
አዲስ አበባ፡- በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የ125 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ጥገና ማከናወኑን የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ። ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የእግረኛ መንገድ ግንባታ እያካሄደ መሆኑን ገለጸ።
ባለስልጣኑ ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ እንዳመለከው፤ በ2012 በጀት ዓመት 130 ኪ.ሜ አስፓልት መንገድ ለመጠገን አቅዶ ነበር። ባለፉት አስራ አንድ ወራት 125 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር አስፓልት መንገድ ጥገና አካሂዷል። ይህም አፈፃፀሙ የእቅዱን 97 ከመቶ ነው።
እንደ ባለስልጣኑ ገለጻ፤ በበጀት ዓመቱ አስራ አንድ ወራት ውስጥ ጥገና እና ደረጃ ማሻሻል ከተደረገላቸው የአስፋልት መንገዶች መካከል በማዕከላዊ ሪጅን ኢኖቬሽን ሚኒስቴር – ፍልውሃ አደባባይ፣ ብሔራዊ ቲያትር – ካዛንቺስ፣ ግቢ ገብርኤል፣ ሀገር ፍቅር ቲያትር ፊት ለፊት (ፓርኪንግ)፣ ጌጃ ሰፈር (ደረጃ ማሻሻል)፣ በሰሜን ሪጅን ከስድስት ኪሎ ሽሮ ሜዳ፣ ከስድስት ኪሎ ሚኒሊክ፣ ከመነን – ወለጋ ሰፈር፣ ከመነን ት/ቤት – ምስካየ ህዙናን መድሃኔ ዓለም ቤ/ክ፣ ቤላ – አቦ ቤ/ክ፣ ከባልደራስ – ካዛንቺስ፣ ከድንበሯ ሆስፒታል – ሾላ ለም ሆቴል፣ ኮተቤ ዩኒቨርሲቲ – ሰላም ዳቦ ቤት መንገዶች ይገኙበታል።
በምዕራብ ሪጅን ከመድሃኒ ዓለም ት/ቤት – አበበ ቢቂላ ስቴዲየም፣ ከአውቶብስ ተራ – ኳስ ሜዳ፣ ከአውቶብስ ተራ – ጎጃም በረንዳ – አዲስ ከተማ ት/ቤትጀርባ፣ አንፎ አደባባይ – ታጠቅ አምቦ መንገድ፣ ጦር ሃይሎች – ሙሉ ወንጌል ቤ/ክ፣ እንዲሁም በምስራቅ ሪጅን አዲሱ ቦሌ ስቴዲየም፣ ሪቬንቲ፣ ቦሌ ብራስ፣ አቦ ሳሪስ – ቡልቡላ፣ የፓርላማ አባላት መኖሪያ
ጀርባ፣ ገርጂ የፓርላማ አባላት መኖሪያ፣ ቦሌ አትላስ ቺቺኒያ ጥገና ማድረጉን ባለስልጣኑ አብራርቷል።
በተመሳሳይ በደቡብ ሪጅን ጎተራ ማሳለጫ – ቃሊቲ ቀለበት መንገድ፣ ላፍቶ ድልድይ፣ ዳማ ሆቴል – ሃና ማሪያም ድልድይ፣ ላፍቶ መብራት፣ መካኒሳ አቦ ጀርባ፣ ቄራ ሶፊያ ሞል የመንገድ ጥገና ማድረጉን አስታውቋል።
ባለስልጣኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከአስፓልት ጥገና በተጨማሪም የጠጠር መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የውሃ መውረጃ ቱቦ እና የመንገድ መብራት ጥገናዎችንም ማከናወኑን አመልክቷል። ከ184 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በመመደብ በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች የእግረኛ መንገዶችን እየገነባ እንደሚገኝ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በዚሁ በጀት ዓመት ባለስልጣኑ ባጠቃላይ ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የእግረኛ መንገድ ግንባታን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሶ፣ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ ሙሉ ለሙሉ አጠናቆ ለእግረኞች አገልግሎት ክፍት እንደሚያደርግም ጠቁሟል።
የእግረኛ መንገድ ግንባታ እየተከናወነ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል ከመገናኛ- አያት፣ ከሚሊኒክ ሆስፒታል- ስድስት ኪሎ፣ ከአክሱም ሆቴል – አድዋ ድልድይ፣ ከሰዓሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን- ኢትዮ ቻይና ኮሌጅ፣ ከብራስ ክሊኒክ – አትላስ ሆቴል – ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን፣ ከጎሮ አደባባይ – አይሲቲ ፓርክ፣ ከሆላንድ ኤምባሲ- የሺ ደበሌ፣ ከገላን ኮንዶሚኒየም – ደብረ ዘይት መንገድ፣ አቃቂ ቃሊቲ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ፣ ጀሞ ሚካኤል አካባቢ፣ ጀሞ ሶስት አካባቢና ሌሎችም እንደሚጠቀሱ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2012
አስናቀ ፀጋዬ