የኮረና ቫይረስ አደጋ በየቀኑ እያሻቀበ ነው። የእኛም መዘናጋት ጨምሯል። የሰው ሁኔታ ሲታይ ተያይዘን እንለቅ የሚል ውሳኔ ላይ የተደረሰ ይመስላል። ማስክ ማድረጉ ብቻውን መፍትሄ አይሆንም። ለግዜውም ቢሆን መከላከያ ተደርገው የተወሰዱትን ርቀትን መጠበቅ፤ እጅን መታጠብ፤ ሳልና ማስነጠስ ካላቸው ሰዎች መራቅ የእኛ ኑሮና ሁኔታ አይፈቅድም እንጂ ቤት ውስጥ መቀመጥ ስርጭቱን ለመግታት ዓይነተኛ መፍትሄ ነው።
በከፋ ሁኔታ በአራቱም ማዕዘናት የተሰራጨው ኮረና ቫይረስ የአለምን ታሪክ ባህላዊ አኗኗር ኢኮኖሚ ፖለቲካና ማሕበራዊ ግንኙነቱን ሁሉ እንዳይመለስ አድርጎ ቀይሮታል። የሰውን ልጅ የቴክኖሎጂ ምጥቀትና የደረሰበትን ጣሪያ ሁሉ የፈተነና ውድቅ ያደረገ ቫይረስ ነው።
የዓለምን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ በስሌትና ቀመር ነው የተፈበረከው የሚሉ ምሁራን ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ። አንድ ቀን ያፈጠጠው እውነት በአለም አደባባይ መውጣቱ አይቀርም። እየሠፋ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ፈጣን የሥርጭት አድማስ ለመመከት ምንም አቅም የሌላቸው እኛን ጨምሮ ሌሎችም ድሀ ሀገሮች ለግዜው ያላቸው ብቸኛ አማራጭ በየመንግስታቸው የሚሰጠውን የጥንቃቄ መመሪያ ማክበር ብቻ ነው።
ሌላው ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው ነገር የባሕላዊ ሕክምና አዋቂዎቻችንን የተለያዩ ግኝቶች በላቦራቶሪ መሞከርና የተሻለ ውጤት ያለውን ፈጥኖ ወደስራ ማስገባት ነው። ሞቱ ካልቀረ መሞከሩ ትልቅ ብልህነት ነው። ውጤታማ ከሆነ እንጠቀምበታለን፤ የጎንዮሽ ችግር ካለው ይቀራል። በመሞከራችን ግን አንጎዳም። የእኛ ሰዎች ከፈረንጆቹ የበለጠ ሊያውቁ አይችሉም ከሚለው ራስን የማሳነስና በነጮች ከማምለክ አባዜ እንውጣ። እነሱማ መድኃኒቱን ለማግኘት በስሌታቸው መሰረት አንድ ዓመት ከስድስት ወር ይፈጃል ብለዋል። ይሄን የተናገሩት ዶ/ር ፋውቺን ጨምሮ እውቅ ሳይንቲስቶቻቸው ናቸው።
ጭራሹንም አንድ የምዕራቡ አለም ኢኮኖሚስት ደግሞ ኮሮና ቫይረስ 10 አመት አብሮን ይቆያል ማለቱ አለምን ሲያንጫጫ ነበር። የእኛ ሕዝብ ኑሮ እንደሚታወቀው ከእጅ ወደ አፍ ነው። አብዛኛው በየዕለቱ ሮጦ ያገኘውን ሰርቶ ያገኛትንም ቋጥሮ ነው ወደ ልጆቹ የሚገባው፡ ለፍቶ ተንከራቶ አዳሪ ነው።
የምዕራቡ አለም መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ለኮሮና ቫይረስ መድኃኒቱን በማግኘት ረገድ ከፍተኛ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል። እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትንቅንቁ የገበያ ውድድሩ እጅግ ከፍተኛ ስለሆነ ገና ብዙ ጦርነት ይደረግበታል።
ከሚሊዮኖች ሞትና ስቃይ እልቂት ከጀርባ የሚቆምሩና እነሱ ከሞት የሚቀሩ የሚመስላቸው ሰብዓዊነት የሚባል የሌላቸው አውሬዎች የሞሉባት ዓለም ነች። በሕዝብ ሞትና ስቃይ ቢሊዮኖች ዶላሮችን ደርበው ደራርበው ለማትረፍ ሌት ከቀን እየሮጡ ነው። ዓለም እንዲህ ነች።
መድኃኒቱ ተገኘ ከተባለ እንደተለመደው የአለም ሀገራት ሁሉ ሕዝባቸውን ከሞት ለማዳን ያለ የሌለ ገንዘባቸውን አውጥተው በዶላር መንዝረው ከአውሮፓ መድኃኒት አምራች ካምፓኒዎች ወዲያው ይገዛሉ። የሞቀ የጨሰ ንግድ ይሉሀል ይሄ ነው። በአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታ መድኃኒቱ ቢገኝም ይፋ ላያወጡት ይችላሉ። እስከዛው የዓለም ሕዝብ ይረግፋል። እነሱ ስለትርፍና በቢሊዮን ዶላሮች ለማትረፍ ይሯሯጣሉ።
ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ በራስ አለመቆምና ክፉው ድህነት በሀገራት ላይ ያመጣው ጣጣ ነው። ኮሮና ቫይረስ ካስከተለው ውስብስብ ችግር በከፍተኛ ደረጃ ልንማርበት ይገባል። ይሄ የጨፈገገና ጨለማ የመሰለው ቀን ያልፋል። ትንሽ ቆይተው ደግሞ ሌሎች አዳዲስ በሽታዎችን በዓለም ላይ ይለቃሉ። ይሄ ጥርጥር የለውም።
ዋናው ነጥብ እንዴት እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ከዚህ በኋላ በሁሉም መስክ ብቁ ንቁና ዝግጁ ሆነን መጠበቅ አለብን የሚለው ነው። ሀገርን ተረባርቦ ማልማት፤ በሕክምናው ዘርፍ ዘመናዊውንና ባህላዊውን አቀናጅተን ተመጋግቦ እንዲሰራ ማድረግ፤ ሰፋፊ የበሽታዎችና የመድኃኒቶች የጥናትና የምርምር ማእከሎችን በአዲስ አበባም በየክልሎችም መክፈትና የተበታተነውን እውቀት አሰባስቦ የጋራ ውጤት ማምጣት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።
ከድህነት፣ ከተመጽዋችነትና ከተረጂነት ፈንቅለን እስካልወጣን ድረስ በሕይወታችንም ሆነ በሞታችን የሚወስኑት የሌላው ዓለም ሰዎች ይሆናሉ ማለት ነው። የታዳጊ ሀገራት ምሁራን ይሄን የእርስ በእርስ መናቆርና መባላት የውጭ ኃይሎች አጀንዳ አስፈጻሚነታቸውን ትተው ለሕዝባቸው ልማት፣ ዕድገትና ብልጽግና ሰፊ የጤና አገልግሎት እንዲያገኝ መስራት ነው የሚጠበቅባቸው። ከዚህ መማርና ስለድሀ ሕዝባቸው ሀገራቸውና ወገናቸው
ማሰብ ካልቻሉ በእርግጥም በሚኖሩባቸው የአውሮፓ ሀገራት በቅንጡ ሕይወት ስለራሳቸው ምቾትና ድሎት ብቻ የሚያስቡ ናቸው ማለት ነው።
አፍሪካን ለመመዝበር ለመዝረፍ ዛሬም አሰፍስፈው ይገኛሉ። ይሄ ብቻ አይደለም። በበሽታውም በምኑም ብለው የአፍሪካን ሕዝብ ማራገፍ ይፈልጋሉ። ተቀበልነውም አልተቀበልነውም እውነቱ ይሄ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠር የአለም ሕዝብ ያልቃል። ሞት ይነግሳል። በዚህም የአለምን ሕዝብ ቁጥር የመቀነስ ቀመራቸው ተሳካ ማለት ነው። በሽታውንም መድኃኒቱንም ፈጣሪዎች እነሱው መሆናቸውን ብዙዎቻችን በቅጡ አልተረዳነውም።
ነጮች ሁሉን አዋቂ፣ አድራጊና ፈጣሪ ናቸው ከሚለው ደካማ አስተሳሰብ መላቀቅ ግድ ነው። ኢትዮጵያውያን ብዙ መስራት ብዙ መፍጠር ብዙ ማድረግ ለዓለምም መድሀኒት መሆን ይችላሉ። ለዚህ ደግሞ ወደ ራሳችን የባሕል ሕክምና አዋቂዎች እናተኩር፤ መፍትሄ ያሉትንም እንሞክር።
ጥንት የነጮች ሕክምና ወደ ሀገራችን ሳይገባ ለተለያዩ በሽታዎች መድሀኒት የሚቀምሙት የሚሰጡት የራሳችን የባህል ሕክምና አዋቂዎች ነበሩ። ምናልባት የመመጠኑ ልኬት የማበጀቱ የንጽህናው ጉዳይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ስለሆነ ለዚህ ከዘመናዊው የህክምና ዶክተሮቻችን ጋር የጋራ መፍትሄ ማበጀት ይቻላል። መድኃኒቱን ሞክሮ በምን መልኩ ለሕዝብ ማዳረስና ሕዝባችንን ከሞት ፈጥነን ማዳን እንደሚገባን ወስኖ ወደስራ መግባት ነው የሚበጀው። አውሮፓ መድኃኒት እስኪያገኝ እኛ ማለቅ የለብንም ።
ገና መድኃኒቱ ከአውሮፓ በምርምር ተገኝቶ በፋብሪካ ተመርቶ ለአለም ሕዝብ እስኪሰራጭና እስኪደርስ ድረስ ( ክትባትም ይሁን ኪኒን ) ምን ያህል ዜጎቻችንን እንደምናጣ ምን ያህል ቤተሰብ እንደሚበተንና እንደሚያልቅ ግምት ውስጥ ሊገባ ይገባል።
የውጭዎቹን ምክርና አዋቂነት አሜን ብለን ተቀብለን ለሞት መዘጋጀት ወይንስ የራሳችን የምንለውን ሕዝብን ከእልቂትና ከሞት የሚታደግ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ነው የሚሻለን።ምርጫና ውሳኔው የእኛው ነው። መንግስትም በጉዳዩ የተለየ ትኩረት ሰጥቶ ሊያስብበትና ሊወስንበትም ይገባል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 16/2012
ወንድወሰን መኮንን