የግሪክ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት በተማሪዎች ላይ ያደርሳል በተባለው የተመሳሳይ ፆታ ወሲባዊ ትንኮሳና ቀለምን መሠረት ያደረገ የትውልድ አምካኝ ተግባር ላይ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲሁም ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም ተከታታይ ዘገባ መሥራታችን ይታወሳል:: በመቀጠልም ጥር 20 ቀን 2012 ዓ.ም በዘገባው የተካተተው መምህር ኃይሉ ፍቃዱ ትምህርት ቤቱ ያሳረፈባቸው ቅጣት እንዲነሳላቸው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደወሰነላቸውም መዘገባችን ይታወሳል:: ለዛሬም በትምህርት ቤቱ ላይ አንድ ወላጅ በተቋማችን የፖስታ አድራሻ ያደረሱንን መልዕክት ይዘንላችሁ ቀርበናል::
ለትውስታ
ግሪክ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በሥራ ላይ የነበረ ሲሆን፤ የተቋቋመውም በኮሚዩኒቲ ሥም ነው:: ይሁን እንጂ በግቢው ሁለት ክፍል ሲኖር አንደኛው አዳሪ ሌላው ደግሞ በከፍተኛ ገንዘብ በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓተ ትምህርት የመማር ማስተማሩን የሚሰጥበት ነው:: ምንም እንኳን ትምህርት ቤቱ ኮሚዩኒቲ በመሆኑ ነዋሪነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ ግሪካውያንን እንዲያስተምር ቢጠበቅም ዳሩ ግን ተግባሩ ከዚህ የተለየ ነው::
ልጆቻቸው የውጭ ትምህርት ዕድል እንደሚያገኙ በመንገር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚሰበስባቸውን ልጆች አዳሪ ትምህርት ቤት እንደሚያስገባ በዘገባው መግለፃችን ይታወሳል:: በአዳሪ ትምህርት ቤቱ የሚገቡት ተማሪዎች እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በግሪክ ቋንቋና ሥርዓተ ትምህርት በመሆኑ የትምህርት ቆይታቸውን ሲጨርሱ በኢትዮጵያ ውስጥ በየትኛውም ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ገብቶ የመማርም ሆነ የመቀጠር ዕድል አያገኙም:: አንዳንዶቹም የትምህርት ዕድሉ እንደማይሰጣቸው ነበር የገለጹልን:: በዚህም የግሪካውያኑ የቤት ሠራተኞች፣ የጽዳት እንዲሁም የወሲብ ባርያዎች እንደተደረጉም በዘገባው መካተቱ ይታወቃል:: በተያያዘ የአገሪቱ ባህልና እሴት በማይፈቅድ ሁኔታ ወንዶቹ ጭምር በግሪካውያኑ ቄሶችና መምህራን እንደሚደፈሩና ትምህርት ቤቱ ግብረሰዶምም እያስፋፉ መሆኑን ተጠቂዎች ለተቋማችን አቤቱታቸውን አቅርበው ነበር:: ዘርን መሠረት ያደረገ የቀለም መድልዎ እንደሚስተዋልም በመምህር የቀረበ ቅሬታ በዘገባው ተስተናግዷል::
ቅሬታውን ተቀብለን ባደረግነው ማጣራት ትምህርት ቤቱ አራት የተለያየ ማህተም እንደሚጠቀም ደርሰንበታል:: ቅሬታዎቹ ላይ ምላሽ የሰጡን የትምህርት ቤቱ ተወካይ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት እንደማይፈልጉ በመግለጽ፤ ከፆታዊ ትንኮሳው ጋር ተያይዞ የተነሱትን ጉዳዮች ግን አስተባብለው ነበር:: ቄሶቹም ወደ ትምህርት ቤቱ እንደማይመጡ ቢናገሩም በግቢው ያገኘናቸው ሠራተኛ ግን ወጥ ቤት ድረስ እንደሚገቡ ብሎም የግሪካውያኑ መምህራንና የተማሪዎቹ ማደሪያ በአንድ
የአዋቂ እርምጃ እንደማይራራቅ አሳይተውናል::
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጠው የትምህርት ሚኒስቴር ቅሬታውን እንደሚያውቀው በመግለጽ፤ መፍትሔ እንደሚሰጥ አሳውቆ ነበር:: ይሁን እንጂ ዳግም ጉዳዩ ከምን ደረሰ? ሚኒስቴሩ የወሰደው እርምጃስ አለ ወይ? በሚል በሠራነው ዘገባ ችግሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲገባበት መጠየቁ ተገልፆልን ነበር:: አልያ ግን በትምህርት ቤቱ ላይ እርምጃ መውሰድ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ሊያጠለሽ ይችላል የሚል ምላሽ አግኝተናል:: በተያያዘ ትምህርት ቤቱ በሌላኛው ማለትም በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ሥርዓት ትምህርት መሠረት መማር ማስተማሩን በሚሰጥበት የእንግሊዝኛ ክፍሉ ከአንድ ተማሪ ከ30 ሺህ ብር በላይ የሚሰበስብ ቢሆንም ግብር ከፋይ አለመሆኑንም መዘገባችን ይታወሳል::
ግሪክ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ‹‹ዜጎች በአገራቸው መማርም ሆነ መሥራት እንዳይችሉ በሚያደርግ ትምህርት አሰጣጥና በግብረሰዶም ተግባር ላይ ተሰማርቶ ትውልድ እያመከነ ነው›› በሚል ቅሬታ እንደቀረበበትና ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም ‹‹ትምህርት ቤቱ ትውልድ ገንቢ ወይስ አምካኝ?›› በሚል ርዕስና ጥቅምት 26 ቀን 2012 ዓ.ም ደግሞ ትምህርት ሚኒስቴር መፍትሔ እንደሚሰጥ የገባው ቃል ከምን ደረሰ? በሚል መስተናገዱ ይታወሳል:: በወቅቱ የቀረበበትን ቅሬታና አራት የተለያዩ ማህተሞች የመጠቀሙን እንቆቅልሽ በተመለከተ የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ያስተባበለ ሲሆን፤ ትምህርት ሚኒስቴር ግን በትምህርት ቤቱ ተገኝቶ እንዳረጋገጠና የቅሬታውን ተገቢነት አምኖ መፍትሄ እንደሚሰጥ ቢገልጽም የተወሰደ የመፍትሔ እርምጃ አለመኖሩን በተከታታይ ዘገባችን አውጥተናል::
ለጋዜጠኛ ፍዮሪ ተወልደ የፍረዱኝ አምድ አዘጋጅ
አዲስ ዘመን ዕለታዊ ጋዜጣ
አዲስ አበባ
ነሐሴ 1 ቀን 2011 ዓ.ም በጋዜጣው ፍረዱኝ አምድ ላይ ‹‹ትምህርት ቤቱ ትውልድ ገንቢ ወይስ አምካኝ›› በሚል ርዕስ በግሪክ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ላይ የተፃፈውን ተመለከትኩኝ:: እኔም አንዱ የትምህርት ቤቱ ቤተሰብና ጉዳዩ የሚመለከተኝ በመሆኑ ደጋግሜ ባነበብኩት ቁጥር ጥያቄ እየጫረብኝ ስለተቸገርኩኝ ነው:: የአምዱን አዘጋጅና ፀሐፊ በማመስገንና በማድነቅ ለግንዛቤ ወይም ለተጨማሪ ሥራ የሚነሳሳ ሀሳቤንና ጥያቄ አዘል አስተያየቴን እንደሚከተለው ላቅርብ::
አስተያየቴ ከቅሬታ አቅራቢዎች ይልቅ ከትምህርት ቤቱ ተወካይ እና መንግሥትን በመወከል ማስተባበያ ከሰጡት የትምህርት ሚኒስቴሩ ኃላፊ ሃሳብ ላይ ያተኩራል::
- እንደ መግቢያ
ከርዕሱም ሆነ ከጽሑፉ ይዘት እንደተረዳሁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በደል ደረሰብን ከሚሉት በላይ በዜጎች እና በሀገር ላይ የትምህርት ቤቱ አመራር እየሠራ ያለውን ከፍተኛ ወንጀል በጥልቀት ያሳየ ይመስላል:: በወጣት አበበ ሥም የመጣውን የትምህርት ዕድል ለሌላ ሰው መሰጠቱ ምን ያህል በርካታ ዕድሎች በሽያጭ እና በሀብታም ልጅ ቅያሬ የተከናወነ ይመስለኛል:: በትምህርት ቤቱ ብልሹ አሠራር መሠረት ዜጎች በተለይም ወጣቶችና ሕፃናት ለትምህርት ቤቱ አመራሮች የጥቅማ ጥቅም ማሟያ እንደሚያገለግሉ ተረድቻለሁ::
የባለጉዳዩን አበበን ችግር እንደ አበበ ብቻ አላየውም:: ከሙያዬ አንፃር በዜጎች ላይ ያለውን ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነልቦናዊና ሰብአዊ እንዲሁም ሞራላዊ ቀውስ ስብዕናን የሚያሳጣ ስለሆነ በቀላሉ የሚታይ አይደለም:: ሰብአዊ ፍጡር በገዛ ሀብቱና ሀገሩ እያስራቡ ውሾቻቸውን መመገባቸው በምሬት ለወሲብ ንግድ ተዳዳሪነት የተዳረጉ እህቶቻችንን ስናስብ በእኛ ላይ የሞራል ጥያቄ የሚያስነሳ ሲሆን፤ ሥልጣን አልባ ስለሆንን ጥያቄያችንን ለአምዱ ከመላክ ውጪ አማራጭ የለንም:: ምናልባትም በተለየ መልኩ የሚቀርብላቸው ምግብ ጤናማነቱ መታየት አለበት:: መድኃኒትም ሊሆን ይችላል-የሚያመክን መድኃኒት::
በመምህሩ የቀረበው በትምህርት ቤቱ የሚታየው ቀለምን መሠረት ያደረገ ልዩነትና ኢ-ባህላዊ ተግባር (ግብረሰዶም) ከወንጀል ያለፈ ወንጀል ነውና አቅልሎ ማየት አይገባም:: ይህን ክፉ ተግባር በቀላሉ ለመፈፀም ከመዋቅሩና ከባለሥልጣን ጋር ባለው ግንኙነት ተማምኖ ስለሆነ የምርመራ ጋዜጠኝነት ሥራ ያስፈልገዋልና ዓይናችን ሁኑ:: በአጠቃላይ የጽሑፉ ሂደት የግለሰቦች አቤቱታ ብቻ ሳይሆን የአገርን ክብር የሚነካና ሰንካላ ዜጎች ፈቅደው እዚህ ያደረሱት በመሆኑ የአሁኑን አቤቱታ መሠረት በማድረግ አገራዊ ክብርን መመለስ አለበት:: አጋጣሚው ብዙ የሚያሳይ ሲሆን፤ የግብረሰዶም ሰንሰለት አንዱ ሊሆንም ይችላልና ችላ ሊባል አይገባም:: በዝርዝር መታየት አለበት::
- ትምህርት ቤቱ የሰጠው ምላሽ
/ማስተባበያ/
እንደ ምንም በተደጋጋሚ አነበብኩት:: በአንድ ጉዳይ ላይ ማስተባበያ እንዴትና መቼ እንዲሁም ለማን በምን መልኩ እንደሚሰጥ ሞያዊ አካሄድ ወይም መመሪያ ይኑረው አይኑረው ባላውቅም በተለምዶ ዲፕሎማሲዊ /ትህትናዊ/ የራስን ስህተት መከላከያና መሸፈኛ አንደኛው መንገድ መሆኑ ይገባኛል:: ይሄ የሚሆነው እኛ ራሳችን ያለን ዕውቀትና የጉዳይ መጠንና ደረጃ ከአድማጩ /አንባቢው/ ተመልካቹ አስተሳሰብ ጋር ተዛምዶ ግምት ውስጥ በማስገባት ይመስለኛል:: እና ግለሰባዊ ስብእናና ህሊና ወሳኝ ቦታ አላቸው:: በዚህ መግቢያነት የትምህርት ቤቱ የሰው ሀብት አስተዳደር የሰጡትን ስለመከተው አንድ የሰው ሀብት አስተዳደር ሞያና ኃላፊ ምን እንደሚጠበቅበት-በተለይ በትምህርት ሴክተሩ- ያለበትን ድርብ ኃላፊነት ስለምረዳ ኃላፊው የሚመሩት ተቋም ብቻ ሳይሆን ያለባቸውን ኃላፊነት በውል ተረድተውታል ወይ የሚል ጥያቄ አነሳለሁኝ::
ተረድተውታል ከተባለ ወደዚህ ቃለ መጠይቅ ሲመጡ ከዋና ወንጀለኞቹ ጋር ተነጋግረው ምን ማለት እንዳለባቸው መመሪያ ወይም የጉርሻ ተስፋ ይዘው እንደመጡ ለመገመት አያስቸግርም:: በእኔ ዕይታ ግን እርሳቸው የሰጡት አጠቃላይ ሀሳብ ትምህርት ቤቱን ወንጀል በግልጽ የሚሳይ መሆኑን ማረጋገጥ ይቻላል:: ከጽሑፋቸው በመነሳት ያላቸውን የሞራልና ጉዳዩን አቅልሎ ማሳየት መሞከር የጉዳዩ ተካፋይ መሆናቸውን በብዙ መልኩ ጠቁመዋል:: ያላቸው የሦስት ዓመት ቆይታ ለትምህርት ቤቱ ሳይሆን ለእርሳቸው ምን እንዳተረፈላቸው መገመት ይቻላል::
ትምህርት ቤቱ ፍቃድ ያገኘበትና ግብር የሚከፍልበት ስያሜ መለያየቱን እያዩ ግንኙነት የሌለው ብለው ሲነግሩ የጤና ነው ለማለት ያስቸግራል:: ያለማወቅም አይደለም – ጥቅምና መመሪያ የጋረደው የሞራል ውድቀት ወይም ከላይ እንዳልኩት ቦታውም ሆነ ለትምህርት ቤት የማይገባ ኃላፊነት ይመስለኛል:: እባክዎ ሰው ሐብት አስተዳደሩ (Human resource manager) ኃላፊነት ከበይነ መረብ (ኢንተርኔት) ትንሽ ያንብቡ:: ሙያው ትልቅና ዋና በመሆኑ – መቅለል የለበትም ባይ ነኝ:: እድሩ የትምህርት ቤቱን ሠራተኞች እስከያዘ ድረስ ከትምህርት ቤቱ ጋር አይገናኝም ከማለት ለመማር ማስተማሩና ለሠራተኞች ጤናማ ግንኙነት ያለውን ድርሻ በመረዳት አዎንታዊ ሥራ ቢሰራ ጥሩ ነበር::
ባልናገር እመርጣለሁኝ አባባላቸው ተመችታኛለች:: ለምን ብዬ ላጥቃቸው:: ለምን? 80 ጡረተኞችን እየደገፈ ነው የሚለው አባባል፤ ለትርፍ አልተቋቋምንም ግብረሰናይ ሥራ እየሰራን ነው፤ በሚል ያቀረቡት ሀሳብ ለወጣቱ የመጣው የትምህርት ዕድል ለሌላ ለምን ተሸጠ ብዬ እሟገታለሁኝ:: ከሁሉም በላይ ‹‹…›› ኢትዮጵያውያን ይህን ዕድል አግኝተው ቢማሩ ምን ችግር አለው …›› የሚለው አባባላቸው:: አንድ ትምህርት ተቋም ለምን ዓላማ እንደሚቋቋም እንዴት እንደሚመራ በምንም መልኩ አያውቁትም:: የትምህርት ቤቱ ዋነኛ ችግር ምንጭ የአስተሳሰብና የዕውቀት መማሪያ ከመሆኑ በተጨማሪ ማስተማርን እንደ ሽፋን በመጠቀም ለሌላ ዓላማ እንደሚሰራ ለመረዳት አይከብድም:: በተለይ መምህሩ የሰጠው ሀሳብ ይህን የሚያሳይ ይመስለኛል::
በጣም በጣም የሚገርመው ‹‹… የደረሰ ልጅ የደረሰች ልጅን ሊከጅል ይችላል:: ይህ ደግሞ ተፈጥሯዊ ነው…›› ያሉት አባባል የትምህርት ቤቱን አስተሳሰብና ኃላፊዎቹ እየሄዱበት ያለውን አቅጣጫ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል:: እንዲያውም ይፋ የሆነ ወሲብ ንግድም ሊኖር ይችላል ባይ ነኝ:: በተረፈ የደረሰች ልጅ እንደማያሳልፉ ጥሩ ማሳያ ነው:: ይሄ ልምድና አስተሳሰብ ወደ ያልደረሰች ልጅ እንደማይሄድም ማረጋገጫ የለም:: ስለሆነም አባባሉ ሊተነተንና ሊፈተሽ ይገባል:: በእርግጥ የትምህርት ሚኒስቴር ኃላፊው የፆታ ጥቃት ማስረጃ የለውም በማለት በትምህርት ቤቱ ሥም የሰጡት ማስተባበያ ሲታይ – ጉዳዩ ችላ የሚባል አይደለም:: በተለይ ሴት ልጅ ያላቸው ወላጆች፤ አሁን አሁን መስቀል እየያዙ ወንጀል ከሚሠሩት አንዱ የቤተክርስቲን መታወቂያ ይዘው ስለሆነ ባይገርምም ከትምህርት ቤቱ ጋር መያያዙ ለብዙ ትምህርት ቤቶች ጥሪ ይመስለኛል:: የባህልና ቱሪዝም እንዲሁም የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ጉዳዩን ባያልፉት ጥሩ ነው::
- ከትምህርት ሚኒስቴር በኩል
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ኃላፊ የሰጡት ምላሽ ባለፈው በሸገር ሬድዮ ዜና ላይ የሰማሁት በመሆኑ ባይደንቀኝም:: የበለጠ አሳስቦኛል:: ኃላፊው ለተነሳው ወንጀል በሙሉ የሰጡት ምላሽ ዕውነት ጤናማ ነውን ያስብላል:: ‹‹በችኮላ የሚወሰድ እርምጃ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ሊያበላሽ ይችላል…›› ኢትዮጵያዊ ዜጎችን እያመከኑ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖችን በሕግ ብሎ መጠየቅ እንዴት ከአገራት ጋር ይያያዛል:: የአገራችን ግንኙነት ከወንጀል ጋር ከተያያዘ ኤርፖርት በሀሽሽ የሚያዙት የውጭ አገር ሰዎች ለምን ይታሰራሉ? ነው ወይስ አንባቢ ምንም አይረዳም ወይም ጋዜጠኛዋ አያውቁም ነው:: እንኳን የራሱ አገር ዜጎች የሌሎች አገሮች ዜጎችን በትምህርት ተቋማት ውስጥ አደጋ ከደረሰባቸው የማዳንና የመጠበቅ ግዴታ አለበት:: ይህን ሳያውቁት አይቀሩም ከጀርባቸው ምክንያት ከሌለ – በዘመድ የተያዘ ኃላፊነት ስለሆነ የአቅምና የሞራል ችግር ወይም ከትምህርት ቤቱ የተበረከተ ጉርሻ ያስያዘው ህሊና አልባ ዳኝነት – ዘመኑ ጥቅም ህሊናንና ሞራልን ስለሚያሳጣ ጉዳዩን የያዙት የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በጥልቀት ሊይዙት ይገባል:: የኃላፊው የጥቅም ግንኙነት ያለውን መመሪያም ሆነ አገሪቱን ሕግ አያስጠብቅም ዜጎችንም ለማዳን ሞራል ያንሳቸዋል::
በተረፈ ወጥነት ያለው መመሪያና የተባለው የቅንጅት ሥራ አስፈላጊ ቢሆንም በዚህ መድረክ እንደ መሸሻ የቀረበ ይመስለኛል:: ምክንያቱም ያሉትን ለመፈጸም ያለባቸው ኃላፊነት ያስገድዳቸዋልና ለምን አልፈፀሙም የሚል ጥያቄና ተጠያቂነት መከተል አለበት- ለተነሳላቸው የወሲብ ትንኮሳ ጥቆማ ጉዳዩን ለፖሊስ ለምን አልጠቆሙም? ማጣራት ሥራቸው ካልሆነ ጉዳዩን ለሚመለከተው ማድረስ ነበረባቸው:: በእኔ እይታ ያላቸው የጥቅም ግንኙነት ይህን ለማድረግ እንደማያስችላቸው ነው የተረዳሁት:: ትምህርት ቤቱ አይዞህ ባይ ባለሥልጣናት ስለነበሩትና ስላሉት ይመስለኛል ይህን ያህል ክፉ ሥራ የሠራው::
ለመሆኑ፡ ትምህርት ቤቱ ነገረ ፈጅ (የሕግ ሙያተኛ) የለውምን? ካለውስ ሥራው ምንድን ነው? ድርጅቱን ለወንጀል በማነሳሳት የሕግ ድጋፍ መስጠት ወይስ ወደ መጥፎ ነገር እንዳይሄድ ማድረግ? ካለ ይሄም አካል መጠየቅ አለበት:: ይህን ያህል ወንጀል ሲፈፀም ለምን ዝም አለ? የፍትሐ ብሔር ሕግ እኮ ሰዎች ማድረግ የሚገባቸውን እንዲያደርጉ ማስገደድ ነው::
- ማጠቃለያ
ጉዳዩ በቀላሉ የሚታይ ስላልሆነ የጋዜጣውም ሆነ የአምዱ አዘጋጆች በጥልቀት እንዲመለከቱት ጥያቄ አቀርባለሁኝ:: ከተጠቀሱት ውጪ የእፅ/ የሀሺሽ ንግድ እና ሕገወጥ የብር ምንዛሬ ወንጀል ውስጥ እጃቸው ሊኖርበት ይችላል ብዬ እገምታለሁ:: የትምህርት ቤቱ አመራሮች ከባለሥልጣን ጋር ባላቸው ትስስር ብዙ በይፋ የማይታዩ በማስረጃ የማደገፉ ወንጀሎች እየሠሩ ሊሆን ስለሚችል ሰንሰለቱን የመበጠስ ሥራ ሊሠራ ይገባል ባይ ነኝ::
የትምህርት ቤቱ የሠራተኞች ማህበር በሕይወት ካለ ትምህርት ቤቱን ለማዳን ወላጆችን በማካተት የራሳቸውን ሥራ መሥራት እንዳለባቸው ይሰማኛል:: ለነገሩ የትምህርት ቤቱ አመራር ሠራተኛ ማህበሩን የክፉ ሥራ ተባባሪ ካልሆንክ በማለት እንዳሰናከለው ከጽሑፉ መረዳት ይቻላል:: ይሁን እንጂ ሁሉም ወላጆች በተገኙበትና በተሳተፉበት የትምህርት ቤቱ ጉዳይ በድጋሚ መታየት አለበት:: የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የሠራተኛው ፌዴሬሽንም ስለሠራተኛው መጠየቅ አለባቸው::
ከሁሉም በላይ መንግሥት ይሄ ክፉ ሥራ ያልገባበት እንደሌለና ከግልና ከውጭ አገር ዜጎች ጭምር እጃቸው እንዳለበት የሚያሳይ ሲሆን፤ በውጭ አገር ዜግነት ሰበብ የእኛው አገር ባለሥልጣናት እየባለጉ በመሆኑ በየቦታው የሚቀመጡት ባለሥልጣናት ከውሸት ዲግሪያቸው በተጨማሪ የሞራልና የስብዕና ዲግሪያቸው መስፈርት እንዲሆን እጠይቃለሁኝ::
አመሠግናለሁ ታዛቢ ወላጅ
ግልባጭ፡ ለትምህርት ሚኒስቴር
ለግሪክ ኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
ፍዮሪ ተወልደ