የከተማ ውበት ከሆኑ መሰረታዊ ነገሮች መካከል አንዱ ጽዳት ነው። ጽዳቱ ያልተጠበቀ ከተማ ለነዋሪዎቹ የጤና ጠንቅ ከመሆን ባለፈ ለኑሮም ሆነ ለመልክም ገጽታ ጥሩ ምሳሌ አይደለም። ከዚህ አንጻር የእኛዋ አዲስ አበባ ከተማ ለነዋሪዎቿ ጽዱና ምቹ ትሆን ዘንድ የተለያዩ ጥረቶች ይደረጋሉ። እነዚህ ጥረቶች በእርግጥ ዋል አደር እያሉ ፍሬ የሚያፈሩ ቢሆንም አሁንም የከተማዋ ጽዳት ብዙ ሊወራለት እንዲሁም በርካቶች ሀላፊነታቸውን ሊወጡለት የሚገባው ጉዳይ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት ከአካባቢ አካባቢ የመለያየቱን ያህል ስራውም ጠንካራና ደካማ እንደሆኑ በርካታ ማሳያዎችም አሉ።
ኢትዮጵያ የአካባቢ ተፈጥሮ ደህንነትን የሚያስጠብቁ ደንቦች፣ ሕጎች እና መመሪያዎችን በዝርዝር ያወጣች ሀገር ብትሆንም የደረቅም ሆነ ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ጉዳይ ዛሬም አነጋጋሪ ነው። በፋብሪካ አካባቢ የሚገኙ ወንዞች በፍሳሾች መበከላቸው፤ ፕላስቲክና በካይ ኬሚካሎች በየቦታው መጣላቸው በአካባቢው ተፈጥሮ ላይ ከሚያደርሱት ብክለት በተጓዳኝ የጤና ጠንቅም መሆናቸው ይነገራል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ከመኖሪያ ቤቶች፣ ከተቋማት እና ከልዩ ልዩ ድርጅቶች የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በማሰባሰብ፣ በማጓጓዝና በማስወገድ እንዲሁም በአስፓልት መንገዶች ላይ የሚመነጨውን ደረቅ ቆሻሻ በሰው ኃይልና በዘመናዊ ማሽነሪ ታግዞ በማፅዳት ከተማዋን ፅዱ፣ ውብና ለኑሮ ተመራጭ እንድትሆን የማድረግ ጥረቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ሆኖም የፅዳት ጉዳይ በተቋማት ጥረት ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ ሁሉም የበኩሉን ይወጣ ዘንድ ደግሞ ግድ የሚል ነው። ደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ ከተያዘ ሀብት፤ ካልተያዘ ደግሞ የጤና ጠንቅ በመሆኑ ከቤትም ሆነ ከድርጅት የሚመነጩ ደረቅ ቆሻሻዎች አካባቢን ሳይበክሉ መወገዳቸውንም ማረጋገጥ እንደ ዜጋ ከሁላችንም የሚጠበቅ ሀላፊነት ነው።
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አደጋ አንጻር ደግሞ ራስን ቤትንና አካባቢን ማጽዳት አስፈላጊ በመሆኑ እኛም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ ከሆኑት ከወይዘሮ ሀይማኖት ዘለቀ ጋር እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ዙሪያ ቃለ ምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው የከተማዋን ጽዳት ከማስጠበቅ አንጻር የተሰጠው ተግባርና ሀላፊነት ምን ይመስላል?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ኤጀንሲው የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ከተማዋን ጽዱ እና ውብ የማድረግ ሀላፊነት የተጣለበት ነው። ከዚህ አንጻር የከተማዋን ደረቅ ቆሻሻ በአግባቡ ማንሳት ደግሞ የሚመለከተው ስራ ነው። ከ 10 ሩም ክፍለ ከተሞች እስከ 121 ወረዳዎች ድረስ በመውረድና መዋቅር እንዲኖር በማድረግ በየቀኑ ከመንገድ፣ የቤት ለቤት፣ የተቋማትንና የድርጅቶችን ቆሻሻ በማንሳት በአጠቃላይ ከተማዋን ጽዱ የማድረግ ስራ ይሰራል።
አዲስ ዘመን ፦ ያለበት ሀላፊነት ትልቅና ብዙ ነው፤ ግን ምን ያህልስ ተሳክቶለታል ማለት ይቻላል?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ከቤት፣ ከመንገድ፣ ከተቋማትና ከድርጅት የሚሰበሰበው ቆሻሻ በየቦታው ወይም በየጣቢያዎቹ ተከማችቶ ማጓጓዝ ይጠበቅብናል ፤ አጓጉዘንም ረጲ የሀይል ማመንጫ በማድረስ እስከ 60 በመቶ ያለው የከተማዋ ቆሻሻ ወደ ኤሌክትሪክ ሀይልነት እንዲለወጥ እናደርጋለን። በተለይም ከመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ በየወሩ ከ 60 በመቶ በላይ አዲስ አበባ ላይ የሚመረት ቆሻሻ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሀይል ስር በሚተዳደረው ረጲ የሀይል ምንጭ እየሆነ ነው።
ቀሪው 40 በመቶ ደግሞ እዛው ረጲ ላይ ባለው 19 ሄክታር መሬት ላይ የማስወገድ ስራ ይሰራል። እዚህ ላይ ግን ከዚህ 19 ሄክታር መሬት የተወሰነውን ለአረንጓዴ ልማት የማዋል ስራም እየተሰራ ነው። እንደ አጠቃላይ ሲታይ ግን ተቋሙ “ቆሻሻ ሀብት ነው” ፤ በሚል መርህ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በእያንዳንዱ ግለሰብ የሚመረተውን ቆሻሻ በመልክ በመልኩ በመለየት ለሚፈለገው ዓላማ የማዋል ተግባርም ያከናውናል።
አዲስ ዘመን ፦ ቆሻሻን የመለየት ስራው በምን መልኩ ነው የሚከናወነው ፤ ተለይቶስ በምን ዓይነት ጥቅም ላይ ይውላል ?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ለምሳሌ የውሃ መያዢያ ኮዳዎች፣ ፌስታል፣ ማዳበሪያ፣ ጀሪካን፣ የተለያዩ የመዋቢያና የጽዳት ምርት መያዢያ እቃዎች፣ ጠርሙስና ብርጭቆ፣ ወረቀቶች፣ ብረታብረትና ኤሌክትሮኒክሶች ይለያሉ። ይህንንም የልየታ ስራ ለእያንዳንዱ ግለሰብ ግንዛቤው እንዲኖረው እያደረግን ሲሆን፤ አሁን ባለው ሁኔታ በተለይም የፕላስቲክ ውሃ መያዣ ኮዳዎችን በመሰብሰብና መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እስከማግኘት ተደርሷል።
አዲስ ዘመን ፦ የፕላስቲክ ውሃ መያዣዎችን በመሸጥ የተገኘው ገቢ ይታወቃል?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ አዎ ይታወቃል የውሃ መያዣ ኮዳዎችን አሰባስቦ ለውጭ ካምፓኒዎች በመሸጥ በተሰራው ስራ በዓመት እስከ 99 ሚሊየን ብር ገቢ
ማግኘት ተችሏል። በሌላ በኩልም ከሚበሰብሱ ቆሻሻዎች ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ማምረት ተችሏል። ይህ ደግሞ 121ዱም ወረዳዎች በየቦታው ሳምፕሎችን በመውሰድ የተሞክሮ ልውውጥ እንዲያደርጉና ሁሉም በየቤቱ የሚበሰብሰውን ከማይበሰብሰው በመለየት ሁሉም ጥቅም እንዲሰጡ የማድረግ ስራ እንዲሰሩ እየተደረገ ነው። በዚህም 588 ቶን ማዳበሪያ (ኮምፖስት) ማግኘት ተችሏል።
ይህ ደግሞ አሁን እየተከናወነ ላለው ለሸገር ፕሮጀክትም ተፈጥሯዊ ማዳበሪያን በማቅረብ አስተዋጽኦ እያደረገ ለዜጎችም የስራ እድል እየፈጠረ ነው።
አዲስ ዘመን፦ በየመንደራችን ከምናያቸው ወጣቶችና ሴቶች ጀምሮ በየደረጃው የተፈጠረውን የስራ እድልን እንዴት መግለጽ ይቻላል? ምን ያህሉስ ውጤታማ ናቸው?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦አሁን ላይ ወደ 50 የሚጠጉ የግል የጽዳት ድርጅቶች ተፈጥረዋል፤ እነዚህ ደግሞ የራሳቸውን የሰው ሀይል ቀጥረው ያሰማሩ በመሆናቸው ቆሻሻን ለማመላለስ የሚጠቅማቸውን ወደ 126 ኮምፓክተር ይዘው ነው ወደ ስራው የገቡት። በተጨማሪም 78 ማህበራት 6ሺ 500 በላይ አባላትን በማቀፍ ቆሻሻን ቤት ለቤት በመሰብሰብ ስራ ላይ የተሰማሩ አሉ።በመንገድ ጽዳት በኩል ከ 4ሺ 600 በላይ ሰራተኞች አሉ። ከዚህ አንጻር ዘርፉ በርካታ የሆነ የሰው ሃይል የተሰማራበት ነው።
አዲስ ዘመን፦ ኤጀንሲው በርካታ የሰው ሀይልን የሚይዝ ከሆነ በዓመት ወደስራ እንድታሰማሩ የሚሰጣችሁ የስራ አጥ መጠን ይኖራልን? ካለስ በዚህ ዓመት ምን ያህል ተሰጥቷችሁ ምን ያህሉ ላይ ውጤታማ ሆናችሁ?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ኤጀንሲው ከተጠበቀው በላይ ዜጎችን ወደስራ እያስገባ ነው። ለምሳሌ ኮምፖስት በቤታቸው የሚያመርቱ አባወራና እማወራዎችን ወደ ስራ ማስገባት በቅርብ የተጀመረ ነው ግን ከፍተኛ ውጤት ታይቶበታል። ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልም እንደዚያው።
በከተማ አስተዳደሩ በዓመት የተቀመጠልን አንድ ሺ ያህል ዜጎችን ወደስራ ማስገባት ቢሆንም ኤጀንሲው እቅዱን ሙሉ በሙሉ ከግብ አድርሶታል። በተለይም በዚህ ዓመት ከተቀመጠው በላይ ማሳካት ይቻል ነበር ግን በዓለም ብሎም በአገራችን ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ የፈጠረው ስጋት በተለይም መልሰን ጥቅም ላይ እያዋልን ወደውጭ በምንልካቸው ቆሻሻዎች ላይ ተጽዕኖ በማሳደሩ የሰው ሀይሉንም ማሰማራት አልቻልንም።
ሌላው በዘርፉ ላይ ከመንግስት ሀላፊዎች ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ሁሉ ግንዛቤያቸው ውስን ነበር፤ የሚያውቁት አንድ ነገር ቢኖር ቆሻሻ ከቤታቸው፣ ከቢሯቸውና ከድርጅታቸው መወገዱን ብቻ ነው።
በመሆኑም ኤጀንሲው ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የገንዛቤ ፈጠራ ስራዎችን አከናውኗል።
ለምሳሌ የስራ እድል ፈጠራ አምጡ ሲሉን የሚያስቡት የመንገድ ጽዳቱን ወይም ቆሻሻን በመሰብሰብ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ብቻ ነው፤ ከዚህ በላይ ሊታያቸው አይችልም።ነገር ግን በዘርፉ ያለን ሰዎች ደግሞ ቆሻሻ ከመሰብሰብም በላይ ሀብት ሊሆን የሚችል ነው።
አዲስ ዘመን፦ እናንተ ለመንግስት የስራ ሀላፊውም ይሁን ለነዋሪው ግንዛቤ መፍጠር ተችሏል?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ምናልባት ይህንን ጉዳይ የሁሉም የማድረግ ላይ ኤጀንሲው ውስንነት አለበት። ከዛ በተጨማሪ ግን የኪነጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም ሌሎች ስራውን እየረዱና የአቅማቸውን ያህል ግንዛቤውን እያሳደጉልን አይደሉም። ከዚህ አንጻር ህብረተሰቡ ቆሻሻ የማይጠቅም እንደሆነ እያሰበ ነው፤ ኤጀንሲው ግን ቆሻሻ ቆሻሻ ብቻ ሳይሆን ሀብት ነው በሚል እየሰራን ከመሆኑም በላይ በየቦታው እናቶችን፣ እንዲሁም ወጣቶችን በማሳተፍ ላይ ነው። በዚህ ተሳትፎ ውስጥ ብዙ ወጣቶች ከቆሻሻ የተለያዩ አስገራሚ የሆኑ የፈጠራ ስራዎችንም ይዘው ሲወጡ እየተመለከትን ነው።
አዲስ ዘመን፦ የአገልግሎት ጊዜያቸውን የጨረሱ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎችና የውሃ ኮዳዎች ከዚህ ቀደም እየተሰበሰቡ ለመልሶ አገልግሎት ወደ ውጭ ይላኩ ነበር፤ አሁን ደግሞ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የውጭ ንግዱ ቀርቷል፤ ታዲያ እነዚህ አካባቢን ለመበከል ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ቆሻሻዎች የማስወገዱ ስራ ምን ያህል በጥንቃቄ እየተከናወነ ነው?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ እውነት ነው እነዚህ ቆሻሻዎች ለአካባቢ ጥበቃ ምቹ ያልሆኑና በካይነታቸውም ከፍተኛ የሆነ ነው፤ ግን ተፈላጊነታቸው በውጭ አገር ብቻ ባለመሆኑ አገር ውስጥም ገበያ ስላላቸው የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፉ እቃዎች በመጠቀም የተለያዩ የፈጠራ
ስራዎችን የቤት ውስጥ መገልገያና ሌሎች ቁሳቁሶችን እየሰሩና እየተጠቀሙ ላሉ ይሸጣሉ። ከዚህ አንጻር በአካባቢ ላይ ተጽዕኖ የሚያደርስበት ሁኔታ በእጅጉ ቀንሷል። ስለዚህ አሁን ላይ ስለ ቆሻሻ ጥቅም ያልገባው አለ ለማለት የማያስደፍር ከመሆኑም በላይ በስራው ላይ የተሰማሩትም ቢሆኑ የበለጠ ገቢን ለማግኘት በማሰብ በተገቢው ሁኔታ እየሰበሰቡ ነው።
አዲስ አበባ፦ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገዱ የከተማዋን እድገትና የህዝቧን ቁጥር ያማከለ ስላለመሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ በእርግጥ ይህ ጥያቄ ለከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች መቅረብ ያለበት ነው። እኛም በተደጋጋሚ እንደ ችግር የምናነሳው በመሆኑ። ከዚህ በፊት ሁለት የቆሻሻ ማስወገጃዎች በሰንዳፋና በረጲ ነበሩ። አሁን ግን ይህንን ሁሉ ችግር እየሸፈነ ያለው የረጲ ቆሻሻ ማስወገጃ ብቻ ነው። ሰንዳፋ ተዘግቷል ለምን ተዘጋ ማለት አይቻልም፤ የህዝብ ጥያቄ ነበረበት፤ የአዲስ አበባ ቆሻሻ እዛ ሄዶ መጣል የለበትም ተባለ፤ ትክክልኛ ጥያቄ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ተዘግቷል። አሁን እንግዲህ አንድ ለእናቷ ሆና ለከተማዋ ያለችው ማስወገጃ ረጲ ብቻ ናት። ይህ ደግሞ እንደተባለው የህዝብ ቁጥሩና የከተማዋን እድገት የሚመጥን ካለመሆኑም በላይ በተለይም የሀይል ማመንጫው አንድ ነገር ሆኖ ቢቆም የከተማው ቆሻሻ ከፍተኛ ችግር ላይ ነው የሚወድቀው።
ረጲ ላይ ደግሞ ሁሉም እንደሚያውቀው ማስወገጃው መንሸራተት አጋጥሞት በበርካታ ሰዎች ላይ አደጋ ማድረሱ ይታወቃል። በእርግጥ ይህንን ሁኔታ ለመቀየር የኢትዮጵያ መንግስት ከጃፓን መንግስትና ከተባበሩት መንግስታት (ዩኤን ሀቢታት) ጋር እየተሰራ ባለው ስራ መንሸራተቱን ለመቀነስ ተችሏል። አሁን ላይም ለነዋሪዎች ስጋት የሚሆንበት ሁኔታ ተቀይሯል። ይህም ቢሆን ግን አሁንም የሀይል ማመንጫው በሆነ ቴክኒካል ችግር ስራውን ቢያቆም ምንድን ነው የሚኮነው እያልን እናስባለን፤ በቅርቡም የከተማው ምክር ቤት በስፍራው ጉብኝት ሲያደርግ ጠይቀናል፤ በዚህም ሌሎች አማራጭ ማስወገጃ ቦታዎች ሊኖሩ ይገባልም ብለናል። እንደ ጃፓን ያሉ አገሮች ከመቶ በላይ የማስወገጃ ጣቢያዎች ያሏቸው ናቸው፤ የአዲስ አበባ ከተማን ቆሻሻ በአንድ ማስወገጃ ጣቢያ መቋቋም በጣም ከባድ ስለሚሆንና ወደፊትም ችግር ውስጥ መግባት ስለሚመጣ እንዲታሰብበት እየወተወትን ነው።
አዲስ ዘመን፦ የከተማ አስተዳደሩ ምላሽ ምንድን ነው?
ወይዘሮ ሀይማኖት ፦ ምላሹ ጥሩ ነው፤ ግን ጉዳዩ ግዜ የማይሰጥ በመሆኑ እኛ ደግሞ አንገብጋቢነቱን ነው እየገለጽን ያለነው። አንድ ነገር ላይ ተማምኖ መቀመጥ እንኳን አዲስ አበባን ለሚያክል ከተማ ቀርቶ ለትንንሽ ከተሞችም መልካም ስላልሆነ ሁል ጊዜ አማራጭ ሁለት ይኑረን እያልን ነው። የከተማ አስተዳደሩ ምላሹ ጥሩና ለማዘጋጀትም ቁርጠኝነቱ ቢኖርም ከጊዜ አንጻር ግን አሁንም መርዘም ስለሌለበት ቶሎ እንዲፈጸም እንፈልጋለን።
ከተማዋ ሁሌም አዳዲስ ሰዎች የሚመጡባት በየቀኑ የነዋሪዎቿ ቁጥር የሚጨምርባት እንደመሆኑ የህዝቡ ቁጥር ባደገና ወደመካከለኛ ገቢ ደረጃ በተሸጋገረ ቁጥር የሚያመነጨው ቆሻሻ ሸክም እየሆነ ነው የሚሄደው። አሁን ላይ ሩቅ አሳቢ ሆነን በርከት ያሉ ማስወገጃዎችና የመልሶ ጥቅም ላይ ማዋያ ተርሚናሎች ሊኖሩን ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ረጲ ቆሻሻን ከማከማቸት ባለፈ ለሀይል ማመንጫነትም እያገለገለ ነው፤ ከዚህ አንጻር ውጤታማነቱን እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ረጲ ከ 60 በመቶ በላይ ያለውን የከተማዋን ቆሻሻ በመሰብሰብ ሸክማችንን እያቃለለ ነው። አንዳንድ ጊዜ አቅሙ በጣም ይጨምርና ከ60 በመቶ አልፎ እስከ 80ና 90 በመቶ ድረስ ሀይል ያመነጫል። በእርግጥ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል በኩል የሚነሳው አትራፊ አለመሆኑና መንግስት እየደጎመው የሚሄድ ፕሮጀክት እንደሆነ ነው፤ እዚህ ላይ ግን ማህበራዊ ሀላፊነትን መወጣት የሁላችንም በመሆኑም ጣቢያው ቆሻሻን መሰብሰቡ በራሱ ትልቅ ውጤት ነው።
ጣቢያው በዚህን ያህል ቆሻሻን እየተቀበለ ወደ ሀይል የሚለውጥ ከሆነ የረጲን ሌላውን ክፍል ወደ አረንጓዴ ልማት ለምን አናስገባም በሚል አምና 10 ሺ ችግኝ ተተክሏል፤ ዘንድሮም ይህንኑ ለመድገም ችግኝ ተከላው ተጀምሯል። ይበልጥ ደግሞ ተጨማሪ የሀይል ማመንጫ ቢኖረን አካባቢውን አሳምረን ለከተማዋ ተጨማሪ ገጽታን ለመፍጠር እንፈልጋለን።
አዲስ ዘመን ፦ረጲ ይህንን ያህል ሀይል
እያመነጨ ከሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ለምንድን ነው አዋጭ አይደለም ያለው?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ እዚህ ላይ ምናልባት የእነሱን ሀሳብ መስማት ሊያስፈልግ ይችላል፤ ሆኖም በእኛ በኩል ሌላ ቦታ ያሏቸው የሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በሙሉ ትርፍ የሚያመጡ ናቸው። ይህ ግን አትራፊ አይደለም ነው የሚሉት።
አዲስ ዘመን፦ እኮ ሀይል ካመነጨ ወይ አቅሙን ማሳደግ ነው እንጂ እንደማይሰራ ፕሮጀክት ለምንድን ነው ትርፋማ አይደለም የሚሉት?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ለምሳሌ በሀይል ማመንጫው ላይ የሚሰሩት ባለሙያዎች በሙሉ ቻይናውያን ናቸው፤ እውቀቱ ገና ለአገር ውስጥ ባለሙያዎች አልተላለፈም። ለእነሱ የሚወጣው ወጪ ደግሞ ብዙ ነው። ስራው ላይ ኢትዮጵያውያን ቢኖሩም ብዙ ስራ የሚሰራው በቻይናውያኑ ነው። ምናልባት የተጠበቀ የነበረው ባለፈው ዓመት ስራውን ለአገር ውስጥ ባለሙያዎች አስተላልፈው ይወጣሉ ነበር ግን ያ አልሆነም።
እኛ ግን የምናየውና ሁሌም በምናደርጋቸው ንግግሮች ውስጥ የምንገልጸው ይህ ማህበራዊ ሀላፊነት ነው። ማህበረሰቡ ጽዳቱ በተጠበቀ አካባቢ ውስጥ የመኖር መብት አለው በመሆኑም ጣቢያው እንደሚባለው አትራፊ እንኳን ባይሆን ይህንን ሸክም መቀነሱ ለመንግስት ትልቅ እገዛ ነው። እናንተም ከዚህ አንጻር እዩት እያልናቸው ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ባለንበት ወቅት ኮሮና ቫይረስ ተከስቷል፤ ዋናው መከላከያው ደግሞ የራስንና የአካባቢን ንጽህና መጠበቅ ነው፤ በመሆኑም ህብረተሰቡ ጽዳቱን እንዲጠብቅ እናንተም ከእያንዳንዳችን ቤት የሚወጣውን ቆሻሻ በአግባቡና በወቅቱ ከመሰብሰብ አንጻር ያለው ዝግጁነት ምን ይመስላል?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ከዚህ ቀደም ወርሃዊ የጽዳት ፕሮግራም ነበረን፤ በተለይም ከለውጡ በኋላ ስራውን ከፍተኛ የመንግስት አመራሮቹ ሳይቀሩ እየተሳተፉበት ነበር፤ ይህ ደግሞ ትልቅ የህዝብ ንቅናቄን ፈጥሯል። በዚህም እንደ ኤጀንሲ በየወሩ 5 መቶ ሺ ህዝብ በጽዳት ስራው ላይ ተሳታፊ ሆኗል ብለን ነው የምንገምተው።
ኮሮና ቫይረስ ወደ አገሪቱ ከገባ በኋላ ግን በአስሩም ክፍለ ከተሞች በ 121 ወረዳዎች በየሳምንቱ እሁድ ሁሉም አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጎ የቤቱን 20 ሜትር ርቀት ድረስ እንዲያጸዳ እያደረግን ነው።
የመንግስት ተቋማትም ሁልጊዜ በየሳምንቱ አርብ እስከ 50 ሜትር ርቀት የጽዳት ስራ እንዲሰሩ እየተደረገ
ነው።ከዚህ አንጻር አሁን ላይ ህብረተሰባችን በጽዳት ጉዳይ ላይ የተሻለ ለውጥ እየመጣ ነው።ይህ የጽዳት ስራ በገንዘብ ሲተመንም ከ171 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ወርሃዊ ጽዳት በህብረተሰቡ ተሰርቷል እንላለን።
አዲስ ዘመን፦ በየቀኑ ከቤታችን፤ ከመስሪያ ቤቶችና ከንግድ ተቋማት ቆሻሻን የሚሰበስቡ ወጣቶች እነሱ ስራቸውን ቢሰሩም የሚቀበላቸው የሚያጡበትና ቆሻሻው የመኪና መንገዱን ዘግቶ የሚታይበት ሁኔታ አለና ይህ ምን ሲሆን የሚፈጠር ነው?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ አሁን ያለን አቋም በሳምንት ሁለት ቀን ከእያንዳንዱ አባወራ ቤት ቆሻሻ እንዲወጣ ነው፤ በዚህ መልኩ የወጣው ቆሻሻ ደግሞ የሚያነሳው መኪና እስኪመጣ የተዘጋጁ ማቆያ ቦታዎች አሉን፤ ግን በመካከል አንድ ቦታ ላይ ተከማችቶ ለሚያየው ሰው ሊያስጠላ ይችላል ፤ ሆኖም በ 24 ሰዓት ጊዜ ውስጥ ይነሳል።
አዲስ ዘመን፦ ቆሻሻ የሚያነሱት ወጣቶች ከስራው ተጠቃሚ ሆነዋል? አልሆኑም የሚባል ነገር ስላለ ነው የምጠይቀው፤
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ረጲ የሰበሰቡትን ቆሻሻ ሲያስመዝኑ የሚቆረጥላቸው ደረሰኝ አለ፤ ምክንያቱም ቆሻሻ ሁሉ ስለሚከፈልበት፤ ስራው በተሰራ መጠን ክፍያ ስላለው ሁሉም በ 24 ሰዓት ወስጥ ያነሳሉ፤ አልፎ አልፎ ግን ክፍተቶች አይስተዋሉም ማለት አይደለም።
እነዚህ ማህበራት የተደራጁት በ 2001 ዓ.ም በአነስተኛና ጥቃቅን ዘርፍ ሲሆን፤ በወቅቱ የብድር ሁኔታ ተመቻችቶላቸው ቢጫዎቹን መኪኖች ገዝተው ሲሰሩም ቆይተዋል፤ አሁኑ እዳቸውን ከፍለው ጨርሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ በየወሩ ከ 10 እስከ 20 ሺ ብር ባለው ደረጃ ውስጥ ደመወዝ ያገኛሉ። ከዚህ አንጻር ኤጀንሲው ስራውን በውክልና የሰጣቸው ባለሀብቶች እንጂ በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ አይደሉም።
እነርሱን ወደመካከለኛ ባለሀብትነት እየገቡ ያሉ ብለን ነው የምናስባቸው ምክንያቱም ተቀማጫቸው ብቻ ወደ 64 ሚሊየን ብር ደርሷል።በቀጣይ ኤጀንሲው በአስሩም ክፍለ ከተማ ያለውን ስራውን አሳልፎ ለእነሱ ለመስጠት ያስባል። በመሆኑም የገቢያቸውን 20 በመቶ ስለሚቆጥቡ ብዙ ያላቸውና ያን ያህልም ተጎድተዋል ሊባልላቸው የሚችሉ አይደሉም።ተጎድተዋልም ከተባለ ደግሞ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ በመሆኑ ለስኬታቸውም ለውድቀታቸውም ተጠያቂዎቹ ራሳቸው ናቸው።
አዲስ ዘመን ፦ በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ከኮቪድ 19 ማብቃት በኋላ ቱሪስቶች በብዛት
ሊመጡባቸው የሚችሉ ተብለው ከሚገለጹ ከተሞች መካከል አዲስ አበባ አንዷ ናትና በጽዳቷ በኩልስ ኤጀንሲው ምን ያህል ዝግጁ ሆኗል?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ይህ ዘርፍ ከነበረበት በጣም መሻሻሎችን እያሳየ ነው፤ አሁን ያሉት አመራሮች ጽዳት ላይ ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ያላቸው በመሆኑም በዚህ ደረጃ መነሳሳቱ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።
በሌላ በኩልም ኤጀንሲው ከክፍለ ከተማና ከወረዳ ጋር የተሳሰረ ከመሆኑም በላይ የጽዳትን ጉዳይ ግንዛቤ የሚፈጥሩ ብቻ 1ሺ 500 ሰዎች አሉን፤ በመንገድ ጽዳቱ በኩል ከ 4 ሺ 600 በላይ ሰዎች ተሳታፊ ናቸው፤ በዚህ ውስጥም መንገዶች በቀን ሶስት ጊዜ ይጸዳሉ፤ ይህ ብቻም አይደለም አንደኛ ደረጃ (vip)። ሁለተኛ ደረጃ ተብለው ተለይተው ነው የጽዳት ስራዎች እየተሰሩ ያሉት። ሆኖም ጽዳት በባህርይው ከፍተኛ የሆነ ክትትል የሚፈልግ በመሆኑ ጠዋት ተጸድቶ ከሰዓታት በኋላ ይቆሽሻል፤ ይህ ደግሞ ጠዋት የተጸዳውን ስራ ሁሉ ገደል ነው የሚከተው፤ በመሆኑም ኤጀንሲው ለስራው ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቱም በላይ ክትትልና ድጋፉን አጠናክሮ እየሰራ ነው።
አዲስ ዘመን ፦ ኤጀንሲው የአጭርና የረጅም ጊዜ እቅዱ ምንድን ነው?
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ ወደፊት የጽዳት ስራውን ለሌሎች ባለሀብቶች በሀላፊነት የመስጠት እቅድ አለው። ይህንን ካደረገ በኋላ ሙሉ ትኩረቱን የክትትልና የድጋፍ ስራው ላይ ይሆናል።ሌላው ረጲ ላይ ያለውን ሁኔታ ለነዋሪዎች ምቹ አረንጓዴና የተሻለ እንዲሆን በተለይም የሀይል ማመንጫው አቅሙን የሚያሳድግ ከሆነ ወይም ሌላ ሊረዳው የሚችል የሀይል ማመንጫ ከተገኘ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለመናፈሻነት ለማዋል እቅድ ይዟል።
በተለይም አሁን የከተማ ግብርና ከመጣ በኋላ በቤት ውስጥ የሚዘጋጅ የአትክልት ማዳበሪያን የማምረቱን ሂደት አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሴቶች በመስጠትና በቤታቸው ሆነው ለምግብነት አውለዋቸው ከተራረፉ ነገሮች እንዲያዘጋጁና ገቢ እንዲያገኙ የማድረግ ስራም ታስቧል።
በጠቅላላው ዘርፉ በርካቶች የተሻለ ኑሮን እንዲኖሩ የተሻሉ ባለሀብቶች እንዲወጡ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ ያለውን አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል።አዲስ አበባ እንደ ስሟ ታድሳና ከቆሻሻ ጸድታ ለሌሎች የክልል ከተሞችም ሞዴል ሆና እንድትቀጥል ለማድረግ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ሀይማኖት፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 17/2012
እፀገነት አክሊሉ