የኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ብሔራዊ ማሕበር የመመስረት እንቅስቃሴ ከ1949 ዓ.ም አንስቶ ሲደረግ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ። የመጨረሻ የምስረታ ሒደቱ ዕውን የሆነው ታኅሣሥ 23 ቀን 1952 ዓ.ም ነው። ማህበሩም የኢትዮጵያ ዕውራን ተራድዖ ሕብረት ድርጅት በሚል መጠሪያ እስከ 1973 ዓ.ም ዘልቋል።
ከ1973 ዓ.ም በኋላ የአሁኑ መጠሪያው የኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ብሔራዊ ማህበር ሆኗል። ጥቅል ዓላማው የዓይነሥውራንን ሰብዓዊ ክብር፣ መብትና ጥቅም ማስከበር ቢሆንም ይህንን ለማሳካት የሚያስችለው ጠንካራ አቅም የሌለውና በዓመት ከመንግሥት የሚያገኘው ድጋፍ በዓይነሥውራን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማቃለል ይቅርና በቅጥር ግቢው በቀን አገልግሎት ለሚያገኙት ከ 700 በላይ ዓይነሥውራን እንኳን በቂ አለመሆኑን የዛሬው ፍረዱኝ ባያችን ያብራራሉ።
ለችግሮቹ በርካታ ምክንያቶች መጥቀስ ቢቻልም አንዱ መነሻ ግን ማህበሩ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የተሰጠው ስፋቱ 30 ሺህ ሜትር ካሬ የሆነ ሕጋዊ ይዞታ ለሌላ ወገን ተላልፎ መሰጠቱ ነው።
የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሱልጣን ኢስሙ የማሕበሩ አባላት እየተንገላቱ ሳለ ቦታውን የወሰዱት ደግሞ ማህበሩ ቀደም ብሎ በይዞታው ላይ ያስገነባቸውን ቤቶች ለሆቴል፣ ለጋራዥና ለትልልቅ ንግድ አገልግሎቶች እያከራዩ ተጠቃሚ የሆኑት ናቸው።
እኛም ለዛሬ የቅሬታውን መነሻ፣ ደጋፊ የሰነድ ማስረጃዎችን እንዲሁም ሕጉ ምን ይላል ስንል ይዘንላችሁ የቀረብን ሲሆን፤ በቀጣይ ደግሞ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተለውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንዲሁም ቅሬታ የቀረበበትን አካል ምላሽ ይዘን እንደምንቀርብ ለመግለጽ እንወዳለን።
የቅሬታው መነሻ
ይዞታው በቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ለኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ብሔራዊ ማህበር የተሰጠ ሲሆን፤ ዓይነሥውራኑ እንዲደራጁና ሥራ እንዲሠሩ ከተፈቀደ በኋላ ግን በሒደት በይዞታው ላይ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ሌላ ማህበር መፍጠራቸውን የኋሊት በትዝታ ተጉዘው ሁኔታውን ያስረዳሉ። ይዞታውንም ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠሩት ያስታውሳሉ። በዚህም የዓይነሥውራንና አካል ጉዳተኞች ማቋቋሚያ ድርጅት (ዓአማድ) ለ15 ዓመት ተቋሙን እንዲያስተዳድር ከስምምነት ተደርሶ እንደነበር ይናገራሉ።
ከ15 ዓመት በኋላ ግን ራሱን ችሎ የማምረቻ መሣሪያዎችና ቦታ ኖረውት ተቋሙን ለቆ እንዲወጣ ከስምምነት መድረሳቸውንም በማከል። ለቆ ሲሄድም የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ለማሕበሩ ቀሪ እንዲሆኑ ስምምነት እንደነበር ነው አቶ ሱልጣን የሚናሩት። ሆኖም በስምምነቱ መሠረት ራሱን ሳይችል በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ድርጅቱ ከሰመ። ይህንን ተከትሎም በተቋሙ ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞችን ብሔራዊ ማህበሩ እንዲረከብ ጥያቄ ቀረበለት፤ይህ ደግሞ ከውል ውጪ ለውይይት የቀረበ አዲስ ሐሳብ በመሆኑ የገንዘብ አቅምም ስላልነበረ ማሕበሩ ሐሳቡን ለመቀበል እንደሚቸገር መግለጹን ያስታውሳሉ።
በዚህ ሒደትም ዓአማድ የተሰኘው ድርጅት ሙሉ በሙሉ ከሰመ። በመካከል በይዞታው ላይ ይሠሩ የነበሩ ዓይነሥውራን ሌላ ሕጋዊ ሠውነት ያለው ማህበር እንዳቋቋሙ ይናገራሉ።
ማሕበር ማቋቋማቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ብሔራዊ ማህበር በኋላም የኢትዮጵያ ዕውራን ተራድዖ ሕብረት ድርጅት መሆናቸውንና ብሎም ይዞታው ከመጀመሪያው ለእነርሱ እንደተሰጠ አድርገው ማቅረብ በመጀመራቸው ክርክሩ እንደተጀመረ ያስረዳሉ። በዚህ ደረጃ ያለና የተወሳሰበ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽም፤ በአሁኑ ወቅት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው በሁለቱ ሥም ተደርጎ መሠራቱ የመንግሥትን ሕግ የማስከበር አቅም ማጣት ብቻ
ሳይሆን የሕገወጥ ድርጊት አባሪና ተባባሪነት የሚያሳይ ነው ሲሉ ይኮንናሉ።
በሕግ ሥልጣን የተሰጠው አካል ሕገወጥ ድርጊቱን ለመቀልበስ ጥረት ከማድረግ ይልቅ የእኩይ ተግባሩ ተሳታፊ መሆኑን በአንድ ይዞታ ላይ በሁለት ተቋማት ሥም ተሠርቶ እንዲወጣ የተደረገው ካርታ አመላካች እንደሆነ ይናገራሉ። በሌላ በኩልም ይዞታው የብሔራዊ ማህበሩ መሆኑ እየታወቀ ካርታው ሳይመክን፣ በቦታው ላይ የሚገኙ ግንባታዎች ፣ ማህበሩ ያፈራቸው ንብረቶች ባሉበትና ውሳኔ ሳያገኙ ከሕግ ውጪ ለማይመለከተው አካል መብት መስጠት አግባብ አይደለም በማለት ያወግዛሉ። ‹‹እንዴት አንድ ንብረት ለሁለት አካል ይሰጣል?›› ሲሉም ይጠይቃሉ።
ዋና ሥራ አስኪያጁ ካርታው እንዴት እንደተሠራ ማሕበሩ ዕውቅና እንዳልነበረው በመግለጽ፤ አማራጩ የተወሰደው ማሕበሩ ጥያቄውን ለከተማ አስተዳደሩ በማቅረቡ እንደሆነ ያብራራሉ። በዚህም ጉዳዩን የሚያጠና ከፍትሕ፣ ከሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮና ሌሎች አካላት የተውጣጡ አካላትን ያቀፈ ኮሚቴ ተቋቁሞ ባጠናው መሰረት የንብረቱ ሕጋዊ ባለቤት እንደሆነ አረጋግጧል። ነገር ግን በቦታው ላይ ያሉ ዜጎችም ዓይነሥውራን በመሆናቸው ለእነርሱም መፍትሔ ሊበጅ ይገባል የሚል የውሳኔ ሐሳብ ቀረበ። መፍትሔ ተደርጎ የተወሰደውም ካርታን በሁለቱ ሥም መሥራት ነው። ይህ ተግባር ላይ ከመዋሉ በፊት በሠራተኛና ማሕበራዊ ጉዳይ ቢሮ አማካኝነት ውይይቶች መካሄዳቸውን የሚያስታውሱት አቶ ሱልጣን፤ ውሳኔው ሕጋዊ መሠረት የሌለው በመሆኑ ማሕበሩ አለመስማማቱን ገልጸዋል።
ማሕበሩ የተቃወመው በጋራ ሥም ይሠራ የተባለው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ጉዳይ በአሁኑ ወቅት ይዞታውን እየተጠቀመበት ላለው ወገን ደስታን የፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ በተጨማሪም በቦታው ላይ ያሉት ዓይነሥውራን በጣት የሚቆጠሩ ሲሆኑ፤ እየተጠቀሙ ያሉት በርካቶቹ ጉዳት አልባ መሆናቸውንም ነው የሚናገሩት። ጉዳዩን አስመልክቶ የሚመለከታቸው አካላት ጋር ቢያቀኑም “አንድ አይደላችሁ እንዴ?” የሚሉ ጥያቄዎች በፍትሕ አካላት ዘንድ እንደሚቀርብላቸው በማንሳት፤ ተከራካሪዎቹ ዓይነሥውር መሆናቸው የፍርድ ሒደቱን ማዛባቱን በኀዘን ይናገራሉ። ለፍርድ ቤት ክርክርም በአሁኑ ወቅት በይዞታው ላይ እየተጠቀመ የሚገኘው አካል የማህበሩን ማስረጃ እንደሚያቀርብ ይጠቁማሉ።
ማሕበሩ ፍርድ ቤት ይዞታውን የተመለከተ ካርታ በማቅረብ ክስ ሲመሠርት፤ ይህንን ወደጎን በማለት ይዞታው የማን እንደሆነ መረጃ እንዲሰጠው የልደታ ክፍለ ከተማን ይጠይቃል። የክፍለ ከተማው አስተዳደር የማን እንደሆነ እንደማያውቅ መረጃ እንደሰጠ በመግለጽ፤ ይህ እርስ በእርስ የሚጋጭ ሐሳብ ባለበት ደግሞ ፍርድ ቤቱ የክፍለ ከተማው አስተዳደር ይዞታው የማን እንደሆነ አላውቅም በማለቱ የመጠየቅ መብት እንደሌላቸው እንደገለጸላቸው ነው የሚያብራሩት። ይሁን እንጂ በአስተዳደሩ ሥር የሚገኝን ይዞታ የማን እንደሆነ አላውቅም ማለት ይቻላል ወይ? በማለት ይሞግታሉ። ያኛው ወገን ፍርድ ቤቱ እንደወሰነለት አድርጎ እንደሚቀርብና በአሁኑ ወቅት ይዞታውን በግፍ በመነጠቃቸው ፍትሕ እንደተዛባባቸው በመግለጽ ከማህበሩ ምስረታ ጀምሮ ያሉ ደጋፊ የሰነድ ማስረጃዎችን ያሳዩን ጀመር።
ክፍለ ከተማው ከዚያ በፊት ይዞታው ሰፊ በመሆኑ በ1998 ዓ.ም መጀመሪያ የጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ 15 ፎቅ ለመሥራት በጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ መሠረት ተወስዶ እንደነበር ያስታውሳሉ። በኋላም የከተማ አስተዳደሩ የፕሮግራም ለውጥ ማድረጉን በመግለጽ ከምስጋና ጋር ይዞታውን እንደመለሰላቸው ይናገራሉ። ነገር ግን ከሦስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ፍርድ ቤት ይዞታውን አስመልክቶ ላቀረበው ጥያቄ፡-
ሰነዶች
የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገሥት መንግሥት በአገር ግዛት ሚኒስቴር የሕዝብ ፀጥታ ጥበቃ ማህበሩ ለመመዝገቡ የምስክር ወረቀት መስጠቱን ያመለክታል። ሰነዱ የኢትዮጵያ ዕውራን ተራድዖ ሕብረት ድርጅት እንዲመዘገብ ግንቦት 13 ቀን 1959 ዓ.ም ለማህበሩ ቀርቦ ስለነበር በሕግ እንደተፈለገው መሆኑ ስለተረጋገጠ የማህበሩ መቋቋምና ስለዚሁ ጉዳይ የቀረበው የማህበሩ መመስረቻ ጽሑፍ ወይም የማህበሩ የውስጥ ደንቦች ተገቢ ያልሆነውን አንደኛውን ሠርዝ /ተገቢ/ የሚያደርገውን ተፈላጊዎች ሁሉ ፈጽሞ የተገኘ በመሆኑ በሕግና በመመሥረቻ ጽሑፉ እንዲሁም በውስጠ ደንቡ የተሰጠውን ዓላማ መብት ሥልጣንና ግዴታ እንዲኖረው ጳጉሜ 3 ቀን 1959 ዓ.ም መፈቀዱን ያትታል።
የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ስለማይንቀሳቀስ ንብረት አስመልክቶ የልደታ ወረዳ ግዛት የካርታ ቁጥር 14018 ስፋቱ 30 ሺህ ሜትር ካሬ የሆነ ይዞታ ለኢትዮጵያ ዕውራን ተራድዖ ሕብረት ድርጅት ማስተላለፉን የሚገልጽ ሰነድ ሌላው ከማህበሩ ያገኘነው ማስረጃ
ነው። ቦታው ከግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በስጦታ እንደተላለፈና በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት የማይንቀሳቀስ ንብረት ምዝገባ ክፍል ግንቦት 1955 ዓ.ም መመዝገቡን በወቅቱ ምክትል ከንቲባ በነበሩት ፊታውራሪ አርአያ ሥላሴ ዘለቀ ፊርማ ወጪ የተደረገው ሰነድ ያሳያል። ዋናው ካርታ ለመጥፋቱ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ መጋቢት 30 ቀን 1959 ዓ.ም በቁጥር 690 ማስታወቂያ ወጥቶ ተቃዋሚ ባለመቅረቡ ከቀሪው ካርታ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ግልባጭ (ኮፒ) ተደርጎ እንደተሰጠ አብራርቶ በሰነዱ አስቀምጧል።
የኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በሀገርና ሕዝብ ደህንነት ጥበቃ ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ደህንነት ጥበቃ ድርጅት በቁጥር ሀው9፣3/2/1/036/1006 በ30/4/1973 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ዕውራን ተራድዖ ሕብረት ድርጅት የላከው ደብዳቤ ሌላ የተመለከትነው ሰነድ ነው። በደብዳቤው የማሕበሩ መጠሪያ ሥም የኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ብሔራዊ ማሕበር እየተባለ እንዲጠራ መጠየቁን በማስታወስ፤ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ታኅሣሥ 4 ቀን 1973 ዓ.ም በቁጥር 2.በ/አ3/3/7 ለአገር ውስጥ ደኅንነት ጥበቃ ድርጅት መጻፉን ያትታል።
የማህበሩን የመተዳደሪያ ደንብ አንቀጾች ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችን በመጠቆም ለድርጅቱ መላኩን ደብዳቤው አስፍሯል። በዚህም መሠረት ከጥር 1 ቀን 1973 ዓ.ም ጀምሮ ማህበሩ የኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ብሔራዊ ማህበር ተብሎ እንዲጠራ መፍቀዱ በግልጽ ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ዓይነሥውራን ብሔራዊ ማኅበር ዘጠነኛ ጠቅላላ ጉባዔ 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ መጥራቱን የካቲት 13 ቀን 1984 ዓ.ም ከተያዘው ቃለጉባዔ መመልከት ችለናል። አስቸኳይ ስብሰባ ለመጥራት መነሻ የሆነው አጀንዳም በማኅበሩ ውስጥ የተፈጠረውና በማኅበሩ ሕልውና ላይ አደጋ ያስከተለ ሁኔታ ላይ መነጋገር በማስፈለጉ መሆኑን ቃለጉባዔው አስፍሯል።
የጠቅላላ ጉባዔው ከሁለት ወራት በፊት ባካሄደው ስብሰባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ስለቅሬታ አጣሪ ኮሚቴዎች መቋቋም የወጣው መመሪያ ማህበሩን የማይመለከት ከመሆኑም በላይ የአባላቱን ቅሬታ የሚያጣራና ስለማህበሩ ገንዘብና ንብረት ቁጥጥር የሚያደርግ አካል ያለ በመሆኑ የኮሚቴው መቋቋም እንደሚያስፈልግ መወሰኑን ያብራራል።
ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በጥቂት ዓይነሥውራን ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ለተለያዩ የመንግሥት አካላት ባቀረበው አቤቱታ መነሻነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት በተቋቋመው ብሔራዊ ቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ኃላፊ ዘንድ ማህበሩ ተጠርቶ ቻርተሩ ባጎናፀፈው የዴሞክራሲ መብት ተጠቅመው የፈለጉትን ኮሚቴ ሊያቋቁሙ እንደሚችሉ እንደተገለጸለት የተሰጠውን ማብራሪያ ቃለጉባኤው አስቀምጧል።
ከውሳኔው የተቋቋመው ኮሚቴ ሕጋዊ ባለመሆኑ በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት የአባልነት ግዴታቸውን ያሟሉ አባላት ብቻ ተሰብስበው ኮሚቴውን ማቋቋም ይገባቸዋል በሚል ለኮሚቴው ኃላፊ ማሕበሩ ማስረዳቱንና ተቀባይነት ማግኘቱን ሰነዱ ያመለክታል። በዚህም መነሻ 400 የሚጠጉ አባላት ተሰብስበው ከዚህ በፊት ከተመረጡት በተጨማሪ ሁለት ግለሰቦችን ጨምረው የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴው መቋቋሙን አስፍሯል። ኮሚቴውም ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ ማህደሮችን ሲያገላብጥ ከቆየ በኋላ ተፈጽሟል ለተባለው ጥፋት ተጨባጭ ማስረጃ ባለማግኘቱ የምርመራውን ሪፖርት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ልኮ ውሳኔ እንዲሰጥበት ከማድረግ ይልቅ ከ200 የማይበልጡ ዓይነሥውራን በመሰብሰብ በሕጋዊ መንገድ ተመርጦ በሥራ ላይ ያለው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ተወግዷል በማለት ይህንን ኮሚቴ የሚተካ የሽግግር ቦርድ የሚባል አካል ምርጫ ተካሂዷል።
ከምርጫው ሁለት ቀናት አስቀድሞ ምርጫው መካሄዱ የሚያስከትለውን ውጤት በመዘርዘር እንዳይካሄድ በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከማህበራዊ ጉዳይ ዘርፍ ምክትል ሚኒስትር ጋር ውይይት ተካሂዶ እንደነበር በቃለጉባዔው ላይ ተብራርቷል። ከዚያም ቀደም ሲል አንድ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን፤
ጥናቱን አጠናቅቆ ሪፖርቱን አቅርቧል። ነገር ግን በዚህ ሁሉ ጥረት የተገኘ ውጤት ባለመኖሩ ችግሩ ተባብሶ የማህበሩ ህልውና አደጋ ላይ እንደወደቀ በጽሑፉ ተቀምጧል።
የተደረገውን ሕገወጥ ምርጫ ተከትሎ ርክክብ እንዲፈፀም መጠየቁን በመጥቀስ፤ ማሕበሩም በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ጥቂት አባላት ሕገወጥ በሆነ መንገድ ለተመረጠ አካል በመላው ኢትዮጵያ በሚገኙ አባላት ሥም የተረከበውን ገንዘብና ንብረት ለማስረከብ የማይችል በመሆኑ ጉባዔ መጥራቱን ያብራራል። ከዚህ በኋላ በጉዳዩ ላይ የሚደረገው ውይይት ምን መልክ ይዞ መቀጠል አለበት በሚለው ላይ አባላት ውይይት ማድረጋቸውን በቃለጉባዔው ላይ ሰፍሯል።
በጠቅላላ ጉባዔ ላይ በነበረው ውይይት ማህበሩ ከፖለቲካ ነፃ ሆኖ የተቋቋመ እንደመሆኑ ከተቋቋመበት 1952 ዓ.ም ጀምሮ መተዳደሪያ ደንቡ ሲረቀቅም ሆነ የአባላት ምርጫ ሲካሄድ የማንም የፖለቲካ ኃይል ተፅዕኖ ወይም ጣልቃ ገብነት ስላልነበረው በተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ መነሻ መተዳደሪያ ደንቡ የሚሻርበት ምክንያት ያለመኖሩ፣ መተዳደሪያ ደንቡን መለወጥ አልያም መሻሻል የሚያስፈልግ ቢሆን እንኳ ደንቡ በሚያዘው መሠረት በጠቅላላ አባላት ፈቃድ የሚፈፀም እንጂ በጥቂት የአዲስ አበባ ዓይነሥውራን ያለመሆኑ፣ በጥቂቶች የተደረገው ምርጫ ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ መላ አባላትን በመናቅና ሕገወጥ በሆነ መንገድ ስለተካሄደ ምርጫም ሆነ በሌሎች የማሕበሩ የውስጥ ጉዳዮች ላይ የማህበሩ ጽሕፈት ቤት በሚገኝበት አካባቢ ካለው የቀጣና አራት ፀጥታ ጽሕፈት ቤት እና ከሌሎችም የፖለቲካ አካላት የሚተላለፉ ትዕዛዞች ቆመው ማህበሩ ግንኙነቱ በቀጥታ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ብቻ እንዲሆን መንግሥት ውሳኔ እንዲያሳልፍ፣ የጠቅላላ ጉባዔው በአንደኛው አስቸኳይ ስብሰባው ያሳለፈው ውሳኔ ተጥሶ ቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ መቋቋሙ ተገቢ ያለመሆኑ ታልፎ ለቅሬታ አጣሪ ኮሚቴዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ከተላለፈው መመሪያ ውጪ የተቋቋመው የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ከሥልጣኑ ውጪ የሽግግር ኮሚቴ ማቋቋሙ ሕገወጥ መሆኑ፣ ጥቂት ዓይነሥውራን በሕገወጥ መንገድ እየተሰበሰቡ በሕጋዊ መንገድ የተመረጠውን አካል እንዳስወገዱ በማድረግ ቦርድ የሚያቋቁሙ ከሆነ ማህበሩ አመራሩ የተዘበራረቀና ዕምነት የማይጣልበት ሆኖ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ በጎ አድራጊዎች የሚያገኘውን ድጋፍ እንዲያጣ በማድረግ በማህበሩ ስር የሚተዳደሩትን ሠራኞችና ተማሪዎች ጉሮሮ የሚዘጋ በመሆኑ፣ በጉባዔው ለሚተላለፉት ውሳኔዎች ለተፈፃሚነታቸው የመንግሥት እገዛ እንዲያገኙ አግባብ ላላቸው የመንግሥት አካላት የሚተላለፉ ቢሆንም ተገቢው ትኩረት ሳይሰጠው ከቀረ የማህበሩ ችግር ተባብሶ ከዚህ ደረጃ ላይ በመድረሱ ካሁን በኋላ የሚተላለፉት ውሳኔዎች በመንግሥት ዘንድ ክብደት እንዲያገኙ የሚሉ ነጥቦች በጉባዔው መነሳታቸውን ሰነዱ አስፍሯል።
በማህበሩ ላይ የተቃጣው አደጋ እየከፋ መሄዱን እንደሚያመለክት የጉባዔው አባላት መገንዘባቸውን የሚያብራራው ቃለጉባዔው፤ የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካይ ጉዳዩን ለሚመለከተው አካል በመግለጽ መንግሥት የጽሕፈት ቤቱን ሠላም እንዲያስከብርና ሥራውን በሠላም ማካሄድ እንዲችል ጥረት እንዲደረግ በጥብቅ ማሳሰቡንም ሰነዱ ያመለክታል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለሥልጣን ጉጉ በመሆኑ ለመልቀቅ ፈቃደኛ እንዳልሆነ አድርገው በማቅረብ የፖለቲካ ሠዎች ችግሩን ከዚህ አንፃር እንዲያዩት እያደረጉ መሆናቸው በጠቅላላ ጉባዔው ተነስቷል። በመሆኑም ደንቡ በሚፈቅደው መሰረት አጠቃላይ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረጉ ችግሩን ሊፈታው ስለሚችል በዚህ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
በነጥቦቹ ላይ በተደረገ ውይይት በደንቡ መሠረት አጠቃላይ ምርጫ መካሄዱ ለችግሩ መፍትሔ ሊሆን ስለሚችል በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ፣ በቅሬታ አጣሪ ኮሚቴው በተጠራ ስብሰባ በጥቂት የአዲስ አበባ ዓይነሥውራን የተቋቋመው የሽግግር ቦርድ ሕገወጥ ስለሆነ እንዲፈርስ፣ የመተዳደሪያ ደንቡ ይሻሻል የሚለው ጥያቄ ከሚሻሻለው አንቀጽ ጋር በአባላት ጥያቄ ከቀረበ ደንቡን የሚያሻሽሉ ሙያው ያላቸው ሠዎች በሥራ አስፈፃሚው ኮሚቴ ተመርጠው የደንቡ
ማሻሻያ ተዘጋጅቶ ለሚመረጠው ጉባዔ እንዲቀርብ፣ የማሕበሩን ጉዳይ በቅርብ በመከታተል ላይ የሚገኘው የቀጠና አራት ፀጥታ ጽሕፈት ቤት የጉባዔውን ውሳኔዎች ተረድቶ ለአፈፃፀሙ እንዲተባበር፤ በተለይ
የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለማህበሩ ሕልውና ልዩ ኃላፊነት ስላለበት ለምርጫው አፈፃፀም ተገቢውን እገዛ እንዲያደርግ መወሰኑን ሰነዱ ያትታል።
በመጨረሻም ጉባዔው በጉዳዩ ላይ በዝርዝርና
በጥልቀት በመወያየት አስፈላጊ ጥናቶችንም በማካሄድ በማህበሩ ሥር በሲቢኤም የሚረዱ ማዕከሎች ተለይተው ራሳቸውን ችለው እንዲተዳደሩ፣ ማዕከሎቹ የሚጠቀሙባቸውና ማህበሩ በባለይዞታነት የሚገለገል ባቸው የኢትዮጵያ ዓይነሥውራን አባላት ንብረት የሆኑ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ለአብነት መሬት፣ ሕንፃ፣ ዛፍ፣ ሣር፣ ወዘተ… የማህበሩ ንብረት ሆነው እንዲቆዩ፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ማዕከሎቹ በእነዚህ ንብረቶች ስለሚጠቀሙበት ሁኔታ አግባብ ካለው አካል ጋር በዝርዝር በመወያየት ሥምምነት እንዲፈራረም እንዲሁም የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለውሳኔው አፈፃፀም የረጂው ድርጅት ሲቢኤም ተወካዮች ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ሥርዓት ባለው መንገድ የሚከናወንበትን ሁኔታ እንዲያመቻች በሙሉ ድምፅ መወሰኑን ቃለጉባዔው ያብራራል።
በሌላ በኩል የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ እና የማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ባደረጉት ስብሰባ፤ የአመራር አካላቱ ምርጫ በአንድ ወር ውስጥ እንዲካሄድ፣ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የተካሄደው የሽግግር ኮሚቴ ምርጫ የመንግሥት ዕውቅና የማይሰጠው መሆኑ፣ የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴው በምርጫው ያገኘው ተጨባጭ ማስረጃ ቢኖር ይህንኑ በመመሪያው መሠረት ለሚመለከተው አካል እንዲልክ እንዲሁም ምርጫው ተጠናቆ ሕጋዊ ርክክብ እስከተከናወነ ድረስ አሁን በሥራ ላይ ያለው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሥራውን በሠላም መቀጠል ስላለበት ጽሕፈት ቤቱን በሕገወጥ መንገድ የያዙት ግለሰቦች በአስቸኳይ እንዲለቁ እንዲደረግ አግባብ ላላቸው የመንግሥት አካላት በመሥሪያ ቤቱ በኩል ጥያቄ እንዲቀርብ መወሰኑን ሰነዱ ያመላክታል።
ማህበሩ በአፍሪካ የሲቢኤም ኃላፊ ከነበሩት ሚስተር ቫይላድ ጋር ተፈጥረው በነበሩ ችግሮችና ጠቅላላ ጉባዔው ችግሮቹን ለመፍታት የሄደበት እርቀት ዙሪያ የተነጋገረ ሲሆን፤ በዚህም ኃላፊው ማዕከላቱ በውሳኔው መሠረት ከማህበሩ ሲለዩ በሚመርጡት አደረጃጀት ሌሎችንም የአካል ጉዳተኞችና ማየት የሚችሉ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ማጠቃለል በሚችል መልኩ ተደራጅቶ ዕርዳታውን ማግኘት እንደሚችል በሰነዱ ለመመልከት ችለናል።
ይህንን ተከትሎ ማህበሩ ከዓይነሥውራንና አካል ጉዳተኞች ማቋቋሚያ ድርጅት ጋር የዝውውርና የንብረት አጠቃቀም ስምምነት ማድረጉን የሚያሳዩ የሰነድ ማስረጃዎችን ተመልክተናል። በዚህም መሠረት የተቋቋመው የዓይነሥውራንና የአካልጉዳተኞች ማቋቋሚያ ድርጅት እየተባለ ይጠራ በነበረው ተቋማት መካከል ለ15 ዓመታት ፀንቶ የሚቆይ ውል መታሰሩን ሰነዱ ያመለክታል። በዚህም የሚንቀሳቀሱና የማይንቀሳቀሱ የንብረትና አባላት ዝርዝር ርክክብ መደረጉን ከማህበሩ ያገኘናቸው ሰነዶች ያመለክታሉ።
አዋጁ ምን ይላል?
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የከተማ ቦታን በሊዝ ስለመያዝ የወጣ አዋጅ ቁጥር 721/2004 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ የወጣውን ደንብና መመሪያ መሠረት በማድረግ ባለሞያዎችን በጉዳዩ ላይ አነጋግረናል። በሰጡን ምላሽም ሌላ ካርታ መሥራቱ ተገቢ ሆኖ ከተገኘ በቅድሚያ የመጀመሪያው የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ መምከን ይኖርበታል። ግን በአንድ ይዞታ ላይ ለሁለት ተቋማት የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ መስጠት እንደማይቻል ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
ሌላው ወገን
በአሁኑ ወቅት በይዞታው ላይ የሚገኙትና በማህበሩ ማስረጃ በመጠቀም አለአግባብ ተጠቃሚ ሆኗል በሚል ቅሬታ የቀረበበትን ሁለገብ የዓይነሥውራንና የአካል ጉዳተኞች ማሰልጠኛና ማቋቋሚያ የተሰኘውን ማህበር በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት በሚገኘው ይዞታ በመገኘት አነጋግረናል። ሆኖም በጉዳዩ ላይ ተወያይተው ምላሽ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑና በአሁኑ ወቅት የተሠራው ካርታ በሁለቱ ሥም መሆኑን ድርጅታቸው ተገቢ ነው ብሎ እንደማያምን በመግለጽ፤ የተደራጀ መረጃ አዘጋጅተው ሲጨርሱ ምላሽ እንደሚሰጡን አሳውቀውናል። በመሆኑም ከድርጅቱ መረጃውን እንዳገኘን ከሚመለከተው አካል ምላሽ ጋር አድርገን ለአንባቢያን እንደምናደርስ ማሳወቅ እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ሰኔ10/2012
ፍዮሪ ተወልደ