ተማሪም፣መምህርም ሆነ ጋዜጠኛ ሆኜ ባሳለፍኳቸው ዓመታት ኩረጃ ነውር መሆኑን አስረግጬ ተምሬያለሁ፤ አስተምሬያለሁም። ዛሬ ግን ለበጎ ይሁን እንጂ ኩረጃም አሪፍ ነው የሚል አቋም እንዲኖረኝ የሚያስገድድ ነገር አጋጠመኝና ያንን ላወጋችሁ ወደድኩ። ያለውን የወረወረ ንፉግ አይባልም አይደል ብሂሉ! ግን ግን እዚህ ላይ እንዲሰመርበት የምፈልገው ጉዳይ አሁንም ቢሆን በትምህርት ላይ ኩረጃ አስፈላጊ አለመሆኑንና ስርቆት ነውር መሆኑን ፈጽሞ እንዳልካድኩ ነው። ሌላው የለፋበትን ዕውቀት ያለምንም ድካም በኩረጃ ማግኘት ክብርን ከማጉደሉም በላይ ስርቆት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነውና።
ሀገራት በቴክኖሎጂ የሚበልጽጉት ሁሌም አዲስ ነገርን በራሳቸው ፈጥረው አይደለም አንዳንዴ ኮርጀውም እንጂ። እንዴት አትሉኝም? እግር ጥሏችሁ ወደ ኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ብታቀኑ የቴክኖሎጂ ክምችት የሚል አንድ ክፍል ታገኛላችሁ። በዚህ ክፍልም ማንም ሰው ወስዶ ሊጠቀምባቸው የሚችል በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች አሉ። ቴክኖሎጂዎቹ ቻይናን ጨምሮ ከተለያዩ ምዕራባውያን ሀገሮች በጭንቅ የተወለዱና የተቀመጣላቸው የባለቤትነት መብት ጥበቃ ቆይታ በመጠናቀቁ ማንም ሰው ወስዶና አሻሽሎ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ናቸው።
ይህ ማለት እንግዲህ በአጭር አማርኛ የተፈቀደ ኩረጃ ማለት ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት በስልጣኔ ማማ ከፊት ቀድመዋል የተባሉ ሀገራት ጭምር ህጋዊ በሆነ መንገድ ቴክኖሎጂን ይኮርጃሉ። በኩረጃው ላይም የራሳቸውን ፈጠራ ያክሉበትና በጥቅም ላይ ያውሉታል። ይህን ፈጠራ መነሻ በማድረግም አዳዲስ ፈጠራዎችን ያከናውናሉም። ስለሆነም ስርቆት አይሁን እንጂ በጎ በጎውንና የተፈቀደውን መኮረጅ ሐጥያት አይሆንም ማለት ነው። ሐጥያት የሚሆነው ክፉና አጥፊ ነገርን ለእኩይ ዓላማ መኮረጅ ይመስለኛል።
አገራችን ሁለት ዓይነት ገጽታ የሚስተዋልባት አገር እንደሆነች ብዙዎች ሲገልጹ ይስተዋላል። ጥቂቶች ቢሆኑም ገንዘቤን የት ላጥፋ ብለው የሚጨነቁና እጅግ የተጋነነ ህይወት የሚመሩ እንዲሁም የሚላስ የሚቀመስ
አጥተው ችግር ጢባጢቤ የምትጫወ ትባቸው የሚሊዮን ምስኪን ዜጎች መኖሪያ። በምሽቱና በሳምንት መጨረሻዎች አዲስ አበባንና አንዳንድ የሀገሪቱን ከተሞች ለተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ ኑሮው ፍስሐን የተሞላና ፈጽሞ ችግር የሌለ የሚያስመስል ነው። ከትልልቅ መናፈሻዎች እስከ ሆቴሎችና ግሮሰሪዎች ቤት ሞልቶ ውጪው እስኪጣበብ ድረስ ይበላል፤ ይጠጣል፤ ይጨፈራል…ወዘተ
ላብን ጠብ አድርገው ያፈሩት ሀብት እስከሆነ እጅግም መረን አይልቀቅ እንጂ መብላት መጠጣቱና መዝናናቱ በምንም መመዘኛ ስህተት ነው ሊባል አይችልም። ይሁንና እኔና ቤተሰቤ እንዲህ ተመችቶን ብስል ከጥሬውን ስንበላና ስንጠጣ እንዲሁም ስንዝናና ሚሊዮኖች ግን የዕለት ጉርስ አጥተው መማር እንደተሳናቸው፣ እንኳን ሰው እንስሳት እንኳ ሊጠጡት የማይገባውን ውሃ እየጠጡ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እንዳሉን ልናስታውስ ግድ ይለናል። ያለዚያ መዝናናቱ ግንጥል ጌጥ ይሆንና የአዕምሮ ወቀሳን ማስከተሉ አይቀሬ ነው።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ የተናገረው ንግግር ዛሬም ድረስ ከአዕምሮዬ አልወጣም። ወቅቱ 2004 ዓ.ም አካባቢ ሲሆን፤ በዚያን ወቅት ለግድቡ ግንባታ ህዝባችን የቦንድና ሌሎችም ድጋፎች ያጧጧፈበት ጊዜ ነበር። ይህ ሰው ሰዎች በመጠጥ በሚዝናኑበት አካባቢ ቆሞ የአባይን ግድብ መሙላት እኮ ቀላል ነው። እያንዳንዱ ድራፍት ጠጪ አንድ አንድ ጃምቦ ወደ ዓባይ ቢደፋ ግድቡ በአንዴ ነበር ከአፍ እስከ ገደፉ የሚሞላው ይል ነበር ንግግሩ። ንግግሩ በመዝናናት ላይ የነበሩትን ሰዎች በከፍተኛ መጠን ቢያስቃቸውም ለኔ ግን መልዕክቱ እጅግ ጥልቅ ነበር።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመላ ኢትዮጵያ በዓመት የሚጠጣው የቢራ መጠን በሚሊዮን ሄክቶ ሊትር የሚለካ ነው። እስኪ አስቡት በዚህ መጠን ከሚጠቀመው ህዝብ በቀንም፣ በሳምንትም ሆነ በወር ከሚጠጣው ሦስትም ሆነ አራት ቢራ አንዱን ትቶ ገንዘቡን ለተቸገሩ ሰዎች ቢለግስ ምን ያህል ሚሊዮን ብር ተዋጥቶ ስንት ወገኖችን ከችግር አያላቅቅምን? ለዚህም ነው ያውም በዚህ ክፉ ዘመን መዝናናቱና ገንዘብ መርጨቱን ገታ ተደርጎ እኛም የአንድ ጃምቦአችንን አስር ወይም አስራ ሁለት ብር ለአንድ ቤተሰብ ማዕድ በማጋራት ታሪክ እንሥራ ማለቴ።
በየከተሞች ያሉ ካፍቴሪያዎችን ብንመለከት የሻይ፣ ቡናና ማኪያቶ ተጠቃሚው ቁጥር የትየሌለ መሆኑን እንረዳለን። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ ሻይ ቡና ወይም ማኪያቶ የምንለው አስፈልጎን ሳይሆን ከጓደኛ፣ ከወዳጅ ወይም ከእንግዳ ጋር አረፍ የምንልበትን መቀመጫ ፈልገን ይመስለኛል። ሳያስፈልገን ልማድ ሆኖብንም በቀን ሦስት አራት ጊዜ ቡና ወይ ሻይ የምንጠጣም ብዙዎች ነን። እናም ከእነአካቴው መተውን ተትን በቀን ከምንጠጣው ሁለት፣ ሦስት፣ አራት ቡና፣ ሻይ ወይ ማኪያቶ የአንዱን ዋጋ ጠርቀም አድርግን ለአንድ ቤተሰብ ማዕድ ለማጋራት ብናውለው ምንያህል ዜጎቻችንን ከችግራቸው በፈወስን።
ያነሳሁትን ነጥብ ለማጠናከር የደቡብ ኮሪያውያንን ታሪክ እዚህ ጋር ማንሳቱ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል። ዕድል ገጥሞኝ ደቡብ ኮሪያን ስለጎበኘሁ ዕድገቷንና ያለችበትን ደረጃ ምድራዊ ገነት ብሎ ከማለፍ ውጪ በቃላት ገልጾ ለማለፍ ያዳግተኛል። ጠንካራዎቹና ብልሆቹ ኮሪያውያን አገር መውደድን በተግባ ተርጉመው የምትገርም አገር ፈጥረዋል።
ይህቺ ሀገር ከ50 እና 60 ዓመት በፊት የነበረችበት ድህነት ግን አንጀት በጥስ የሚሉትና ለመናገርም የሚከብድ እንደነበር ዜጎቿ ያወጋሉ። ይሁንና በወቅቱ የነበረው መንግሥት ሲያደርገው የነበረው የፀረ ድህነት ትግል ከጫፍ የደረሰው ደቡብ ኮሪያውያን ሴቶች ያላቸው ወርቃቸውን የሌላቸው ደግሞ ጸጉራቸውን እየቆረጡ እየሸጡና የሴተኛ አዳሪነትን ሥራ ሳይቀር እየሠሩ ያገኙትን ንዋይ ለሀገራቸው ልማት እንዲውል በመለገሳቸው ነበር። ደቡብ ኮሪያውያን እነዚህን እንስት ጀግኖቻቸውን በብሄራዊ ጀግናነት በየዓመቱ የሚያስቡበትና ክብር የሚሰጡበት ቀን እንዳላቸውም ሰምቻለሁ። ለአገር ዕድገት ሲባል የሚከፈለውን ይህን መሰሉን አኩሪ ገድል ስንመለከት እኛስ ምን አደርገናል ከማስባሉም በላይ የቡናና የሻይ ሂሳብን ለወገን መለገስ ምን አላት የሚል ጥያቄ ወደ አዕምሯችን መምጣቱ አይቀሬ ይሆናል ።
ከላይ የጠቀስናቸው ተግባራት ዓላማቸው ቅዱስ ስለሆነ እኛም እንደ አገርና ህዝብ ቴክኖሎጂን ለመቅዳትና ለማበልጸግ ሀገራት ያደጉበትን የመረዳዳትና አገር የመውደድ ተግባር ኮርጀንም ቢሆን ብንጠቀም ፋይዳው ብዙ ነው እላለሁ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 15/2012
ፍቃዱ ከተማ