
የዓባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ አጀንዳ ሲፈጠር ከግብጻውያን ዘንድ ደጋግመን የምንሰማው ዓይናችሁን ጨፍኑ ላሞኛችሁ ዓይነት ዜማ አለ። ኢትዮጵያ ብዙ ወንዞች ስላሏት ዓይኗን ከዓባይ ታንሳ የሚል። ይህንን ዘመን ያለፈበትን የውሸት ህሳቤ ከተጨባጩ የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ስናስተያየው ግን እውነታው እንደ ሰማይና ምድር ተቃራኒ ሆኖ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያ ካሏት ተፋሰሶች ውስጥ ከሚመነጨው ውሃ 92 በመቶው ወደውጭ የሚፈስ ነው። ስለዚህም ኢትዮጵያ ብዙ ወንዝ እንጂ ብዙ ውሃ የሌላት አገር ናት ማለት ነው። በአካባቢ እንክብካቤ ሥራዎች ዙሪያ በነበሩ ጉድለቶችና ከደኖች መመናመን ጋር ተያይዞም ታገኘው የነበረው የዝናብ ውሃ መጠንም በየጊዜው እየቀነሰ እንደመጣ ጸሐይ የሞቀው ሀቅ ነው።
ኃይል ከማመንጨት አኳያ ስንመለከት፤ ግብፅ የተለያዩ የኃይል ማመንጫ ዘዴዎች በመጠቀም 45‚000 ሜጋ ዋት ኃይል እያመነጨች ለሕዝቧ 100% ኤሌክትሪክ ተደራሽ አድርጋለች። ከ 45‚000 ሜጋ ዋት ውስጥ 2‚100 ሜጋ ዋቱ ምንጩን ዓባይ ካደረገው የአስዋን ግድብ የሚገኝ ነው። የኢትዮጵያን ያየን እንደሆነ ከተለያዩ የኃይል ማመንጫ ዘዴዎች በመጠቀም 4‚400 ሜጋ ዋት ብቻ እያመረተች ሲሆን ከዚህም የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ከውሃ ኃይል የሚመረተው ነው። በዚህም ስሌት የኤሌክትሪክ ተደራሽ የሆነው ሕዝብ ከ 44% አይበልጥም። እዚህ ላይ መታወቅ ያለበት ግብፅ የአባይ ውሃን 85 በመቶ ከምታመነጨዋ ኢትዮጵያ በኃይል ማመንጨት በ10 እጥፍ ልቃ መገኘቷ ነው። በተለይ ከ 80% የሚበልጠው የገጠር ሕዝብ የኢነርጂ ምንጩ ማገዶ በመሆኑ በጭስና በኩራዝ ህይወቱን እየገፋ ይገኛል።
ግብፅ በመስኖ ልታለማው ከምትችለው 4.42 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 3.6 ሚሊዮን ሄክታሩን (81.4%) በላይ የሚሆነውን አልምታለች። ኢትዮጵያ ከሦስቱ ለናይል ከሚያበረክቱት ተፋሰስ ወንዞች ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ሄክታር በመስኖ ልማት ሊለማ የሚችለው መሬት ውስጥ ከ20‚000 ሄክታር በላይ በመስኖ አላለማችም። በአጠቃላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በመስኖ የለማው መሬት ከ 6 – 7 % አይበልጥም።
ኢትዮጵያ በዝናብ ከሚገኝ ውሃ ጥገኛ ሆና በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ እያመረተች ህዝቦቿን መመገብ ተስኗት በየዓመቱ ዜጎቿን ለመመገብ የለጋሾችን እጅ እንደምትጠብቅ ዓለም የሚያውቀው እውነታ ነው።
ከላይ የተገለጹትን እውነታዎች ላየ በዓባይ ወንዝ ዙሪያ የሰፈነው ኢፍትሃዊነትና በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ እየተጎዳች ያለችው ጉዳት እጅግ ያንገበግበዋል። ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ ከሰሞኑ ለአዲስ ዘመን መረጃ የሰጡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህርና የዓባይ ውሃ ጉዳይ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ “እንደናይል የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት በበላይነት ተቆጣጥረው የሚጠቀሙበት ወንዝ በዓለም የለም” ሲሉ ገልጸዋል።
ክብርና ምስጋና ለኢትዮጵያ ህዝብ ይድረሰውና ይህ ሁኔታ ግን መጋቢት 24/2003 ዓ/ም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀልብሶ ዓባይን እየረገሙና እያወገዙ መኖሩ አብቅቷል። በዓባይ ዙሪያ የዘመናት ቁጭት የነበረባቸው ኢትዮጵያውያን ከህጻን እስከአዋቂ ያለምንም ልዩነት ግድባቸውን በመደገፍ ከጅማሬ ወደፍሬ አቃርበውታልና። መላ ኢትዮጵያውያን ከትርፋቸው ሳይሆን ከጉድለታቸው በመቆጠብ በቦንድ ግዥ፣ በ8100 ኤ የገቢ ማስገኛና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ በታሪክ ውስጥ ተመዝግቦ የሚኖር ደማቅ ገድል ፈጽመዋል።
የኢትዮጵያን የኃይል አቅርቦት 115 በመቶ የማሳደግ አቅም ያለው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለ24 ሰዓታት ያለምንም መቋረጥ ተገንብቶ አሁን ላይ ውሃ ወደሚይዝበት ምዕራፍ ተቃርቧል። ይህ ሁነት የግድቡን የመሰረት ድንጋይ ከማስቀመጥና ለግድቡ ሥራ ሲባል የዓባይን ወንዝ አቅጣጫ የማስቀየር ሥራዎች ከተሰሩባቸው ሁነቶች በመቀጠል ሶስተኛውና ወሳኙ ምዕራፍ ነው።
ኢትዮጵያ ማንንም ሳትጎዳና የራሷንም ጥቅም አሳልፋ ሳትሰጥ የግድቡን ሂደት ለዚህ ደረጃ ማብቃቷ ትልቅ ደስታን የሚፈጥር ነው። ግድቡ እውን ሆኖ ከጅማሬ ወደፍሬ እንዲቃረብ መላ ኢትዮጵያውያን ያበረከቱት አስተዋጽኦም ታላቅ ነውና እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እንወዳለን!
አዲስ ዘመን ሰኔ 9/2012