ምንም እንኳን ሶስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የአገሪቱን ሁለንተናዊ እርምጃና የፖለቲካ ጉዞ በበላይነት ሲዘውር የቆየ መሆኑ ቢነገርለትም፤ ከህዝቦች የመልካም አስተዳደርና ችግር ብሶትና የዴሞክራሲ ተስፋ መመናመን ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ህዝባዊ እንቢተኝነት የመጣውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ በሀሳብ አሸናፊ ሆኖ ወይም ተሸናፊነቱን አምኖና ልዩነትን አቻችሎ ከለውጥ ጋር መራመድ አቅቶት ራሱን የነጠለ ስለመሆኑ ሁሉም የሚገነዘበው ነው። በዚህ ሳይበቃውም የትግራይን ህዝብ ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ለመነጠል ዘርፈ ብዙ የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን በማሰራጨት ህዝቡ ተረጋግቶ ወደ ልማቱ እንዳይገባ፤ እንዲሁም ህልውናውን ለማስቀጠል ራሱን ከህዝብ ጋር አጣብቆ ለማቆየት ሰፊ ጥረት እያደረገ ስለመሆኑም ይነገራል።
በዚህ መልኩ የሚገለጸው ህወሓት ዛሬ ላይ ከህዝብ የተሰጠውን አንድ እድል በአግባቡ መጠቀም ካለመቻሉም በላይ ከትግራይ ህዝብ ከተነጠለ ህልውና እንደማይኖረውና የከፋ ችግር ሊደርስበት እንደሚችል በመስጋትም ህዝቡን ለከፋ አፈናና ጭቆና እየዳረገው ስለመሆኑም ይነገራል። ለዚህ ተግባሩም ያሉትን አማራጮች ሁሉ እየተጠቀመ ነው፤ አሁን ላይ ግን ሁሉ ነገር ተሟጥጦበት አንድ ጥግ ላይ ስለመቅረቱም ይገለጻል። ለመሆኑ የህወሃት ጉዞ ከትግራይ ህዝብ የትግል ጉዞና ዓላማ አንጻር እንዴት ይገለጻል? በአባላቱ የሚስተዋለው በተለያየ ምክንያት ከኃላፊነት እየለቀቁ ወደጥግ መኮብለልስ ከትግራይ ህዝብ ክብር አንጻር አንዴት ይታያል? በሚሉና ሌሎች ተያያዥ ክልላዊ እና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሑልሚካኤል ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ ይዘን ቀርበናል።
አዲስ ዘመን፡– የትግራይ ህዝብ የዘመናት ትግል ዓላማ እና ግብ ምን ነበር?
አቶ ነብዩ፡– አብዛኛውን ጊዜ የትግራይ ህዝብ ለምን እንደታገለ በግልጽና በእውነት ሲገለጽ አይታይም። ነገር ግን እውነታው ምንድን ነው ብለን ስንፈትሽ፤ የትግራይ ህዝብ የታገለው ለእኩል ተጠቃሚነት እና ለአገር ባለቤትነት ነው። ይሄ ምን ማለት ነው ከተባለም፤ የትግራይ ህዝብ በታሪኩ እንደምንረዳው ጉዞው ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ አገርን መስርቶ የመጓዝ፣ በዛ ላይ ደግሞ የተሻለ ተጠቃሚነትን እውን የማድረግ ጉዞ ነበረ እየተጓዘ የቆየው።
ይህ ህዝብም ከዚህ ሁሉ በኋላ ሊያካሂደው የሚችለው ትግል ምን እንደሚሆን ግልጽ ነው። ምክንያቱም አመጣጣችንና ታሪካችን ወደፊት በምን መልኩ መሄድ እንዳለብን የመወሰን አቅም ስላለው ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ለምንድን ነው የታገለው ስንል በግልጽ መቀመጥ ያለበት፣ የትግራይ ህዝብ ለእኩል ተጠቃሚነት እና ለአገር ባለቤትነት ነው የታገለው የሚለው ነው።
አዲስ ዘመን፡– በትግራይም ሆነ በሌሎች ህዝቦች የትግል ሂደት በተፈጠሩት ድርጅቶች ግንባርነት የተወለደው ኢህአዴግ ከድል ማግስት የነበረው ጉዞ ከትግራይ ህዝብም ሆነ ከኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የትግል ጉዞና ፍላጎት አኳያ እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ነብዩ፡– በኢህአዴግ መሪነት በተለይም ከድሉ ማግስት ያለው የ27 ዓመቱ ጉዞ በአጠቃላይ ሲገለጽ የዴሞክራሲ እና የልማት ተስፋ የታየበት ነው ተብሎ ሊገለጽ ይችላል። ነገር ግን ይህ የልማትና የዴሞክራሲ ተስፋ በትክክለኛው ጎዳና እንዲቀጥል የማድረጉ ወሳኝ ስራ ባለመሰራቱ በ27 ዓመቱ የተሰራው በጎ ስራ የተቀለበሰ እስኪመስል ድረስ ወደኋላ ያለበት እና የወደቀበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይህ ውድቀት የተፈጠረውም በየጊዜው መምጣት የነበረባቸው ለውጦች መምጣት ባለመቻላቸው ነው። አንድ ሀሳብ ላይ ተቸክሎ የመቆየት፣ መጀመሪያ አካባቢ ለድል ያበቃህን ሀሳብ ሁሌም ለድል እንደሚያበቃህ የማሰብ እና ቶሎ ያለመለወጥ የመቸከል ችግር ስለነበረ ነው።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ህዝቦች የተለያዩ ተጨማሪ ፍላጎቶችን እየፈጠሩ በመምጣታቸው ብሎም ጊዜውም በራሱ በዛኛው ወቅት በነበረው አካሄድ መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደረሰ። ይሄንን የህዝብ ፍላጎትም ሆነ የጊዜ ሁኔታ ማስተናገድ የሚችል መሪነትም
በመታጣቱ ህዝብ ለምሬት፤ በኋላም ደግሞ ለአመጽ እንዲነሳሳ አድርጓል። ስለዚህ በአጠቃላይ የ27 ዓመቱ ጉዞ የዴሞክራሲ እና የልማት ተስፋ ጭላንጭል የታየበት፤ ነገር ግን መስተካከልና መሻሻል ያለባቸው ነገሮች በጊዜ ባለመሻሻላቸው ሂደቱ የተቀየረበትና አሁን በንጽጽር በጣም አዲስ የሚባል ምዕራፍ ላይ እንድንደርስ ያደረገ ነው። የህዝቡ በተለይም የወጣቱ ንቅናቄ ደግሞ ትልቅ ለውጥ አስከትሏል።
አዲስ ዘመን፡– የህዝቡን ንቅናቄ ተከትሎም ቢሆን ከ27 ዓመታት የኢህአዴግ ጉዞ በኋላ ከሁለት ዓመት በፊት አገራዊ ለውጥ እውን ሆኗል። ይህ ለውጥ የህዝቦችን ጥያቄና ፍላጎትን መሰረት ያደረገ ነው ብለው ያምናሉ? እንዴት?
አቶ ነብዩ፡– ይህ የመጣው አገራዊ ለውጥ በህዝቦች ፍላጎትና በህዝቦች ግፊት የተፈጠረ መሆኑ ለሁላችንም ግልጽ ነው። በኢህአዴግ ውስጥም ለውጥ ይፈልግ የነበረ ኃይል ይሄንን የህዝብ ስሜትና እንቅስቃሴ በደንብ ተገንዝቦ ለማስተናገድ በመቻሉ አገራዊ ለውጡ እንዲወለድ ሆኗል። ስለዚህ ህዝቡ በነቂስ ወጥቶ ለውጥ እንደሚፈልግ ፍላጎቱን የገለጸበት እንደመሆኑ ሁሉ ለውጡ ሙሉ በሙሉ ህዝባዊ ነበረ ማለት እንችላለን።
ይሄም ኢህአዴግ ወደ 98 በመቶ አሸነፍኩ ባለበት ማግስት መሆኑ ምን ያህል ስር የሰደደ የዴሞክራሲ፣ የመልካም አስተዳደር ክፍተት እንደነበረ እና ህዝቡም በትክክል ችግሩን ሲያብላላው ቆይቶ በመጨረሻ መፍትሄ ሲያጣ በኃይል ለውጡ እንዲፈጠር ወደማድረግ መሄዱን ማሳያ ነው። እናም ለውጡ ሙሉ በሙሉ ህዝባዊ ንቅናቄ የተደረገበት ሲሆን፤ ለውጡም ህዝባዊ ነው። ስለዚህ ለውጡ እውነተኛ የህዝቦችን ተሳትፎ ያሳየ፤ የህዝቡንም ፍላጎት ያንጸባረቀ ሲሆን፤ የመጣው አዲሱ የለውጥ አመራርም የህዝቡ ፍላጎት የወለደው መሆኑ ግልጽ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ከለውጡ ማግስት ህወሓት ወይ ራሱን አርሞ ካልሆነም ልዩነቶቹን አቻችሎ ከለውጡ ጋር መጓዝ ተስኖት ለብቻው መቆሙ ከምን የመነጨ ይመስሎታል?
አቶ ነብዩ፡– የህወሓት ከአገራዊ ለውጡ ማፈግፈግ ግትርነት እና ራስ ወዳድነት የወለደው ነው። እኔ ካልመራሁ፣ እኔ ይበልጥ ካልተጠቀምኩ፣ እኔ ገዝፌና ተልቄ ካልታየሁ ማለት እንደ አገር የሚያስኬደን ነገር አይደለም። ይህች አገር የሁላችንም ነች። ብዙ የፖለቲካ ኃይሎች ያሉ እንደመሆኑም እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎችም አማራጭ ሀሳባቸውን አቅርበው ህዝቡ የሚመርጣቸው ከሆነ በህዝቡ ፍርድ የሚሆን ይሆናል። ነገር ግን የህወሓት እኔ በበላይነት፣ በአንባገነንነት የማልመራው አገር አገር አይደለም ይፈርሳል፤ ለውጡም ትክክለኛ ለውጥ አይደለም ብሎ መንቀሳቀስ በጣም አሳፋሪ ተግባር ነው።
ህወሓት ማድረግ የነበረበትም የለውጡ አካል ሆኖ የትግራይ ህዝብ ትክክለኛ ፍላጎትም እኩል ተጠቃሚነት እና የአገር ባለቤትነት ብሎም የሁሉም ህዝቦች እኩልነት ተከብሮ በእኩልነት የምንኖርባት አገር ማድረግ ነበር። ለዚህ በትክክል ቆርጦ ተነስቶ ቢሆን ኖሮ እኩልነትን ተቀብሎ መቀጠል ነበረበት። በመሆኑም ራሱን ከለውጡ ማግለሉ በእኩልነት እንደማያምን የሚያሳይ ተግባር ነው። ምክንያቱም ህወሓት ትግሉ ሲወለድም ሆነ በለውጡ ሂደት ተሳታፊ ነበረ። መጨረሻ ላይ ግን የእኔን ልዕልና አያረጋግጥም በማለት ነው ትቶት የሄደው።
ስለዚህ ይሄ የማፈግፈግና የመፈርጠጥ ተግባር በተለይ የትግራይን ህዝብ እየመራሁ ነው ከሚል ኃይል የሚጠበቅ አልነበረም። ተግባሩም የትግራይ ህዝብን ክብር የሚነካ፤ የትግራይ ህዝብን የትግል ዓላማም የረሳና የካደ፤ የትግራይ ህዝብን ታሪክ ያላወቀ፤ በመቻቻልና በእኩልነት የምንኖርባትን አገር መጻኢ እድሏን በደንብ ያለመገንዘብ፤ በጣሙን ራስ ወዳድነት ያጠቃውና ግትርነት የተሞላበት አስተሳሰብና አካሄድ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ህወሓት ከለውጡ ራሱን ማግለሉን ተከትሎ በርካታ የህወሓት አመራሮች ከድርጅቱ ራሳቸውን በማግለል ላይ መሆናቸው፤ በርካቶችም ወደ ብልጽግና እየገቡ መሆናቸው እየታየ ነው። በእርሶ እምነት ይህ ለምን እየሆነ ያለ ይመስሎታል?
አቶ ነብዩ፡– ቀደም ብሎ በተወሰነ መልኩ ለመንካት እንደሞከርኩት፣ ለውጡ በህዝብ ግፊት የመጣ፣ የህዝብ ፍላጎትና ብሶት የወለደው ለውጥ ነው። ይህ ሲባል በአመራሩ ውስጥም ለውጥ የሚፈልግ ሀይል ነበረ። ይህ
ለውጥ ፈላጊ አመራር ደግሞ የህዝቡን ስሜት ያዳመጠ ሲሆን፤ ለውጥ ያስፈልገናል፣ ትክክለኛ መንገድ ላይ አይደለንም፣ ህዝባችን እስኪነግረንና ይሄም በአመጽ እስኪገለጽ ደረስ መጠበቅ የለብንም የሚል ነበር። እንደ መሪም ለውጥ የሚያስፈልገን በየትኛው ሰዓት ምን መደረግ እንዳለበት የማወቅና የመምራት ኃላፊነቱ የእኛ ስለሆነ ለውጥ ያስፈልገናል የሚል ኃይል ነበረ። የህዝቡ ግፊትም ሲመጣ ያስተናገደው ይሄው ኃይል ነው።
ስለዚህ በህወሓትም በተመሳሳይ መልኩ ለውጥ የሚፈልጉ፣ በትክክልም ለህዝብ አጀንዳ የሚቆሙ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እንዳሉ ይታወቃል። ከዚህ አኳያ አገራዊ ለውጡ ሲመጣ እና ህወሓት እንደ ድርጅት ከአገራዊ ለውጡ ራሱን ሲያገልል በውስጡ ያሉ ለውጥ ፈላጊ አመራሮች ለመወሰን ትንሽ ተቸግረው ቆይተዋል። አሁን ግን ሁሉም ነገር ግልጽ እየሆነ ስለሆነ እና የህወሓትም መንገድ ወዴት እንደሆነ ብሎም የአገራዊ ለውጡ መንገድ ደግሞ ወዴት እንደሆነ ግልጽ እየሆነ ስለመጣ ለመወሰን የማይቸገሩበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
አሁን እንደሚታየውም በግልጽ አገራዊ ለውጡን እንደሚደግፉ፣ የህወሓትም መንገድ ልክ እንዳልሆነ እና ከአገራዊ ለውጡ ጎን መቆም እንዳለባቸው አምነው በግልጽ ወደ አገራዊ ለውጡ መቀላቀል ጀምረዋል። ይህ የሚያሳየው ደግሞ በህወሓትም የለውጥ ኃይል መኖሩን ሲሆን፤ ይሄን የለውጥ ኃይል የማየት፣ የማበረታታትና የመሳብ ስራው ደግሞ አገራዊ ለውጡ ውስጥ ያለው ኃይል ግዴታ ይሆናል። ይሄው ስራም በዚህ መልኩ ተሰርቶም ህወሓት ጋ የነበሩ አመራሮችም ወደ አገራዊው ለውጡና የብልጽግና ጉዞው እየተቀላቀሉ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በዚህ መልኩ የለውጡን ጉዞ የደገፉና የተቀላቀሉ የህወሓት አመራሮች የመኖራቸውን ያህል፤ አሁንም ህዝቡን እንደ ከለላ ተጠቅመው በህዝቡ ውስጥ ያሉ የህወሓት ቡድኖች ከትግራይ ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት አንጻር እንዴት የሚገለጹ ናቸው?
አቶ ነብዩ፡– እኛ ማዕከል አድርገን የምንሰራው የትግራይ ህዝብን ስለሆነ፤ የትግራይ ህዝብ ምን እየሰራ ነው? ምንስ እያደረገ ነው? የሚለው በግልጽ መቀመጥ ስላለበት በዛ ልጀምር። ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ የትግራይ ህዝብ ምንድን ነው እያደረገ ያለው? ካልን፤ መልሱ፣ የትግራይ ህዝብ ባለፉት ሁለት ዓመታት አገርን ነው እያዳነ ያለው የሚል ነው። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብም የራሱን እርምጃ ከወሰደ ወይም ደግሞ በዛ ፍጥነት አገራዊ ለውጡን ደግፎ ከወጣ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ግልጽ ስላልሆነ ነገሮችን ሰከን ብሎ የማየት ስራ ነው እየሰራ ያለው።
ምክንያቱም ህወሓት ቀላል ኃይል አይደለም፤ ይህንን ሀይል በአንድ እርምጃ ጥግ ማስያዝ ስለማይቻል እና ብዙ መዘዝ ሊያመጣ ስለሚችል ነገሮች በስክነት ታይተው አገራዊ ለውጡ ወዴት እየሄደ ነው? ህወሓትስ ምን ማድረግ ይችላል? የሚሉ ነገሮችን ሚዛን ላይ አስቀምጦ ነገሮችን በሰከነ መንገድና በጥሞና እየተመለከተ ነው ያለው። ይህ ተግባሩ ደግሞ አገር የማዳን ተግባር ነው። ምክንያቱም ሁሉም መውሰድ የሚችለውን እርምጃ ወደመውሰድ ከገባ የለየለት ምስቅልቅል ሊፈጠር ይችላል። ስለዚህ አንዱጋ ሞቅ ሲል አንዱጋ ትንሽ ቀዝቀዝ ማለት ካልቻለ እና ሁሉም ከጋለ ምን ሊፈጠር፣ ምንስ ሊፈነዳ እንደሚችል አይታወቅም።
እናም የትግራይ ህዝብ ነገሮችን በጥሞና እያየ፣ እየተመለከተ ነው ያለው። ይህ ጥሞናውም አገር የማዳኛ ትልቅ መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ ቆይቷል። በዚህ አጋጣሚም የትግራይ ህዝብ ትልቅ ምስጋና የሚገባው ህዝብ ነው። የትግራይ ህዝብ ነገሮችን በጥሞና ይመለከታል ማለት ግን፤ የትግራይ ህዝብ መጥፎ ነገር ይሸከማል ማለት አይደለም። መጥፎና ጥሩውን ለይቶ መሄድ እንዲችል እና ለመወሰንም እንዲመቸው እርምጃውን በስክነት የሚከውን መሆኑን የሚያሳይ ነው። ይሄ ስክነቱም ለአገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ሊሰመርበት ይገባል።
እዚህ ጋ ልብ ሊባል የሚገባው የትግራይ ህዝብ በአጋጣሚው ለህወሓት ተጨማሪ እድል እንደሰጠው ለሁላችንም ግልጽ ነው። ህዝቡ ይሄን ሲያደርግም ምናልባት ከውድቀታቸው ተምረው በተሻለ ሀሳብና አካሄድ በመጓዝ የአገርን ህልውና እና የትግራይን ህዝብ ተጠቃሚነትም ያስጠብቃሉ የሚል ተስፋ ኖሮት ነበር አንድ ተጨማሪ እድል ለመስጠት የቻለው። ነገር ግን ህወሓት ይሄንን እድል መጠቀም አልቻለም። ይልቁንም አሁንም በባሰ መልኩ አምባገነንነቱንና ኃላፊነት የጎደለው ተግባሩን፣ ብዝበዛውን፣ የመልካም አስተዳደር እጦቱን፣ ሁሉንም ነገር ወደባሰ ደረጃ እየወሰደው ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ለህወሓት የሰጠው አንድ የመጨረሻ እድል እንዳበቃለት አሁን ግልጽ ሆኖ በተለያየ መልኩ በትግራይ ውስጥ የህዝብ እንቢተኝነት፣ የወጣቶች አመጽ እየታየ ነው ።
ይሄ ደግሞ ህወሓት በምንም መልኩ አንድ ሺ እድል እንኳን ቢሰጠው መሻሻልና መለወጥ የማይችል ቡድን መሆኑን እና በፍጥነት በአዲሱ ትውልድ ኃይል መተካት እንዳለበት ግልጽ የሆነበት ሁኔታ ነው። ስለዚህ ህወሓት የትግራይ ህዝብን የሚከስበትም የሚያገለግልበትም አቅምም ሆነ ፍላጎት ከዚህ በኋላ የለውም። የትግራይ ህዝብም አንድ እድል ብቻ ነበር የሰጠው፤ ያ እድልም እንደባከነ ለሁላችንም ግልጽ ስለሆነ በቀጣይነት የአዲሱ ትውልድ ፓርቲዎችና ኃይሎች ወደ ኃላፊነት እንዲመጡ ህዝቡ ትልቅ የሆነ ፍላጎት እያሳየ ነው ።
አዲስ ዘመን፡– የቀረው የህወሓት ስብስብ ዛሬ ላይ በሀሳብ ማሸነፍ ወይም የሀሳብ ተሸናፊነታቸውን አምኖ መቀበል ተስኗቸው በህዝቡ ጉያ ተሸሽገው መቐሌ ያሉ መሆናቸው ሳያንስ፤ የትግራይ ህዝብና ወጣት ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በጥርጣሬ ዐይን እንዲተያይና በስጋት እንዲኖር የሚያደርጉ ፕሮፖጋንዳዎችን ማሰማት የእለት ተዕለት ስራቸው ሆኗል። በዚህ ላይ እርሶ ምን ይላሉ?
አቶ ነብዩ፡– ስለ መሸሸግ ካወራን የትግራይ ህዝብ ህወሓትን የመሸሸግ ፍላጎት የለውም። እንደዛ አይነት ተግባርም ከዚህ በፊት አልፈጸመም። የትግራይ ህዝብ ቅድም እንዳልነው ነገሮችን በስክነት ለመመልከት ጽሞና ላይ ነው ያለው። ህወሓትም ከትግራይ አብራክ የተገኘ እንደመሆኑ መጠን አንድ ተጨማሪ እድል ይሰጠው በሚል የህዝብ ውሳኔ እስካሁን ዋና ኃይሉን መቐሌ ላይ አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ነው። ስለዚህ ስለ መሸሸግ ስናወራ ምናልባት ህወሓት ተሸሽጎ ሊሆን ይችላል፤ የትግራይ ህዝብ ግን ህወሓትን እንዲሸሸግ ፈቅዷል ወይም አድርጓል ለማለት ግን በጣም አስቸጋሪ ነው። ከዚህ አኳያ መሸሸግ ስንል በደንብ ግልጽ መሆን አለበት።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የትግራይ ህዝብ እና ህወሓትም የተለያዩ ናቸው። አንድን ህዝብ ፓርቲ ነው ብሎ ከአንድ ድርጅት ጋር እኩል ነው ማለት በራሱ ስድብ ነው፤ ወንጀልም ነው። ምክንያቱም ህዝብ ህዝብ ነው፤ ህዝብ ደግሞ በሚገባው ክብር ነው እንጂ መገለጽ ያለበት፤
በአንድ ድርጅት በቀጥታ መገለጹ በጣም አስከፊ ነው። ኢ-ሳይንሳዊ ከመሆኑም በላይ፤ ስልጡን የሆነ አገላለጽም አይደለም፤ የህዝቡን ክብርም የሚነካ ነው። ከዚህ አንጻር ተመልክቶም የሚሸሸግና ሸሻጊም ያለ መስሎ መታየት የለበትም።
ከዚህ ባለፈ ግን ህወሓት የመጨረሻውን እድል አግኝቶ፣ ያንንም አባክኖ አሁን ጥልቅ በሆነ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነው። ከዚህ በኋላም ኢትዮጵያ ውስጥ ለህወሓት የሚሆን የፖለቲካ እድል እንደሌለ፤ ህወሓትም የፖለቲካ ኃይል ሆኖ መቀጠል የሚችልበት እድል ከዜሮ በታች በመሆኑ የቀቢጸ ተስፋ የፕሮፖጋንዳ ስራ ላይ ተሰማርቷል። ይሄንን ስራም ህወሓትን የሚነካ አጀንዳ በመጣ ቁጥር የትግራይ ህዝብን እንደሚነካ፣ ትግራይን አደጋ ውስጥ ለመክተት እንደታሰበ ተደርጎ በጣም ከፍተኛ የሆነ አውዳሚ ፕሮፖጋንዳ እየነዛ ነው ።
ይህ ፕሮፖጋንዳም እጅጉን ኃላፊነት በጎደለው መልኩ እየተካሄደ ነው። ተግባሩም የቀቢጸ ተስፋ ምልክትም ነው። ከትግራይ ህዝብ ጉያ ከወጣሁኝ ምንም የሚረባ ነገር አይጠብቀኝም ወይም ከፍተኛ አደጋ ይጠብቀኛል ከሚል ጥልቅ ፍርሃት የመነጨ የቀቢጸ ተስፋ ፕሮፖጋንዳ ነው። ይህ ደግሞ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም። ለህዝብም የሚጠቅም አይደለም። ለልማት አጀንዳችንም ሆነ ለብልጽግና ጉዟችን የሚጠቅም አይደለም። ለአገርም፣ ለምንም የሚጠቅም አይደለም። ለራሳቸውም የሚጠቅማቸው ነገር አይደለም።
የሚጠቅማቸው ነገር ተቀራርበውና ተደራድረው ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ነው። ከዚህ ውጪ የማያዋጣ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት፤ ህዝብ በማደናገር እና ሽብር በመንዛት የሚኬድ ጉዞ ሊኖር አይችልም። የትግራይ ህዝብም አሁን ይሄን በጥንቃቄ ተመልክቶ አውቆታል። ምን አይነት ፕሮፖጋንዳ እየተነዛ እንደሆነና ምን ያክል ውሸት እንደሆነ ከዚህም ባለፈ ትክክለኛው ምስል ምን እንደሆነ በደንብ ግልጽ እየሆነለት ነው። በከፍተኛ ንቃት ውስጥም ነው የሚገኘው። የኢትዮጵያ መንግስትም ሆነ ብልጽግና ፓርቲም ከትግራይ ህዝብ ጋር ምንም አይነት ተቃርኖ እንደሌለው፣ ሊኖረውም እንደማይችል ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም በፓርላማ መግለጫቸው ላይ በግልጽ አስቀምጠውታል። ስለዚህ ህወሓት የሚነዛው ፕሮፖጋንዳ የቀቢጸ ተስፋ እንደሆነ፤ እና ይሄም ምንም አይነት ውጤት ሊኖረው እንደማይችል ተገንዝበው ከዚህ ድርጊታቸውም በቶሎ መቆጠብ ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን፡– አሁን በክልሉ ባለው የህወሓት አገዛዝ የትግራይ ህዝብና ወጣቶች አዲስ ሀሳብ የማድመጥ ብሎም የማመንጨትና አቅርቦ የመታገል ነጻነት በምን ደረጃ የሚገለጽ ነው?
አቶ ነብዩ፡– የትግራይ ህዝብ ሁሌም ለውጥ ሲፈልግ የሚኖር ህዝብ ነው። የተሻለ ነገር ሲኖርም ቶሎ ብሎ ለውጥን የማስተናገድ ባህል ያለው፤ በጣም ተራማጅ የሚባል ህዝብ ነው። ስለዚህ ይህ ህዝብ ባህሉና ታሪኩ ይህ ሆኖ ሳለ፤ ባጠቃላይ ባለፉት 45 ዓመታት ህወሓት እኔ ከምነግርህ ውጪ ምንም አይነት ሀሳብ መስማት የለብህም፤ የእኔ መንገድ ብቻ ነው ትክክለኛ መንገድ በማለት በጣም አፋኝና ጨቋኝ የሆነ ስርዓት ዘርግቶ አዳዲስ ሀሳቦች እንዳይወጡ፤ አዲሱ ትውልድ ለኃላፊነት ዝግጁ እንዳይሆን፤ ኃላፊነት መውሰድ እንደሚችልም እንዳያምን እየተደረገ፤ ህዝቡም ከህወሓት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌለው እስኪያስብ ድረስ አማራጮች እየጠፉና እየተደፈጠጡ፤ አማራጭ ሀሳብ ይዘው የሚመጡ ሰዎችም ለከፋ እንግልት እና ለህይወት መስዋዕትነት ሁሉ እየተዳረጉ ቆይተዋል። ይህ በግልጽ እንደሚታየው የአፈናና የአምባገነንነት ስርዓት ተግባር ነው።
አሁንም ይሄው ተመሳሳይ ዝንባሌ በህወሓት ዘንድ አለ። ነገር ግን ህዝቡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ለውጥ እንደሚያስፈልግ እና ለዚህም ትክክለኛው ሰዓት እንደሆነ፤ ከዚህ በፊትም የነበረው አካሄድ በጣም አፍራሽ እንደሆነ በመገንዘብ የለውጥ ፍላጎትን በግላጭ ወደመግለጽ እየተሸጋገረ ነው። ከእነዚህ ኃይሎች መካከል እኛም እንደ ትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አንድ ተጠቃሽ ኃይል ነን። ምክንያቱም ለውጥ ያስፈልገናል፤ የተለያዩ ሀሳቦችና አማራጭ መንገዶች ያስፈልጉናል።
ዞሮ ዞሮ የምንፈልገው ግብ ህዝብን በእኩልነት ተጠቃሚ ለማድረግ እስከ ሆነ ድረስ በተለያየ መንገድም
ብንጓዝና ብንታገል ችግር የለውም በሚል ይሄንን አዲስ ሀሳብና አዲስ ኃይል የመፍጠር ተግባር እኛም እንደ ትግራይ ብልጽግና ፓርቲ እየሄድንበት ነው። ብዙ ለውጥም የፈጠርንበት ነው። ህወሓት ግን አሁንም ከእሱ ውጪ ሌላ ኃይል እንዳይኖር እና አማራጭም እንዳይኖር የማፈን ተግባር እየሰራ ነው። ነገር ግን ሂደቱን ማንም ሊያስቆመው አይችልም። ምክንያቱም የትውልዶች ሂደት ነው። አዲሱ ትውልድ ወደኃላፊነት መምጣትና የተሻለ አማራጭ ይዞ የመታገል አዝማሚያ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ገብቶ በሁላችንም እየተበረታታ ነው ።
አዲስ ዘመን፡– ለውጡን ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ከሰሞኑ በገዛ ፈቃዳቸው ኃላፊነታቸውን መልቀቃቸውን መግለጻቸው ይታወቃል። ወይዘሮዋ ከኃላፊነት መልቀቃቸውን የገለጹበትን መንገድ እርሶ እንዴት አዩት? ከኃላፊነት መነሳታቸውስ በፌዴሬሽኑ ስራ ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ አለ ብለው ያምናሉ?
አቶ ነብዩ፡– የወይዘሮ ኬሪያ ተግባር ዞሮ ዞሮ የትግራይ አጀንዳ ስለሆነ በትግራይ አጀንዳነት እኔም ሀሳብ መስጠት በምችልበት ደረጃ ብቻ የተወሰነ ሀሳብ እሰጣለሁ። የወይዘሮ ኬሪያ ተግባር ቅሌትና እብደት የተቀላቀለበት ነው። ምክንያቱም ህዝብና መንግስት አምኖና አክብሮ ትልቅ ኃላፊነት ሰጥቶ እና እርሳቸውም ኃላፊነቱንም አክብረው ተቀብለው እየሰሩ ቆይተው፤ በድንገት አጀንዳቸውን፣ ሀሳባቸውንና የልዩነት ነጥባቸውን እንኳን ግልጽ አድርገው ህዝብ እንዲያውቀውና እንዲወያይበት፤ መፍትሄም እንዲገኝበት ባልተደረገበት ሁኔታ ዝም ብሎ ትልቅ ኃላፊነትን በንቀት መተው ተገቢ አይደለም። ለምን ቢባል ያ ኃላፊነት ከህዝብ የተቀበሉት ነው። ምክንያቱም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወከልበት አንዱ ምክር ቤት ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ህዝብን ኃላፊነት እንደ ዋዛ ዝም ብሎ ጥሎ መፈርጠጥ በጣም አሳፋሪ ነው።
በተለይ ወይዘሮዋ የህወሓት አባል እንደመሆናቸው እና ህወሓትም የትግራይን ህዝብ አስተዳድራለሁ እንደማለቱ መጠን፤ ተግባሩ የትግራይ ህዝብን ክብር የሚነካ ነው። በተለይ ህዝብን እንዲያገለግሉም የመንግስትነት ቦታውን የተቆናጠጡ ሰዎች በዚህ መልኩ ኃላፊነታቸውን ችላ ሲሉ፣ ለህዝብም ክብር በማይመጥን መልኩ ስራ ጥሎ መፈርጠጥና መኮብለል በጣም አሳፋሪ ተግባር ነው። ወይዘሮ ኬሪያ የልዩነት ሃሳብ እንኳን ቢኖራቸው ሀሳባቸውን አንስተው መሟገት ይችሉ ነበር። ለዚህም ዴሞክራሲያዊ የሆነ ስርዓት አለ። የኃላፊነት ደረጃቸውም የተሻለ ተደማጭነት ያለው በመሆኑ ደጋፊም ሊያፈሩ ይችሉ ነበር።
ምክንያቱም ሁላችንም ሀሳብ እንፈልጋለን፤ ለዚህች አገር የተሻለ ከሆነ ደግሞ የእርሳቸውንም ሀሳብ ተቀብለን የመተግበር የሁላችንም ሚና ሊሆን ይገባል። ነገር ግን ሆን ብሎና ዝም ብሎ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ የህዝቦችን ክብር በሚነካ መልኩ፤ የራስን የግለሰብን ክብርም ሆነ የፓርቲን (የህወሓትን) ክብርም በሚነካ መልኩ መኮብለል በጣም አሳፋሪ ተግባር ነው። ሂደቱም በጣም የተሳሳተ ፤ ራስን በራስ ማጥፋት ተብሎ ሊገለጽ የሚችል፣ በወንጀልም የሚያስጠይቅ ነው። ምክንያቱም በክብር የተቀበልከውን ትልቅ ኃላፊነት በክብር እና በተገቢው መልኩ ነው ማስረከብ ያለብህ እንጂ ዝም ብሎ አለምክንያት በመኮብለል መሆን የለበትም።
እናም ሂደቱ በጣም የተሳሳተ ነው። ለህወሓትም ትልቅ ዋጋ ያስከፍላል። የውድቀታቸው መጨረሻ ይሄ መሆኑንም ያሳያል። ውድቀትንም እንደ ባህል አጎልብተው የያዙት መሆኑንም ያሳዩበት ነው። በመሆኑም ተግባሩ በፓርቲው ውስጥ መፈርጠጥ፣ መውደቅ እንደ ባህል ጎልብቶ ያለ መሆኑን በግልጽ ማሳያ ሆኗል። ከዚህ ባለፈ ግን የወይዘሮ ኬሪያ ኃላፊነት መልቀቅ በፌዴሬሽኑ ስም፣ ዝናና ስራ ላይ የሚያመጣው ተጽዕኖ በፍጹም ሊኖር አይችልም። ምክንያቱም ይሄ የግለሰብ ቅሌትና ውርደት ነው፤ ምናልባት ከዛም ከፍ ካለ የህወሓት ውድቀትና ቅሌት ነው።
ከዚህ ውጪ ግን ፌዴሬሽኑ እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ አክብሮና ህወሓትም አንድ ኃይል እንደመሆኑ ከህወሓትም አገር ማገልገል የሚችሉ አሉ ብሎ አክብሮ ስልጣንና ኃላፊነት ሰጥቷል። ይህ ደግሞ ምን ያክል በእኩልነት እየተዳኘን እንደቆየን፤ እኩል እንድንቀሳቀስ እየተደረገ እንደነበረ አመላካች ነው። እነዚህ ሰዎች ግን ከኃላፊነታቸው ያጠሩ እንደሆኑ የሚያሳይ ነው። ስለዚህ የወይዘሮ ኬሪያ ከኃላፊነት ራሳቸውን ማግለል
በፌዴሬሽኑ ስም፣ ዝና፣ ቁመናና ስራ ላይ ምንም አይነት ተጽዕኖ ያመጣል ብዬ አልገምትም፤ እንደዛም አይሆንም።
አዲስ ዘመን፡– ወይዘሮዋ ኃላፊነታቸውን ለመልቀቃቸው ምክንያት አድርገው ያቀረቡት ህገ መንግስቱን ለመናድና ፌዴራሊዝሙን ጨፍልቆ አምባገነን መንግስት ለመፍጠር የሚደረገው ጉዞ አካል ላለመሆን የሚል ነው። በዚህ ላይ የእርሶ ምልከታ ምንድን ነው?
አቶ ነብዩ፡– ፌዴራሊዝሙ የተቋቋመው የህወሓትን የበላይነት ለማረጋገጥ አይደለም። የህዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተቋቋመ ስርዓት ነው። ስለዚህ ይህን ስርዓት አብላጫው እየደገፈው በሂደቱ ላይም ተሳትፎ እያደረገ ባለበት ሁኔታ፤ እነሱ አክብረውት የማያውቁትን ሕገመንግስት ተጣሰ ለማለት መሰረታዊ ሞራልም የላቸውም። ምክንያቱም ህዝብም ያመጸውና ለውጡም የመጣው ሕገ መንግስቱ ስላልተከበረ ነው። አምባገነን የሆነ ስርዓት ስለዘረጉ ነው። ይህ ሆኖ እያለ አይናቸውን አጥበውና እንደገና ተመልሰው ስለ ሕገመንግስቱ መከበር፣ ስለ ዴሞክራሲያዊነት ሊያወሩ መሰረታዊ የሚባል የሞራል ብቃትም ልዕልናም የላቸውም።
በተጨባጭ ደግሞ አሁን ያለው አገራዊ ለውጥ ህዝብ የወለደው ብቻ ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ወጥቶ የፈጠረው ለውጥ ነው። ሂደቱም በጣም የተሻለ የዴሞክራሲና የፖለቲካ ምህዳር የተከፈተበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። ይሄ ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያውቀውና የሚያምንበት ነው። ስለዚህ ህወሓት የእኔ ልዕልና ካልተረጋገጠ ሕገ መንግስት ተጥሷል፤ የእኔ ልዕልና ካልተረጋገጠ አንባገነን መንግስት ነው የመጣው የሚል አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ የመንዛት ተግባር ላይ ነው ።
ስለዚህ ሕገመንግስቱም፣ የፌዴራል ስርዓቱም ለህዝቦች እኩልነት ተብሎ፣ በትግራይ ህዝብ መስዋዕትነት ታጅቦና በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል እውን ሆኖ ስራ ላይ ያለ እንጂ፤ የህወሓት ወይም የአንድ ቡድን ተጠቃሚነትና የበላይነትን ለማረጋገጥ አይደለም። እናም አክብረውት የማያውቁትን እና በእውነት ተግብረውት የማያውቁትን የፌዴራል ስርዓት አሁን ተጣሰ ለማለት መሰረታዊ ሞራልም የላቸውም፤ ማንንም ሊያታልሉ የማይችሉበት ምክንያትን ነው እንደ ምክንያት የደረደሩት።
አዲስ ዘመን፡– ከትግራይ ህዝብ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ጋር የሚነሱ በርካታ ጉዳዮች የሚደመጡ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በነበረው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ ጥያቄና መልስ ውሎ ወቅት የትግራይ ክልልና ህዝብ በፌዴራል መንግስቱ እየተገፋ ነው የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎች ከምክር ቤቱ አባላት ተነስተው በጠቅላይ ሚኒስትሩም ምላሽ እንደተሰጠባቸው ይታወቃል። ለመሆኑ በዚህ ዙሪያ የተነሱ ጥያቄዎችን እና የተሰጠውን ምላሽ እርሶ እንደ አንድ የትግራይ ተወላጅ እንዴት አገኙት?
አቶ ነብዩ፡– ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ቀርበው የሰጡት መግለጫ ሁሉንም በጣም ያስደሰተ፤ ብዙ ነገሮችንም ግልጽ ያደረገ ልዩ መግለጫ ነበር። በጣም ብዙ የትግራይ ተወላጆችም ሆኑ ባጠቃላይ የትግራይ ህዝብም በተለይ ከትግራይ ጋር ተያይዘው በተነሱ አጀንዳዎች ዙሪያ በተሰጡ መልሶች የተፈጠሩ ግልጽነቶች ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማው ነው እኛ የተመለከትነው። ባጠቃላይም እንደ አገር ምን እየተሰራ ነው የሚለውንም በደንብ ግልጽ የሆነበት፤ ወዴት እያመራን እንደሆነም ግልጽ የሆነበት እና በጣም ውጤታማ የሆነ የፓርላማ ቆይታ ነበረ። በተለይ ከትግራይ ጋር ተያይዞ የነበረው ውዥንብር ሙሉ ለሙሉ ውሸት እንደሆነ፤ የትግራይ ህዝብ ከለውጡ እንዳልተገለለ ያስረዳ ነው።
እኛም እንደ ትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ወደ አገራዊ ለውጥና ወደ ብልጽግና ፓርቲ ስንገባ የትግራይ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል፤ የትግራይ ህዝብ ጥያቄ ደግሞ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የተለየ አይደለም፤ በዚህች አገር ባይተዋር የሚሆን ማንም ህዝብ የለም፤ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ይህችን አገር በመመስረትና በመጠበቅ ትልቅ አስተዋጽዖ ያበረከተ ህዝብ ነው፤ ኢትዮጵያም ሁሉንም ህዝብ በእኩልነት አቅፋ የምትኖርና የምትቀጥል አገር ነች፤ የትግራይ ህዝብም በዚህ ሂደት ተሳታፊ ያልሆነበት ጊዜም አልነበረም፤ ያፈገፈገበት ጊዜም አልነበረም፤ አሁን ደርሶ ደግሞ ወደኋላ የሚያፈገፍግበት ምንም አይነት ምክንያት የለም፤ ለውጡም የትግራይ ህዝብም ፍላጎት፤ የትግራይ
ህዝብም ትግል ውጤት ነው፤ በሚል እሳቤ ነው።
የፌዴራል መንግስትም ህዝቦች በተሻለና በእውነተኛ እኩልነት እንዲኖሩ ለማድረግ ትልቅ ስራ እየሰራ ነው ያለው። ደግሞም ማንንም ህዝብ ያገለለ አካሄድ ለማንም ሊጠቅም አይችልም። በተለይ የትግራይ ህዝብን የሚያክል ትልቅ ህዝብ ያገለለ አካሄድ ሊኖርም አይችልም፤ ሊኖርም ከተሞከረም ትልቅ አደጋ የሚኖረው ነው የሚሆነው። ስለዚህ በአጠቃላይ በታሪክም ስናየው የትግራይ ህዝብ አገርን እየመሰረተ፤ አገርን እየጠበቀና የሚገባውን ተጠቃሚነትም እያረጋገጠ በአንድነትና አብሮነት የኖረ ህዝብ ነው። ከዚህ በኋላም ይሄው የሚቀጥል ነው የሚሆነው።
አሁን ደግሞ በተጨባጭ የብልጽግና ፓርቲና መንግስት የትግራይ ህዝብን የሚያገልበት ምንም ምክንያት የለውም። ሀሳቡም በፍጹም ሊኖረው አይችልም። እኛም እንደ ትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ይሄንን የትግራይ ህዝብ ፍላጎት እና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በቅርበት የመከታተል ስራ ለመስራት ነው ወደዚህ የመጣነው። ስለዚህ አንዳንድ ፕሮፖጋንዳዎች በተለይም የትግራይን ህዝብ ከልማት ተጠቃሚነትና መሰል ጉዳዮች ያገለለ ነገር እንዳለ፤ እንዲሁም የለውጡ ተጠቃሚ እንዳይሆን የማድረግ ዝንባሌና ተግባር እንዳለ አድርጎ የሚነዛው ወሬ ሁሉ ውሸት እንደሆነ በግልጽ ተረጋግጧል።
በተለይም ከበጀት ጋር ተያይዞ ያለው እውነት፤ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከላከል ጋር ተያይዞም ይነዙ የነበሩ አሉባልታዎች ከአሉባልታነት የዘለሉ እንዳልሆኑ ግልጽ ሆነዋል። ለምሳሌ፣ የዚህ ዓመት የትግራይ ክልል በጀት ከ42 በመቶ በላይ ማደጉ፤ ከኮሮና መከላከል ስራ ጋር በተያያዘም እስካሁን ወደ 46 ሚሊዮን ብር በጥሬ እና በቁሳቁስ ድጋፍ እንደተደረገ ተገልጿል። የኮሮና መከላከል ጉዳይ ደግሞ የሰብዓዊነት ተግባርም ነው። ስለዚህ ከጫፍ እስከ ጫፍ አደጋው አለ፤ አደጋውን ደግሞ እንደ አገር ነው መከላከል ያለብን፤ እንደ አገርም ብቻ ሳይሆን እንደ ዓለምም መከላከል ስላለብን በዚህ መልኩ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተናበበ ስራ ነው እየተሰራ ያለው። አንድም ትግራዋይ በኮሮና ምክንያት እንዳይሞት የፌዴራል መንግስት ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ያለው።
ለዚህም ሰሞኑን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በክልሉ ጉብኝት አድርገው እዛ ያለውን ሁኔታም እየተከታተሉ ነው። የዓለም ጤና ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይም በየክልሉ እየዞሩ ሁኔታዎችን እየተከታተሉ ነው። እናም ምናልባት ቅሬታ እንኳን ካለ ማቅረብ ይቻላል። ነገር ግን አንዳችም ቅሬታ የለም፤ በቂ የሆነ ድጋፍም እየተደረገ ነው። እኛም እንደ ትግራይ ብልጽግና ፓርቲ የጎደለ ነገር ካለ እየተከታተልን እንዲሟላ እያደረግን ነው። ስለዚህ ለውጡን ተከትሎ ባሉት ጊዜያት የኮሮና ቫይረስ መከላከል ዘመቻውን ጨምሮ፤ በበጀቱም፤ በልማት ስራው እንቅስቃሴዎችም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች የትግራይ ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱ ተረጋግጦለት እየኖረ ነው ።
አዲስ ዘመን፡– ከህወሓት ባህሪ አንጻር አሁናዊ የክልሉ ሁኔታ በተለይም ከሰላምና ደህንነት አንጻር እንዴት የሚገለጽ ነው? ከለውጡ ማግስት የፌዴራል መንግስት ለክልሉ ከሰጠው ትኩረት ባለፈ እናንተ ወደ ብልጽግና ፓርቲ ገብታችሁ ስትሰሩ ከህዝቡ ፍላጎት አንጻር ለክልሉ ህዝብ የተሻለ ተጠቃሚነት የሚያግዝ ምን የተለየ ሀሳብ ይዛችሁ ነው?
አቶ ነብዩ፡– የትግራይ ሁኔታ በዚህ ሰዓት በጣም አሳሳቢ እና በጣም ከፍተኛ የሆነ አፈና፣ ጭቆና፣ ብዝበዛ፣ ግድያን ጨምሮ እየተፈጠረ ነው ያለው። በተለይ ህወሓት ከዚህ በኋላ ሌላ እድል የለኝም ብሎ የጣረ ሞት እርግጫ ሊባል የሚችል ተግባር እየፈጸመ ነው ያለው። ነገር ግን የህወሓት ተግባር አይደለም ትልቁ ተግባር፤ ትልቁ ተግባር የህዝባችን ተግባር ነው። ህዝባችን ምን እያሰበ ነው? ምን እያደረገ ነው? የሚለውን ነገር ነው እኛም መመልከት እና መቀበል የምንፈልገው። ምክንያቱም ሕወሓት ያበቃለት ስርዓት ስለሆነ የፈለገውን ነገር ቢያደርግና የፈለገውን ያክል ቢከፋም ሆነ ቢጨቁን የሚያመጣው ለውጥ የለም። ሁሉም ነገር ጥግ ይዟል። ስለዚህ ማሰብ ያለብን ስለመጪው ጊዜ ነው። ስለ መጪው ጊዜ ስናስብ ደግሞ ህዝባችንን ማዕከል አድርገን ነው።
ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ፍላጎት እና እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? የሚለውን ስንመለከት፤ የትግራይ ህዝብ አሁን በጣም ትልቅ የሆነ ንቃተ ህሊና ይዞ ለውጥ እየፈለገ ነው የሚገኘው። ይሄንንም በተግባራዊ እንቅስቃሴ እያጀበው ነው የሚገኘው። በወጣቱ ትውልድም በቅርብ ጊዜም
“ፈንቅል” የሚባል የወጣቶች እንቅስቃሴ መቀጣጠሉ ይታወቃል፤ ህዝብም እንደ ህዝብ በተለያየ መንገድ ብሶቱንና የለውጥ ፍላጎቱን እየገለጸ ነው ያለው። ስለዚህ ትግራይ ውስጥ አሁን ያለው ሁኔታ በጣም ትልቅ ተስፋ ነው እያየን ያለነው። የህወሓትን ተግባርም አሁን ህዝብ ነቅቶበት አዋጪ እንዳልሆነ እና የትም እንደማይደርስ ታውቆ የህወሓት መንገድና ኃይል ጥግ የያዘበት፤ የህዝብ ኃይልና የለውጥ ፍላጎት እየገነነ የመጣበት ብሎም ትልቅ ተስፋ የተያዘበት ጊዜ ነው።
እኛ ከመጀመሪያውኑ ለምንድን ነው ወደ ብልጽግና ፓርቲ የገባነው? ምንስ ለውጥ ፈልገን ነው? ይሄስ ለውጥ ስንቀላቀልስ በአገርም ሆነ በክልል ደረጃ ምን ለውጥ ማምጣት ፈልገን ነው? የሚሉ ጉዳዮችን ከግንዛቤ በማስገባት ነው። ለዚህ ደግሞ ሁሉም ነገር ከታሪክ ነው የሚነሳው። ይህች አገር እንዴት ተፈጠረች የሚለውን ቁንጽል በሆነ ደረጃ ሳይሆን በምልዓት ቁጭ ብሎ ማየት ይገባል። በዚህም የሶስት ሺህ እና ከዚያም በላይ ታሪኳን አይተን ይህች አገር ምንድን ነች? ህዝቦቿስ ምንድን ናቸው? ምን ይፈልጋሉ? ወዴትስ ይሄዳሉ? የሚሉ ነገሮችን ከታሪክ ነው የምናውቀው። ከዚህ አኳያ ሲታይ ቅድምም እንደተገለጸው የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትፈጠር ትልቅ ስራ የሰራ ህዝብ ነው። ሂደቱ ላይም ብዙ መስዋዕትነት እየከፈለ አገር የማነጽ እና አገራዊ አንድነትን እውን ለማድረግ ትልቅ ስራ እየሰራ የቆየ ህዝብ ነው። ከዚህም የሚገባውን ተጠቃሚነት እውን እያደረገ የመጣ ህዝብ ነው። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ ከመጣው አገራዊ ለውጥ ወደኋላ የሚሸሽበት ምንም ምክንያት የለም። አገራዊ ለውጡም የትግራይ ህዝብም ፍላጎት ነበረ። የትግራይ ህዝብም በከፋ አፈና ውስጥ ሆኖ እንኳን ይታገልና መስዋዕት ይከፍል ነበር። ስለዚህ አገራዊ ለውጡ የትግራይ ህዝብ ፍላጎት እና የትግል ውጤትም ስለሆነ፤ በአገር ደረጃም አገር ማዳን ስላለብን፤ እኛም ደግሞ እንደ ትግራይ ህዝብ ልጆች የቆየ የትግራይ ህዝብን የፖለቲካ ፍላጎትና አካሄድ ማስቀጠል ስላለብን ይሄንን ስራ ለመስራትና ህዝባዊ ኃላፊነታችንንም ለመወጣት ነው የመጣነው። ይሄ መሰረታዊ ዳራው ነው።
ከዛ ቀጥሎ ደግሞ የአገራዊ ለውጡ ምንነት ነው። አገራዊ ለውጡ ደግሞ በጣም አቃፊ፤ እውነተኛ ዴሞክራሲ፣ እውነተኛ ፌዴራሊዝም ለመተግበር የመጣ፤ አገራዊ አንድነትን እውን ለማድረግ የመጣ፤ የኢትዮጵያ ልማት ወደተሻለ ደረጃ እና ወደ ብልጽግና ለማሳደግ ቆርጦ የተነሳ፤ የለውጥ ጉዞውና ኃይልም ከጫፍ እስከ ጫፍ ህዝባዊ ቅቡልነትና ድጋፍ ያለው ኃይል በመሆኑ በዚህ ኃይል ውስጥ ገብቶ መሳተፍ የዜግነት ግዴታችን አድርገን ስለቆጠርነውም ነው። በዚህም ይህቺ አገር ወደተሻለ ምዕራፍ ትሄዳለች፤ ህዝቦቿም የተሻለ ህይወት ይኖራቸዋል፤ የትግራይ ህዝብም የተሻለ ህይወትና የተሻለ ተጠቃሚነት ይኖረዋል ብለን ስላመንን፤ እናም ህዝባዊ ዓላማ ይዘን እንዲሁም ታሪካዊ መሰረታችንን አክብረን ነው ወደ ብልጽግና የተቀላቀልነው።
በዚህም እስካሁንም ብዙ ለውጦች አምጥተናል። በመቀላቀላችንም በራሱ የአገር አንድነት ላይ በጣም ትልቅ ተስፋ ፈጥረናል። ከዛ በተጨማሪም በተለያየ ቦታ ተበትኖ የነበረው ትግራዋይ ሰላም እንዲሰማው፤ በአገሬ ተከብሬ ሰርቼ መኖር እችላለሁ፤ የትግራይ ህዝብም የነበሩ አንዳንድ ውዥንብሮች ውሸት እንደሆኑ እና አማራጭ ይፈልግ የነበረበትን መሻትም እውን እንደሆነለት፤ በአጠቃላይ የአገር አንድነታችንን እውን ያደረግንበት፤ በአገር ደረጃም ሆነ በትግራይ ህዝብም ዘንድ የተሻለ ተስፋን የፈነጠቅንበት፤ ወጣቶችም አማራጭ ሀሳብ ደፍረው የመፈለግ ዝንባሌ እንዲኖራቸው፤ እንዲደፍሩና ወደ ኃላፊነትም እንዲመጡ፤ በአገራቸው ጉዳይ ያገባናል እንዲሉ የማበረታታት ቁልፍ ስራም ሰርተናል። ባጠቃላይ በጣም ትልቅ ለውጥ በአገርም በክልልም ደረጃ አምጥተናል ብለን ነው የምንገመግመው።
አዲስ ዘመን፡– ለውጡ ካመጣቸው ጉልህ ፋይዳዎች መካከል አንዱ የኢትዮጵያና ኤርትራ ችግር እልባት ማግኘቱ ነው። ይሁን እንጂ የህወሓት ቡድኖች የኢትዮጵያና ኤርትራን መልካም ግንኙነት እንደ ስጋት ከመመልከትም በላይ የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት አድርገው ሲገልጹት ይደመጣል። ይህ ከምን የመነጨ ይሆን? የሁለቱ አገራት ግንኙነትስ ለትግራይ ህዝብ ስጋት ሊሆን የሚችል ነውን?
አቶ ነብዩ፡– የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ግንኙነት ጉዳይ መጀመሪያውኑ መበላሸት ያልነበረበት፤ አይደለም ወደ ጦርነት መግባት ቀርቶ በምንም መልኩ እክል ሊገጥመው
የማይገባ ግንኙነት መሆን ነበረበት። ያው ሁላችንም የምናውቀው ነገር ተፈጠረ። ይህ ደግሞ ሁላችንንም ያሳዝነናል። ይህ ታሪክም ባይፈጠር የሁላችንም ምኞትና ፍላጎትም ነበር። ነገር ግን የተፈጠረው አውዳሚ ጦርነት ሁላችንንም ዋጋ አስከፍሎን እና ከዛም በጣም ትልቅ ትምህርት ተምረን በስተመጨረሻም ደግሞ ሁላችንም (የኢትዮጵያም የኤርትራም ህዝብ) ስንፈልገው የነበረው አንጻራዊ ሰላም ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ጉዳይ ደግሞ ከማንኛውም ህዝብ በላይ በዋናነት የትግራይ ህዝብ ይፈልገዋል። ይህ እንዲሆንም ሲወተውት ቆይቷል። ስለዚህ የኢትዮጵያና ኤርትራ አንጻራዊ ሰላም የትግራይ ህዝብ ትልቅ ድል ነው ብለን ማስቀመጥ እንችላለን። በተፈጠረው ሰላምም እስካሁን ያለው አመርቂ ነው፤ በቀጣይም ከዚህ በላይ እየተሻሻለ መቀጠል አለበት። ለዚህም ወደታች ወርዶ በድንበር አካባቢ ያለው ግንኙነትም በደንብ የማሻሻል ስራዎችን በቀጣይነት መስራት ያስፈልጋል። ከዚህ በኋላም ከዛ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም።
ይህ ሆኖ እያለና ትልቅ ተስፋም ፈጥሮ ሳለ፤ ግንኙነቱ የሁለቱ መሪዎች ብቻ ነው የሚል ስሞታ አለ። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር እነዚህ መሪዎች የሚመሩት ህዝብና አገር አለ። ስለዚህ መሪዎቹ ሲገናኙ የሚገናኝ ህዝብ አለ፤ እናም መሪዎቹ ሲገናኙ አገሮች እየተገናኙ ነው ማለት ነው። ስለዚህ መሪዎቹ ህዝባቸውንና መንግስታቸውን የሚወክሉ ናቸው። ሆኖም በዛ ደረጃም እንኳን ቢሆን ግንኙነት መጀመሩ በራሱ በጣም ትልቅ እምርታ ነው። ስለዚህ መጀመሪያ ይሄንን ማክበር አለብን። ይሄን ካደረግን በኋላ ነው መጨመርና መቀጠል ያለበት ነገር ካለም መጠየቅ ያለብን። ስለዚህ ከዚህ ለውጥ እና ከኢትዮጵያና ኤርትራ ሰላም እውን መሆን ጀርባ የህዝቦች ተጠቃሚነትና አንድነት አለ። የኢኮኖሚ መተባበር አለ። መጻኢ እድላችንም ጥሩ የመሆን እድሉም ግልጽ ነው።
ሆኖም ህወሓት እንደሚለውና እንደሚሰጋው የኢትዮጵያንና ኤርትራን መልካም ግንኙነት ለትግራይ ጎጂ የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም። ምክንያቱም ሰላም በመታጣቱ ቁጥር አንድ የተበደለውና የተጎዳው የትግራይ ህዝብ ነው። ስለዚህ ሰላሙ ቀድሞ የሚጠቅመው የትግራይን ህዝብ ነው። ነገር ግን በህወሓት በኩል የሚነዛ ፕሮፖጋንዳ አለ። ሆን ተብሎ የትግራይ ህዝብን ለመጉዳት፤ ህወሓትን ለመጉዳት፤ ወዘተ… የሚል ፕሮፖጋንዳ አለ። ይሄ ግን ፍጹም ከእውነት የራቀ ነው።
ምናልባት ህወሓት የራሳቸውን ጥቅምና ልዕልና ከማስከበር አንጻር አደጋ እየታያቸው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን አንድ ነገር ለአገርና ለህዝብ አደጋ እስካልሆነ ድረስ ተቀባይነት ይኖረዋል። ለህወሓትም አደጋ የሚሆንበት እድል ካለ በሰላማዊ መንገድ በድርድር ተቀራርቦ በመፍታት ነው እንጂ መሄድ ያለብን እንዲሁ አፍራሽ የሆነ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት፤ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬና መቃቃርን በመዝራት አይደለም። ምክንያቱም ያ ሂደት ምን አይነት ውጤት እንዳለው ሁላችንም የምንገዘነበው ነገር ነው። እናም በስህተት ላይ ስህተት ባይጨመር መልካም ነው። ባጠቃላይ የኢትዮጵያና ኤርትራ አንጻራዊ ሰላምና ግንኙነት እውቅናም የተቸረው ትልቅ ስራ ነው፤ በቀጣይነትም እየተሻሻለና እያማረ የሚሄድ በጣም ትልቅ ተስፋ ሰጪ የሆነ ግንኙነት ነው። በዛም መልኩ ነው መገለጽ ያለበት።
አዲስ ዘመን፡– ካለው ወቅታዊና ክልላዊ የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር የትግራይ ህዝብም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ሊገነዘቡ ይገባል የሚሏቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
አቶ ነብዩ፡– የመጀመሪያው ነገር ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ አንድ እንዳልሆኑ ለሁላችንም ግልጽ መሆን አለበት። በተለይ በፖለቲካው ዓለም ላይ ያሉ ሰዎች ይሄንን በግልጽ መገንዘብ አለባቸው። ባጠቃላይ ህዝቡም አንድ ህዝብና አንድ ፓርቲ አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ፤ በሳይንስም በሞራልም አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉም መገንዘብ አለበት። በቋንቋም ቢሆን በዛ ደረጃ መገለጽ የለባቸውም። ምክንያቱም አንድ ህዝብ የሆነ ድርጅት ነው ማለት በጣም አሳፋሪ፤ ክብርም የሚነካ ነው።
ምናልባት ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የታሪክ ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል። ይህ ግንኙነት ደግሞ ጠንካራ ግንኙነት ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ጊዜ ግን እንደዛ አይነት ግንኙነት የላቸውም። ምክንያቱም አሁን የትግራይ ህዝብና ህወሓት በዳይና ተበዳይ ናቸው። አሁን መገለጽ የሚችሉትም በዚህ መልኩ ነው። በሳይንስም ደረጃ ከሄድን ህዝብና ፓርቲ አንድ ናቸው ማለት በጣም ስህተት ነው።
ከዚህ በተጓዳኝ ሁሉም የህወሓት አባላትና አመራሮች
አጥፊ ናቸው ብሎ ማለትም ተገቢ አይደለም። ምክንያቱም በጣም ብዙ ቅን የሚያስቡና ህዝብን የሚያስቀድም ብቻም ሳይሆን ስለ ህዝብ ቀድመው መስዋዕት የሚሆኑ ቆራጥ የህዝብ ልጆች አሉ። የትግራይ ህዝብ ታሪክ፣ ባህልና ማንነትም ይሄንን ነው የሚያሳየው። ህዝብንና አገርን የማስቀደም ጉዳይን፤ የጋራ ተጠቃሚነትን፤ አብሮ መኖርን የሚያውቅና ይሄንንም ለሌሎች ያስተማረ ትልቅ ህዝብ ነው። ስለዚህ ጥቂት ሰዎች በሚያጠፉት ጥፋት ህዝብን መፈረጅ፤ ባጠቃላይም ሁሉም እንደዛ እንደሆነ ማሰብ በጣም ስህተት ነው።
ስለዚህ መጀመሪያ ግልጽ መሆን ያለበት የትግራይ ህዝብ እና ህወሓት የተለያዩ እንደሆኑ ሲሆን፤ ድርጅትና ህዝብ መሆናቸውን መገንዘብም ይገባል። በታሪክ ሂደት የፈጠሩት ግንኙነት የነበረ ቢሆንም፤ ግንኙነቱ መጀመሪያ አካባቢ ከነበረው ጥብቅ ቁርኝት መሃል ላይ እጅጉን የላላ ሆኗል። አሁን ላይ ደግሞ ሆድና ጀርባ ተብሎ ወደሚገለጽ ደረጃ ደርሷል። እናም ይሄንን በየምዕራፉ መረዳቱ ተገቢ ነው። ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ ህወሓት ውስጥም ብዙ ህዝባዊ ኃይሎች መኖራቸውን ተገንዝቦ እነርሱን ማክበርና መደገፍ እንዳለብን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም አስምረውበታል። በዚህ መልኩም ስልጡን የሆነ ፖለቲካ ነው ማካሄድ ያለብን እንጂ ይሄ የጅምላ ፍረጃ አካሄድ ስህተት ነው የሚለው ጉዳይ ሊሰመርበት ይገባል።
ከዚህ ባለፈ ግን የትግራይ ህዝብ በአጠቃላይ በሀገር ካለው ተጠቃሚነት አልጎደለም፤ አሁንም እኩል ተጠቃሚነቱ ተረጋግጦለታል። ይሄንንም እኛም በቅርበት እየተከታተልን ነው። ይሄው ተጠብቆ እንዲሄድም በግንባር ቀደምትነት እየሰራንም ነው። ሌሎች ኃይሎችም ይሄንን አይክዱም፤ ሊክዱም አይችሉም። ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ ምን አይነት ታሪክ እንዳለው፣ ምን አይነት ባህሪና ማንነት እንዳለው በግልጽ ስለሚታወቅ ነው። ምናልባት እነዚህ ነገሮች አንዳንዴ የሚዘነጉት የእልህ ፖለቲካ ውስጥ ስለምንገባ ነው እንጂ የትግራይ ህዝብ ማንነት፣ ታሪክ በደንብ ይታወቃል።
ስለዚህ ትግራይን ያገለለ አካሄድ ሊኖር አይችልም፤ ይሄንን የሚያስብ አካል እንኳን ካለ ከፍተኛ የሆነ ውድቀት ነው የሚጠብቀው። ይሄንን ውድቀት ደግሞ ማንም ዝም ብሎ አያስተናግደውም። ስለዚህ አሁንም የህዝቦች እኩልነት አለ፤ እኩል ተጠቃሚነት አለ፤ የትግራይ ህዝብም የአገር ባለቤትነቱ፣ የእኩልና ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱ አይጓደልም። እንዳይጓደልም እኛ በቅርበት እየተከታተልን እና ትግል ሲያስፈልግም እየታገልን ነው ። ስለዚህ የትግራይ ህዝብ እኩል ተጠቃሚ መሆኑ፤ ተጠቃሚነቱም እንደሚቀጥል ግልጽ ሊሆን ይገባል። በፖሮፖጋንዳ የሚነዙ አንዳንድ ውዥንብሮችም ውሸት እንደሆኑ እና መረጃዎች ሲመጡም በጥንቃቄ መርምሮ የማየት፤ ማን ምን አይነት አካሄድ እየተከተለ ነው የሚለውን ነገርም በደንብ እያጤነ መሄድ ያስፈልጋል። በመሆኑም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ ከተያዘ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻም እንደ አገር ዛሬ ካለብን ችግርና ፈተና ወጥተን ብሩን ነገን ከማየት አንጻር ከግለሰብ እስከ መንግስት ለአገርና ህዝብ ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ ሰጥቶ ከመስራት አኳያ ከማን ምን ይጠበቃል በሚለው ላይ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለ?
አቶ ነብዩ፡– ይህቺ አገር የሁላችንም ነች። የሁላችንንም ተሳትፎም ትጠብቃለች። በተለይ በዚህ አስከፊ ጊዜ ብዙ ችግር እየገጠመን ነው ያለው። ከኮቪድ 19 እና ተጓዳኝ አደጋዎች ጋር ተያይዞም በአንድ መቆም ያለብን ጊዜ ላይ ነው ያለነው። ከኮቪድ 19 እና ከተጓዳኝ አደጋዎቹ በተጨማሪም፤ የህዳሴ ግደቡ የህዝቦችን አንድነትና ርብርብ የሚፈልግ ነው። የጣና ሐይቅ፣ የአክሱም ሐውልትና ሌሎችም ቀላል የማይባሉ ፈተናዎችና ችግሮች ናቸው።
በተለይ ደግሞ ከዓባይ ጋር ተያይዞ ከሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ትንኮሳዎች እየመጡ ስለሆኑ፤ እነዚህን ሁሉ ችግሮች ለመፍታት ሁላችንም እንደ አንድ ሰው መቆም አለብን። አገር ማስቀደም አለብን። ምክንያቱም አገር ካለችን ነው እኛም የሀሳብ ልዩነታችን ሊስተናገድ የሚችለው። እናም ይህች አገር የሁላችንም እንደመሆኗ የሁላችንም ተሳትፎ ያስፈልገናል፤ እኩልነት ያስፈልገናል፤ መከባበርና መቻቻል ያስፈልገናል። እንደ አንድ ሰው ቆመንም በተለይ አሁን የተፈጠረውን ችግር ተጋፍጠን አልፈን የተሻለ አገር፣ የተሻለ ትውልድ እንዲፈጠር ሁላችንም የየበኩላችንን ሚና መወጣት አለብን።
አዲስ ዘመን፡– ለቃለ ምልልሱ ስለተባበሩኝ አመሰግናለሁ።
አቶ ነብዩ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሰኔ10/2012