
አዲስ አበባ፡- በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ስር በሚገኘው የሚሌኒየም ማገገሚያ ማዕከል ውስጥ ከኮሮናቫይረስ (ኮቪድ-19) ያገገሙ 87 ሰዎች ከማዕከሉ መውጣታቸው ተገለጸ።
የማዕከሉ ክሊኒካል ዳይሬክተር ዶክተር ውለታው ጫኔ በአሁኑ ወቅት በማዕከሉ ውስጥ 656 ኮሮናቫይረስ በምርመራ የተገኘባቸው ሰዎች ህክምናቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸው፤ ከነዚህ ውስጥ 157 ሰዎች የመጀመሪያ የላቦራቶሪ ምርመራ ውጤታቸው ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸውን (ኔጋቲቭ) ማሳየቱን፤ 87 ሰዎች ደግሞ ሙሉ በሙሉ አገግመው ዛሬ ከማዕከሉ እንዲወጡ መደረጉን ተናግረዋል።
ማዕከሉ 40 የጽኑ ሕሙማን መኝታዎችና 1 ሺህ
ጽኑ ያልሆኑ ሕሙማን ታካሚዎች አገልግሎት መስጠት የሚችል ሲሆን፤ የላቦራቶሪ፣ የመድኃኒት ቤት፣ የጤና ባለሙያዎች ልብስ መቀየሪያ፣ መታጠቢያዎችና ሌሎች ክፍሎች አሉት።
በተጓዳኝም ከማዕከሉ የጥበቃ ሠራተኞች ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት ባለሙያዎች ሥልጠና ተሰጥቷል ። በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ በምርመራ ከተገኘባቸው ሰዎች ውስጥ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ 620 ሰዎች ማገገማቸው ይታወቃል።
የአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ የኮቪድ-19 ህክምና ማዕከል ሆኖ ህሙማንን መቀበል የጀመረው ከግንቦት 25 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑ ይታወሳል።
ምንጭ፡- (ኤፍ.ቢ.ሲ)
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012