አዲስ አበባ፡- የገጠርና የከተማ የጤና ኤክሴቴንሽን ፕሮግራም በተሟላ መልኩ እየተተገበረ እንዳልሆነና ሰፊ ክፍተቶች እንደሚታዩበት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት በሃያኛ መደበኛ ስብሰባው የጤና ሚኒስቴርን የ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ተመልክቷል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው ሪፖርቱን ተከትሎ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ማሻሻያ በማድረግ በተሟላ መልኩ ለመተግበር አቅዶ ባለፉት ስድስት ወራት ቢንቀሳቀስም አፈፃፀሙ ዝቅተኛ የሆነበት ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲብራራለት ጠይቋል፡፡
የጤና ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን በምላሹ የ2010 ዓ.ም የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አፈፃፀም ለምክር ቤቱ ሲቀርብ ፕሮግራሙ መቀዛቀዝ እንደነበረበት ተገምግሞ በ2011 ዓ.ም በተሻለ መንገድ ወደፊት ሊወስዱት የሚችሉ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል፡፡ በተለይም በክልሎች የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራምና የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ያሉባቸውን ችግሮች በመለየት የማጣጣሚያ ማንዋል ተዘጋጅቶ በስራ ላይ ውሏል፡፡ ይህም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት አስችሏል፡፡
በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማሻሻል እየተሰሩ ካሉ ተጨማሪ ስራዎች ውስጥም ፕሮግራሙ ከህብረተሰቡ ፍላጎት እኩል እንዲሄድ የሁለተኛው ትውልድ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ተቀርፆ ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡
ፕሮግራሙ የጤና ኤክስቴንሽንን ሙያ ከደረጃ 3 ወደ ደረጃ 4 ማሳደግ፣ አጠቃላይ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን ከነበረበት 16 ወደ 18 ፓኬጅ ማሳደግ፣ የሞዴል የጤና ኬላ ግንባታ ማካሄድና ሶስት የጤና የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በአንድ ቦታ መመደብን እንደሚያካትት አስታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
በአስናቀ ፀጋዬ