
አዲስ አበባ:- የቡሬ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ በመንግስትና በአልሚዎች ከሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች ጎን ለጎን መሰረተ ልማት የማሟላት ስራ እያከናወነ እንደሚገኝ ገለጸ።
የከተማዋ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዱኛው ጥላሁን በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ ኢንዱስትሪዎች ሲጠናቀቁ እስከ 400 ሺ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል ይፈጥራሉ፤ ኢንዱስትሪዎቹን ተከትሎ የሚመጣውን ዜጋ ሊሸከም የሚችል የመሰረተ ልማት የማሟላት ስራ እየተሰራ ይገኛል።
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፤ ከተማዋ የፌዴራል ኢንዱስትሪ ፓርክ የሚገነባባትና በክልሉ መንግስት የኢንዱስትሪ ዞን ተብላ የተመረጠች በመሆኗ፤ የተለያዩ ባላሀብቶች ሙዋለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ወደ ከተማዋ እየመጡ እንደሚገኙ ፤ ለኢንቨስተሮችና ለሰራተኞች ምቹ ለማድረግ በከተማዋ በመንግስትና በአልሚዎች ከሚገነቡ ኢንዱስትሪዎች ጎን ለጎን መሰረተ ልማቷን ለማሟላት እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ለአብነትም ከተማ አስተዳደሩ በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከአለም ባንክ በተገኝ 51 ሚሊዮን ብር 101 ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህ ውስጥ የመንገድ ጠረጋና ከፈታ፣ የኮብልስቶን ማንጠፍ፣ የጠጠርና የአስፋልት መንገድ ስራ፣ የመብራትና የውሃ መስመር ዝርጋታ እየተከናወነ እንዳለና ከግማሽ በላይ የሚሆኑትም መጠናቀቃቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
ኃላፊው ቡሬ ከተማ የዕድሜዋን ያህል ባታድግም
አሁን ላይ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ጠቁመው፤ በተያዘው በጀት ዓመት 56 ባለሃብቶች በተለያዩ ዘርፎች ለማልማት ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥ 33ቱ ለከንቲባ ጽህፈት ቤት ጥያቄያቸውን አቅርበው አስገምግመዋል ብለዋል።
ኃላፊው በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ለመገንባት ከአንድ ነጥብ አምስት እስከ 50 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 12 ባለሀብቶች በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ሙዋለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ከተማ አስተዳደሩ ይሁንታውን መስጠቱን ገልጸው፤ አልሚዎቹም ከተማ አስተዳደሩ የሰጣቸውን ይሁንታ ይዘው ወደ ዞንና ክልል በመሄድ የማጸደቅ ስራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላም በኩል የክልሉን የነዳጅ አቅርቦት ችግር ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትና በከተማዋ በአንድ ሺ 500 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ የነዳጅ ዴፖ በአንድ ባለሀብት እየተገነባ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልጸዋል።
ኃላፊው በአሁኑ ወቅት የቤት አቅርቦት ችግር ባይኖርም በቀጣይ በከተማዋ ከሚፈጠረውን የስራ እድል ጋር በተያያዘ ችግሩ እንዳይኖር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን መንግስት እንዲገነባ ከወዲሁ የከተማ አስተዳደሩ አመራር ጥያቄ ማቅረቡን ጠቁመው፤ አንድ ባለሀብት በግሉ ሪል ስቴት ለመገንባት ቦታ በመጠየቁ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ውሃና መብራት የከተማ ቁልፍ ችግር መሆኑን ኃላፊው ጠቁመው፤ ከተማ አስተዳደሩ ችግሩን ለማቃለል እየተጋ የሚገኝ ቢሆንም፤ የመብራት ችግር አገር አቀፍ ስለሆነ የፌዴራል መንግሥት ጉዳዩን እልባት እንዲሰጠው ጥያቄ ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
ሶሎሞን በየነ