። የመጀመሪያው ህክምና መታደል ሲሆን፤ ሁለተኛው እዳና አደራ ነው። ባለ እዳ ለመሆን ታማኝ መሆንን ይፈልጋል። በዚህም በየቀኑ ባለ እዳ እንደሆኑ፣ አሁን የሚመሩት ሆስፒታል ሰራተኛና ታካሚ ደህንነት በየግል ባይደርሱም ጉዳያቸው እንደሆነም ይናገራሉ። እዳ ያለበት ሰው ደግሞ ሁልጊዜ ይሰጋል። ግን ስጋቱ በደህንነት ይለወጣል፤ አንዳንዴ እዳ ላይከፈል የሚችልበት ሁኔታም ይኖራልና ያንን ሳይደረግ ሲቀር ደግሞ የሚታዘንበትም እንደሆነ ያብራራሉ።
የአገር አበርክቶ
‹‹የተለየ ሥራ ሰርቻለሁ ብዬ አላምንም። የነበሩና መሰራት ያለባቸውን ነው ያከናወንኩት። ለአብነትም ቢሮክራሲዎች እንዲቀንሱ፤ ሁሉ ነገር ከእጅ ንክኪ ነጻ ሆኖ በቴክኖሎጂ ሥራዎች እንዲከናወኑ መደረጉ፤ በሽተኛው ሳይንገላታ ህክምና በስልክ እንዲያገኝ ቴክኖሎጂውን ማዘመን መቻል በትንሹም ቢሆን ሰርቻለሁ እንድል አድርጎኛል›› ይላሉ።
እዚህ ቦታ ላይ ሲቀመጡ ሦስት ነገሮችን ለመስራት አቅደው እንደመጡ ያጫወቱን እንግዳችን፤ ተቋሙ ትልቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እርስ በእርስ ለመግባባት ይቸግራል። ስለዚህም በግል መራመድንና አለመስማማትን መፍታት የመጀመሪያው ነው። ከዚያ ሁለተኛ ሥራቸው እንዲሆን ያቀዱት በሰራተኛው ላይ የባለቤትነት ስሜት መፍጠር ነው። ሦስተኛውና የመጨረሻው እቅዳቸው ደግሞ ተቋሙ ምላሽ ሰጪ ብቻ ሳይሆን መሪ እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህንንም በተወሰነ መልኩ እያሳኩ መሆኑን ያነሳሉ።
ጥቁር አንበሳ በዓመት ከ500 ሺህ በላይ ሰው የሚታከምበት ብቸኛ የተቸገሩ መርጃ ድርጅት ነው። በጤና ተቋማት ብቸኛ የጤና የይግባኝ ቦታ ነው። ለመድኃኒት ከፍተኛው በጀት በዓመት 80 ሚሊየን ብር የሚሰጠው እና ለሁሉ ደራሽ ነው። ይሄ ማንነቱ እንዲቀጥል ማድረጉ ላይ እየሰሩ መሆኑን አጫውተውናል።
በጣም የከፋ የህብረተሰብ ችግር እስኪመጣ ድረስ ከኮሮና ጋር ያልተያያዙትን ህክምናዎች ተቋማቸው እየሰጠ እንደሆነ የሚያነሱት እንግዳችን፤ በሌላ ህመም መጥተው ችግሩ ካለባቸው የራሱ ክትትል ክፍል ስለተዘጋጀ ወደ ለይቶ ማቆያ እስኪላኩ ድረስ እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግም ወደ 32 አልጋዎች እንዳዘጋጁ፤ በሽታው ቶሎ ስለማይታወቅ ብዙዎች ተጋላጭነት ሊኖር ይችላልና ይህም እንዳይሆን በማድረግ ለወቅታዊ ሁኔታም መልስ ለመስጠት እየሰሩ መሆናቸውንም ይናገራሉ።
በሌላ በኩል የጥቁር አንበሳ ሥራ በሆስፒታሉ ብቻ አይደለምና በሁሉም ሆስፒታል ውስጥ አስፈላጊ በሆነ ጉዳይ ላይ ገብተው የሚሰሩበት አሰራርም ተዘርግቷል። በዚህም ለአብነት በኮሮና ምክንያት ብቻ በየእስፔሻሊቲው በርከት ያሉ ዶክተሮችን በኤካ ኮተቤና መሰል ሆስፒታሎች እንዲያገለግሉ ተልኳል። በተመሳሳይ የማማከር ሥራ እንዲሰሩ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ባለሙያዎችን ወስዷል። በተቋሙ ውስጥ ያሉ ድጋፎች ሁሉ ከመሪነት ጋር የሚያያዙ ስለሆኑ በተቻለ መጠን እየተገበሩት መሆኑን እንደሚያምኑ ይናገራሉ።
‹‹ አለመኖር ›› የፍልስፍና እሳቤ
የመኖር ፍልስፍናቸው በህዝብ ዘንድ እንዲሰርጽ ይፈልጋሉና ‹‹አለመኖር›› በሚል ርዕስ የፍልስፍና መጽሀፍ ጽፈው ይሄው ለአንባብያን ብለዋል። በመፅሀፉም ሆነ በንግግራቸው እንዳሉን፤ መኖር መታደል ነው። ከእኛም በፊትም ሆነ በኋላ ብዙ የማናውቃቸው ሰዎች በዚህች ምድር ላይ ኖረዋል። ግን አናውቅም፣ አልነበርንም አንኖርም። ምክንያቱም መኖር የሚጀምረው በመካከል ስለሆነ። በነበሩትና በኖሩት፣ በሞትና በውልደት፣ በወጣትነትና በእርጅና መካከል ነው።
መካከል ላይ ያለ ሰው ደግሞ ቋሚ እንዳልሆነ
ይረዳል፤ በአንድ ቦታ ላይ ብቻ እንደማንቆም ያውቃል። ይህ ደግሞ የጊዜ ጥቅምን ያስተምራል። በቆይታችን የምንችለውን፣ የማንችለውን፣ የምንሆነውን፣ ለአገርና ለራሳችን የምናደርገውን እየተረዳን እንድንቀጥልም መሰረት ይሆናል ይላሉ።
መኖር ስንወለድ የነበረ ዓለም ስለሆነ በቀደመ ዓለም ውስጥ እንድንኖር ያደርገናል። ምክንያቱም ከእኛ በፊት የነበሩ ሰዎች አለምን ለእነርሱ እንዲመቻቸው አድርገውታል። እናም እኛም በሰሩት አለም፣ አስተሳሰብና የአኗኗር ዘዬ ውስጥ እንድንመጣ ሆነናል። ምርጫችንም እነርሱ ብቻ ሆነዋል። ግን አንድ ነገር ማድረግ ይቻለናል። እዚያ መሀል ውስጥ ሆነን ቦታ መፈለግና ማግኘት። ከዚያ መኖራችንን እናሳያለን። በራሳችን መመራትን እንጀምራለን።
መኖር ዝም ብለን መጥተን ኖረን የምንወጣው አይደለም። ከቀደመው ምን እንደሚጠቅም መረዳትም ነው። ለቀጣዩ ትውልድ የምንሰራውና እንዲከተለን የምናደርግበት ነው። ስለዚህም በሚለወጥ ዓለም ውስጥ እኛ መጥተን ቦታ ይዘን እኛ ለውጠነው የምንሄድ ፍጡራን ነንና ሂደቱን በተሻለ ማንነት ስንገነባው ነው መኖር ጀመርን ማለት ያለብን።
‹‹መኖራችንን መኖር ያለብን እንደገባን ነው›› ብለው የሚያምኑት እንግዳችን፤ ሰው የብሩህ አዕምሮ ባለቤት ነው። እውነት፣ እውቀት ለእርሱ ብቻ የተሰጡት። ስለሆነም ያንን ይዞ የተፈጠረ በመሆኑ ለራሱ በሚመስለው መንገድ ሊጠቀምበት ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ግን መሰረታዊ የመኖር እውነታውን መዘንጋት እንደሌለበት ይመክራሉ። የዛሬው አይጠቅመኝም መባል የለበትም። ምክንያቱም በመሀል ስላለ የሚቆይ መሆኑን ማሰብ ይገባዋል። በትልቅ መስመር ውስጥ ትንሽ ነጥብ ልንሆንም እንችላለንና ከዚያ ውስጥ ላለመጉደል መጣጣርም ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን በዚያው እንጠፋና የማይታወቁት ውስጥ እንገባለን ይላሉ።
ሰው እንዲህ ሁን ተብሎ የሚሆን ፍጡር አይደለም። እንዲያስብ ሆኖ የተፈጠረ ነው። ስለዚህም በራሱ የሚሆነውን አስቦ መንቀሳቀስ አለበት ። በአብዛኛ
ከሰው ጋር የማያጋጨውን፣ በተለመደው መንገድ መሄድን፣ የተፈቀደውን ነገር ብቻ ይዞ መቀጠልን ባህል አድርገናል ይላሉ።
ከእኛ በፊት የተፈጠረ ዓለም የተለየ ቦታ ነበረው። በዚያ ቦታ ላይ ሆኖ ማፈንገጥን፣ ማሰብን፣ ማወቅንና መበልጸግን ሊከለክልም ሊፈቅድም ይችላል። በእነዚህ ሁለት መስመሮች ውስጥ ያለው ሰውም ለመኖር ሲል ሁለቱንም ተቀብሎ ያስኬዳል። ግን መኖርን ከዚህ በተቃራኒው ማየት ይገባል። ለሌላ ሰው መኖርን በሚጠቅም መልኩ። አንድ ህጻን ልጅ ጥያቄ ሲጠይቅ አይባልም ፤ ስታድግ ይገባሀል እየተባለ መቀጠል ሳይሆን እየጠየቀ የራሱን ዓለም እየፈጠረ እንዲጓዝ በማድረግ ሊሆን ይገባል። አማራጭ የሌለውና የተቀበለውን ይዞ የሚቀጠል ልናደርገው አይገባም የሚለው ፍልስፍናቸው ነው።
ኢትዮጵያዊ አኗኗር
ኢትዮጵያዊ መኖርን ለመናገር የምንስማማበትን
ነገር ይዘን መቀጠል አለብን። እኔ እንደኖርኩት፣ እንደተቀበልኩትና እንዳደኩበት ለሌላው ሰው ሆኖሎታል ብሎ ማመን ከባድ ነው። ምክንያቱም መኖራችን እንደመልካችን ይለያያልና እርሱም በራሱ ሚዛን አይቶ ነው መኖርን የሚበይነው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ አኗኗርም ኢትዮጵያ እንደሰጠችን ሁኔታ ይሆናል ብለው ያስባሉ።
ለእርሳቸው ኢትዮጵያዊነት መኖር አንድ ቦታ ላይ የማይቆም፤ በየቀኑ ‹‹ባወኩት ልክ እየጨመርኩ የምሄደው እኔነት ነው›› በማለት ይገልፁታል። ከሌሎች ጋር መኖር፣ ከልጆች ጋር በልጅነት ጊዜ አብሮ መቦረቅና ጊዜውን መሻገር ነው። የወደፊት ህልምን አሻግሮ መመልከት ነው። በነጻ ተምሮ በሰዎች ምልከታ ትልቅ የሚባለው ደረጃ ላይ መድረስም ነው። ግን በሌላው ይህ ሳይሆንለት ለቀረው ሌላ ትርጉም አለው ይላሉ።
መኖር በኮሮና
‹‹መኖር ጊዜ የሚፈልግ ነው። እናም ቦታና ወቅት ከሰው መኖር ጋር በእጅጉ ይቆራኛሉ›› የሚሉት እንግዳችን፤ የህዳር በሽታ በወቅቱ የኖሩ ሰዎች ምን የት እንደተከሰተ ያውቁታል፤ ያስታውሱታል። ኮሮናንም ዛሬ ያለነው እናውቀዋለን። ይህንን ስንረዳ አዲስ አበባ ያለነውና በክልል ያለው በእኩል ደረጃ ሁኔታውን ሊገልፀው አይችልም ይላሉ። ስለዚህም እያንዳንዱ ዘመን ለእያንዳንዳችን ብዙ ትምህርት እንደሚሰጥ ያምናሉ። ብዙ ችግሮችንም እንድናልፍ ከማስገደዱ ባለፈ ግን፤ እንደዚህ ወቅት ሁሉንም እኩል ያደረገ መቼም ገጥሞ አያውቅም በማለት ሁኔታውን ያስረዳሉ።
ሁሉም በእኩል ይወጣው ዘንድ ስለታሰበ ሊሆን ይችላል ኮሮና በመኖራችን የመጣው የሚሉት ዶክተር ዳዊት፤ ሁሉም ሰው አንድ ነገር ማወቅ አለበት። ይኸውም ከዚህ ትውልድ በፊት የነበሩት ያልኖሩት እዚህ ዘመን ላይ ያለ ትውልድ ብቻ የሚገጥመው አንዳች ችግር የለም። እነርሱ ችግሩን ተጋፍጠው እንዳለፉት አሁንም እናልፋለን የሚል ጠንካራ ስነ ልቦና ማዳበር እንደሚገባ ይመክራሉ። እናም ኮሮናን መቆጣጠር በምንችልበት ሁኔታ ታግለን ለሌሎች ችግር የሌለበት አገር ማስረከብ ይጠበቅብናል የሚል መልእክት ያስተላልፋሉ። ጦርነት ላይ ወታደር ይዋጋል ሌላው ምግብ ያቀብላል። ርሀብ ሲሆን ደግሞ ያለው የሌለውን እያገዘ ይኖራል። ኮሮና ግን ለሁሉም የመጣ በመሆኑ የሁሉንም ሥራ ይጠይቃል። ልዩ የሚያደርገውም ይኸው ባህሪው ነው። እናም ኮሮና ሁሉንም ሊያጠቃ ይችላል። በዚያው ልክ ሁሉም መከላከል የሚችለው ነውና ይህንን አውቀን ለመኖር መስራት አለብን ባይ ናቸው።
ቤተሰብ
ዶክተር ዳዊት የሦስት ልጆች አባት ናቸው ። ቤተሰባቸው ያሉበትን የስራ ሁኔታ እንደሚረዱላቸውና እንደሚጨነቁላቸው ያውቃሉ። በተለይ እርሳቸው የጤና ችግር ስላለባቸው የሚሰጉት ለእርሳቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ግን ይህም ሆኖ ለቤተሰብ መጠንቀቅ ይገባልና ክፍል ለይተው ብቻቸውን እንደሚያሳልፉ፤ ከእነርሱ ጋር መገናኘት ካለባቸውም በርቀት እንደሆነ አጫውተውናል።
ልጆቻቸው ለእርሳቸው ከመጨነቃቸውም በላይ አቅርበውና አቅፈው አለመጫወታቸው በጣሙን ያስከፋቸዋል። ሆኖም በምድር ላይ ያለውን የሰው ልጅ ችግር ሲታይ ይህንን ችግር ብሎ መውሰዱ ተገቢ እንዳልሆነ ይረዳሉ። እናም ይህም ያልፋል ብለው እንደሚተው ይናገራሉ።
መሰነባበቻ
‹‹ስኬት እንደመስፈሪያው ነው። አንዳንድ ሰው በገንዘብ፣ በእውቀት፣ በሥራ፣ ከሰው ጋር በመኖር ይሰፍረዋል። ሁሉም ግን ስህተት አይደለም። ስህተት የሚሆነው ሁሉም በአንዱ ነገር ብቻ ስኬትን ሲሰፍረው ነው፤ ሁሉም ሰው በመስፈሪያው የተሳካለት ነው። በዚያው ልክ በራሱ መስፈሪያ የጎደለበት ነው። እናም አሰፋፈራችን ሲስተካከል ስኬታችንን እናገኛለን።›› ይላሉ። ኢትዮጵያውያን መሆን ያለባቸው የሌላን ሰው ጥፋትና ሸክም መሸከም ሳይሆን ሸክሙን አውርዶ ከስህተቱ እንዲመለስ ማድረግ ነው። ስርዓት የተቋቋመው ሰው አንድ ነገር እንዲሆን አይደለም። ይልቁንም አሰራር እንዲሻሻል፤ ሰው እንዲማር ነው ይላሉ።
በመጨረሻ የሚያነሱት ሃሳብ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያተኩራል ‹‹አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ማለት ሰው አለመርዳት ማለት አይደለም መነካት ያለበትን ሰው ተጠንቅቆ ማገዝ እንጂ›› ይላሉ። ያለፉት ትውልዶች በፈጠሩልን ዓለም ውስጥ መኖራችንን በማንሳትም፤ ይሄም ትውልድ ትቶት የሚሄደውን ዓለም ለሌሎች የተመቸ ማድረግ እንደሚገባው ገልፀው ሃሳባቸውን ይደመድማሉ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 21/2012 ጽጌረዳ ጫንያለው