አዲስ አበባ፡- የቡና ኤክስፖርት መጠን ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በስድስት ወራት ውስጥ አራት በመቶ ሲቀንስ፤ በገቢ ደግሞ 13 በመቶ ወይም 47 ነጥብ 9 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መቀነሱን የቡናና ሻይ ባለስልጣን ገለጸ፡፡
በባለስልጣኑ የገበያ መረጃና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ዳዊት ይታገሱ እንደገለጹት፣ የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ መቀነሱ መሰረታዊ ችግር ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ በመውረዱ ምክንያት ቡና ላኪዎች ዋጋው እስኪጨምር በመጠባበቅ በበቂ መጠን አይልኩም፡፡ አንዳንድ ላኪዎችም ኮንትራት ይዘው ወደ ውጪ መላክ በሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ እያሉ የምርቱ ጥራት ይቀንስና ገዢዎች ኮንትራታቸውን ይሰርዛሉ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የቡና ኤክስፖርት በቀነሰበት በአሁኑ ወቅት ቡናውን በተሻለ ጥራት የሚያቀርቡ ማህበራት፣ አልሚዎችና ገዝተው የሚሸጡ የተለያዩ ድርጅቶች አሉ፡፡ እነዚህ ድርጅቶችም ከዓለም አቀፍ ዋጋም ሆነ ከሀገሪቷ ዋጋ በላይ በመሸጥ ተጠቃሚ ናቸው፡፡ የተሻለ ጥራት የተሻለ ዋጋ ያስገኛል ያሉት አቶ ዳዊት፤ የምርቱን ጥራት ማስጠበቅ ወሳኝ በመሆኑ ጥራቱን ለማስጠበቅ እስከታች ድረስ በመውረድ ለአርሶ አደሩና ለአልሚዎቹ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከዓለም አቀፉ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር በሀገር ውስጥ ከፍተኛ የቡና ምርት አለ፡፡ ከፍተኛ ምርት መኖሩም ለኤክስፖርቱ መቀነስ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ነገር ግን በብዛት ኤክስፖርት መደረግ ያለበት ቡና በህገወጥ መንገድ በሀገር ውስጥ መሸጡ ትልቅ ችግር ነው ይላሉ፡፡ በቀጣይም እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ከተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎችን በመውሰድ፤ መቆጣጠር የሚያስችሉ አዋጆችንና ደንቦችን በማውጣት በየደረጃው የቁጥጥር ስራዎች ይሰራሉም ብለዋል፡፡
የምርቱ አቅርቦት በአሁኑ ወቅት በጣም ከፍተኛ ቢሆንም የቡና ኤክስፖርት ቀንሷል የሚሉት ደግሞ አቶ ከፍያለው ጄቲ የሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የጥራትና ክምችት ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ በዓለም ላይ የቡና ገበያው እንደዚህ አይነት የዋጋ መውረድ ሲያጋጥመው በ13 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የዘንድሮው የመጀመሪያው ነው፡፡ በመሆኑም ኤክስፖርቱን ለማሻሻል የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ላኪዎችንም ጨምሮ ከታች ጀምሮ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ገበያው በሚፈቅደው መሰረት በመሸጥ ገበያውን መቀላቀል ይገባቸዋል ይላሉ፡፡
በዋናነት መሰራት ያለበት ከማሳው ጀምሮ ግብርናው ላይ ነው የሚሉት አቶ ከፍያለው፤ የኢትዮጵያ ቡና በከፍተኛ መጠን የሚመረትና ተመራጭ ቢሆንም ከታች ከወረዳ ጀምሮ ቡና ያለበት አካባቢ ክትትሉና ድጋፉ የወረደ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ቡናው ለኮንትሮባንድ እየተዳረገ ይገኛል፤ ይህ ደግሞ አገሪቷ ማግኘት ያለባትን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረቱም ባሻገር ኢኮኖሚውን ይጎዳል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
ፍሬህይወት አወቀ