በዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በተለይም ደግሞ ታዳጊ ሀገራት ተፅዕኖውን ሊቋቋሙት የሚችሉት አይደለም። የሙቀት አማቂ ጋዞች መጨመር ሙቀታማነትንና ተደጋጋሚ ድርቅን እንዲባባስ እያደረገው ነው። ለዚህ ጋዝ መጨመር ደግሞ የደን መጨፍጨፍ በመንስኤነት ይጠቀሳል። በኢትዮጵያም በደን መጨፍጨፍ ምክንያት በዓመት 20 ሚሊዮን ሜትሪክቶን የሙቀት አማቂ ጋዝ ወደ አየር እንደሚለቀቅ መረጃዎች ያሳያሉ።
የደን ሽፋን ለአንድ አገር የሚሰጠው ጥቅም እጅግ በርከት ያለ ነው። ከእነዚህም ውስጥ የከርሰ ምድር ውሃን በአስተማማኝ ደረጃ ለማግኘት፤ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ለመጠበቅ፤ ምርታማነትን ለማሳደግና ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀውን የካርቦንዳይኦክሳይድ መጠን ለመቀነስ መርዳቱ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
የአገር የህልውና ጉዳይ የሆነውን ደን መጠበቅና መንከባከብ የአማራጭ ጉዳይ አይደለም። ለዚህም ሲባል በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚን መገንባትና በኅብረተሰብ ተሳትፎ ደንን ማልማት ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑ ይታመናል።
ደንን ማልማት አካባቢን ከብክለት መከላከል እጅግ ሰፊና ወሳኝ ጉዳይ ነው። የደን ምንጣሮ በመከላከል እንዲያገግም ማድረግ፤ የደን ልማት ስራዎችን ሳይታክቱ መስራት፤ የተፈጥሮ ሀብቶች በዘላቂነት መጠበቅና መንከባከብ አስፈላጊ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ እንደ አገር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። ከልሎችም የዚሁ አካል በመሆን እጅግ መልካም የሚባሉ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ። በዚሁ ዙሪያ ሀሳባቸውን ያካፈሉን የኦሮሚያ ክልል የአካባቢ፣ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ቦና ያዴሳ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተሰጡት ኃላፊነቶች በርካታና ሰፊ ስራዎች የሚጠይቁ ናቸው ይላሉ፡
አቶ ቦና እንደሚገልጹት፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሦስት ዋና ዋና ተግባራት ላይ ትኩረት በማድረግ ይሰራል። እነዚህም በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ በተለያዩ ዘርፎች የሚሰሩ ስራዎችን ማስተባባር፤ የደን ጥበቃና እንክብካቤ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ደን ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች መምራትና ማስተባበር፤ በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የአካባቢ ብክለት የሚያደርሱ ተቋማትን የመቆጣጠርና እርምጃ የመውሰድ ስራዎችን ያካተቱ ናቸው።
በክልል ደረጃ የአካባቢ ደን ተጽፅኖ ግምገማ አዋጅ ያለ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ከዚህ አንጻር አየርን፣ ውሃንና አካባቢን የሚበክሉ በተለይ አገልግሎት ሰጪና ማምረቻ ተቋማት መኖራቸውን ጠቁመው፤ በተለያየ ጊዜ በተደረገ ክትትልና ቁጥጥር በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት በአዋጁ መሠረት ተግባራዊ የማያደርጉና አካባቢን በሚበክሉ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን ገልጸው፤ ህጉ በሚፈቅደው መሠረት አሻሽለው ሲመጡ ተመልሰው ወደ ስራ የሚገቡ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ።
የአካባቢ ብክለት ተጽፅኖ ግምገማ የሚያደርጉ ተቋማት ቢኖሩም፤ በአካባቢ አያያዝ ዙሪያ እቅድ ሲያዘጋጁ የነበሩት 15 በመቶ የማይበልጡ መሆናቸውን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ ይሁንና በዘንድሮ ዓመት እስከ ሦስተኛ ሩብ ዓመት በተሰሩ
ስራዎች 66 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል። በዚህም 4ሺህ የሚሆኑ ማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እቅድ እንዲያዘጋጁ ተደርጓል። በተለያየ ጊዜ በተደረገ ድንገተኛ ክትትልና ቁጥጥር በአካባቢ ላይ ብክለት የሚያደርሱ 22 የሚሆኑ ተቋማት ላይ የማምረት ሂደት እንዲያቆሙ የማድረግ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ ከመቶ በላይ ለሚሆኑ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል። እርምጃ ከተወሰደባቸው ተቋማት ውስጥ ያለባቸውን ችግር በመቅረፍ ወደ ስራቸው የተመለሱ እንዳሉ አመልክተው አምና በአካባቢ ብክለት አያያዝ ጥሩ አፈጻጸም ላሳዩ 17 ለሚሆኑ የማምረቻና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እውቅና መሰጠቱን ጠቁመዋል። በዘንድሮ ዓመት በተደረገው ክትትልና ቁጥጥር ከፍተኛ መሻሻል እየታዩ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
እንደ አቶ ቦና ማብራሪያ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ስራዎች በተመለከተ ሴክተር መስሪያ ቤቶች፤ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGO) በሚቴግሽን (Mitigation) እና በአዳፕቴሽን (adaption) የተሰሩ ስራዎች መገምገም፣ የማስተባባርና ስልጠና የመስጠት ስራ እየተሰራ ይገኛል። ሚቴግሽን ወደ አካባቢ አየር የሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋዞችን በማስቀረት ለምሳሌ ደን በመትከል የደን ሽፋንን በመጨመር ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቁ ሙቀት አማቂ ጋዞች ከአየር ተስቦ በእጽዋት አካል ውስጥ በስር፣ በግንድና በቅጠል የሚያቆዩበትን ሁኔታ የመፍጠር ስራዎችን የሚያጠቃልል ነው። አዳፕቴሽን ደግሞ የአየር ብክለት ለውጥ ማቋቋሚያ ስልት ሲሆን ለምሳሌ ቆላማ ቦታዎችና ውሃ አጠር የሆኑ አካባቢዎችን በመስኖ እንዲለሙ በማድረግ በአየር ንብረት ለውጥ ችግር ምክንያት ህዝቡ እንዳይጎዳ የማቋቋም ስራን መስራት ነው። በዚህ ረገድ 25 የሚሆኑ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በጋራ በመሆን የተሰሩ ስራዎች የሚገመግሙ መሆኑን አመልክተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ ሴክተሮች ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውና በዚህ ረገድ የጎላ ድርሻ ያላቸው እንደግብርና፤ ውሃ ሀብት ቢሮ፤ አርብቶ አደር ኮሚሽንን የመሳሰሉት ናቸው። በየተቋማት ይህንን የሚቆጣጠር ተወካዮች ያሉ ሲሆን ግንዛቤ በማስጨበጥና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም በቼክ ሊስት ሥራዎችን የመቆጣጣር ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ያስረዳሉ።
በክልሉ ያለውን የተፈጥሮ ደን ከልሎ በህብረተሰብ ተሳትፎ እንዲጠበቅና እንዲንከባከብ ከማድረግ አንጻር ህብረተሰቡ ተደራጅቶና የራሱን ህገ ደንብ አውጥቶ ህጋዊ በሆነ መልኩ ደኑን እየጠበቀ እንዲጠቀም እየተደረገ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በተለያዩ ፕሮጀክቶችና በመደበኛ ሰፋፊ ስራዎች መስራታቸውን አመልክተዋል። በኦሮሚያ ውስጥ ካሉ ጥብቅ ደኖች ኢሊባቡር ውስጥ የሚገኘው ያዩ የሚባለው ጥብቅ ደን፤ ባሌ ፓርክ አካባቢ ያለ ደን፤ ጉጂ ቦረና አካባቢና በኦሮሚያ ኢንተርፕራይዝ ስር ያሉ 3 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር የሚሆን ከፍተኛ የተፈጥሮ ደኖች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። እነዚህ ደኖች በኦሮሚያ ደንና ዱር እንስሳት ኢንተርፕራይዝ ስር የሚተዳደሩ ቢሆንም የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የመቆጣጠርና የመከታተል ስራ የሚሰራ መሆኑን ያብራራሉ።
የክልሉ የደን ሽፋን ዓለም አቀፉ የምግብ ደርጅት (FAO) ባስቀመጠው አዲሱ ትርጉም መሠረት ዘጠኝ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ነው። ይህ ማለት ከክልሉ የቆዳ ሽፋን 22 ወይም 23
በመቶ የሚሆነው በደን የተሸፈነ ነው ማለት ነው። በተቀየረው የደን ትርጉም መሠረት የደኑ ቅርንጫፍ የሚሸፈነው አካባቢ 20 ፐርሰንት፤ የሚሸፍነው መሬት 0.05 ሄክታር፤ ከፍታው ሁለት ሜትር ከሆነና እነዚህን ሦስቱን መስፈርት ያሟላ ደን ይባላል። በአብዛኛው ቆላማ አካባቢ የሚገኙት እንደ ግራር ያሉት ዛፎች በፊት እንደደን የማይታዩ የነበሩ ቢሆንም በአዲሱ ትርጉም መሠረት በደን ውስጥ ተካትተዋል። በመሆኑም አምና 1 ነጥብ 9 ሚሊዮን ችግኞች ተተክለው 85 በመቶ የሚሆኑት መጽደቋቸው፤ እነዚህ ችግኞችን ከሶስትና ከአራት ዓመታት በኋላ ደን ውስጥ የሚጠቃለሉ መሆኑን ጠቁመው፤ በሚቀጥሉት 10 ዓመት ውስጥ የኦሮሚያ የደን ሽፋን 30 ፐርሰንት ለማድረስ እቅድ ተይዞ እየተሰራ ነው ይላሉ።
የደን ቁጥጥርን በተመለከተ አንድ ግለሰብ የደን ውጤቶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ሲያዘዋውር ተቋማቸው የይለፍ ፈቃድ የሚሰጥ መሆን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ ደኑ በህጋዊ መንገድ ተቆርጦ፤ በህጋዊ መንገድ ተመርቶ፤ በህጋዊ መንገድ መጓጓዙን መከታታልን ያጠቃልላል። ህገወጥ መንገድ የደን ውጤቶች የሚያዘዋውሩ አካላትን ለህግ በማቅረብ ንብረቱን በመውረስ፤ ለመንግስት ገቢ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። በከተሞች አካባቢ የሚሰሩ የደን ውጤቶች የቁጥጥር ስራ በኢንተርፕራይዝ፤ በድርጅት፤ በግለሰብና በህጋዊ መንገድ ተደራጅተው የሚሰሩ አካላትን ከሚመለከታቸው ከኦሮሚያ ንግድ ቢሮና ገበያዎች ኤጀንሲ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን አመልክተው። ከዚህም ክልሉ ከሮያሊቲ ክፍያ በዚህ ዓመት 60 ሚሊየን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።
ከደን ከሚገኘው ገቢ 5 በመቶው ለአካባቢ ማህበረሰብ እንዲውል ይደረጋል የሚሉት ኃላፊው፤ ለአብነት የኦሮሚያ ህብረት ስራ ኢንተርፕራይዝ ከአንድ ቀበሌ ደን ሲሸጥ ከሽያጩ አምስት በመቶ ለአካባቢው ማህበረስብ በማዋል ማህበረሰቡ ለሚፈልገው የልማት ስራ ያውለዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ደን በተለያየ መልኩ የሚለማ መሆኑን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በደን መልማት ያለበት ባዶ ቦታ ተለይቶ ችግኞች እንዲተከሉ ይደረጋል። በተለይ በስፋት ሬድፕላስ በሚባል ፕሮጀክት በተመረጡ ቦታዎች እየተሰራ መሆኑ ጠቁመው፤ የደን መሬት የነበሩና በተለያየ ምክንያት የደን ይዞታቸው የተጎዳ መሬቶችን መልሰው እንዲያገግሙ፤ ከሰውና ከእንሰሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ፤ በተፈጥሮ ደኑ እራሱ መልሶ በማገገም ወደ ደን ቦታነት እንዲለወጥ ይደረጋል። በሌላም በኩል እዚያ አካባቢ የነበሩትን የተፈጥሮ ደኖች ባዶ ቦታ ላይ የመትከል ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ይገልጻሉ።
ከብዝሕ ህይወት ዙሪያ የሚሰሩ ስራዎች ከእጽዋት አንጻር በተለይ የዛፍና የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችም አሉ የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ እንዳይጠፉ በሁለት መንገድ ተጠብቀው እንዲቆዩ ይደረጋል፤ አንደኛው ከነበሩበት ቦታ ወስዶ ወደ ሚጠበቁበት ቦታ ማስቀመጥ ሲሆን ሁለተኛው ባለበት ቦታ እንዲጠበቁ ማድረግ ነው። ለብዝሕ ህይወት ቦታዎች ተለይተው ብዙ የእጽዋትና የዱር የእንሰሳት የሚገኙበት አካባቢ ከንክኪ ተለይተው ነጻ እንዲሆኑ የማድረግ ስራዎች በተወሰነ ደረጃ እየተሰሩ እንደሆነ አመልክተው ሊጠፉ የተቃረቡትን በመለየትና ከፌዴራል ብዝሃ ህይወት ጋር በመተባበር እንዲጠበቁ እየተደረገ ነው፤ ሀገር በቀል እጽዋት በህግና
በልዩ ሁኔታ በመጠበቅ አለባቸው ተብለው ከተለዩትም እንደ ኮሶ፤ ዝግባ፤ ዋንዛ፤ ወይራ፤ የአበሻ ጥድ የሚገኙበት መሆኑን አብራርተዋል።
የአካባቢ ብክለት ከኮቪድ 19 ጋር ተያይዞ በሁለት መልኩ እንደሚታይ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የአብዛኛዎቹ ፋብሪካዎች ምርት ማቆምና የማምረት አቅማቸው መቀነስ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰው ተጽዕኖ ቀንሷል፤ የሰው እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞል። ይሕ በበጎ ጎኑ የሚታይ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ወረርሽኙን ለመከላከል በብዛት የሚመረቱት ማስክ፤ የአፍና የአፍንጫ ጭንብል፤ የእጅ ጓንት፤ የሳንታይዘር ብልቃጦች እየተበራከቱ መምጣት ይታያል። እነዚህ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ ከዋሉ በኋላ በየቦታው የሚጣሉና የማይቃጠሉ ከሆነ፤ በአግባብ እስካልተወገዱ ድረስ የአካባቢ ብክለት ማምጣታቸው እንደማይቀር ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ የሚታዩ የግንዛቤ ማነስ ችግር መኖሩን የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፤ የአካባቢ ችግር ጊዜ የማይሰጥ፤ የሚያደርሰው ጉዳት ወዲያውኑ የሚታይ አለመሆኑ ጠቁመው። አካባቢ ችግር ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ህብረተሰቡ ዘንድ ያለመገንዘብ ይታያል። የአካባቢ ችግር ከተከሰተ በኋላ ወደ ኃላ መመለስ ከባድ ነው፤ ለምሳሌ ብናነሳ የተፈጥሮ ደን ከወደመ በኋላ ሊመለስ አይችልም። የአካባቢ ጉዳይ የማይተካ ጉዳይ ነው፡ በመሆኑ ይህንን አውቆ ከመጀመሪያ እንክብካቤና ጥበቃ ከማድረግ አንጻር የግንዛቤ ችግር በህብረተሰቡም በመንግስት አካላትም መኖሩን ይናገራሉ።
የአካባቢ ጥበቃ ስራ እንደሌላው ስራ ውጤቱ ወዲያውኑ የሚታይ አይደለም የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ ቀጣይነት ያለውና ተከታታይ ስራን የሚጠይቅ ነው። የአካባቢ ጥበቃ ዘርፍ ብዙ ጊዜ ቋሚ የሆነ የአደረጃጀት የሌለው በመሆኑ በየጊዜው አደረዳጀቱ እየተቀያየረና በተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ስር እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፡ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ከፌደራል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ቀጣይ ወጥ የሆነ መዋቅር በመዘርጋት ቢሰራ ጠቀሜታው ላቅ ያለ መሆኑን አመልክተዋል። በክልሉ ከዚህ በፊት የአካባቢ ጥበቃ፤ የደን፤ የአየር ንብረት ለውጡን ስራን የሚያስተባብር ሴክተር አለመኖሩን ገልጸው፤ አሁን ላይ ባለስልጣኑ በሁሉም ዞንና ወረዳዎችና በ46 ከተሞች አካባቢ ጥበቃ መዋቅር ላይ መኖሩን ተናግረዋል፡፤
ስለዘላቂ እድገት ስናወራ ሦስት መሰረታዊ ነገሮች ወሳኝ ናቸው የሚሉት ዳይሬክተሩ ዋነኞቹም የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ፤ የኢኮኖሚ አዋጭነት ጉዳይ፤ ማህበራዊ ተቀባይነት (Social acceptance) ናቸው። ‹‹ከእነዚህ ውስጥ በአንዱ ላይ ትኩረት አድርገን ሌላውን የምንረሳ ከሆነ የኢኮኖሚ እድገታችን እንቅስቃሴ ቀጣይነት አይኖረውም፤ የምንከተለው አቅጣጫ የአረንጓዴ ልማት አቅጣጫ በመሆኑ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ወሳኝ ነው። ይህንን ካደረግን እያደግን፤ በኢኮኖሚ እየለማን፤ ሀገራችንን፤ ከተማችንን፤ ገጠራችንን ጽዱና አረንጓዴ እናደርጋለን። ለዚህም የሚመለከታቸው ሴክተሮች፤ ግለሰቦችም ሆነ ማህበረሰቡ ለማደግ የሚያስፈልጉን እነዚህን ሶስት ነገሮች በመገንዘብ ከሰራን ውጤቱ ጥሩ ይሆናል ›› በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2012
ወርቅነሽ ደምሰው