ቁም ነገር እያስጨበጠ ያዝናናል። የበርካታ አርቲስቶችን ዘፈን በማስመሰል ለብዙዎች የሳቅ ምንጭ ሆኗል። በተለይ ደግሞ አስቴር አወቀን በማስመሰል የሚወዳደረው የለም። የአትሌት ቀነኒሳ በቀለን የሩጫ ስልት ማስመሰል ሌላው መለያው ነው። በዚህም ሥራው አድናቆትን ከአትሌቱ ሳይቀር እንደደረሰው ይናገራል። በማስመሰልም የተዋጣለት ኮሜዲያን መሆኑን አስመስክሯል። ከልጅነቱ ጀምሮ ወደ አርቲስትነቱ እንዲመጣ በር የከፈተለት ይሄው ብቃቱ ሲሆን ‹‹አልቀበልም›› በተሰኘው ነጠላ ዜማው የብዙዎችን ጆሮ ገብቷል። አንድነትን የሚሸረሽሩ ሃሳቦችን ወደ ጎን ጥሎ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በማንሳት ውስጥ ቀስቃሽ ፣ ወኔ አነሳሽ ሥራ በማቅረብ ተቀባይነት አግኝቷል። አድናቆትም ተችሮታል። በዘፈኑ መጠሪያ ‹‹አልቀበልም›› ብለው የሚጠሩት ብዙዎች ናቸው – አርቲስት አዝመራው ሙሉሰው።
ከሥራ ውጭ ውሎ
ሥራው ሰዎችን ቁምነገር እያስጨበጡ ማዝናናት ቢሆንም በእረፍት ጊዜው ለራሱም መዝናናት ይወዳል። የሚዝናናው የተለየ ነገር በማድረግ ሳይሆን ለሥራው
ተጨማሪ እውቀትን ሊጨምሩለት የሚችሉ እና ቀደም ሲል የሰራቸውን ሥራዎቹን ደጋግሞ በማድመጥ ነው።‹‹ ለሥራ ከሀገር ወጥቼም ቢሆን ሙዚቃ ከመስማት ውጭ ብዙ አያዝናናኝም›› ይላል።
በቤት ውስጥ ከቤተሰቦቼ ጋር በተለይ ደግሞ ከልጁ ጋር በመሆን መጫወት በጣም እንደሚያዝናናው ይናገራል። ‹‹ሁሌም የምናፍቀው ይሄንኑ ነው›› የሚለው አርቲስቱ ከጓደኞቼ ጋር በመገናኘት ከተለመደው ሥራችን ወጣ በማለት ማሳለፍ የሁል ጊዜ ምርጫዬ ነው ይላል።
እንዲሁም በእረፍት ጊዜው መጽሐፍ፣ መጽሔት እና ጋዜጣን ማንበብ በጣም ያዝናናዋል። በቤት ውስጥ የሰዎችን ድምፅ በማስመሰል እና ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ደግሞ የኮሜዲ ሀሳብ ያላቸውን ዘፈኖች በመምረጥ ጊዜውን ያሳልፋል። ‹‹ገጠር ተወልጅ በማደጌ ታሪካዊ ቦታዎችንና የገጠር ቤተክርስቲያኖችን መጎብኘት ያስደስተኛል። ተፈጥሮን ማድነቅም ምርጫዬ ነው ›› ሲል አጫውቶኛል።
ማህበራዊ ሕይወት
እንደ እቁብ ፣እድር በመሳሰሉ የማህበራዊ ህይወት ብዙም ተሳታፊ አይደለሁም የሚለው አርቲስት አዝመራ ሰርግና ኀዘን ላይ ግን የሚያጣው እንደሌለ
ይናገራል። ከጓደኞቹ ጋር የአንድ ማህበር አባል በመሆን እንቅስቃሴዎችን ያደርጋል። ድጋፍ የሚያስፈልገውን የገጠር ቤተክርስቲያን ለመጠገን እና እርዳታ ለማድረግ በሙያው የበኩሉን አስተዋፅኦ ያበረክታል።አንዳንድ ሀገራዊ ጥሪዎች ላይ በስፋት በመሳተፍ ይታወቃል።
በቀጣይ የአቅሜን ለሀገሬ የሚል ምኞት አለው።
የምግብና የአልባሳት ምርጫ
‹‹ይህን ጥያቄ ባትጠይቀኝ ደስ ይለኝ ነበር›› የሚለው አዝመራው እኛ ኢትዮጵያውያን ከባህላዊ ምግባችን ውጭ ምን የተሻለ ምግብ ልንመርጥ እንችላለን ሲል መልሶ ይጠይቃል። አቻ የሌለው ኢትዮጵያዊ ምግባችንን በማድነቅ። ሆኖም ‹‹ ብዙ ጊዜ ቤት ያፈራውን እመገባለሁ። በሥራ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ የምመገበው እቤት ነው። ቅቤ በሽሮ የመጀመሪ ምርጫ ሲሆን አዘውትሬም እመገባለው። ዶሮ ወጥ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደሚወደው በጣም እወዳለሁ።›› ሲል በፈገግታው ፈገግ አስደርጎናል።
‹‹የባህል ልብስ እወዳለው፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ በነጻነት መንቀሳቀስን ስለምመርጥ ሸሚዝ በጅንስ ሱሪ ይመቸኛል። የሁል ጊዜ ምርጫዬም ይሄው ነው›› ሲል አጫውቶናል።ማንኛውም ፕሮግራም ላይ የጉዳዩ አካል ካልሆነ በስተቀር የተለመደ የዘወትር አለባበሱ መታወቂያው ጅንስ በሸሚዝ ነው።ፕሮግራም ሲኖረው በሱፍና በኢትዮጵያዊ የባህል ልብስ ደምቆና አምሮ መዋልን ይመርጣል።እንደ ኢትዮጵያዊ ኑሮ እንደ ኢትዮጵያዊ መሞት ምርጫዬ ነው።
መልዕክት
የወቅቱ ወረርሽኝ በጣም አስፈሪ ስለሆነ ልንጠነቀቅ ይገባል። በሀገራችን የበሽታው ቁጥር እየጨመረ ነው መጠንቀቅ ካልቻልን ጉዳቱ ከፍተኛ ነው። ‹‹እራሳችንን ከኮሮና ከጠበቅን ለሀገር ባለውለታዎች ነን። ሁሉም ሰው በመተባበር ከዚህ በሽታ ሀገሩን እና ወገኑን ማዳን›› አለበት ሲል ይናገራል። ሁሉም ሰው መልካም ያልሆኑ ነገሮችን በተለይ ደግሞ ለሀገር አንድነትና ሰላም የማይጠቅሙ ነገሮችን ‹‹አልቀበልም የማለት ልምዱን ማጠንከር አለበት ሲል ይመክራል።
‹‹ ሰው ያለ ሰው፤ ሀገር ያለ ሰው፤ ሰው ያለ ሀገር መኖር አይችልም። ያለ ሀገር ሁሉም ባዶ ስለሆነ ቀድመን አንድነታችንን ማጠናከር አለብን ›› ሲል አሳስቧል።
እኛም ‹‹ሀገሬ… ሀገሬ… ውበትና ክብሬ ፤ ባንቺ ነው ማማሬ›› የሚለውን ጋበዝን። ቸር እንሰንብት! ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 14/2012
ሞገስ ፀጋዬ