
አዲስ አበባ:- “ድርድር ሰጥቶ የመቀበል መርህ ሆኖ ሳለ እየተደራደርን ያለው ምንም መስጠት ከማትፈልግ ነገር ግን ሁሉንም መውሰድ ከምትፈልግ አገር ጋር ነው” ሲሉ የውጭ
ጉዳይ ሚኒስትሩ አስታወቁ ። ሁሉንም ልውሰድ ከሚል ኃይል ጋር መደራደር በጣም አስቸጋሪ መሆኑንም ገልጸዋል ።
የግብጽ ባለስልጣናት ግድብ የመገንባት አቅም እንዳይኖረን ብዙ ጥረዋል፣ አቅም ሲኖረን እንዳንጀምር ብዙ ደክመዋል ያሉት ሚኒስትሩ፤ ስንጀምርም እንዳንቀጥል ለማድረግ ወጥተዋል
ወርደዋል፣ ኢትዮጵያን ማዳከምና ማጠልሸት ዘላቂ ግባቸው አድርገው እየሰሩ ይገኛሉ ሲሉም ተናግረዋል።
ይህንን ሁሉ ችለን እየተደራደርን ነው፤ አሁንም በድርድሩ
አንድ እግራቸውን ኒውዮርክ ሌላ እግራቸውን ድርድሩ ላይ አድርገው ቀጥለዋል ያሉት አቶ ገዱ፤ ድርድሩ ሳይጀመር ፈረሰ ብለው መግለጫ እንደሚያወጡና ለማፍረስ ፈልገው ኢትዮጵያን እንደሚከስሱ ጠቁመዋል።
‹‹ውሃውን እናንተ እንዳትነኩት ለእኛ ስጡን የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ በ19 ኛና በ20 ክፍለ ዘመን ሰርቶ ሊሆን ይችላል በ21 ኛው ክፍለ ዘመን ግን ያረጀ እና ያፈጀ አስተሳሰብ ስለሆነ በምንም መልኩ ተቀባይነት የለውም›› ብለዋል። ግብጾች በፍትሃዊነት የመጠቀሙን ሁኔታ ከተቀበሉት ስምምነቱ በአጭር ጊዜ ሊያልቅ እንደሚችል ጠቅሰው፤ በግብጽ በኩል ያሉ ተደራዳሪዎች ትልቅ መሰናክል እየሆኑ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም ግብጽ ጉዳዩን ወደ መንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ወስዳው እንደነበር አስመልክተው፤ አሁንም በከፊል እየተደራደረች በሌላ በኩል ጉዳዩን ወደእዛ ለመውሰድ የምታደርገውን ጥረት በይፋ ቀጥላበታለች፤ ይህ መንገድ አያዋጣም፣ ኢትዮጵያ ጉዳዩ የአፍሪካውያን በመሆኑ አፍሪካዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት እምነቷ እንደሆነ አመልክተዋል ።
የናይል ውሃ በጠቅላላው የተፋሰሱ አገራት ውሃ ነው። በተመሳሳይ መልኩ ከኢትዮጵያ የሚመነጨው ጥቁር አባይ የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብጽ ነው። ውሃውን በጋራና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ መጠቀም አለብን ያሉት ሚኒስትሩ፣ ይህንን ሃሳብ እስካልተቀበሉ መግባባት አይቻልም ብለዋል።
‹‹ጉዳዩን ወደተባበሩት መንግሥታት ይውሰዱት፣ የፈለገ ውን ነገር ይበሉ፣ ኢትዮጵያንም ስሟን ያጥፉ፣ አንዳንዴ እንደሚያደርጉትም ያስፈራሩ፤ በግዛታችን የሚገነባውን ግድብ እና ከአባይ ውሃ የመጠቀም መብታችንን በምንም መንገድ አሳልፈን አንሰጥም፤ ይህንን ማወቅ አለባቸው፣ ለግብጽ ህዝብም ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፣ ሁል ጊዜ እያምታቱ መኖር አይቻልም›› ሲሉም አክለዋል።
አቶ ገዱ በ2015 (እ.አ.አ) ከነበረው የመርህ ስምምነት ውጭ ሌላ መተሳሰሪያ የሌለን በመሆኑ ግብጽ ድርድሩን አቋርጣ የምትወጣና ድርድሩ የሚፈርስ ከሆነ ከግብጽ ጋር የሚያስተሳስር ምንም አይነት ውል የለንም ፤ከግብጽና ከሱዳን ጋር ያለን ስምምነት እስካሁን አንድ ብቻ መሆኑንና ይኸውም እ.አ.አ በ2015 የተፈረመው ስምምነት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ግብጾች በ1959 ያደረጉት ስምምነት ሁሉንም ውሃ
ለግብጽና ለሱዳን የሚደለድል በመሆኑ ያንን አንቀበልም ያሉት የውጭ ግዳይ ሚኒስትሩ ፣ ድርድሩ እንደገና ተጀምሮ አምስተኛ ቀኑን እንደያዘና ኢትዮጵያ ችግሩ በድርድር መፈታት አለበት ብላ ስለምታምን እስካሁን በድርድሩ መቀጠሏን አስታውቀዋል።
የውሃው አመንጪዎችና የግድቡ ባለቤቶች ሆነን ግድቡን በራሳችን ግዛት እየገነባነው ብንገኝም የተፈጠረውን ችግር ለዘለቄታው ስምምነት ላይ እንዲደረስ እንፈልጋለን ያሉት አቶ ገዱ ስምምነቱ ላይ መድረስ የሚቻለው ግን ድርድሩ የአባይ ውሃ አጠቃቀም በፍትሃዊነት ላይ ሲመሰረት ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል ።
አቶ ገዱ የግብጽ ሕዝብ እና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በምክንያት የሚደራደር እና በሰጥቶ መቀበል የሚያምን፣ ለህዝቦች የጋራ ጥቅም የሚገዛና ኃላፊነት የሚሰማው መንግሥት እንዲሆን ጫና እንዲያሳድሩም ጥሪ አስተላልፈዋል። ኢትዮጵያ የውሃውም፣ የችግሩም፣ የመፍትሄውም ባለቤቶች ስለሆንን በድርድር ከመጨረስ ውጪ ሌላ መንገድ የለም ብላ እንደምታምን ፤ በቴክኒክ ደረጃ የሚደረገው ውይይት ዳግም እንዲጀመር ሱዳኖች ያደረጉትን አስተዋጽኦ በማንሳትም አመስግነዋል።
ግብጽ በአንድ በኩል እየተደራደረች በሌላ በኩል ደግሞ ወደተለያዩ አካላት በተለይ ለመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን ለማቅረብ ጥረት እያደረገች በመሆኑ የዚህ አይነቱ አካሄድ ለድርድሩ ውጤታማነት ተግዳሮት እንደሚሆን አሳስበዋል ።
ግብጽ የምትሰጠው የላትም፤ በድርድር የሚሰጧትን አትቀበልም፣ በዚህ ምክንያት ዘንድሮም እየተደራደርን እንገኛለን ያሉት ሚኒስትሩ ፣ በድርድርና በጋራ ተጠቃሚነት ስለምናምን ችግሩን ለመፈታት አሁንም ከግብጽ ጋር እየተነጋገርን እንገኛለን ብለዋል።
ኢትዮጵያ 86 በመቶ የናይል በተለይም የአባይ ውሃ ምንጭ ናት ያሉት አቶ ገዱ፤ ግድቡ እየተሰራ ያለው መቶ በመቶ በመንግሥትና በኢትዮጵያ ሕዝብ መዋጮ ሆኖ፣ እየተደራደርን ያለነው ውሃም ሆነ ምንም አይነት አስተዋጽኦ ከማታበረክተው፣ ግድቡ ሲገነባም ምንም አስተዋጽኦ ከሌላት ከግብጽ ጋር ነው ብለዋል።
በቀጣይነት ስማችንን በዓለም አደባባይ ከሚያጠፉት፣ የአባይ ውሃ ምንጭ ኢትዮጵያ ቢሆንም ምንም መንካት የለባችሁም ከሚሉን ጋር እየተደራደርን ያለነው በጋራ ተጠቃሚነት ስለምናምን ብቻ እንደሆነ አቶ ገዱ ጠቁመዋል ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
ዘላለም ግዛው