
አዲስ አበባ፡- አበበች ጎበና ህጻናት ክብካቤና ልማት ማህበር በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ለችግር ለተጋለጡና ከዚህ ቀደም ድጋፍ አግኝተው ለማያውቁ 340 ሰዎች የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።
በትናንትናው ዕለት ባካሄደው የድጋፍ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት ላይ የተገኙት አበበች ጎበና ህጻናት ክብካቤና ልማት ማህበር የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ይትባረክ ተካልኝ እንደተናገሩት፤ ማህበሩ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ ለመቀነስ የሚደረገውን አገራዊ ርብርብ ለማገዝ የበኩሉን ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል።
በተለይም ወረርሽኙ እየተባባሰ ከመጣበት ከሚያዚያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የዘወትር አጋሮቹን ሜንሽን ፎር ሜንሽን ስዊትዘርላንድንና ፕላን ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያን በመጠየቅ በወረርሽኙ ምክንያት ይበልጥ ለችግር ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን እየረዳ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኃላፊው አንዳሉት ፤ የአሁኑን የድጋፍ አሰጣጥ መርሐ ግብር ለየት የሚያደርገው ከዚህ ቀደም ድጋፍ አግኝተው ለማያውቁ እጅግ አሳዛኝ በሆነ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች የተሰጠ መሆኑ ነው ብለዋል።
ድጋፉ የተደረገላቸው ዜጎች ጧሪ ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የማይችሉ አካል ጉዳተኞች፣ በሞትና በልዩ ልዩ ምክንያት ዋነኛ የቤተሰብ አስተዳዳሪያቸውን ያጡና በከፍተኛ ችግር ውስጥ በሆኑ ህጻናት ልጆችና ሴቶች የሚተዳደሩ ቤተሰቦች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኃላፊው እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች ለተደራሽነት በጣም አስቸጋሪ የሆኑና ብዙውን ጊዜ በመንግሥትና በተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በሚደረጉ ድጋፎች ሳይታዩ የቆዩ መሆናቸውን ገልጸው፤ ማህበሩ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በበጎ ፈቃደኞች በማስጠናትና
ችግረኝነታቸው ከሚኖሩበት ቀበሌ እንዲረጋገጥ በማድረግ ለተመረጡ 340 ግለሰቦች በነፍስ ወከፍ ቢያንስ ለአንድ ወር የሚበቃ ፍርኖ ዱቄት፣ ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ዘይት፣ ሳሙና፣ ፊት መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ (ሳኒታይዘር) አከፋፍሏል።
ከሚያዚያ ወር መጨረሻ ጀምሮ አበበች ጎበና ህጻናት ክብካቤና ልማት ማህበር የትናንትናውን ጨምሮ
እስካሁን ድረስ በአጠቃላይ በ 870 ሺ 342 ብር ወጪ በወረርሽኙ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ለተጋለጡ 1 ሺ 880 ሰዎች የጥሬ ገንዘብ፣ የምግብና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉንም አስታውቀዋል።
በወረርሽኙ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ከሚደረገው የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎችን በመጋበዝ ትምህርት እንዲያገኙ
በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ማከናወኑን እና በዚህም የቫይረሱን ስርጭት መከላከል በሚቻልባቸው መንገዶች ዙሪያ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመንም 240 ሺ 340 ብር መሆኑንም የማህበሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ይትባረክ አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
ይበል ካሳ